Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ልጓም ያጣው የስኳር ዋጋ

በገበያ ውስጥ በኅብረተሰቡ ዘንድ በከፍተኛ ደረጃ ከሚፈለጉና መሠረታዊ ከሚባሉ ምርቶች መካከል አንዱ ስኳር ስለመሆኑ ገበያው ራሱ ይነግረናል፡፡ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖች ስኳር በእጅጉ ይፈለጋል፡፡ ብዙዎች ለልጆቻቸው ቢያንስ ዳቦ በሻይ ለማቅረብ የግድ ስኳር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ስለዚህ ስኳር ጥቂት ለማይባሉ ወገኖች ረሃብ ማስታገሻ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በየዓመቱ ፍላጎቱ እየጨመረ የመጣው የስኳር ምርት ግን በፍላጎቱ ልክ እየቀረበ አይደለም፡፡ ዋጋውም በፍጥነት እየሰቀለ ነው፡፡ በቂ ነው ተብሎ የሚሠራጨውን ምርት እንኳን በአግባቡ ሸማቹ እጅ ባለመድረስ አልተቻለም፡፡ ይህ ደግሞ የስኳር ዋጋ ከልክ በላይ እንዲሰቀል አድርጓል፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዋጋው ዕድገት አስደንጋጭ የሚባል እየሆነ ነው፡፡ ከወራት በፊት አንድ ኪሎ ስኳር መቶ ብር ገባ ተብሎ ጉድ እንዳልተባለ በወራት ልዩነት ወደ 150 ብር አሻቀበ ሲባል ቢያስደነግጠን አይገርምም፡፡

መንግሥት ልክ የሲሚንቶ ግብይትን መስመር ለማስያዝ እንዳልቻለው ሁሉ የስኳርም ግብይት ትርምስምሱ ከወጣ ሰነባብቷል፡፡ የኢትዮጵያ በስኳር ምርት ቀዳሚ ከሚባሉ አገሮች መካከል አንዷ ትሆናለች፣ ከራሷ ፍላጎት በላይ አምርታም ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ታገኝበታለች ተብሎ እንዳልተደሰኮረ አሁን ላይ በወር አንድ ኪሎ ስኳር ለማግኘት ከብዷል፡፡ እጥረቱ ሳያንስ ለአንድ ኪሎ ስኳር እየተጠየቀ ያለው ዋጋም ማቆሚያው የት ሊሆን እንደሚችል ለመገመት አዳግቷል፡፡

ኢትዮጵያን ከስኳር ምርት ያንበሻብሻሉ የተባሉ ትልልቅ ፋብሪካዎች በየቦታው ተጀምረው ሙጃ ሲበቅልባቸው ግን እያየን ነው፡፡ ነባሮቹም ቢሆኑ ከአቅም በታች እያመረቱ ስለመሆናቸው መነገሩ ብዙ የተዘመረለት የተትረፈረፈ የስኳር ምርት ጉዳይ በወሬ መቅረቱን ያመላክታል፡፡፡

የተሰጠው ተስፋ ሁሉ ቀርቶ አሁን በሌለ የውጭ ምንዛሪ ስኳር ከውጭ ማስገባት መደበኛ ተግባራችን የሆነውም የጀመርነውን ዳር ባለማድረሳችን ነው፡፡ ስኳር አምርተው እንደ ልብ ለገበያ ያቀርባሉ የተባሉ ፋብሪካዎች አሁን ምን ላይ እንደሆኑ እንኳን ለማወቅ ተቸግረናል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ፋብሪካዎች ያስወጡት ወጪ ሲታሰብ እንደ አገር ያከሰሩን መሆናቸውንም እንዳንዘነጋ ያደርገናል፡፡ ለማንኛውም በዕቅዳችን ልክ ባለመጓዛችን ማምረት ያልቻልነውን ምርት በውጭ ምርት ለመሸፈንና በውጭ ምንዛሪ ለመግዛት ተገደናል፡፡ ችግሩ ደግሞ በመከራ የሚመጣውንም ስኳር በአግባቡ ማደል አለመቻሉ ደግሞ የበለጠ ያሳምማል፡፡

የስኳር ገበያ አሁንም በመንግሥት እጅ ከመሆኑ አንፃር አጠቃላይ የግብይት ሒደቱና ሥርጭቱም በእርሱ የሚፈጸም በመሆኑ ምርቱን በሸማቾች ማኅበራት በኩል በማደል እየሠራ ቢሆንም፣ ማኅበራቱ በፍላጎቱ ልክ ለሸማቾች እያቀረቡ አይደለም፡፡ ስኳር በአግባቡ ያለማሠራጨት ብቻ ሳይሆን ከፍላጎቱ መጨመር አንፃር በየሸማቾች ማኅበር ይሸጥ የተባለው ስኳር በጎን ለነጋዴዎች የሚሸጋገር ሆኖ መገኘቱ ነገሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል፡፡

ለሸማቾች ማኅበራት የተሰጠው ስኳር ለማን መቼ ተሰጠ የሚለው ቁልፍ ጉዳይ ቁጥጥር እየተደረገበት ባለመሆኑ፣ እንዲሁም በፍላጎቱ ልክ እየቀረበ ባለመሆኑ የስኳር ገበያን መራር እያደረገው ቀጥሏል፡፡ መንግሥት በቅርቡ እንደገለጸውም በፍላጎቱ ልክ ምርቱን አስገብቶ አለማሠራጨቱም በራሱ ለስኳር ገበያ ግለት ምክንያት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በፍራንኮ ቫሉታ ከቀረጥ ነፃ የገበያውን ወደ 1.8 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር እንኳን በገበያ ዋጋ ለመሸጥ አለመቻሉ የሚያሳየን ደግሞ የግብይት ሥርዓቱ መጠለፉን ነው፡፡

በመንግሥት የግብይት ሰንሰለት በተለይ ዝቅተኛ ለሚባለው የኅብረተሰብ ክፍል በአግባቡ መሠራጨት ያለበትን ምርት ሥርዓት ባለው መንገድ ያለመከወኑ ሚስጥር ደግሞ ከሌብነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ መንግሥት ቁጥጥር እያደረገበት የሚቀርብ ምርት ነው እየተባለ በሸማቾች የማይገኝ ስኳር በየመደብሩ በውድ ዋጋ ለመሸጡ ዋና ምክንያትም የስኳር ገበያ የግለሰቦች መጠቀሚያ እየሆነ መምጣቱን ያሳየናል፡፡ ከሸማች ማኅበራት ይልቅ በየመደብሮች በግልጽም ሆነ በሚስጥር የሚሸጠው ስኳር ያልጠፋበት ምክንያትም ‹‹በተመጣጣኝ ዋጋ›› ለሸማቾች ይድረስ የተባለው ስኳር በጎን ለሕገወጦች የሚሻገር በመሆኑ ጭምር ቢሆንም ይህንን መቆጣጠር አልተቻለም፡፡ ስለዚህ ችግሩን አብሶታል፡፡

ሌላው የስኳር ገበያን ካተረማመሱት ሕገወጥ ተግባራት መካከል በወራት ልዩነት በኮታ ለድርጅቶች የሚሰጠው ስኳር ነው፡፡ የንግድ ፈቃድ ያለውና ስኳርን በግብዓትነት በመጠቀም አገልግሎት እንሰጣለን የሚሉ ድርጅቶች ለሥራቸው ተብሎ የሰጣቸውን ስኳር በግል አየር ባየር ይሸጣሉ፡፡

ይህ ከደሃው ሸማች ተቀንሶ የሚሰጣቸውን ስኳር እነሱ እንደ ገቢ ምንጭ እያደረጉት መሆኑ በግልጽ እየታየ ይህንን እንኳን ማስተካከል አልተቻለም፡፡ ጊዜው ባለፈበት ፈቃድ ሁሉ ለድርጅት እየተባለ የሚሰጥ ስኳር ሕገወጥ የስኳር ንግድን አብሶታል፡፡ ስኳር የሚነካው አገልግሎት የማይሰጥ ሁሉ ቀኑን ጠብቆ ስኳር እያወጣ እዚያው ትርፍ ይዞበት ይሸጣል፡፡

ይህ ራሱ በገበያ ውስጥ የሚፈጥረውን እጥረት ቀላል ካለመሆኑም በላይ ሕገወጥ ነጋዴዎች የስኳር ዋጋን እንዳሻቸው እንዲሰቅሉs እያደረገ ነው፡፡ የስኳር ገበያ ችግር የዛሬ ብቻ ሳይሆን የረዥም ዓመታት ችግር እንደመሆኑ መጠን አሁንም ይህንን ገበያ ለማስተካከል አለመቻሉን ግን ያስገነዝበናል፡፡  

ሰሞኑን መንግሥት 110 ሺሕ ኩንታል ስኳር እንዲገባ ተፈቀደ የሚለው ዜና እንደ ትልቅ ነገር የመገለጹ ምክንያት የሚነገረንም የስኳር ገበያን መስመር ለማስያዝ ባለመቻሉ በአገር ውስጥ በቀላሉ ማምረት ባለመቻላችን ቢሆንም ችግሩን በአንድ መንግሥት ላይ የምንወረውረው አይሆንም፡፡

ለሕገወጥ የስኳር ግብይትና ለዋጋ ጭማሪው የብዙዎች እጅ አለበት፡፡ ሕገወጥነትን ለመከላከልና ገበያን ለማረጋጋት ግን የመንግሥት ድርሻ ከፍ ስለሚል እየታየ ያለውን ችግር በመገንዘብ መንግሥት የስኳር ገበያን ጠጋ ብሎ መመልከት ይኖርበታል፡፡

እንዲህ ያለው ጥቆማችን የዛሬ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ የቀረበ ቢሆንም ጆሮ ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ ስለዚህ ቢያንስ አሁን መንግሥት ስኳር የሚያስገባበትን ዋጋ አሁን ከሚሸጥበት ዋጋ አንፃር መዝኖ አንድ ኪሎ ስኳር 150 ብር መሸጥ እንደሌለበት በማወቅ ዋጋ ቆርጦ ሸማቹን ሊታደግ ይገባል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት