ሰላም! ሰላም! ወገኖቼ ይህ አድካሚ ዓለም እንዴት እያደረጋችሁ ነው? አንዱን ችግር ስንሸኘው አንዱ እየተተካ መከራ አየን እኮ፡፡ በቀደም ዕለት ተኝቼ በህልሜ ይመስለኛል ሰው ሁሉ ደላላ ሆኖ አያለሁ። ሕፃኑ፣ አዋቂው፣ የተማረው፣ ያልተማረው ምን አለፋችሁ የቀረ የለም። የክፋቱ ክፋት ደግሞ ህልም ውስጥ ሆኜ ህልም እንደሆነ ገብቶኛል። ባለራዕይ ብትሆን አልፈኸው ልትሄድ ነው አትሉኝም? እንዲያው እኮ፡፡ ‹‹ለምንድነው የአዋቂ አጥፊው እየበዛ አገራችን መከራዋ አልቆም ያለው?›› ብዬ አንዱን ልጠይቀው ስጎትተው ነቃሁ። ችግራችን ብቻ መሰላችሁ ፈጣን? ህልማችንም እኮ ነው ሳንጨብጠው ሽው እያለ አስቸገረን። የምር፣ ብቻ ለማንም ምንም ሳልል ማንጠግቦሽ አገነፋፍላ የሠራችውን ቁርስ ቀማምሼ ከቤት ወጣሁ። ያው ሐሳቤ ያለው ግን የህልሜ ፍቺ ላይ ነው። ካዛንቺስ አካባቢ የቀጠረኝ ከባድ መኪና ሊገዛ የሚፈልግ ደንበኛ ስለነበረኝ የምሄደው ወደ እዚያው ነው። ስደርስ ዓይኔን ማመን አቃተኝ። አንድ ሕንፃ ሥር በግራና በቀኝ ረጅም የሰዎች ሠልፍ፡፡ ምን ተፈጠረ ብዬ ጠጋ ስል፣ ሁሉም ብብታቸው ሥር ሰነድ መሳይ ጥራዝ ይዘው ጥሪ ይጠባበቃሉ፡፡ አንዱን ልጅ እግር ቢጤ፣ ‹‹ሠልፉ ለምን ዓላማ ነው?›› በማለት ጥያቄ ሳቀርብለት ፈጠን ባለ አነጋገር፣ ‹‹አዲስ ቢዝነስ ለመጀመር ሥልጠና ለመውሰድ ነው…›› ሲለኝ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ማስታወቂያ ትዝ ብሎኝ ፈገግ አልኩ፡፡ አንዴ ፈገግ እንዲል ፎቶግራፍ አንሺ!
እንደ እኔ እንግዳ ደራሽ የሆኑ፣ ‹ምንድነው ይኼ ሁሉ ሰው?› ሲባባሉ አንዱ ወፈፍ ያደረገው፣ ‹‹እኔም መጀመርያ ወዶ ዘማች መስለውኝ ነበር። እንደ ምንም ብዬ ሳጣራ ብድር አግኝተው የሀብት ጉዞ ለመጀመር የሚያስፈልግ ሥልጠና ለማግኘት ነው አሉ በፀሐይ የሚጠበሱት…›› ብሎ ትምባሆውን እያቦነነ ጥሎን ሄደ። የልጅ እግሩንና የወፈፌውን ምላሽ ከሰማሁ በኋላ የህልሜ ፍቺ አይከሰትልኝ መሰላችሁ? አገር ምድሩ ደላላ ሆኖ ያሳየኝ ለካ የሰው ልጅ እንጀራ ፍለጋ ተንከራታች እንደሚሆን ሲገልጽልኝ ነው። እሱ ሲገልጽ ደግሞ እስከ እንጥፍጣፊው አይደል? እኔ ራሴ የድለላ ሥራ ውስጥ የገባሁት የተዋጣለት ተንከራታች ከነበርኩ በኋላ መሆኑ ትዝ አለኝ። ሁሉም ነገር ወዲያው ገባኝ። ይኼ ሁሉ ወጣት ዲግሪ ይዞ ደላላ የሆነው ወዶ መሰላችሁ? እኔ በታክሲ ስዛክር ቤቱ ቁጭ ብሎ በ‘ዋትስአፕ’ እና በ‘ቴሌግራም’ ሻጭና ገዥ፣ አከራይና ተከራይ ያገናኛል። ‘ደግሞ የዚህ አገር ዲግሪ’ አትበሉ ‘ፕሊስ’፡፡ እንኳን የተማረው ፊደል የማይለየው ማይም ሳይቀር ‘ሎግ ኢን-ሎግ አውት’ በቻለበት ዘመን እንዲህ ይባላል? ለማንኛውም ከደላላ ተራ አውጥቶ ወደ ሀብት ማማው የሚያደርስ ሥራ ፈጠራ የሚያስገኝ ሥልጠና ስለተጀመረ፣ ሥራ ፈላጊ ወገኖቼ ፈጠን ፈጠን በሉ ለማለት ነው፡፡ ‹‹ካልተሳፈሩበት ቶሎ ተሽቀዳድሞ ጊዜ ታክሲ አይደለም አይጠብቅም ቆሞ›› ተብሎ የለ፡፡ ምን ያልተባለ አለ!
በተያያዘ ጨዋታ ብዬ ልቀጥል አስቤ ሳቄ ቀደመ። ከአንድ ተራቢ ወዳጄ ጋር እያወራን ልክ እንዳሁኑ ‘በተያያዘ ጨዋታ’ ብዬ ልቀጥል ስል፣ ‹‹ምን ማያያዝ ያስፈልጋል? ከተያያዘ ዝም ብለህ አትቀጥልም? ደግሞ ከመቼ ወዲህ ነው ጨዋታ የሚያያዘው አንበርብር? አንተም እንደ ዘመኑ ወሬ አነፍናፊዎች አንዱን ከሌላው እያማቱ ማውራት ተጋባብህ?›› አለኝ። ነግሬያችሁ እንደሆነ አላውቅም እንጂ ሰበር ዜናን ልክ እንደ ‘ሲሪየስ ፊልም’ በ‘ሲዝን’ የሚያዘጋጅ ብቸኛ ዘጋቢ የእኛዎቹ ዩቲዩበሮች ናቸው ብሎ ያምናል። ለምሳሌ ባለፈው ሰሞን በተከታታይ የተለቀቁ አዕምሮ ግራ አጋቢ አገራዊ አጀንዳዎችን፣ አንዱን ከአንዱ በማምታታትና በቀጭን መስመር በማያያዝ ዩቲዩበሮቻችን የሽቀላ ጥማቸውን ያፋፍማሉ ይላል። እናም እንዲህ እያለ ይቀልዳል። ራሱ ቀልዶም ራሱ ይስቃል። ቀልደው የሚስቁ ጤነኞች ናቸው ብለን እንለፈው። አንተላለፍ ብለን እኮ ነው እንጂ መንገዱም በነገር ፈላጊዎች ያዝ ተደርጓል፣ አልሰማችሁም እንዴ? ብዙ ሰምተናል!
ምን ላያይዝ ነበር ተያይዤ የቀረሁት እናንተ? ውሎ አድሮ ህልሜንና ግጥምጥሞሹን ለባሻዬ አጫወትኳቸው። ሥጋቴን አልተናገርኩም። ሁሉንም ዝርግፍ ማድረግ ባህላችን አይደለም። እሳቸው ምን አሉኝ ታዲያ፣ ‹‹አሁንስ ቢሆን ደላላ ያልሆነ ማን አለ?›› ብለው ጀመሩ። ‹‹እንዴት?›› ስላቸው፣ ‹‹በዓይንና በከንፈር ውበት፣ በፎቶሾፕ የፈረጠመ አካል፣ ማር ማር በሚል አነጋገር፣ በአማላይ ቅስቀሳ፣ በአለባበስ ዝነጣ፣ በቄንጠኛ አሾፋፈር፣ ኧረ ምኑ ቅጡ። ምን የማንደለልበት ነገር አለ?›› ሲሉ ‘እውነታቸውን እኮ ነው’ እያልኩ በልቤ ፈዝዤ ቀረሁ። ‘እኔ ቤቴ ወገብ የሚሰብር አልጋ ላይ እየተኛሁ፣ እከሌ ተንቀባሮና ልጥጥ ብሎ ዘመናዊ መኪና የሚነዳው ማን ስለሆነ ነው?’ አለኝ በቀደም መጥቶ ‘ኮሮላ’ ያጋዛሁት ደንበኛ። በኋላ ሲጣራ ለካ ‘እከሌ’ የሚባል ሰው መንግሥት መሥሪያ ቤት በሹፍርና ተቀጥሮ ‹‹V8›› ሲነዳ ዓይቶት ነው። አንዱ ደግሞ ‘ፌስቡክ’ ላይ የተዋወቃት ልጅ ነበረች አሉ። ገና በአካል ሳይተያዩና ሳይጨባበጡ ሌት ተቀን እንጋባ እያለች አላስቀምጥ አለችው። ‘በቃ ላገባ ነው’ ብሎ አካባቢውን አተራመሰው። ‘እሰይ’ ተባለ። ያው ከላይ እስከ ታች መበደር ነው የምናውቀው፣ ቤተሰብ ተበዳድሮ ደገሰ። እንዲያው ግን፣ ‘ሙሽሪትን ይዘሃት መጥተህ አስተዋውቀን እንጂ’ ምናምን አይባልም? ለምንድነው ለድግስና ለጭፈራ የምንቸኩለው? ኧረ የአስተርጓሚ ያለህ!
እንዳይደርስ የለ የሠርጉ ቀን ደረሰና ሙሽሪት ቤት ‘ፌስቡክ’ ላይ በተለጠፈላቸው የጉዞ መመርያ (GPS መሆኑ ነው) እየተመሩ ሚዜዎችና አጃቢዎች ደረሱ አሉ። የወጉን ‘እንግባ አናስገባም’ ተብሎ ተጋፍተው ሲገቡ ሙሽራው ድንገት በቆመበት ተዝለፍልፎ ወደቀ። ይቅርታ ለካ ‘ፌንት በላ’ ነው የሚባለው። ‘ሶሪ!’ ሽብር ሆነ። ‹‹ምንድነው?›› ሲባል የሚናገር የለም። ገሚሶች ቀዝቃዛ ውኃ ሲቸልሱበት ገሚሶቹ ደግሞ የሳትነው መመርያ እንዳለ ብለው የሙሽሪትን ‘ፌስቡክ አካውንት’ መጎርጎር ይጀምራሉ። ለካ አጅሪት ሌላ፣ መከረኛው ‘ፌስቡክ’ ላይ የተሰቀለው ፎቶዋ ዕንቁ የመሰለች ሞዴል ሌላ። በአጭሩ አልተገናኝቶም ሆኖ ነው። እንኳን ሙሽራው ሚዜዎችና አጃቢዎች ‘ፌንት’ ከማድረግ የተረፉት ውኃ ቶሎ መረጨት በመጀመሩ ነው ተባለ። ደግሞ ይኼንን ሰምተው ነገር ጠምዛዦች ሕዝቡ በረሃብ እየረገፈ ነው ብለው እንዳያወሩ እንጂ ‘ፌንት’ መብላቱስ ግድ የለም ይደርሳል፡፡ ለማንኛውም ይህ ወሬ ሰሞኑን አንዱ ፌስቡክ አካውንት ላይ ተለጥፎ ነበር የከረመው፡፡ ለማንኛውም ይሰውራችሁ ነው የሚባለው!
እንዲህ ዓይነቱን ነገር ሳስታውስ ስማችን እንዳይበላሽ ፈራሁ። ለነገሩ ምን ያልተበላሸ ስም አለን? የዚያን ደንበኛዬን ጉዳይ ዳር ለማድረስ እየተጣደፍኩ ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር ጥቂት ሰዓት ሳገኝ ፍርኃቴን ነገርኩት። እሱ ደግሞ ያው ከያዘ የማይለቅ ነው እንደምታውቁት። በተማረና ባልተማረ መሀል ያለው የሞጋችነት ልዩነት ሰፊ መሆኑ ቢታመንም፣ የምሁሩ የባሻዬ ልጅ ግን ከምሁራኑ ተርታም ቢሆን ለየት ያለ ነው። ‹‹አንተ ደላላ የሚለው ስም ተበላሸ ብለህ ትጨነቃለህ? ምን ያልተበላሸ ስም፣ ምን ያልተወላገደ ትርጓሜ ያልያዘ ስም አለ? ነጋዴ ብትል፣ መንግሥት፣ ፍትሕ ብትል ዴሞክራሲ፣ ምርጫ ብትል ኮሚቴ፣ ስብሰባ ብትል ቢሮክራሲ ምን ትርጉሙን ያልሳተ ስም አለ?›› ሲለኝ የት ልግባ? የት ልግባ? ‹‹ኧረ እባክህ ሰው እንዳይሰማ ድምፅህን ቀነስ አድርግ…›› ስለው፣ ‹‹ሰው ብትል ፈጣሪ፣ ወንድ ትላለህ ሴት፣ ባል ትላለህ ሚስት …›› እያለ ቀጠለ። ‘ምን ዓይነት ጣጣ ነው በገዛ እጄ እስኪ አሁን’ አልኩና ጥዬው ላጥ። ደሳሳ ጎጆዬን አቀና ብዬ ጠማማ ስያሜ ስቆጥር ለጥያቄ ብጠራ ለማን አቤት እላለሁ? የ500 ሆነ የ5,000 ብር ጥያቄ አለ ብልስ ማን አቤት ሊለኝ? አይደል እንዴ? እናም ባገኘው ቦታ ሁሉ ነገር እየዘረገፈ ያስቸገረኝን የባሻዬን ልጅ ምን እንደማደርገው እያሰብኩ ስጓዝ አንዱ ሊስትሮ ‹‹ይጠረግልሽ? ነይ ቁጭ በይ…›› ሲለኝ ሰማሁት። ዘወር ብዬ ሳየው አንድ ፍሬ ልጅ። ‘አሁን ከዚህ ልጅ ጋር ፆታዬን መልስ፣ አልመልስም’ ትግል መግጠም አለብኝ? ብዬ እሱንም ጥዬው ሄድኩ። ታዲያ በዚህ ዓይነት በየሄድንበት ከታገልንማ ‘ምን ያላልንበት ዳገት የለም ካለችው እንስሳ በምን ተሻልን? ነገሩን ማለቴ ነው፡፡ ደግሞ ሌላ ነገር እንዳታመጡ!
እናላችሁ እንዲያም እንዲህ ብሎ ሥራ ሳልሠራ አላድርም። ደንበኛዬን የሚፈልገውን መኪና አጋዝቼው ‘ኮሚሽኔን’ ስቀበል ደግሞ ሌላ መጣ። ይኼኛው ዳያስፖራ ነው። የአገሪቷን ዕድገትና ፈጣን ለውጥ ታዝቦ ‘ኢንቨስት’ ለማድረግ እንዲመቸው ስድስት ወራት መቆየት ይፈልጋል። ለእሱና ነፍሰ ጡር ባለቤቱ የሚሆን እስከ 60 ሺሕ ብር የሚከራይ ቤት አግኝቼለት ሳሳየው ሰውዬው የለም። ‘አይ ሀብታም መቼ ይሆን ዳያስፖራ ያለው?’ እያልኩ በውስጤ ሐሳብ እንዳበዛ ስነግረው፣ ‹‹ምን ላድርግ ብለህ ነው?›› ብሎ ጀመረ። ‘እንዴ ዳያስፖራም የሚያደርገው ያጣል? እንደ እኛ ሰው ነው?’ እያልኩ፣ ‹‹ምነው ችግር አለ?›› ስለው፣ ‹‹ሚስቴ አላስቀምጠኝ ብላለች። ለአገሯ አፈር አብቅቻት አፈር አማረኝ ትላለች። ጉለሌ አልቀረኝ ኮተቤ፣ መረሬ ትላለህ ቀይ፣ ዘግኜ ስወስድ ‘የለም ያማረኝ የ‘ስቴት’ አፈር ነው’ አትለኝ መሰለህ? ተመልሶ እዚህ በመምጣቱ ሐሳብ መጀመርያም ደስተኛ አልነበረችም፣ ለነገሩ…›› ብሎ በብስጭት ተወራጨ። ‘እግዚኦ፣ ሰው በስንቱ አፈር ይልሳል?’ እያልኩ እንደ ምንም ቤቱን እንዲከራየው አግባባሁት። አደራ ለማንጠግቦሽ አልነገርኳትም ከአፋችሁ እንዳይወጣ። ደግሞ በኋላ ‘ዳያስፖራ’ መሆን አማረኝ ብትለኝ ‘አፈር ስሆንልሽ?!’ እያልኩ ለምኜም እንደማልይዛት አውቄዋለሁ። እህ፣ ጠፍቶ የኖረው ሁሉ ሲመለስ ፍሪዳ እየታረደ ሲያይ ቤት የሰነበተው ‘ሂድ ሂድ’ አይለውም ሊባል ነው? እንዴት ያለ የዋህነት ነው በፈጣሪ!
በሉ እንሰነባበት። ኮሚሽኔን ተቀብዬ ለተወሰኑ የጠርሙስ ቢራዎች የሚሆነኝን ቆንጥሬ፣ የቀረውን ቤት ቀርቅሬ ወደ ተለመደችዋ ግሮሰሪ አመራሁ። እንደገባሁ በሩቁ ያየሁት ምሁሩን የባሻዬ ልጅ ነው። ምን አዲስ ነገር ይኖረው ይሆን እያልኩ ሄጄ አጠገቡ ተቀመጥኩ። እሱ እንደለመደው መናገር ሲጀምር፣ ‹‹ምንም ቢሆን ያለኸው ሦስተኛው ዓለም ነው…›› ሲል አንዱ ከሩቅ ልክ ውሎ ገባችን እንደሚያውቅ ሁሉ ሲናገር ሁለታችንም ክው አልን። ለካስ ሰውዬው ሌላ ጨዋታ ይዞ ነው። ቀዝቃዛውን ቢራ እየተጎነጨን ዕፎይ ከማለታችን፣ የባሻዬ ልጅ በጥሞና አንድ የግሪክ አፈ ታሪክ አጫወተኝ። ‹‹ሲሲፈስ ይባላል። በግሪክ አፈ ታሪክ የኦሎምፒያ አማልዕክት ዋና አለቃ በሚባለው ዚውስ የተፈረደበት ግዞተኛ ነው። ዚውስ የፈረደበት የባህር አምላክን ሴት ልጅ ጠልፎ ሲያስወስዳት ሲሲፈስ ዓይቶ ለባህር አምላክ ስለነገረው ነው። ፍርዱ ምን ይመስልሃል ታዲያ አንበርብር?›› አለኝ። እንዲህ በተረትና በምሳሌ ሲያጫውተኝ ደስ ስለሚለኝ፣ ‹‹አንተው ንገረኝ እንጂ እኔ ማይሙ ምኑን አውቄ?›› አልኩት ፈታ እያልኩ። ‹‹ፍርዱ አንድ ረጅም ተራራ ጫፍ ላይ እንደ ኳስ የሚንከባለል ግዙፍ ቋጥኝ እየገፋ ማድረስ ነው። አደረስኩት ሲል ቋጥኙ ግን ተመልሶ ይንከባለላል። በአጠቃላይ የእኛም ነገር እንደ ሲሲፈስ ሲሆንብኝ እየተናነቀኝ ነው…›› ሲለኝ በሚገባ ተረዳሁት። በተለይ በተለይ፣ የተበላሹ ስሞቻችን ካልተስተካከሉ ትውልድ የሲሲፈስን ታሪክ ሲቀባበል እንደሚኖር ተገለጸልኝ። የተማረ ይግደለኝ እንዳልል ያልተማረ ነው የሚቀብረኝ። እስኪ ከሕልፈታችን በፊት የተበላሹ ስሞቻችን ይስተካከሉ። ‘የተማረ እየገደለ ያልተማረ ይቀብረናል’ የሚለው አባባል ምን ማለት ነው? ቆይ ግን በሰከነ መንፈስ ስናይ እኮ አባባሉ ከበድ ይላል፡፡ ሰከን ስንልና ሰከር ስንል ልዩነቱ ቁልጭ ብሎ ይታየናል፡፡ ሰከን ያሉት አስተውሎት አላቸው፡፡ የሰከሩት ደግሞ ጌሾ ወስዷቸዋል፡፡ በመታበይ ጌሾ የሰከሩት መሰሉኝ ነጋ ጠባ የሚበጠብጡን፡፡ አሁን ግን የማይነካ እየነካኩ ነውና እንጃላቸው፡፡ መልካም ሰንበት!