Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ቀን:

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡ በተለያዩ ቦታዎች የተከሰቱ ግጭቶች ያደረሱት ውድመት በቅጡ ሳይጠገን ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችም ወደቤታቸው ሳይገቡ ከሁለት ዓመታት በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ጦርነት ይበልጡኑ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊና ፖለቲካዊ ኪሣራ አድርሷል፡፡

ከሦስት ወራት በፊት በተደረሰ የሰላም ስምምነት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መፍትሔ ቢያገኝም፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በብሔር የሚነሱ ግጭቶች ለኢትዮጵያ ፈተና ሆነዋል፡፡

ግጭቶች ለኢትዮጵያውያን ከመከራ በስተቀር ለውጥንና ዕድገትን አላመጡም፡፡ በተቃራኒው ለሰዎች ሞትና ስቃይ እንዲሁም ለንብረት መውደም ምክንያት ሆነዋል፡፡ ግጭቶች ወደ ጥቃት ከመቀየራቸው በፊት መፈታት ባለመቻላቸውም ኢትዮጵያውያን ለዛሬው ውጥንቅጥ ተዳርገዋል፡፡ መስዋዕትነት እየከፈሉም ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

መሠረታዊ ችግሩ ከምን ይመነጫል?

የእርቅና የሰላም ባለሙያና አማካሪ አቶ ጋረደው አሰፋ እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ ለምትገኝበት ሁኔታ በተለይ ከግጭቱ፣ ከብጥብጡና ከጦርነቱ ጋር የተያያዘው ችግር ራስን በአግባቡ ካለማየት፣ ካለመፈተሽና እውነትን ከመካድ የመነጨ ነው፡፡

በግጭት ወይም በብጥብጥ ምክንያት የሞቱ፣ የተፈናቀሉ፣ በችግርና ድህነት ውስጥ ያሉት ኢትዮጵያውያን ሲታዩ፣ ኢትዮጵያን በዓለም በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ አገሮች ያስቆጥራታል፡፡ ይህ ደግሞ ባለፉት አራት ዓመታት ተባብሶ ይገኛል፡፡

‹‹ለችግሩ መነሻው ራስን መካድና መጋፈጥ አለመቻል ነው›› የሚሉት አቶ ጋረደው፣ ሰላም ሳይኖር ሰላም ነው፣ ዕድገት ሳይኖር ዕድገት አለ የሚሉና ሌሎችንም በተመለከተ ራስን ለማሳመን የሚዋሸው ውሸትና የተሄደበት ርቀት ለችግሩ እንዳደረሰ ይገልጻሉ፡፡

ይህ በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት፣ በኢኮኖሚ፣ በሃይማኖት ጉዳዮችና በሌሎችም ውስጥ ያለ ችግር ሲሆን፣ ችግሩና ሕዝቡ ያለበትን ሁኔታ ተረድቶ ለዚያ ተመጣጣኝ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ይህንን ለመቀባባትና በሕዝቦች መካከል መከባበር ሳይኖር መከባበር እንዳለ፣ ሃይማኖቶች እየተናቆሩ የሃይማኖት ኅብረት እንዳለ ማስመሰል እንዲሁም ራሱን እንደተለየ ማኅበረሰብ አድርጎ መቁጠር ችግሩን ማባባሱንም ያክላሉ፡፡

ለአብነት ያህልም፣ በብሔር ስብጥር ራስን በጣም ብዙ አድርጎ ማቅረብ፣ ብዙ የተለያየ ሃይማኖት እንዳለና በውስጥ መቻቻል አለ ብሎ ማስመሰል፣ በሕዝቦች መቻቻል በዓለም አንደኛ እንደተሆነ አድርጎ መናገርና በአጠቃላይም እውነቱን በመሸፋፈን ብዙ ርቀት መኬዱ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ቀውስ መዳረጉንም ይናገራሉ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ 80 ብሔር ወይም ቋንቋ አለ ቢባልም ይህ ከሌሎች አገሮች የተለየ እንዳልሆነ፣ ናይጄርያ ከ200 በላይ፣ ብራዚል ከ300 በላይና በሌሎችም አገሮች ብዝኃነት መኖሩን፣ በኢትዮጵያ ብዙ ብሔር አለ፣ ተቻችሎም ይኖራል ብሎ ከማውራት ይልቅ፣ በብዝኃነት እንዴት በጋራ መኖር ይቻላል? ሌሎች አገሮች ልዩነታቸውን ይዘው እንዴት በጋራ ኖሩ? ብሎ ከመጠየቅና ወደ መፍትሔው ከመምጣት በተፃራሪ ችግሩ የተሸፋፈነበት መንገድ የተሳሳተ መሆኑም ለግጭት እንዳደረሰም ገልጸዋል፡፡

ችግሩን የሚያጎላው ማነው? መሪዎች? ልሂቃን? ወይስ ሕዝብ?

እንደ አቶ ጋረደው፣ በአጠቃላይ ሲታይ የማኅበረሰብ ወይም የሕዝብ ጦርነት የለም፡፡ ሕዝብ እንዋጋ ብሎ ወደ ጦርነት፣ እንጋጭ ብሎ ወደ ግጭት አይገባም፡፡ ትልቁን መኪና ትንሽ ሞተር እንደምታንቀሳቅሰው ሰዎችንና ሕዝብን ወደ ግጭት የሚመሩት ልሂቃንና በፖለቲካ፣ በሃይማኖትና በሌሎችም ዘርፎች ያሉ መሪዎች ናቸው፡፡ ወደ ጦርነት የሚያስገቡት ደግሞ ለሕዝብ ጥቅም ሳይሆን ለራሳቸው በሆነ ጥቅም ነው፡፡ እነሱ በአብዛኛው የሚጣሉት በሀብትና በሥልጣን ሲሆን፣ ይህንን ለማሟላት ሲፈልጉ ሕዝብን ከኋላቸው አድርገው ይማግዳሉ፣ እንደ መሣሪያ ይጠቀሙበታል፡፡

ይህ የተለመደና በዓለም ላይ በተከሰቱ ትልልቅ ጦርነቶች ውስጥ የታየም ነው፡፡ ለአብዛኞቹ ጦርነቶች መነሳት የሆኑትም ሁለት ሰዎች ናቸው፡፡ በደቡብ ሱዳን በርካታ ሰዎች እንዲያልቁ ምክንያት የሆነው ግጭት የተነሳው በሁለት ሰዎች ነው፡፡ በኢትዮጵያም የተፈጠረው ጦርነትና ብጥብጥ በጥቂትቶች ምክንያት ነው፡፡

ሕዝብ የማይመቸው ጉዳይ ላይ የዴሞክራሲ፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ ጥያቄ ሊያነሳ ይችላል፡፡ ይህ ብሶት ሲኖር፣ መሪዎች፣ ልሂቃን ተማርን ያሉ ሰዎች ለግጭት ምክንያት ያደርጉታል፡፡ የሚስፋፋው ደግሞ ባለማወቅ፣ በድንቁርናና በጅምላ ማሰብ ውስጥ ባሉት ነው፡፡ ጦርነት የሚያስነሱት ጥቅማቸው በሚሊዮን የሚቆጠር ሊሆን ቢችልም፣ የሚወድመው በቢሊዮንና ከዚያ በላይ በሚቆጠር ነው፡፡ በጦርነት የሚያልቀውም ሕዝቡ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም በማኅበረሰቡ ውስጥ የሥነ ልቦና፣ የመስተጋብርና ሌሎችም ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡

መፍትሔው ምንድነው?

‹‹ካለፈው ልምዳችን መሪዎች ተጣልተው ሲታረቁ እንዴት እንደምናጨበጭብ እንደገና ሲጣሉ እንዴት እንደምንኳረፍ አሁን በሕይወት ያለን ምስክሮች ነን፤›› የሚሉት አቶ ጋረደው፣ ጠቀላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ከአራት ዓመታት በፊት ኤርትራ ገብተው ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ባደረጉት መጨባበጥ ኢትዮጵያና አስመራ ውስጥ የነበረው ደስታ የሚዘነጋ አለመሆኑን ያስታውሳሉ፡፡

‹‹ይህ ጥሉ የሕዝብ እንዳልነበር ለማሳየት በቂ ነው፡፡ በመሆኑም ለመፍትሔው መሠራት ያለበት በሕዝቡ ላይ ሳይሆን በመሪዎች ላይ ነው፤›› በማለትም፣ ከከፍተኛ እስከ መካከለኛ አመራሮች ላይ ከተሠራ በሕዝብ መካከል ያለውን ለማስተካከል ቀላል እንደሆነ፣ የኢትዮጵያ የችግር ማነቆ ያለው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ባሉት በመሆኑ እነሱ ላይ መሥራት እንደሚገባና የላይኛው አካል ካልተረዳና ካልተስተካከለ ሰላምን ማምጣት እንደማይቻል ይጠቁማሉ፡፡

እውነተኛ የሆነና ማስመሰል የሌለበት ጥልቅ ውይይት ማድረግ፣ የተጠያቂነት ሥርዓት መዘርጋትና ሰላም ተኮር ሥራ የሚሠራበትን ማስተካከልም ከመሪዎች ይጠበቃል፡፡

አክቲቪስቶችና በየትኛውም መስክ ያሉ አመራሮች ወደቀልባቸው ተመልሰው የአገራቸውን ችግር መፍታትም አለባቸው፡፡ ብዝኃነት ቢኖርም እየተከፋሉ አገር ማበልፀግ ስለማይቻል አብሮ፣ በጋራና በውበት የሚሠራበት መንገድ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን በሰላማዊ መንገድ ለማምጣት መሪዎችና ልሂቃን ወደቀልባቸው ተመልሰው መነጋገር፣ መመካከርና ለሕዝብ ተጠያቂ በሚሆኑበት መስመር መሄድ አለባቸው፡፡

ለዚህ በጎ ህሊናና ፈቃደኝነት ያስፈልጋል ያሉት አቶ ጋረደው፣ መሪዎች ወደ ውይይት ከመጡ ኢትዮጵያ ውስጥ የማይፈታ ችግርና ግጭት እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

በከፍተኛ የሥልጣን እርከን ደረጃም ሆነ በመካከለኛ ደረጃ ላሉት ባለሥልጣናት ፖለቲከኞች ችግራችሁን ፍቱ ብሎ ማን ይንገራቸው?

እንደ አቶ ጋረደው፣ ይህ የሁሉም ኃላፊነት ነው፡፡ ባለሙያውም፣ የአገር መፍረስና መጎዳት የሚታየው ሰውና መገናኛ ብዙኃን በሙሉ ጥፋተኝነታቸውን በሚያሳይ መንገድ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡

መንግሥት ይቀያየራል፡፡ በመሆኑም ሰለማዊ በሆነ መንገድ አንዳንዶችን በማሠልጠን፣ በማኅበረሰቡ በኩል ተፅዕኖ በመፍጠር እነዚህ ሰዎች ወደ ሰላም እንዲመጡ መምከር ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም ተረባርቦ መናገር ከቻለና ጥቂት ሰዎች እጅ ላይ ያለውን ቁልፍ ካስከፈተ፣ ማኅበራዊ ሀብትን ተጠቅሞ ሰላሙን ማምጣት ይቻላል፡፡

በማኅበረሰቡ ውስጥ በዕድርና በዕቁብ በመጠቀም፣ በመመካከር፣ በመነጋገር፣ በሽምግልናና በሌሎችም መንገዶች ሰላምን ማበልፀግም ይቻላል፡፡ ለዚህ ደግሞ በመንግሥት የማይመራ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና እርቅ ያስፈልጋል፡፡

ምክክሩን ሕዝብ ሊመራው እንደሚችል፣ ኢትዮጵያ 80 ብሔር ቢኖራት፣ ከእያንዳንዱ ሁለት ሁለት የተከበሩና በማኅበሰቡ የሚደገፉ ቢመረጡ፣ የእርቅ ካውንስል ቢያቋቁሙ፣ ከእነዚህ ውስጥ እንደ ዴዝሞንድ ቱቱ ያሉ ተመርጠው ኮሚሽን ቢኖርና እነዚህ የብሔርና የተለያዩ ጥያቄዎችን የሚያነሱ ፖለቲከኞችን እየጠሩና እያወያዩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር በሐቀኝነት ቢሠሩ፣ ችግሩ ከዚህ የሚያልፍ አይሆንም፡፡ ነገር ግን በዚህ መልኩ እንዲሠራ ይፈለጋል ወይ? የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ማንንም ሰው የመጥራትና ወደ አገራዊ ምክክሩ እንዲገባ የመጠየቅ ሥልጣን ስላለው በቅንነት፣ በተነሳሽነት፣ በአስተሳሰብ ልቀው፣ ያለባቸውን የሕዝብ ኃላፊነት በመረዳት በአገር ውስጥና ውጭ ያሉትን ልሂቃን ሁሉ ወደ መድረክ እንዲመጡና እንዲወያዩ ማድረግም ይጠበቅበታል፡፡ ያለውም አማራጭ ፖለቲከኞች ተወያይተው ችግሩን እንዲፈቱ ማድረግ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...