Friday, July 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ፈቃድ ያገኙ የሬዲዮ ይዘቶች በቴሌ መተግበሪያ ቀረቡ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ኢትዮ ቴሌኮም ከዓመታዊ ገቢው ከአሥር በመቶ በላይ በአጋር ድርጅቶች በኩል ለማግኘት አቅዷል

ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ፈቃድ ያላቸው ተቋማትና ግለሰቦች፣ የሬዲዮ ፕሮግራም ይዘቶችን እንዲያቀርቡ የሚያስችል አገልግሎት በቴሌ መተግበሪያ መቅረብ ጀመረ፡፡

አገልግሎቱን የሚያቀርቡ ግለሰቦችና ድርጅቶች እንደ መደበኛ የሬዲዮ ሥርጭት ይዘቶች አስፈላጊ የመሠረተ ልማቶች/የስቱዲዮ ፋሲሊቲ ማሟላት ሳያስፈልጋቸው፣ በግል ኮምፒዩተር ብቻ የሬዲዮ ቀጥታ ሥርጭት ሊያቀርቡ የሚችሉበት አማራጭ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ‹‹ኩሉ ኔትወርክ›› ከተባለ ድርጅት ጋር በመሆን ያቀረበውና ‹‹እልፍ ፕላስ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው የሥርጭት አውታር (ስትሪሚንግ ፕላትፎርም)፣ የአገር ውስጥና የውጭ አገሮች የሙዚቃና የሬዲዮ አገልግሎት አማራጮችን ይዞ ይቀርባል ተብሏል፡፡

በመተግበሪያው በተለምዶ የሬዲዮ ሥርጭቶች ከሚቀርቡበት መንገድ በተለየ አድማጮች በቀላሉ እንዲያደምጡ ከማስቻሉ በተጨማሪ፣ የፕሮግራም አዘጋጆች ቢሮ ውስጥ ተገድበው በአንቴና ሥርጭት ታግዞ የሚያቀርቧቸውን ይዘቶች በኢንተርኔት አማካይነት በቀላሉ እንዲያቀርቡ ያስችላል ተብሏል፡፡

በሦስት ዘውግ ተከፍሎ በሚቀርበው የሬዲዮ አገልግሎት የሕግ፣ የሕፃናትና የቤተሰብ፣ የድለላና ግብይት፣ የዓለም አቀፍ ሙዚቃ ይዘቶች የሚቀርብባቸው አገልግሎቶች የመጀመሪያዎቹ ናቸው፡፡ መንፈሳዊ ይዘት ያላቸው አገልግሎቶች በመተግበሪያው ከመቅረባቸውም በላይ፣ የአገር ውስጥ የኤፍኤም ሬዲዮ ሥርጭቶችንም በመተግበሪያው ማድመጥ የሚቻል መሆኑ ተገልጿል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም እልፍ ፕላስ የሙዚቃ ስትሪሚንግን ጨምሮ፣ ክላውድና ቴሌድራይቭ (የሞባይል መረጃ ቋት) የተሰኙ አገልግሎቶችን ከአጋሮቹ ጋር ስምምነት በመፈጸም ይፋ አድርጓል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ሼድሊ ትሬዲንግ ፒኤልሲ ከተባለ ድርጅት ጋር ይፋ ካደረጋቸው አገልግሎቶች መካከል ቴሌድራይቭ አንዱ ነው፡፡ በአገልግሎቱ ደንበኞች በሞባይል ስልኮቻቸው ላይ የሚገኙ እንደ ፎቶ፣ ቪዲዮና የመሳሰሉ ከፍ ያለ መጠን ያላቸውን ፋይሎች አስተማማኝ በሆነ የክላውድ መረጃ ቋት ማስቀመጥ ሲፈልጉ ማግኘትና መጠቀም የሚችሉበት መፍትሔ ነው ተብሏል፡፡ በተጨማሪም የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚዎች የሞባይል ስልካቸው ቢጠፋ ወይም ቢበላሽ ፋይሎቻቸውን መልሰው ማግኘት የሚያስችላቸው አገልግሎት መሆኑን፣ የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ማርኬቲንግ ኦፊሰር አቶ ሰይድ ዘርጋው ተናግረዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የግልና የመንግሥት ተቋማት ከፍተኛ የመረጃ ክምችትና አጠቃቀም፣ እንዲሁም ተዛማጅ የክላውድ አገልግሎት ፍላጎትን መሠረት በማድረግ አስተማማኝ የክላውድ ማዕከላት መሠረተ ልማት በማሟላት ቴሌክላውድ አገልግሎትን ለደንበኞቹ ማቅረቡን አስታውሶ፣ አሁን ደግሞ ዘርጋው ከተባለ የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢ ጋር በመተባበር የክላውድ ሶሉሽን አገልግሎቶችን በተለያዩ አማራጮች ማቅረቡን አስታውቋል።

ዘርጋው የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢ ከተባለው ድርጅት ጋር የቀረበው አገልግሎት፣ ተጠቃሚዎች እንደ አስፈላጊነቱ ካሉበት ሆነው የግል መረጃዎቻቸውን ማስቀመጥ፣ መቀመር፣ ለደንበኞቻቸው የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችል የክላውድ አገልግሎት ነው፡፡ በተጨማሪም ደንበኞች የተለያዩ በውጭ ምንዛሪ የፈቃድ ክፍያ በመክፈል ያገኟቸው የነበሩ ሶፍትዌሮችን፣ በተመጣጣኝ ክፍያ በብር ማግኘት የሚችሉበት አገልግሎት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ በበኩላቸው፣ ኩባንያው ከተያዘው ዓመት አንስቶ ለሦስት ዓመታት ተግባራዊ ባደረገው የሦስት ዓመታት ዕቅድ የሚያቀርባቸው አገልግሎቶች ለብቻው ሳይሆን አጋር አካላትን በማስተባበር ለማቅረብ መነሳቱን አስታውቀዋል፡፡

ለአብነትም በዓመቱ መጨረሻ ኩባንያው አገኘዋለሁ ብሎ ከሚጠብቀው የ75 ቢሊዮን አጠቃላይ ገቢ ውስጥ አሥር በመቶ ወይም 7.5 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን፣ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በሚያቀርባቸው አገልግሎት ለማግኘት ማቀዱን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች