Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበቅርቡ የተሾሙት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወቀሳ ተሰነዘረባቸው

በቅርቡ የተሾሙት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወቀሳ ተሰነዘረባቸው

ቀን:

በቅርቡ በተደረገው የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ሹመት የቀድሞው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ግሩፕ ዋና ዳይሬክተርን ተክተው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው የተሾሙት አቶ አብዱራህማን ኢድ ጣሂር፣ ፓርላማ ለስብሰባ ተጠርተው ባለመቅረባቸው ምክር ቤቱን ‹‹ንቀዋል›› ተብለው ወቀሳ ተሰነዘረባቸው፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ወቀሳው የተሰነዘረባቸው ማክሰኞ ጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የፕሮጀክት ግንባታ አፈጻጸምን በተመለከተ የ2013 እና 2014 ዓ.ም. የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ውይይት ለማድረግ በደብዳቤና በስልክ ጥሪ ተደርጎላቸው ባለመገኘታቸው ነው፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ እንደተናገሩት፣ አቶ አብዱራህማን ከዚህ በፊት የነበሩ ሥራዎችን በተመለከተና በቀጣይ የሚቀመጡ አቅጣጫዎችን እንዲወስዱ፣ የኦዲት ግኝት እንዲስተካከል፣ የሚጠበቅባቸውን የአመራር ኃላፊነት እንዲወጡ፣ ለመንግሥት ተጠሪ ጭምር ተነግሮ እንዲመጡ የተነገራቸው ቢሆንም መገኘት አልቻሉም፡፡

- Advertisement -

አክለውም፣ ‹‹ይህ ፍጹም ስህተት ነው፣ የምክር ቤቱን ግርማ ሞገስ ያዋረደ ነው፣ በዚህ ዓይነት መንገድ ማስቀጠል ስለማንችል በቀጣይ ማስተካከያ ይደረጋል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹አቶ አብዱራህማን ያደረግንላቸውን ጥያቄ በመናቅ ጭምር በመካከላችን አልተገኙም፣ ይህንን እንግዲህ ከሚመለከተው የሥራ ክፍል ጋር ተነጋግረን ተገቢው የእርምት ዕርምጃ እንዲወሰድ እናደርጋለን፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

‹‹በመሆኑም ይኼ ምክር ቤት ነው፣ ምክር ቤቱ የኦዲት ግኝትን መነሻ በማድረግ ማንኛውንም የሥራ ኃላፊና ባለሙያ ጠርቶ የማናገር መብቱ የተጠበቀ በመሆኑ፣ እኛ በስልክ ጭምር አናግረናቸዋል፡፡ በመካከላችን ተገኝተው ለምናቀርባቸው ጥያቄዎች እንደ አመራርና ሥራ አስፈጻሚ መውሰድ ያለባቸውን እንዲወስዱ ቢጠሩም አልተገኙም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ዋና ሥራ አስፈጻሚው በዚህ መድረክ እንዲገኙ ተጠርተው አለመገኘታቸው፣ ይኼ ምክር ቤቱን የመናቅና ክብር ያለ መስጠት እንቢተኝነት ተደርጎ ይወሰዳል፤›› በማለት አቶ ክርስቲያን ጠንከር አድርገው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ይዞ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ግሩፕ፣ ከአንድ ዓመት በፊት በሚኒስትሮች ደንብ የተቋቋመ ነው፡፡ ዓላማውም የመንግሥት ሀብቶችንና የሀብት ምንጮችን በማስተዳደርና ተገቢ የሆነ አመራር በመስጠት፣ ከፍ ያለ የውጭ ኢንቨስትመንት፣ ቴክኖሎጂ መሳብና ትርፍን መሠረት አድርጎ የተቋቋመ ነው፡፡

ይሁን እንጂ የኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ግሩፕ ውስጥ ከሚገኙት ድርጅቶች አንዱ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከደንበኞች በውል የተረከባቸውን ፕሮጀክቶች ውል በገባበት ጊዜ ገደብ አለማጠናቀቅ፣ ለፕሮጀክቶቹ የሚያፀድቃቸውን ወርኃዊና ዓመታዊ ዕቅዶች በተሟላ ሁኔታ አለመፈጸም፣ መሰብሰብ የነበረበት በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አለመሰብሰብና በርካታ ችግሮች ተነስተውበታል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ምንም እንኳ ለትርፍ የተቋቋመ የልማት ድርጅት ቢሆንም፣ በኦዲት ሪፖርቱ ኮንትራት ወስዶ ለሠራቸው ሥራዎች የክፍያ ሰርተፊኬት በአማካሪው መሃንዲስ አፀድቆ ለአሠሪው በተላከ በ30 ቀናት ውስጥ ተከታትሎ ክፍያውን የማይሰበስብ መሆኑንና በአጠቃላይ ከተለያዩ ተቋማት የክፍያ ሰርተፊኬት ተዘጋጅቶ ያልተሰበሰበ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ መኖሩ ተረጋግጧል፡፡ በተጨማሪም ከውኃ አገልግሎት ክፍያ ያልተሰበሰበ ከ2.8 ቢሊዮን ብር በላይ ስለመኖሩና በርካታ ሚሊዮን ብሮች አለመሰብሰባቸው የኦዲት ሪፖርቱ ያመላክታል፡፡

በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ የአዳማ አዋሽ መንገድ ከባድ ጥገና ለመሥራትና መንገዱን ከግንቦት 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለአሥር ዓመታት ለማስተዳደር በሁለት ዓይነት የኮንትራት ስምምነት ገብቶ እያከናወነ ቢሆንም፣ መንገዱን የማስተዳደርና የመንከባከብ ሥራውን በገባው ስምምነት መሠረት ባለመወጣቱ በመንገዱ ጉዳት ልክ በየወሩ በትሪሊዮን ብር የሚቆጠር ክፍያ እየተጠየቀ ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡

በዚህም የኦዲት ሪፖርቱ ከአማካሪ መሐንዲስ አገኘሁት ባለው መረጃ መሠረት በግንቦት 2013 ዓ.ም. ብቻ 13.7 ትሪሊዮን ብር፣ እንዲሁም በሐምሌ 2013 ዓ.ም. 20 ትሪሊዮን ብር በአጠቃላይ 39.8 ትሪሊዮን ብር በሁለት ወራት ብቻ እንዲከፍል የተጠየቀ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አመንቴ ዳዲ፣ የከባድ ጥገና ሥራውን ከማስተዳደር ጋር አንድ አድርጎ የያዘው ውል ላይ የታየው የኦዲት ክፍተት ከጅምሩ ከውጭ መጥቶ በቀጥታ የተተገበረ የኮንትራት ውል ነው ብለዋል፡፡ በዚህም ኮርፖሬሽኑን ምንም ዓይነት ገንዘብ የማያስቀጣው ውል በመሆኑ፣ በቀጣይ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ውሉ እንዲሻሻልና መፍትሔ እንዲሰጠው እያየው ነው ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ የቋሚ ኮሚቴው አባላት ይህ ተፈረመ የተባለው ውል ምንም ዓይነት ይዘት ቢኖረውና ኮርፖሬሽኑን ለቅጣት ያልዳረገው ቢሆንም፣ ከጅምሩ ሲፈረም ተቋሙ የሕግ ባለሙያ አልነበረውም ወይ የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡

ወ/ሮ ዘሪቱ ሽፈራው የተባሉ የቋሚ ኮሚቴው አባል ከ39 ትሪሊዮን ብር በላይ የተፈረመበት ውል ከተፈረመ ሰባት ዓመት መሆኑንና በየዓመቱ በኦዲት እየቀረበ እያለ፣ ኮርፖሬሽኑ ውስጥ ያሉ የበላይ አመራሮች እስካሁን ድረስ በቸልታ ዝም ብለው በመመልከታቸው ወቀሳ አቅርበዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ መደንገጥ ያልታየው በተለይ የሕዝብና የመንግሥት ሀብትን በጥንቃቄ ለመቆጣጠር የተሄደበት ርቀት በጣም የወረደና ጥርጣሬ ውስጥ የሚያስገባ መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹እኔም በግል ድንጋጤ ውስጥ ያስገባኝ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን፣ ኮርፖሬሽኑ በውል ስህተት ተፈጠረ የተባለውን የተጋነነ የገንዘብ ቅጣት እስከ ግንቦት 30 ቀን 2014 ዓ.ም. አስተካክሎ ለማምጣት ቃል ገብቶ የነበረ ቢሆንም፣ ምንም ዓይነት ሥራ ሳይሠራ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ዋና መልዕክቱ ከ39 ትሪሊዮን ብር በላይ በሁለት ወራት የሚያስቀጣ ስምምነት እንዴት ፈረማችሁ የሚለው እንደሆነ ገልጸው፣ ‹‹አይበልብን እንጂ ይህ የውል ስምምነት ከውጭ ኩባንያ ጋር ቢሆን ኖሮ አገርን በዕዳ አያሸጥም ወይ?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹በኮርፖሬሽኑ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ውሎችን የሚመለከት የሕግ ባለሙያ የላችሁም ወይ? ያለውን ሕግስ ማየትና ማጣቀስ አይቻልም ወይ ሲሉ?›› ጥያቄ አቅርበዋል፡፡  

ኮርፖሬሽኑን የሚያስተዳድረው የኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ግሩፕ በኦዲት ውይይቱ ላይ እንዲገኝ የተፈለገበት ምክንያት የሚያስተዳድራቸው ተቋማት ግዙፍ ስለሆኑ፣ ዓለም አቀፍ ስምምነት የሚያደርጉ እንደ ኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ አየር መንገድን የመሳሰለ ድርጅቶችን የሚያስተዳድር በመሆኑ በቀጣይ የዕርምት ዕርምጃ እንዲወስድና ስህተቱ እንዳይደገም፣ እንዲሁም ለወደፊት አቅጣጫ ለማስቀመጥ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ እንደሚለው ውሉ ከውጭ መጥቶ በቀጥታ ተግባራዊ የተደረገ ነው የሚለው በቂ ምክንያት አለመሆኑን የገለጹት አቶ ክርስቲያን፣ ኮርፖሬሽኑ ተስማምቶ ውል የፈረመ በመሆኑ የውጭ ድርጅት ቢሆን ኖሮ አስገድዶ ሊያስከፍል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው፣ ኮርፖሬሽኑ በኮንትራት አስተዳደሩ መሠረት በፈረመው ውል ምንም እንኳ የጠፋ ገንዘብ ባይኖርም፣ በተቋሙ ውስጥ ያለውን ግዴለሽነት በኦዲት ሪፖርቱ ለማሳየት መሞከሩን ተናግረዋል፡፡

ይህ የ39 ትሪሊዮን ብር ቅጣት የሚያስቀጣ ውል በአጋጣሚ በመንግሥት ተቋማት መካከል መሆኑ እንጂ፣ ከመንግሥት ተቋማት ውጪ በሆነ የውጭ አገር ድርጅት ወይም ኩባንያ ቢሆን ኖሮ ከባድ ጉዳይ ስለሚሆን በቀጣይ እንዲማሩበት ታስቦ የተሠራ ኦዲት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮናስ አያሌው (ኢንጂነር)፣ በተቋማቸው ውስጥ የኮንትራት ችግር አለባቸው የተባሉት በርካታ ፕሮጀክቶች ከዓመታት በፊት ከመንግሥት ለውጥ በፊት የነበሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በቀደመው ጊዜ እየተፈረሙ ወደ ሥራ የገቡ ውሎች ስለሆኑ፣ አሁን የሚታዩትን ችግሮች ለመፍታት አንዳንዶቹ ውሎቹ እንዲስተካከሉ ጥያቄ እያቀረቡ መሆናቸውን አክለዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ራሱን እያወዳደረ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ‹‹ተቋሙ ከዚህ በፊት ዕዳ ውስጥ የቆየ በመሆኑ ከዕዳ አውጥተን ጥሩ የሆነ እንቅስቃሴ ላይ በመሆን አትራፊ ድርጅት ወደ መሆን እየሄደ ነው፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...