Tuesday, April 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ስንዴን በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለማገበያየት የተዘጋጀው ውል ፀደቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • አራት አዳዲስ ምርቶች በምርት ገበያው እንዲገበያዩም ተወስኗል

ስንዴ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ግብይቱ እንዲከናወን የተዘጋጀው የምርት ውል በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ፀድቆ ተግባራዊ እንዲሆን ተወሰነ፡፡ አራት ተጨማሪ ምርቶችም በምርት ገበያ በኩል እንዲገበያዩ መወሰኑ ተገልጿል፡፡

በውሳኔው እንደተገለጸው፣ ስንዴ ለምግብነት፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ለውጪ ንግድ ስለሚውል፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጥራቱን በጠበቀ የግብይት ሥርዓት ለማገበያየት የሚያስችል ይሆናል፡፡ ከከፍተኛ አብቃይ አካባቢዎች ናሙና በመውሰድ ጥናት አካሄዶ ከባለሙያዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመመካከር ያዘጋጀው የግብይት ውል ሥራ ላይ እንዲውል በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መወሰኑን የሚገልጸው የምርት ገበያ መረጃ፣ በዚህ ውሳኔ መሠረት ምርቱ ወደ ምርት ገበያው እንዲመጣ ለአምራችና አቅራቢዎች ጥሪ በመተላለፉ ላይ ነው፡፡

ስንዴ ከ15 ዓመታት በፊት ምርት ገበያው ሥራ ሲጀምር ያገበያያቸው ከነበሩ ሁለት ምርቶች አንዱ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በአገራዊ ተነሳሽነት ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግ በተገኘው ለውጥ መሠረት፣ አዲስ የግብይት ውል ሊዘጋጅ መቻሉንም ምርት ገበያው አስታውቋል፡፡ ይህም የምርቱን የተለያየ ዓይነት የደረጃ አሰጣጥ መሥፈርቶች መቀበያ ቅርጫፎችንና ሌሎችንም መረጃዎች የያዘ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከአርሶ አደሮችና ከአቅራቢዎች ምርት ለመቀበል የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዝግጁ መሆኑንም ገልጿል፡፡

ግብይቱ ከሚካሄድበት የመጀመርያው ቀን አንስቶ እስካሁን ስለምርቱ ያልነበረው የገበያ መረጃ፣ በምርት ገበያው አማካይነት የሚሠራጭ መሆኑንም የስንዴ ግብይት ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህም አርሶ አደሩ በገበያ ላይ ያለውን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ያግዛል፡፡ ስንዴን በግብዓነት የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎችም ሕጋዊ የምዝገባ ሒደቱን አሟልተው ሲገኙ በምርት ገበያው በኩል መግዛት ይችላሉ፡፡

በዚህ ግብይት ጥራት ያለውን ስንዴ ይገበያያሉ ተብለው ከሚጠቀሱ ውስጥ ዳቦ ቤቶች፣ ፓስታና ማካሮኒ ፋብሪካዎችና ዱቄት አምራቾች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡

የስንዴን ምርት ወደ ግብይት ለማስገባት የተደረገውን ጥረት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የምግብና የእርሻ ድርጅት የፋይናንስ ድጋፍ ያደረጉ መሆኑን የገለጸው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለዚህ ድጋፋቸው ምሥጋና አቅርቧል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ግብጦ፣ ኮረሪማ፣ ባቄላና ሩዝ ግብይታቸው በምርት ገበያው እንዲካሄድ ለማድረግ የተዘጋጁ የምርት ውሎች፣ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ፀድቀው በሥራ ላይ እንዲውሉ ተወስኗል፡፡ ይህም ከወራት በፊት የተካተተውን የዕጣን ምርት ጨምሮ ምርት ገበያው የሚያገበያያቸው ምርቶች ብዛት ወደ 22 ከፍ የሚያደርገው መሆኑን ከምርት ገበያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች