Thursday, May 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜና‹‹የፌዴራል ፕሮጀክቶች የካሳ ክፍያ ለከፍተኛ የወንጀል ድርጊት ምንጭ እየሆነ ነው›› የፍትሕ ሚኒስቴር

‹‹የፌዴራል ፕሮጀክቶች የካሳ ክፍያ ለከፍተኛ የወንጀል ድርጊት ምንጭ እየሆነ ነው›› የፍትሕ ሚኒስቴር

ቀን:

የፌዴራል መንግሥት በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች በሚያካዷቸው የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች ግንባታ፣ ለልማት ተነሽዎች የሚሰጠው የካሳ ክፍያ ለከፍተኛ የወንጀል ድርጊት መጋለጡ ተገለጸ፡፡

መንግሥት በመንገድ፣ በቴሌኮም፣ በውኃ፣ በኤሌክትሪክና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን በሚገነባበት ወቅት ለልማት ለሚፈለግ ቦታ የሚደረገው የካሳ ክፍያ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጸሙ ካሉ ወንጀሎች ዋነኛውና ትልቁ መሆኑን፣ በፍትሕ ሚኒስቴር በወንጀል የተገኘ ሀብት ምርመራና ማስመለስ ዳይሬክተር ወ/ሮ ፀጋ ዋቅጅራ ተናግረዋል፡፡

የካሳ ክፍያ መዘግየት፣ ካሳ የተከፈላቸው ግለሰቦች ማንነት በግልጽ አለመታወቅ፣ ክፍያው ለእነማን እንደተፈጸመ፣ እንዲሁም ‹‹የተከፈለበት አግባብ ሕግን መሠረት ያደረገ ነው ወይ?›› የሚለው ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚያስፈልገው የገለጹት ዳይሬክተሯ፣ ሕግ ያልተከተሉ አሠራሮች ለከፍተኛ የወንጀል ድርጊት እየተጋለጡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በቀድሞው የተቀናጀ መሠረተ ልማት ማስተባበሪያ ኤጀንሲ፣ የ2013/2014 የክዋኔ ኦዲት ግኝት ሪፖርት አፈጻጸም ላይ ሰኞ ጥር 22 ቀን 2015 ዓ.ም. ውይይት አድርጎ ነበር፡፡

በመሠረት ልማት ገንቢ ተቋማት መካከል ያለውን ያልተናበበ አሠራር መፍትሔ ይሰጣል በሚል ከዓመታት በፊት ተቋቁሞ የነበረውና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ የነበረው ኤጄንሲው፣ በ2014 ዓ.ም. እንደ አዲስ በተዋቀረው የአስፈጻሚ አካላት ከነበረበት አደረጃጀት ፈርሶ ወደ ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር መካተቱ ይታወሳል፡፡

ለውይይቱ የተገኙት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ወንድሙ ሴታ (ኢንጂነር)፣ መሠረተ ልማት የሚገነቡ ተቋማት ተቀናጅተው ባለመሥራታቸው ምክንያት በርካታ ሀብት መባከኑን፣ እንዲሁም የተጋነነና ወጥ ባልሆነ የካሳ ክፍያ ሥርዓት በአገር ደረጃ የሚታቀዱ መሠረተ ልማቶች በታቀደላቸው ጊዜና ገንዘብ አንዳይጠናቀቁና አገርን ለተጨማሪ ዕዳ እየዳረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የካሳ ክፍያ ለተገመተላቸው ሰዎች ክፍያውን በወቅቱ አለመክፈል፣ እንዲነሱ የተከፈለባቸው መሠረተ ልማቶች በወቅቱ አለማንሳት፣ እንዲሁም በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች፣ አለፍ ሲልም በአንድ አካባቢ ለልማት ተነሽዎች ወጥ የሆነ የካሳ አከፋፈል ሥርዓትና ቀመር አለመኖሩን አስረድተዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ምንም እንኳ የካሳ አዋጅ ቢኖርም ክልሎች የራሳቸው የሆነ የካሳ ኮሚቴ አቋቁመው በራሳቸው ግምት አከፋፈል ስለሚሠሩ፣ በሁሉም አካባቢዎች ያለው አሠራር ‹‹ጉራማይሌ›› እና ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ እየጠየቀ እንደሆነ አክለዋል፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች በተለይ ለሰብል የሚጠየቀው ካሳ አካባቢው ከሚያመርተው ምርት በላይ እንደሆነ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ደኤታው፣ አልፎ አልፎ ምንም ሰብል በሌለበት ለሰብል ካሳ ብሎ የሚጠይቁ አካላት ስለመኖራቸውም ተናግረዋል፡፡ በአጠቃላይ በክልልና በተዋረድ ባሉ አስተዳደሮች እየተጠየቀ ያለው ገንዘብ ከፕሮክጀቱ ግንባታ ፍላጎት የበለጠ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹የሚጠየቀው ገንዘብ በተጨባጭ የንብረቱ ባለቤት ለሆኑ ሰዎች የሚከፈል ቢሆን ኖሮ ደስተኛ እንሆን ነበር፡፡ ለሰዎቹም ሕይወታቸውን የሚቀይር ይሆናል፡፡ ነገር ግን ይህ እየሆነ አይደለም፡፡ የካሳ ክፍያው በተለያየ ኮሚቴ አደረጃጀት ውስጥ ያሉ ሰዎች የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅና ሽርፍራፊ ገንዘብ ለማግኘት እንጂ፣ መሠረተ ልማቱ በአንድ አካባቢ ተገንብቶ የሕዝቡን ተጠቃሚነትና ዘላቂ ችግር ለመፍታት ያለመ ባለመሆኑ ለመክፈል እየተቸገርን ነው፤›› ብለዋል፡፡

በመሆኑም በክልሎች የሚታየው የመሠረተ ልማት ግንባታ ጥያቄ ከመሠረተ ልማቱ ይልቅ ለካሳ ክፍያው ልዩ ትኩረት የሰጠ መሆኑን የጠቆሙት ወንድሙ (ኢንጂነር)፣ ለዚህ ማሳያ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በየዓመቱ ለመንገድ ግንባታ ከሚበጀትለት አጠቃላይ 70 ቢሊዮን ብር ውስጥ፣ ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ ወይም 16 በመቶ ያህሉን ለካሳ ክፍያ እያዋለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህንን ለሥራ አመቺ ያልሆነና ወጪ የበዛበት የካሳ አሠራር ለማስተካከል ወጥ ሆነ የካሳ ክፍያ ለመዘርጋት የሚያስችል የካሳ ክፍያ አዋጅ በዝግጅት ላይ መሆኑን፣ በተያዘው ዓመት ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በመሻሻል ላይ ባለው ረቂቅ አዋጅ ክልሎችና የአካባቢ አስተዳደሮች ኃላፊነት እንዲወስዱ የሚደረግ ከመሆኑም በላይ፣ ወጥ የሆነ ቀመርና ስታንዳርድ ተካቶበት የሚዘጋጅ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የተጋነነ የካሳ ክፍያው የሚታየው የፌዴራል መንግሥት በሚገነባቸው ፕሮጀክቶች መሆኑን፣ ወጥ የሆነ ሥርዓት ባለመኖሩ የሚጠየቀው የገንዘብ መጠን በሁለት አጎራባች ቀበሌዎች መካከል ሳይቀር፣ የተለያየ እንደሆነ ወንድሙ (ኢንጂነር) ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...