Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዳግም የተመለሰው የኢትዮጵያዊነት ድርጅት

ኢትዮጵያዊነት የዜጎች መብት ማስከበርያ ድርጅት በምኅፃረ ቃል ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ፈቃድ ሰጥቶት የሚንቀሳቀስ ተቋም ነው፡፡ ድርጅቱ 12 ዓመት በፊት በሰሜን አሜሪካ የተቋቋመ ቢሆንም፣ በአገር ውስጥ ከሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ፈቃድ ያገኘው ከሁለት ዓመት በፊት ነው፡፡ ለድርጅቱ መመሥረት ጥንስሱ 1984 .. ከተመሠረተው የኢትዮጵያዊነት ማኅበር እንደሚነሳ ይወሳል፡፡ የድርጅቱን እንቅስቃሴ አስመልክቶ ዋና ሥራ አስኪያጁን አቶ ሞገስ በቀለ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተርየኢትዮጵያዊነት የዜጎች መብት ማስከበርያ ድርጅትን ታሪካዊ ዳራ ምንድን ነው?

አቶ ሞገስ፡- ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን እንደመጣ ያራምድ የነበረው የጎሳ ፖለቲካና ሌሎች አዳዲስ ፖሊሲዎችን ነበር፡፡ ይህ ዓይነቱ ፖለቲካና ፖሊሲ ለአገራችን ያለው አስተዋጽኦ ጠቃሚ ነው? ወይስ ጉዳት ያመጣል? የሚለው ጥያቄ በኅብረተሰቡ ዘንድ ይናኝ ነበር፡፡ ሌላው እንደ ትልቅ ክፍተት የተቆጠረው ጠንካራ የሆኑ በአገራዊ ጉዳይ ላይ በነፃ የሚወያዩ፣ የሚሟገቱ (አድቮኬሲ) የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አለመኖር ነው፡፡ በእርግጥ ባህላዊ የሆኑ ዕድሮች ቢኖሩም ትኩረታቸው ውስን ነው፡፡ ይህንን ችግር የተገነዘቡ በወቅቱ የነበሩ ታላላቅና ታዋቂ ሰዎች በ1984 ዓ.ም. መጋቢት ላይ ‹‹የኢትዮጵያዊነት ማኅበር›› አቋቋሙ፡፡ ከማኅበሩም መሥራቾች መካከል ሜጄር ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ፣ አቶ ሐዲስ ዓለማየሁና ደጃዝማች ዘውዴ ገብረ ሥላሴ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ማኅበሩም ሕዝባዊ ውይይቶችን ማካሄዱን ተያያዘው፡፡ አዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የተለያዩ አዳራሾች ይካሄዱ የነበሩ ውይይቶችም ትኩረታቸው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ በዜግነት ማንነትና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ማዕከል ያደረጉ ነበሩ፡፡ በእነዚህም ውይይቶች ላይ በርካታ ምሁራን ተሳትፈዋል፡፡ ከተሳታፊዎቹም መካከል ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያምና ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት ይገኙባቸዋል፡፡ ከውይይቱ የተሰነዘሩ አስተያየቶችና ለአገር ይጠቅማሉ ተብሎ የታመናቸው ሐሳቦች ለኅትመት እንዲበቁ፣ መንግሥትም ዘንድ እንዲደርሱና የሕዝቡም ግንዛቤ እንዲጎለብት በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

ሪፖርተርየማኅበሩ እንቅስቃሴ መንግሥት ከያዘው አቋም እክል አልገጠመውም?

አቶ ሞገስ፡- እውነት ለመናገር ክፉኛ የሆነ ተግዳሮት ነው የገጠመው፡፡ በሥልጣን ላይ የተቆናጠጠው መንግሥት በማኅበሩ አካሄድ አልተስማማሁም፣ አልተስማማኝም ብሎም ዝም አላለም፡፡ ማኅበሩ እንዲፈርስና አባላቱም ወደ ባዕድ አገር እንዲበታተኑ ነው ያደረገው፡፡ ግማሹ ወደ ሰሜን አሜሪካ፣ ከፊሉ ደግሞ ወደ ተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ተሰደዋል፡፡ ከተባረሩትም መካከል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮችና ዶክተሮች ይገኙበታል፡፡   

ሪፖርተርወደ ውጭ አገሮች የተሰደዱት ምሁራን አገር ቤት ውስጥ የጀመሩትን ሕዝባዊ ንቅናቄ አቆሙ? ወይስ ቀጠሉበት?

አቶ ሞገስ፡- እንቅስቃሴያቸውን በያሉበት አገር ሆነው ተያያዙት እንጂ አላቆሙትም፡፡ በተለይም ወደ ሰሜን አሜሪካ የሄዱት ምሁራን የተለያዩ ማኅበራትን በማቋቋም ጠንካራ የሆነ እንቅስቃሴያቸውን በስፋት ተያያዙት፡፡ እነዚህንም ማኅበራት ይመሩ ከነበሩት መካከል ጌታቸው ኃይሌ (ፕሮፌሰር) እንዲሁም በዕርቁ ይመር (ዶ/ር) ተጠቃሾች ናቸው፡፡ እነዚህም ማኅበራት ከጊዜ በኋላ፣ ‹‹ኢትዮጵያዊነት የዜጎች መብት ማስከበሪያ ጉባዔ›› በሚል መጠሪያ በአንድነት ያሰባሰባቸውን ድርጅት ከ12 ዓመታት በፊት አቋቁመው ተዋሀዱ፡፡ ድርጅቱም በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን  ጋር ዓመታዊ ጉባዔዎችን ያካሂድ ነበር፡፡ ጉባዔውም በታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ በሕገ መንግሥቱና በትምህርት ዙሪያ ያተኮረ ነበር፡፡ የጉባዔውም ውጤት ‹‹ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያን ስተዲስ›› በሚባል ጆርናል በአማርኛና በእንግሊዝኛ እየታተመ በኢትዮጵያና በሌሎቹ አገሮች ይሠራጭ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሰብዓዊ መብትና ሕገ መንግሥት በተመለከተ፣ ለዓለም አቀፍ ኮሙዩኒቲ በማድረስ ለኢትዮጵያ ድምፅ የመሆን አገልግሎት አበርክቷል፡፡  

ሪፖርተርኢትዮጵያዊነት የዜጎች መብት ማስከበርያ ጉባዔ ወደ አገር ውስጥ እንዴት ገባ?

አቶ ሞገስ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ አንዳንድ ለውጦች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረው እንደነበር የትናንት ትዝታ ነው፡፡ ከታዩትም ለውጦች መካከል ለመጀመርያ ጊዜ ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› የሚለው ቃል መቀንቀኑ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ኢትዮጵያዊነትን አንሸዋሮ ነበር የሚያየው፡፡ ጭፍን ጥላቻም ነበረበት፡፡ ኢትዮጵያዊነትን እያቀነቀኑ ደግሞ በውጭ አገር መኖርና መሥራት በቂ አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ከመጀመርያውም ‹‹ጎሳ ተኮር የሆነ ፌዴራዝም›› እንድንከተል ወይም ጥልቅ የሆነ ሥር እንዲይዝ ያደረገው ከ30 ዓመታት በፊት የተጀመረውና ከዚያም በኋላ ከ50 ዓመታት በፊት የነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ግን ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰሜን አሜሪካን በጎበኙበት ጊዜ አንዳንድ የኢትዮጵያውያን ኮሙዩኒቲና ድርጅት አመራሮችን በማነጋገር ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ አበረታተዋቸው ነበር፡፡ ከዚህም ሌላ በአገር ቤት ውስጥ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በአገር ጉዳይ ላይ እንዳይሳተፉ ይከለክል የነበረው አዋጅ ተነስቶ ሊያሠራ በሚችል አዋጅ መተካቱ፣ በወቅቱ የነበረው ድባብ ኢትዮጵያዊነትን ለማራመድ ጥሩ መሠረት ሆኖ በመገኘቱ፣ ‹‹ኢትዮጵያዊነት የዜጎች መበት ማስከበርያ ጉባዔ›› ወደ አገር ውስጥ ለመግባት ቻለ፡፡ ስሙንም ‹‹ኢትዮጵያዊነት የዜጎች መብት ማስከበርያ ድርጅት›› በሚል መጠሪያ ቀይሮ ከኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራትና ድርጅቶች ኤጀንሲ ከሁለት ዓመት በፊት ተመዝግቦና ዕውቅና አግኝቶ መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡

ሪፖርተርድርጅቱ በአገር ውስጥ መንቀሳቀስ የጀመረው ምን ዓይነት ዓላማዎችን አንግቦ ነው?

አቶ ሞገስ፡- በርካታ ዓላማዎች አሉት፡፡ ከእነዚህም መካከል አንደኛው የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማክበር፣ ኢትዮጵያ በልዩነት ውስጥ ያለውን አንድነቷ እንዲጠበቅ፣ ማንኛውም ሰው ወይም ዜጋ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ የመሥራትና የመኖር፣ ሀብት የማፍራትና ሕገ መንግሥታዊ መብቶች እንዲከበሩ የማድረግ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የአንድ ፖለቲካ ብቻ ዓላማ መሆን የለበትም፡፡ የሲቪክ ድርጅቶች ጽንሰ ሐሳብ በአገራችን ያልዳበረና እንጭጭ ስለሆነ ነው እንጂ በየትኛውም ዴሞክራሲ ባለበት አገር ላይ ሲቪክ ድርጅቶች የተጠቀሱትን መብቶች የማራመድ፣ የማንቀሳቀስ ሕዝብንም በእንቅስቃሴው የማሳተፍ መብት አላቸው፡፡ ስለዚህ ይህንን እንደ ሲቪክ ድርጅት ማቀንቀንና መጎትጎት አለበት ብለን እናስባለን፡፡ በአሁኑ ጊዜ እየተራመደ ያለው የዘውግ ማንነት ወይም ደግሞ ብሔርተኝነት፣ ብሔራዊ ማንነትን ወይም ኢትዮጵያዊነትን ወይም የዜግነት ማንነትን ተጭኖ የሚገኝበት ወቅት ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱም ላይ ይህ ነገር እንዲሆን የፈቀዱ አንቀጾች አሉ፡፡ ይህም እንዲቀየር እንፈልጋለን፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን አንድ ሕዝብ ነን፡፡ ከሚያለያዩን ይልቅ አንድ የሚያደርጉን ብዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ የጋራ ማንነትን  ማራመድ አለብን፡፡ ዘውግ ተኮር የሆኑት ማኅበራትም ሆነ ፖለቲካ ፓርቲዎች መጠለያ አላቸው፡፡ ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅንና ኅብረ ብሔራዊነትን የሚፈልጉ ዜጎችም እንዲሁ መጠለያ ያሻቸዋል፡፡ ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያዊነት ኢንስቲትዩት በየቦታው እንዲመሠረትና ሕዝቡንም እንዲያደራጅ እንፈልጋለን፡፡ እንግዲህ ይህን  ለማከናወን የራሱ ሂደት ይፈልጋል፡ ማንኛውም ሰው ከቦታ ወደ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ፣ ማንኛውም ነገር በብሔርተኝነት እንዲጠፈር የተደረገው ለዘመናት በነበሩ ትርክቶች የተነሳ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ደግሞ ይህንን ትርክት በማዳበር ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ ከዚህ አኳያ ለዘመናት የተከማቸውን ተግዳሮት በአንድ ጀምበር እንንደዋለን ብሎ ማሰብ ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ ሒደት ወይም ጊዜ ያስፈልገዋል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ከመጣንበት ጊዜና አሁን ካጋጠሙን ችግሮች ትምህርት መውሰድ አለብን፡፡ ለዚህ የሰሜኑ ጦርነት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ብሔርተኝነት አድጎ ብሔራዊ ማንነትን ወይም ኢትዮጵያዊ የዜግነት ማንነትን ሲጫነው የተፈጠረ ክስተት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ሌሎችም ብሔርተኝነት አቀንቃኞች ከዚህ ትምህርት መውሰድና ወደ ቀልባቸውም መመለስ አለባቸው ብለን እናምናለን፡፡      

ሪፖርተርወደ አገር ቤት ከመጣችሁና ሕጋዊ ዕውቅና ካገኛችሁ በኋላ ከሕዝቡ ጋር የተዋወቃችሁት እንዴት ነው?

አቶ ሞገስ፡- የዛሬ ዓመት መጋቢት 3 ቀን በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባደረግነው ስብሰባ ነው ከሕዝቡ ጋር የተዋወቅነው፡፡ በዚህም ታላላቅ ሰዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ወጣቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የማኅበረሰብ ተወካዮችን ለመተዋወቅ ችለናል፡፡ ዓላማችንንም በመግለጽ ተባባሪነታቸውንም እንደምንፈልግ ነግረናቸዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ይበጃል ብለን ይዘን የመጣነውንም ሐሳብ አስተዋውቀናል፡፡ ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናትም ጋር የመተዋወቅ ዕድል አግኝተናል፡፡ በተለይ ፕሬዚዳንቷ ክብርት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በቢሯቸው ጠርተውን በርቱ፣ ጠንክራችሁ ሥራ ብለው አበረታተውናል፡፡

ሪፖርተርወደ አገር ቤት ከገባችሁ በኋላ ኢትዮጵያዊነትን ማቀንቀን እንዴት አያችሁት?

አቶ ሞገስ፡- ወደ አገር ቤት ከገባን በኋላ ያየነው ኢትዮጵያዊነትን ማቀንቀኑ ተመልሶ መጥበቡ ነው፡፡ በግልጽ ለመናገር መብቶች በብዙ መልኩ ሲገደቡ አስተውለናል፡፡ የዘውግ ብሔርተኞቹ በተጠናከሩበት የኢትዮጵያ ክፍል ላይ እንደተፈለገ መንቀሳስ የለም፡፡ ይህም በመሆኑ ግን ድርጅታችንንና እንቅስቃሴውን በተመለከተ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት ለማስተዋወቅ፣ ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸውን ከማበረታታት ወደ ኋላ ያልንበት ጊዜ የለም፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ሲታይ በርከት ያሉ አባሎቻችን በውጭ አገር ያሉ ምሁራን ናቸው፡፡ በአገር ውስጥም ወደ 150 የሚጠጉ አባላት አሉን፡፡ አሁንም ቢሆን አባላትን እየመዘገብን ነው ያለነው፡፡ ቦርድና ጽሕፈት ቤት አለን፡፡ የተለያዩ ኮሚቴዎችን በማዋቀር እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ አብዛኛውን ድጋፍ የሚያደርጉልን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶችም ሊደግፉን ይገባል፡፡ ምክንያቱም የእኛ ትኩረት ሥልጣን ፍለጋ አይደለም፡፡ ነገር ግን ሕዝባችን ሰላም እንዲያገኝና ኢትዮጵያ እንድትበለፅግ ለማድረግ ብቻ ነው፡፡ አሁን ያለው ሕገ መንግሥትና ጎሳ ተኮር የሆነው ፌዴራሊዝም እንዲሻሻል ነው ፍላጎታችን፡፡ ይህ ዕውን ከሆነ ደግሞ ጠንካራ የሆነ ውትወታ (አድቮኬሲ) መፍጠር ይቻላል ብለን እናስባለን፡፡   

ሪፖርተርኢትዮጵያን በዘውግም ሆነ በጎሳ የመከፋፈሉ ሁኔታ ከመቼ ጊዜ ጀምሮ የመጣ ነው?

አቶ ሞገስ፡- ኢትዮጵያ በጎሳ የመከፋፈሉ ሁኔታ የቆየና ፋሺስት ጣሊያን ይዞት የመጣው ፕሮጀክት ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ መከፋፈል የሚቻለው በዘውግ በልዩነቱ፣ ከዚያም በሃይማኖቱ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ይህም በተለያዩ መጻሕፍት ተጽፎ ይገኛል፡፡ እኛ ይህንኑ የቆየ የፋሺስት ጣሊያን ፕሮጀክት ተቀብለን ከዳር እስከ ዳር ድረስ አቀጣጠልነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ደግሞ ማንም አሸናፊ የማይሆንበት መሆኑን ማጤን ይገባል፡፡ እንዲህ ዓይነት ትርክቶችን ማሸነፍ የሚቻለው አንድም በትምህርት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የእኔነትን ብቻ በመጠየፍ የእኛነትንና የሁላችንነትን የሚያቀነቅን ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ተጋብተን ተዋልደናል፡፡ ለዚህም የኢትዮጵያዊነት ፎረም ብለን በብዙኃን መገናኛ ቋሚ ትምህርት ፕሮግራም ለማከናወን ዝግጅት አድርገናል፡፡ የዘውግ (ንዑስ) ብሔርተኝነት ከብሔራዊ ማንነት ወይም ከኢትዮጵያዊነት ወይም ከዜግነት ማንነት ጋር መዝኖ ማየት እንጂ በቋንቋህ አትማር፣ አትናገር፣ በራስህ ሕዝብ አትተዳደር የሚል አይደለም፡፡ ለምሳሌ ያህል አሜሪካ በብዙ ሒደት ያለፈች ነች፡፡ አንድ አሜሪካዊ ሲጠየቅ ‹‹እኔ ላቲን አሜሪካ/ አፍሪካ አሜሪካ ነኝ›› ነው የሚለው፡፡ ይህም ማለት አሜሪካዊነቱን ማራመድና በቋንቋው የመናገር፣ ከቦታ ቦታ የመሥራት መብቱ የተጠበቀ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ስለዚህም ለምንድነው እኛ ‹‹አማራ፣ ኢትዮጵያዊ ነኝ››፣ ‹‹ኦሮሞ፣ ኢትዮጵያዊ ነኝ›› የሚለው ጽንሰ ሐሳብ እንዲመጣ የማንጥረው፡፡ ይህም ማንነታችንን ወይም የጎሳ ማንነታችንን ሳንለቅ ግን ብሔራዊ ማንነታችን ወይም የዜግነት ማንነታችንን እንዲመጣ ነው የምንፈልገው፡፡   

ሪፖርተርድርጅታችሁ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያቀረበው ምክረ ሐሳብ አለ?

አቶ ሞገስ፡- በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ረቂቅ አዋጅ ላይ ድርጅታችን ንቁ ተሳትፎ አድርጓል፡፡ ሌላውና ትልቁ ያደረግነው ነገር ቢኖር ኮሚሽኑ ለኢትዮጵያ አንድ ዕድል ይዞ የሚመጣ ስለሆነ፣ ሕዝቡ በትክክል እንዲረዳው የግንዛቤና የንቅናቄ ሥራ መሥራታችን ነው፡፡ ወደ 300 ሺሕ የሚጠጉ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ዕጩዎቻቸውን እንዲመርጡ አድርገናል፡፡ ከዚህም ሌላ የድርጅታችን ዝግጁነት ለኮሚሽኑ ገልጸናል፡፡ ከኮሚሽኑ ትልቁ ሥራ አንደኛው አጀንዳ መቅረፅ ነው፡፡ በዚህም ላይ ትኩረት ያደረገ የምክረ ሐሳብና የትብብር ደብዳቤ ለኮሚሽኑ ልከናል፡፡ በዚህም ምክረ ሐሳብ ላይ የድርጅታችንን ዋና ዋና ዓላማዎችና እስካሁን ድረስ እየሠራቸው ስላላቸው ጉዳዮች እንደ መነሻ አሥፍረናል፡፡ ከኮሚሽኑ የውይይት መርህ መካከል ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› አንዱ መሆን እንዳለበትና በተጨማሪም በተለያዩ ዓበይት አገራዊ ጉዳዮች፣ ብሎም በዋነኛነት የችግሩ ሁሉ ቁልፍ ነው ብሎ ድርጅቱ የሚያምነው የሕገ መንግሥቱ ጉዳይ ላይ እንዲያተኩር የአጀንዳ ጥቆማ አቅርቧል፡፡ በተጨማሪም የምክክር ኮሚሽኑ ዓላማ ኢትዮጵያ የገጠሟትን ዋና ዋና ችግሮች ለይቶ ማውጣትና ተግባራዊና ዘላቂ ሊሆኑ የሚችሉ ምክክሮችን ማመቻቸት መሆኑ በመግለጽ፣ ምክክሩ በሐሳብና በፖለቲካ ልሂቃን ብቻ ሳይወሰን በትክክል ሁሉንም የሕዝብ ተወካዮችን ባካተተ መልኩ ቢተገበር ውጤትን ማምጣት እንደሚችል ድርጅታችን እምነቱ መሆኑን ገልጸናል፡፡ በመጨረሻም ድርጅታችን እስካሁን በዚህ አገራዊ ጉዳይ ላይ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በማስታወስ፣ በኮሚሽኑ በኩል ለሚቀርብለት የትብብር ጥያቄ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን በመልዕክቱ አረጋግጧል፡፡  

ሪፖርተርየወደፊት ዕቅዳችሁ ምንድነው?

አቶ ሞገስ፡- በድርጅታችን በርካታ ፕሮግራሞችን ለመተግበር አቅደናል፡፡ ከእነዚህም መካከል የህዝብ ውይይት በአካል ማካሄድና በመገናኛ ብዙኃን ማስተላለፍ፣ በተጨማሪም በዓመት አንድ ጊዜ የሚከበር ‹‹የኢትዮጵያዊነት ቀን›› እንዲኖር እንጥራለን፡፡ በዚህም ቀን ለኢትዮጵያ አንድነት አስተዋጽኦ ያደረጉ በአገር አንድነት ፣ በሥነ ጥበብ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ አበረታችና ውጤታማ ተግባራትን ያከናወኑ፣ ዕውቅና የሚቸራቸው ይሆናል፡፡ ከዚህም ሌላ የኢትዮጵያዊነት ካሌንደርና አፕልኬሽን (የስልክና የኮምፒዩተር) ለመሥራት እንቅስቃሴ ላይ ነን፡፡ በዚህም ካሌንደርና አፕሊኬሽን ላይ ለጋራ አንድነታችን አስተዋጽኦ የሚያደርጉትን ግለሰቦችንንም ሆነ ድርጅቶችን ብናስቀምጥ ሕዝብ ለሕዝብ መቀራረብ ይፈጥራል፡፡ አገር በቀል ዕውቀቶቻችንንም ለማስፋት ይረዳል ብለን እናስባለን፡፡ ከዚህ አያይዞ  የተለያዩ  የአድቮኬሲ ሥራዎችን እናከናውናለን፡፡ ከእነዚህም መካከል  አንዱ ትኩረታችን ቋንቋ ላይ ነው፡፡ አገራዊ የመግባቢያ ወይም ብሔራዊ ቋንቋ በግድ በተግባር ያስፈልገናል፡፡ ይህም የሚጨንቃቸው አንዳንድ ምሁራን ቋንቋውን እንግሊዝኛ እናድርገው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ምንም ቢሆን ግን ይህ መሆን የለበትም፡፡ ምክንያቱም የዳበረ ቋንቋ አለን፡፡ ለምሳሌ አማርኛን ብንወስድ ያደገና በራሱ በርካታ መጻሕፍት የተጻፉበት ነው፡፡ ይህን ቋንቋ 80 ከመቶ ያህሉ ሕዝብ ይናገረዋል፡፡ ስለዚህ ከሃገራችን ተጨብጭ ሁኔታ እና ከሌሎች ሃገራት ተሞክሮ አንጻር ልንወያየበትነ በቶሎ መፍትሄ ልንሰጠው ይገባል፡፡

ሪፖርተርድርጅቱ የበይነ መረብ ውይይት ፕሮግራም እንደጀመረ ይሰማል፡፡

አቶ ሞገስ፡- ድርጅታችን ከተመሠረቱበት ዓላማዎች መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት ለማጠናከርና እንቅፋት የሚሆኑ ንግግሮች የተሳሳቱ መረጃዎች፣ ሕጎች መጤ ባህሎች፣ ፍልስፍናዎችን በጥናትና በተጨባጭ መረጃ ላይ ተመርኩዞ መመርመር፣ መተንተን፣ መሞገትና ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ጋር መምከርና አስፈላጊውን ድጋፎችን መስጠት ይገኝበታል፡፡  ከዚህ አንጻር ድርጅታችን የኮቪድ ወረርሽኝ ከመጣ አንስቶ በበይነ መረብ በተለያዩ ርእሰ ገዳዮች ዙሪያ ምሁራን ጽሑፍ የሚያቀርቡበትና አባላቶቻችንና ደጋፊዎቻችን የሚሳተፉበት ዝግጅት ተከታታይ ዝግጅት አካሒደናል፡፡ ነገር ግን ይህን ፖሊሲ አውጭዎች እና ተግባሪዎች እንዲሁም ሰፊው ሕዝባችን ዘንድ ቢደርስ ጠቃሚ ነው ብለን ስላሰብን አሁን ላይ ሰፋ ያለ ዌቢናር በማዘጋጀት ላይ እንገኛለን ከእነዚህም መካከል ለምሳሌ ብንወስደ ጥቅምት 5 ቀን 2015 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኩነተ ሀገር እና ሕገ መንግሥት በሚል ርእስ ያካሔድነው አንቱ የተባሉ ምሁራን የተሳተፉበት የሙሉ ቀን የበይነ መረብ ኮንፈረንስ ተጠቃሽ ነው፡፡ ሌሎች ተመሳሳይ ዌቢናሮች ያደረግን ሲሆን ለወደፊት ይህንን አጠናክረን በአካል ለማድረግ የሚደግፉን አካላት ካሉ እነሱን በማስተባበር በአካል ለማድረግ አቅደናል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪያችንንም እናስተላልፋለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...

የልጅነት ሕልም ዕውን ሲሆን

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተር አባባል አለ፡፡ አባባሉ የተጎዳን ሰው ለመርዳት፣ የወደቁትን ለማንሳት፣ ያዘኑትን ለማፅናናት፣ ከገንዘብ ባሻገር ቅንነት፣ ፈቃደኝነት፣...

በርካታ ሐኪሞችን የሚፈልገው የጨቅላ ሕፃናት ሕክምና

በኢትዮጵያ የጨቅላ ሕፃናት ሞትን ለመቀነስ ባለፉት አሠርታት የተሠሩ ሥራዎች ለውጥ አምጥተዋል፡፡ ሆኖም በጨቅላ ሕፃናት ሕክምና ዘርፍ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ከነበረው ቢሻልም፣ የጨቅላ ሕፃናት...