ትኩረት የሚሹ የትሮፒካል /ሐሩራማ በሽታዎች በአብዛኛው ተላላፊ ሲሆኑ፣ በዓይን በማይታዩ በሽታን በሚያስተላልፉ ረቂቅ ተህዋስያን አማካይነት ከታመመው ሰው ወደ ጤናማው በተለያዩ መንገዶች በመተላለፍ ሕመምን በማስከተል፣ አልፎም ሰፊ የኅብረተሰብ ክፍልን ለአካል ጉዳትና ለሞት የሚዳርጉ በሽታዎች ናቸው፡፡
የጤና ሚኒስቴር ባዘጋጀው ‹‹ሁለተኛው ትውልድ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም- ትኩረት የሚሹ በሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ፓኬጅ›› ላይ እንደተገለጸው፣ በኢትዮጵያ በኅብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ የጤና ችግር በማድረስ ጎልተው ከሚታወቁት ትኩረት የሚሹ የትሮፒካል በሽታዎች መካከል ትራኮማ (የዓይን ማዝ)፣ ኦንኮሰርኪያሲስ (ፎከት)፣ ተላላፊና የማይተላፍ ዝሆኔ፣ ቢሊሀርዚያ፣ የአንጀት ጥገኛ ትላትሎች፣ ሊምፋቲክ ፊላሪያሲስ፣
ሌሽማኒያሲስ (ካላዛር/ቁንጭር)፣ ድራንኩሊያሲስ (ጊኒዎርም) ይገኙባቸዋል፡፡
እነኚህ በሽታዎች ካላቸው ሥርጭትና እያደረሱት ካለው ጉዳት ባሻገር በሽታዎቹን መቆጣጠርና የኅብረተሰብ ጤና ችግር መሆናቸው እንዲያከትም ከማድረግ አንፃር በተበጣጠሰና በዘመቻ መልኩ ቢሆኑም፣ በቤተሰብና በማኅበረሰብ ደረጃ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራዎች ተጠናክረው ተፈጻሚ እንዲሆኑ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ሚኒስቴሩ አመልክቷል::
የዓለም የጤና ድርጅት በወሰነው መሠረት፣ በየዓመቱ ጥር 22 ቀን (ጃንዋሪ 30) የሚከበረው ዓለም አቀፍ ትኩረት የሚሹ የሐሩራማ በሽታዎች ቀን፣ በጅማ ከተማ በተዘጋጀ መድረክ የታሰበው ‹‹በተባበረ ክንድ አሁኑኑ፣ ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎችን እናጥፋ›› በሚል መሪ ቃል ነው፡፡
በዕለቱ ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎችን ከአገሪቱ ለማጥፋት የሁሉንም ተቋማት ርብርብ የሚጠይቅ ነው ያሉት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ደረጀ ድጉማ (ዶ/ር)፣ በባክቴሪያ በጥገኛ ተህዋስ ወይም በቫይረስ አማካይነት የሚከሰቱ ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአንድ ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ለሕመም፣ ለአካል ጉዳት እንዲሁም ለሞት እየዳረገ መሆኑን ገልጸዋል።
አያይዘውም፣ የበሽታዎቹ ሥርጭት በተለይም በምድር ሰቅ (ትሮፒክስ) አካባቢዎች በስፋት ተሠራጭተው እንደሚገኙ በመግለጽ፣ በኢትዮጵያም አሥራ ሁለት ትኩረት የሚሹ በሽታዎች ተለይተው ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር፣ ብሎም ለማጥፋት የሚያስችል የፕሮግራም መሪ እቅድ ውስጥ ተካተው እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል።
የንጹህ የመጠጥ ውሀ አቅርቦት፣ የግልና የአካባቢ ንጽህና አጠባበቅ፣ እንዲሁም ማኅበረሰቡ ለእነዚህ በሽታዎች ያለውን ግንዛቤ ከፍ ማድረግ እንደ ቁልፍ ተግባር አድርጎ መውሰድ አስፈላጊነቱን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ስኬት የጤና ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ የሚመለከታቸው ተቋማት፣ ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርበው መሥራት አለባቸው ብለዋል፡፡
በዓለም ላይ በርካታ ሰዎችን እያጠቁ የሚገኙት የሐሩራማ በሽታዎች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል በማለት ያሳሰቡት፣ የዓለም የጤና ድርጅት ተወካይ ሮዝ ዲናሚኒ (ዶ/ር) በቀጣይም ድርጅታቸው እነዚህን በሽታዎች ለመከላከል ብሎም ለማጥፋት የሚሠራቸውን ሥራዎች ያጠናክራል ይደግፋልም ብለዋል።
እንደ ዓለም አቀፉ የጤና ተቋም መግለጫ፣ እነዚህ በሽታዎች በብዛት የሚገኙት በአፍሪካ፣ በእስያና በአሜሪካ አህጉሮች ድሃ በሆኑ አካባቢዎች ነው።