Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየትምህርቱ ዘርፍ ቀውስ መገለጫ

የትምህርቱ ዘርፍ ቀውስ መገለጫ

ቀን:

በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓቱ ይበልጡኑ ተማሪ ተኮር እንዳልነበረ ከሚያመላክቱ መጠቆሚያዎች የ2014 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል ፈተናን ከተፈተኑት ተማሪዎች ውስጥ 96.6 በመቶ ያህል ተማሪዎች መውደቃቸው አንዱ ነው፡፡

ዛሬ በውጤቱ ምክንያት እውነቱ ስለተገለጠ እንደ ትልቅ አጀንዳ ተደርጎ መነገሩ ካልሆነ በስተቀር፣ የትምህርት ሥርዓቱ ለተማሪዎች ብቃት ያለው ትምህርት እየሰጠ አይደለም በሚል መተቸት ከጀመረ ግን በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በርካታ ጥናቶች ተሠርተዋል፡፡ የተለያዩ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ ነገር ግን ከውይይትና ከጥናት ያለፉ ባለመሆናቸው በተማሪው ዕውቀት ላይ ያመጡት ብዙም ለውጥ የለም፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በትምህርት ዙሪያ በስፋት እየተነገረ ያለው የብቁ መምህራን እጥረት፣ የድንገተኛ ፖለቲካዊ አጀንዳዎች ጣልቃ መግባት፣ የግብዓት እጥረት፣ ግጭትና ጦርነት፣ የትምህርት ተቋማት ውድመት ለዛሬው ውጤት የራሳቸውን አስተዋጽኦም አድርገዋል፡፡

ሆኖም ግጭት ባልጎላበትና ጦርነት ባልነበረበት ጊዜም የትምህርት ሥርዓቱ ብቁ ተማሪ እያፈራ አይደለም ተብሎ ከመንግሥትም ሆነ ከሌሎች የዘርፉ ተዋናዮች ሲነገር ከርሟል፡፡ ፖሊሲና ሥርዓተ ትምህርትም ተቀያይሯል፡፡ ዛሬ የተፈተኑት፣ ነገና ከነገ ወዲያ የሚፈተኑተም ቢሆኑ በተቃወሰ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ የነበሩ ናቸው፡፡  

ይህ በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ የሚታየው ቀውስ ውጤቱ ዛሬ ገሃድ ወጥቷል፡፡

የትምህርት ቀውስ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የበርካታ በኢኮኖሚ የደኸዩ አገሮች ጭምር መሆኑን ዓለም ባንክ እ.ኤ.አ. በ2019 ‹‹በትምህርት ቤት መገኘት ማለት መማር ማለት አይደለም›› በሚል ያስነበበው ጽሑፍ ያሳያል፡፡

በኢትዮጵያ በርካታ ትምህርት ቤቶች መከፈታቸው ትምህርት፣ መስፋፋቱ ብሎም በርካታ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት መሄዳቸው እመርታ ቢሆንም፣ ዕውቀትና ክህሎት ሳያገኙ እየተመለሱ መሆኑ ግን የትምህርት ቀውስ ስለመኖሩ አመላካች ነው፡፡

በኬንያ፣ በታንዛኒያና በኡጋንዳ ከሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች ውስጥ ሦስት አራተኛው ትምህርትን እንደማይረዱት በሌሎች አገሮችም ማስላት፣ ማንበብና መረዳት የማይችሉ ተማሪዎች በርካታ መሆኑን ወርልድ ባንክ ይገልጻል፡፡

በኢትዮጵያ ‹‹የትምህርት ሥርዓትን በማሻሻል የትምህርት ብቃትን ማረጋገጥ ይቻላል፤›› በሚል እ.ኤ.አ. በ2017 የተጀመረውና በታኅሣሥ 2022 የተጠናቀቀው በ‹‹ሪሰርች ኦን ኢምፕሩቪንግ ሲስተም ኦፍ ኢዱኬሽን›› (ራይዝ) የተሠራው ጥናትም፣ በኢትዮጵያ በትምህርቱ ዘርፍ ተመሳሳይ ችግር መኖሩን ያመላክታል፡፡

ራይዝ ንባብ ላይ አተኩሮ የሠራው ጥናት፣ 68 በመቶ የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች እንዲሁም 51 በመቶ የሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች ‹‹ዜሮ አንባቢ›› ሆነው መገኘታቸውን ይፋ አድርጓል፡፡

ለዚህ ውጤት የተለያዩ ምክንያቶች ቢጠቀሱም፣ የትምህርት ሥርዓቱ ችግር ያለበት መሆኑ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ይህ ደግሞ በየዓመቱ የተማሪዎች ውጤት እየዘቀጠ እንዲሄድ አድርጓል፡፡

በራይዝ በ2014፣ በ2016፣ በ2018 እና በ2021 ከተሠራው ጥናት፣ የ2021ዱ ውጤት ዝቅተኛ ሆኖም ተገኝቷል፡፡

ይህ ደግሞ ትምህርት የሰው ልጅ የሚገነባበት ካፒታል ነው የሚባለውን ይንደዋል፡፡ ትምህርት ግለሰቦችና ማኅበረሰብ የተሻለ እንዲኖሩ ያስችላል የሚለውን በማመንመንም ለማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ይዳረጋል፡፡

በትምህርት ላይ የተፈጠረው ቀውስና በ2014 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል ከተፈተኑ ተማሪዎች ውስጥ 96.6 በመቶ ከግማሽ በታች ማምጣታቸው ምን ዓይነት ማኅበራዊ ቀውስ ያስከትላል? ስንል የዘርፉን ባለሙያ አነጋግረናል፡፡

በመማር ማስተማሩ ሒደት ውስጥ በመምህርነት፣ በትምህርት አስተዳደር፣ ልማትና ጥናት ዘርፍ ከ16 ዓመታት በላይ ልምድ ያካበቱት ባለሙያ አቶ ሔኖክ ማርቆስ እንደሚሉት፣ በ2014 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል ፈተና በማኅበራዊና በተፈጥሮ ሳይንስ ለመፈተን ከተቀመጡ 896,520 ተማሪዎች ውስጥ 29,909 ተማሪዎች ብቻ ከ50 በመቶ በላይ ማስመዝገባቸው ማኅበራዊ ቀውስ ጭምር የሚያስከትል ነው፡፡

በተለይ ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ብዙም ፍላጎት በማይታይባቸው የኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች፣ ሴት ልጆች ከ8ኛ ክፍል እንዲያቋርጡና ወደ ትዳር እንዲገቡ በሚፈልጉ ማኅበረሰቦችና ከሰዓታት ላላነሰ በእግር ተጉዘው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሚከታተሉ ተማሪዎች ዘንድ ይህን ውጤት መስማት ተስፋን የሚያስቆርጥና ከትምህርት እንዲወጡ የሚያደርግ ነው፡፡

ካለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ አንፃርም አብዛኛው ከከተማ ውጭ ያለው ማኅበረሰብ ልጆቹን በትምህርት የመደገፍ ልማዱ አነስተኛ በመሆኑ፣ የዘንድውን ውጤት ሲያውቅ ‹‹ልጄ ተምራ/ተምሮ የትም አትደርስም/አይደርስም፤›› ወደ ሚለው  ድምዳሜ ሊገባ ይችላል፡፡

ተምሮና ሠርቶ ለመኖር የግንዛቤና የሀብት እጥረት ባለበት፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የአምስተኛ ክፍል ተማሪዎች ጭምር ከመማር ይልቅ ስደትን በሚናፍቁበት ሁኔታ ላይ ይህ ውጤት ሲጨመር፣ ሕገወጥ ስደት እንዲበራከትና ከቀዬ መፈናቀል እንዲበዛም ያደርጋል ብለዋል፡፡

ተምሮ፣ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ሥራ መያዝን የሚጠብቅ ማኅበረሰብ፣ ለትምህርት አትኩሮት ሰጥቶ ልጁን ወደ ትምህርት ቤት ለላከ ቤተሰብና ወደ ትምህርት ቤት በሄደ ተማሪ ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖም ከባድ ነው፡፡ የትምህርት ፍላጎትንም ሊቀንሰው ይችላል፡፡

 እንደ አቶ ሔኖክ፣ የአሁኑ ክስተት ልጆቻቸው ወደ ዓረብ አገር እንዳይሄዱ እያስተማሩና እየታገሉ ያሉ ቤተሰቦችንም ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ ለትምህርት የሚሰጠው ሥፍራ እንዲቀንስም ያደርጋል፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያ በትምህርት ላይ ያደረገችው ኢንቨስትመንት ብክነት ይሆናል፡፡ ለዚህ ብክነት መንስዔው ደግሞ ተማሪዎች ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ ችግሩ የአስተማሪ፣ የትምህርት ተቋማት፣ የትምህርት አስተዳደርና ሥርዓተ ትምህርት ላይ ያመዝናል፡፡

ተማሪውን ማዘጋጀትና ማብቃት የትምህርት ዘርፍ፣ የኅብረተሰቡና የተማሪው የጋራ ሥራ ነው፡፡ ‹‹የዘንድሮው ውጤት የወረደው ተማሪው ኩረጃ ለምዶ ነው፣ ኩረጃ ስለቀረ ነው፤›› ብሎ ቀላል ምክንያት ሰጥቶ ማለፍም ትክክል እንዳልሆነ ይገልጻሉ፡፡ የፈተና ዓይነቱም ቢሆን፣ ከዚህ በፊት ከተፈተኑትና በሞዴል ፈተናዎች ከተሰጡት የተለየ እንዳልነበረ ማየታቸውንና የተገኘው ውጤት የፈተናው ይዘት በመክበዱ የመጣ ነው ለማለት እንደማይቻልም አክለዋል፡፡

ከለመዱት አካባቢ ወጥተው በዩኒቨርሲቲዎች መፈተናቸው አዲስነት ቢፈጥርባቸውም፣ ዋናው ችግር ያለው ተማሪዎች ከሥር ጀምሮ የመጡበት የመማር ማስተማር ሥርዓት ነውም ይላሉ፡፡

ከአሁን በኋላ ምን መደረግ አለበት?

 እንደ አቶ ሔኖክ፣ ተማሪን በስፋት መጣል ወይም ማሳለፍ ትክክለኛ መለኪያም ሆነ አካሄድ አይደለም፡፡ አሁን ላይ ተማሪ በስፋት የወደቀበት ምክንያት መፈተሽ አለበት፡፡ ተማሪዎቹ ስምነተኛን እንዴት አለፉ? ከክፍል ክፍል እንዴት ተዘዋወሩ ብሎ መፈተሽና ጥናት መሥራት ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ ቀደም አሥረኛ ክፍል ተፈትነው ወደ ሙያ የሚገቡበት አሠራር በነበረበት ወቅት፣ በመሀል የነበረው የአሥረኛ ክፍል ፈተና ለተማሪው በየሁለት ዓመት የመልቀቂያ ፈተና እንዲወስድ ዕድል ይሰጠው ነበር፡፡ አሁን ከስምንተኛ በኋላ አራት ዓመት ተምረው 12ኛ ሲፈተኑ የራሱ ችግር ሊኖረው ይችላል፡፡

ብሔራዊ ፈተናውን የሚሰጠው አካል ተማሪዎች ከክፍል ክፍል እንዴት ተዘዋወሩ? አልፈው ነው ወይ? ዕውቀት ይዘዋል ወይ? ብሎ ተንትኖ መረጃ የሚያገኝበት አሠራርም ያስፈልጋል፡፡

በየክልሉ ያሉ ከ40 ሺሕ የሚልቁ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን ከክፍል ክፍል ሲያሳልፉ ምን ያህል ቁጥጥር ነበር? ዕውን ተማሪዎች ከክፍል ክፍል አልፈው ነበር ወይ? የሚለው ዕውን እንዳልነበር የ2014ቱ የ12ኛ ክፍል ውጤት አመላክቷል፡፡

‹‹እዚህ ላይ ችግሩ የተማሪው ነው የሚል አመለካከት የለኝም›› የሚሉ አቶ ሔኖክ፣ ለምሳሌ በፈተናው የሒሳብ ትምህርት ከመቶ አሥራ ውስጥ ያመጡ ተማሪዎች እንዴት ነበር ከዘጠኝ እስከ 11 ክፍል የነበረውን ሒሳብ ትምህርት ያለፉት ብሎ ለመጠየቅ ያስገድዳል ብለዋል፡፡

‹‹ተማሪዎቹ እንዴት 12ኛ ክፍል ደረሱ?›› ብሎ ዝርዝር ጥናት ማድረግና ችግሩን ማወቅ በቀጣይ የሚመጡ ተማሪዎችን ከዕውቀት ነፃ እንዳይሆኑ ለማዳን ይረዳልም ይላሉ፡፡

መምህራን ተማሪ እንዳይጥሉ ባሉበት አካባቢ ማኅብረሰብ፣ ሥርዓትም ሆነ ተማሪዎች የሚደርስባቸው ጫና እስከ ምን ድረስ ነው? ብሎ ማየትም ያስፈልጋል፡፡

አንድ ተማሪ ከክፍል ክፍል ያለፈው ማሟላት ያለበትን ዕውቀት ይዞ ነው ወይ? የሚለው ሥርዓት ተዘርግቶለት መታየት አለበት፣ የተሻለ የትምህርት መሠረተ ልማት ቢኖርም፣ ምን ያህል ብቁ መምህራን አሉ? የሚለውና አጠቃላይ የመማር ማስተማሩ ሒደት መፈተሽ አለበት ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ሔኖክ፣ የፈተናውን ይዘት ከመንግሥት አካል ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ውስጥ ባሉ ባለሙያዎች ማስገምገም፣ አሁን የታየው የአንድ ቀን ውጤት ሳይሆን የብዙ ዓመታት ድምር ውጤት በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶት፣ ከዚህ በኋላ ተማሪ በየክፍሉ የሚሰጠውን ትምህርት ማወቁ ተረጋግጦ የሚያልፍበት ሥርዓት መዘርጋት፣ የምዘና ሥርዓቱና ትምህርቱም መታየት አለበት፡፡

በዚህ መጠን ተማሪዎች አለማለፋቸው የሚያሳየው ከክፍል ክፍል የተዘዋወሩበት አሠራር ትክልል እንዳልነበረ ነው የሚሉት አቶ ሔኖክ፣ ይህን 12ኛ ክፍል ላይ ኩረጃ በማስቀረት ብቻ እንደማይለወጥ፣ የትምህርት ጥራት ላይ መሥራት፣ ዘርፉ ላይ ያለውን ችግር ማየትና መፍታት 12ኛ ክፍል ለመፈተን አይደለም ለመድረስ ፈተና የሆነባቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች ችግር መቅረፍ ያስፈልጋል፡፡

አሁን ላይ ተማሪው እንደደረጃው አግኝቷል፡፡ መሠረታዊ ችግር መኖሩ ተመላክቷል፡፡ ስለዚህ ጥሩ ያመጡ ተማሪዎች ከፍተኛ ደረጃ ባላቸው ዩኒቨርሲቲዎች መመደብ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ ትምህርት ሚኒስቴር እንዳለውም ሌሎቹ ወደ ሙያ የሚሄዱበትንና ሌሎች አማራጮችን ተጠቅሞ የተፈተኑትን በትምህርት በማሳተፍ፣ ማኅብረሰቡ በዘንድሮ ውጤት ተስፋ ቆርጦ ልጆቹን የማስተማር ፍላጎቱን እንዳይገድብ ማገዝ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በቀጣይ ግን ተማሪዎች እንደ አቅማቸው የሚማሩበትን አሠራር መዘርጋት፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን መቅረፍ ያስፈልጋል ሲሉም አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...