Wednesday, March 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየ‹‹መንታ መንገድ›› መንገድ

የ‹‹መንታ መንገድ›› መንገድ

ቀን:

በአበበ ፍቅር

በዓረብኛ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ በተለይ በልብ ወለድና በድራማ ከፈር ቀዳጆቹ የሚጠቀሰው ግብፃዊው ቶፊቅ አልሐኪም (1898 -1987) ነው፡፡ ‹‹የግብፅ ቴአትር አባት›› ተብሎም ይታወቃል፡፡ በርካታ ልቦለዶችን፣ ግጥሞችን እና ድርሰቶችን የፃፈ ቢሆንም በዓረብኛ ድራማ ዕድገት ውስጥ ትልቅ ሚና መጫወቱ የሚነገርለት ቶፊቅ ከ70 በላይ ተውኔቶችን ጽፏል፡፡ከሥራዎቹ መካከል ዓለማየሁ ገብረሕይወት አዛምዶ የተረጐመው ‹‹መንታ መንገድ›› አንዱ ሲሆን፣ በአንጋፋው ከያኒ ተክሌ ደስታ አዘጋጅነት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ባለፈው ሳምንት ለዕይታ ቀርቧል፡፡ የመንታ መንገድ ቴአትር ዋና ጭብጡን በሕግ የበላይነት ላይ አድርጓል፡፡

 ቶፊቅ መሠረቱን በጥንት የግብፆች ታሪክ ላይ አድርጎ በ1953 ዓ.ም. የጻፈው ተውኔት የዓረብኛው ርዕስ አልሡልጣን አልኸይር– በግርድፉ ሲተረጐም ‹‹ግራ የተጋባው ሡልጣን›› የሆነው ተውኔቱ የሥልጣንን ሕጋዊነት ጉዳይ ውጤታማ በሆነ መንገድ ይዳስሳል።

እንዲሁም ሥልጣን በጎራዴ መፍትሔ አምጪ ለማድረግ ሲሞከር የፍትሕ ሥርዓቱ ራሱ የሚጣስበት መሣሪያ ራሱ ሥልጣን ሊሆን መቻሉን ያሳያል። በተጨማሪም በወሬ ወለደ የተገፉ፣ የተናቁና የተረሱ ሰዎች ዜጋ ናቸውና አገርን በወሳኝ ጊዜ ላይ እንዴት እንዳዳኗት ሌላው የቴአትሩ ጭብጥ ነው።

ዓለም የመሪዎች ዓለም አቀፋዊ ችግሮችን በስምምነት ወይስ በጎራዴ (በወታደራዊ ኃይል) ለመፍታት የሚያደርጉበትን ጥረት ለማሳየት የሞከረበት እንደሆነ ያሳያል፡፡

‹‹መንታ መንገድ›› በዘመኑ የግብፅ ፕሬዚዳንት የነበረው ጋማል አብዱል ናስር ወደ ሥልጣን የመጡበትን ሕጋዊነት የሞገተበት ሥራው እንደነበርም የጻፉም አሉ፡፡

የ‹‹መንታ መንገድ›› መንገድ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ተውኔቱ ያለ ፍርድ እንዲገደል የተወሰነበት ግለሰብና ዕርምጃውን እንዲወስድ በታዘዘው ባለወግ መካከል የሚደረግ ከረር ባለ ንግግር የሚጀምረው  የንጋቱን የአምልኮት ጥሪ ሲሰማ ግዳጁን ለመፈጸም መጥረቢያውን እየሳለ የሚጠብቀው ባለወግና የንጉሡን ስም በሕዝብ ፊት አንስተሃል ተብሎ በድንገት ከገበያ መሃል ተይዞ ያለምንም ፍርድ ዳኛ ፊት ከመቀረቡና ቃሉን ከመስጠቱ በፊት ሊገደል መሆኑ ያስጨነቀው ግለሰብ ጋር ሲፋጠጡ በመግቢያው ላይ ይታያሉ፡፡

አልፎ አልፎ ሟችና ገዳይ ለመወያየት ይሞክራሉ ሟች ለምን እንደሚገደልና በማን ትዕዛዝ ተይዞ እጅና እግሩ በሰንሰለት ታስሮ ሞቱን እንደሚጠባበቅ አያውቅም፡፡

በአደባባይ የተናገረውን የንጋቱን የአምልኮት ጥሪ ሰምቶ አንገቱን ለመቅላት በጉጉት ለሚጠባበቀው ታዛዥ ግለሰብ የመሞቻ ምክንያቱን ለማስረዳት ይሞክራል፡፡ ነገር ግን ገዳይ የሟችን ንግግር ሰሞቶ ምናልባት የሚያሳዝን ወይም ለሞት የማያበቃ ሊሆን ቢችል፣ ከህሊናው ጋር ተሟግቶ የተሰጠውን ትዕዛዝ ሊተላለፍ እንደሚችል ትዕዛዙን ከተላለፉ ደግሞ የራሱ አንገት እንደሚቀላ በማስረዳት የሟችን ንግግር ፈጽሞ እንደማይሰማ ሲናገር ይታያል፡፡

ደራሲው ብርሃንና ጨለማን፣ ሕግ አልባነትና የሕግ የበላይነትን በተነፃፃሪነት ተጠቅሞባቸዋል፡፡ የደራሲው ዋና ዓላማ የሕግ አውጪው የሕግ ተርጓሚውና የሕግ አስፈጻሚው ሕዝቡና የእምነት ተቋማት ተደጋግፈው ሚናቸውን መጫወት ካልቻሉ አገር አደጋ ላይ ልትወድቅ እንደምትችል ያስረዳል፡፡

ተውኔቱ ዜጎች በየዕለቱ ከየግላቸው ከእውነት ጋር ሲፋጠጡና ሕጉ ትክክል የሚለውን ነገር ለመፈጸም ሲተጉ ያሳያል፡፡ ሆኖም በሕጉ መሠረት ትክክለኛውን ነገር እንዲያከናውኑ ሥልጣን የተሰጣቸው ሰዎች ሕጉን ለራሳቸው መጠቀሚያ ሲያውሉትና ሥልጣናቸውን ተገን አድርገው ሲጨፈልቁት እንዲሁም ትክክል አይደላችሁም የሚላቸውን በግድ ትክክል ነን ብለው ሲሞግቱ ያሳያል፡፡

ሰዎች ከተራ ወሬ ወይም ሐሜት ተነስተው የሚደርሱበት ድምዳሜ የንፁኃንን ህሊና ሊጎዳ መቻሉም እንደ ተውኔቱ አንድ ጭብጥ ሆኖ ተስተውሏል፡፡ በሌላ በኩል የተገፉ፣ የተጣሉና የተናቁ ሰዎች አገርና ሕዝብ አደጋ ላይ በወደቁ ጊዜ አለኝታ ሆነው ሊመጡ የሚችሉበት ዕድል መኖሩን ከተውኔቱ ላይ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በጭፍን የተጠሉና የተገፉ ሰዎች በድንገት እውነተኛ ማንነታቸው ሲታወቅ በሕዝብም ሆነ በመንግሥት ትልቅ አክብሮት እንደሚሰጣቸው ያሳያል፡፡

በሥልጣን ላይ ለመቆየት ጎራዴን፣ ኃይልና ሥልጣንን ተጠቅሞ የሕዝብን ደም ማፍሰስ፣ ወይስ ሕዝብን አወያይቶ በሰላምና በንግግር ከሚሉት የትኛውን አማራጭ መከተል እንዳለበት ለመወሰን የተቸገረና አጣብቂኝ ውስጥ በገባ አንድ የአገር መሪ ላይ ያተኮረውን ተውኔቱን፣ በአዲስ አበባ ለማቅረብ የተጋውን አዘጋጁን ከሁለት ዓመት በፊት  ከአገር እንዲወጣ ማስደረጉ ተነግሯል፡፡

ሃቻምና ቴአትሩን ለተመልካቾች ለማቅረብ አንድ ወር ያህል ሲቀረው በጎ አስተሳሰብ በሌላቸው ሰዎች በኩል ታግዶ እንደነበርና አዘጋጁ ተክሌ ደስታ ተገዶ ከአገሩ እንዲወጣ ተደርጎ እንደነበር ተወስቷል፡፡

ዋነኛ ርዕስ ጉዳዩን በሕግ የበላይነት ያደረገው ቴአትሩ በዚህ ጊዜ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መዘጋጀቱ እጅግ ወቅታዊ ነው ያሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ዋና ዳይሬክተር ማንያዘዋል እንደሻው ናቸው፡፡

 ልማት ሰላምና ዴሞክራሲ የሚረጋገጠው የሕግ የበላይነት ሲከበር ብቻ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የሕግ የበላይነት በተከበረባቸው አገሮች የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበራሉ፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ጎን ለጎን ይሄዳሉ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄዎች በአግባቡ እስኪመለሱ ድረስ ሕግ የማስከበር ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ተገቢውን ዕርምጃ እንዲወሰድ ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል፡፡

የሕግ የበላይነትን የማስፈኑ ተግባር ይዋል ይደር የማይባል ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ነው ያሉት ኃላፊው፣ ለዚህም የኪነ ጥበብና የፕሬስ አስተዋጽኦ ኢትዮጵያን የተሻለችና ልጆች በሰላም፣ በፍቅር፣ በአንድነትና በነፃነት የሚኖሩባት ያደርጋታል ብለዋል፡፡

‹‹ሥልጡን ሕዝብ ቴአትር ያያል›› ያሉት ደግሞ የዕለቱ የክብር እንግዳ የነበሩት ወዳጄነህ መሐረነ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

‹‹ይህንን ስለ ሕግ የበላይነት መከበር፣ ስለ ዜጎች መብት የሚናገር ቴአትር የኢትዮጵያ ባለሥልጣኖች ቢመለከቱትና ትምህርት ቢወስዱበት ምኞቴ ነው፤›› ሲሉም በማጠቃለያው ላይ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡   

ጥቂት ስለ ተርጓሚው

የቶፊቅን ተውኔት ‹‹መንታ መንገድ›› ብሎ አዛምዶ የተረጐመው ዓለማየሁ ገብረሕይወት፣  ቀደም ሲል የኦስካር ዋይልድ ተውኔትን ‹‹ስጦታ›› በሚል ርዕስ ተርጉሞ በሀገር ፍቅር ቴአትር ለመድረክ በቅቶለታል። ፈላስፋዋ፣ የገንፎ ተራራ፣ ብረትና ሙግት፣ ወቴዎቹ፣ አምሳያ ልጅ፣ ውርክብ፣ ቃለ መጠይቅና ሌሎች ሥራዎቹም በመድረክ፣ በራዲዮና በቴሌቪዥን የቀረቡ ናቸው፡፡፡ በቅርቡም የታዋቂውን አሜሪካዊ ደራሲ የአርተር ሚለርን ተውኔት ‹‹የአሻሻጩ ሞት›› ብሎ ወደአማርኛ መልሶታል።

ኪነ ጥበብ አመለካከትን በመለወጥ፣ የባለሥልጣናትንም ሆነ የማኅበረሰብን ሥነ ምግባርን በማነፅ፣ ፍትሕ እንዲሰፍን በማድረግ ረገድ ያላትን ታላቅ ፋይዳ በዚህ ግዙፍና በሳል ቴአትር ውስጥ ማየት መታደል ነው ይላል ስለ ተውኔቱ የቀረበው ሐተታ፡፡ ‹‹በተረፈ ነገር በዓይን ይገባልና ቴአትሩን ይመልከቱ›› ሲል ለቴአትር አፍቃሪያን ጥሪ ያቀረበው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...

አይ የእኛ ነገር!

የዛሬው ጉዞ ከጀሞ ወደ ፒያሳ ነው፡፡ መንገዱ ለሥራ በሚጣደፉ፣...

የዓለም ኢኮኖሚ መናጋት ለወቅታዊው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 16...