Wednesday, March 29, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያ ከገባችበት አረንቋ ውስጥ በፍጥነት ትውጣ!

የአገር ህልውና ከሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ አገር ሰላም ውላ ማደር የምትችለው ደግሞ የሕዝብ ደኅንነት አስተማማኝ ሲሆን ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥት በአገር ህልውና ላይ በተመሳሳይ ገጽ ላይ መገኘት ሲችሉ፣ ለንትክርና ለግጭት የሚጋብዙ ችግሮች ቁጥራቸው ይቀንሳል፡፡ ሕዝብን ሰላሙንና ደኅንነቱን አስከብሮ የማስተዳደር ኃላፊነት ያለበት መንግሥት፣ ከምንም ነገር በፊት ለተቃርኖ በር የሚከፍቱ ብልሹ አሠራሮችን ማስወገድ ይጠበቅበታል፡፡ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊ ጉዳዮችና በሌሎችም የሚያጋጥሙ ልዩነቶችን በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ የማስተናገድ ኃላፊነትም አለበት፡፡ መንግሥት ትልቁ አደራና ኃላፊነቱ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በእኩልነት ማገልገል ሲሆን፣ አገልግሎቱ ተዓማኒነት የሚኖረው ደግሞ በሕግና በሥርዓት ሲመራ ነው፡፡ በሥራ ላይ ካለው ሕገ መንግሥት ጀምሮ አገሪቱ ያወጣቻቸውና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተቀብላ ያፀደቀቻቸው ሕጎች መከበር አለባቸው፡፡ የመንግሥትና የሃይማኖት ግንኙነት በሕጉ መሠረት መከናወን ሲኖርበት፣ አንዳቸው በሌላኛው ጉዳይ ውስጥ እጃቸውን ማስገባት የለባቸውም፡፡ ለአገር ሰላም፣ ደኅንነት፣ ልማትና ዕድገት ሕግ አክብረው መተባበር ይችላሉ፡፡ ኢትዮጵያ አላስፈላጊ ቅርቃር ውስጥ የምትገባው ሕግ ሲጣስ እንደሆነ ይታመን፡፡

በተለያዩ መስኮች ውስጥ የሚስተዋሉ በርካታ ችግሮች እየተጠላለፉ ሃይማኖት ውስጥ ሰተት ብለው እየገቡ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ለያዥና ለገናዥ ያስቸገሩ ድርጊቶችን ለማስተካከል አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተደራጅቶ ለንግግር ዝግጅት እየተደረገ፣ በዚህ መሀል ሃይማኖታዊ ቀውስ ሊያስከትል የሚችል አደገኛ ተቃርኖ ሲከሰት ሰላማዊ አማራጮች ላይ ማተኮር የግድ ነው፡፡ የሃይማኖት ጉዳይ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ከመሆኑም በላይ፣ አንድም በሃይማኖት ውስጥ ያሉ ሕግጋት ችግር መፍቻ ሆነው እንዲያገለግሉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሕግና ሥርዓት ማስከበር ያለበት መንግሥት ገለልተኛ ሆኖ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ቅንነት፣ አርቆ አሳቢነት፣ ሕጋዊነትና የኃላፊነት ስሜት ያስፈልጋሉ፡፡ በቤተ እምነቶች አካባቢም ለአገር ደኅንነትና ህልውና ሲባል መንፈሳዊነትና አገልጋይነት መዘንጋት የለባቸውም፡፡ በፖለቲካውም ሆነ በተለያዩ መስኮች ውስጥ ያሉ ግለሰቦችም ሆኑ አካላት፣ የማይነኩ ነገሮች እየተነካኩ ቀውስ እንዳይፈጠር መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በበርካታ ችግሮች ተተብትባ መፍትሔ አልባ ጉዳዮች ላይ ማተኮር፣ ወይም ችግሮቹን ማባባስ የማይወጡበት ቀውስ እንደሚፈጥር ይታሰብበት፡፡

በአሁኑ ጊዜ በሁሉም ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ መነታረክና አላስፈላጊ ውዝግቦችን መፍጠር ከመጠን በላይ እየተለመደ ነው፡፡ በሁሉም ብሔራዊ ጉዳዮች የግድ መስማማት ባይቻልም፣ ዋና ዋና በሚባሉት ላይ ግን የጋራ ምልከታ ወይም አቋም መኖር አለበት፡፡ ከሚያግባቡ የጋራ ጉዳዮች መካከል የአገር ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት፣ ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት፣ እንዲሁም ህልውና ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች ለድርድር የሚቀርቡ ካለመሆናቸውም በላይ፣ ሁሉም ዜጎች ያለ ምንም ልዩነት በጋራ የሚቀበሉዋቸው መሆን አለባቸው፡፡ ዜጎች በብሔር፣ በእምነት፣ በፖለቲካ አቋምና በሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች የየራሳቸው መገለጫዎች ቢኖሯቸውም በአገር የጋራ ጉዳይ ግን ፈፅሞ ሊለያዩ አይችሉም፡፡ ይህ ማለት ግን በሌሎች በሚለያዩዋቸው ሐሳቦች ወይም ፍላጎቶች በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ መነጋገር፣ መከራከርና መደራደር ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አሠራር ደግሞ የሥልጡንነት መገለጫ ሲሆን፣ እርስ በርስ ከመጋጨትም ሆነ አላስፈላጊ ድርጊቶችን ከመፈጸም ይታደጋል፡፡ በኢትዮጵያ አሁን የሚስተዋለው ተቃርኖ በጊዜ መላ ካልተበጀለት፣ የተያዘው አደገኛ ጎዳና በጣም አስፈሪ ነው፡፡

እንደሚታወቀው በኢትዮጵያ የፖለቲካው ሠፈር በአብዛኛው የሚታወቀው ጠላት በማብዛት ነው፡፡ ለጋራ አገር ጉዳይ መተባበር ሞት በሚመስልበት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ፣ ጠላት የመፍጠርና የማባዛት እንቅስቃሴ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ የሚከናወን ነው፡፡ ቀጥታው ተፎካካሪዎችን በሙሉ ዓይናችሁን አልይ በማለት ማሳደድ፣ ማወከብ፣ ማሰር፣ ባስ ሲልም መግደል ነው፡፡ ይህ የለየለት አምባገነናዊ አካሄድ ለዘመናት ፖለቲካው ቀጭጮ እንዲቀር ያደረገ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚከናወነው ደግሞ የሥልጣኔ ምልክቶችን በማሳየት በሹመትና በጥቅማ ጥቅም አስሮ የሚያደነዝዝ ሲሆን፣ ከፋ ሲል ደግሞ ሰበብ አስባብ ፈጥሮ በረቀቀ መንገድ ማሽመድመድ ነው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ከፖለቲካው ተዋንያን በተጨማሪ ምሁራንና ልሂቃን፣ የግል ዘርፉ ተዋንያን፣ ዳያስፖራው፣ የሲቪል ማኅበረሰቡ፣ የቤተ እምነት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች እንደ አስፈላጊነታቸውና አሳሳቢነታቸው ደረጃ ይበየናሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የረቀቀ ሥልት ለተቃርኖ መነሻ ምክንያት ከመሆኑም በላይ፣ ጽንፈኝነት ሲታከሉበት የቅራኔውን መጠን ያሰፋዋል፡፡ ከዚህ መሰሉ ቅርቃር ውስጥ በፍጥነት በመውጣት አገርን መታደግ ይገባል፡፡

በዚህ ዘመን የሐሳብ ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ እያስተናገዱ የአገረ መንግሥት ግንባታውን በትብብር ማከናወን ሲገባ፣ እንደ ባቢሎን ግንብ ሰዎች መግባባት ሲቸግር መጪው ጊዜ ከባድ እንደሚሆን ለመገንዘብ ምንም ማጣቀሻ አያስፈልግም፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ በየዕለቱ እያጋጠሙ ያሉ ክስተቶች ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን፣ ከትብብር ይልቅ መተናነቅን፣ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን፣ ከመተማመን ይልቅ ጥርጣሬን የሚያጠናክሩ ናቸው፡፡ የብሔርንም ሆነ የእምነት ማንነትን ይዞ አንዲት የጋራ አገርን የእኩልነትና የፍትሐዊነት አምባ ማድረግ እየተቻለ፣ በየቀኑ ክፋትና ሴራ የተጠናወታቸው ድርጊቶች እየበዙ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ለአገር ጠቃሚ አስተዋፅኦ ለማበርከት አቅሙም ሆነ ችሎታው ያላቸው ወገኖች፣ ከአደባባይ እየተገፉ በዝምታ እንዲሸበቡ እየተደረጉ በቅጡ መነጋገር አልተቻለም፡፡ በመደበኛው ሚዲያም ሆነ በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች በአብዛኛው ጎልተው የሚሰሙ ድምፆች፣ ከሰከነ ንግግርና ድርድር ይልቅ የፍለጠውና የቁረጠው ፕሮፓጋንዳ ማስተጋቢያ ሆነዋል፡፡ ስሜት ከሚያሞቁና ለጠብ ከሚቀሰቅሱ ፉከራዎች በስተቀር፣ የደረጁ ሐሳቦች መንሸራሸር ባለመቻላቸው ተቃርኖው ሞልቶ እየፈሰሰ ነው፡፡ የዚህ ውጤቱ ደግሞ ጥፋት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ ከሚታወቅባቸው አኩሪ የጋራ እሴቶቹ መካከል ሕግ አክባሪነት፣ አገር ወዳድነት፣ አርቆ አሳቢነት፣ ትሁትነት፣ ሰብዓዊነትና ሌሎች መልካም ነገሮች ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ አኩሪ እሴቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸሩ ቢሆንም፣ አሁንም አብዛኛው ሕዝብ በመልካም ጎዳና ላይ እንደሚራመድ ማንም የማይክደው ነው፡፡ ይህንን የመሰለ ጨዋና ሕግ አክባሪ ሕዝብ የማይወክሉ አስከፊ ድርጊቶች እየተፈጸሙ ያሉት፣ የተሻለ ትምህርትና ዕውቀት አለን በሚሉ ልሂቃን መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ በአራቱም ማዕዘናት ውስጥ የሚኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የብሔርም ሆነ የእምነት ልዩነት መኖራቸው እስከማያስታውቅ ድረስ ተሳስቦና ተፋቅሮ እየኖረ፣ አካብተናል በሚሉት ዕውቀት ለአገር የሚጠቅሙ በርካታ ተግባራትን ማከናወን የሚጠበቅባቸው ልሂቃን ግን ግጭት ጠመቃ ውስጥ ናቸው፡፡ ሕዝቡ ልዩነቶችን በፀጋ ተቀብሎ ተጋብቶና ተዋልዶ አብሮ እየኖረ፣ እነሱ ግን ይህንን የሚያኮራ መስተጋብር በመበጣጠስ አገር የሚያፈርሱ ፕሮጀክቶችን ይጠነስሳሉ፡፡ በተለይ ፖለቲካው ውስጥ እስከ አንገታቸው የተነከሩ ልሂቃንና አጃቢዎቻቸው፣ ከእነሱ በላይ ኢትዮጵያ የሌለች ይመስል ህልውናዋን እየተፈታተኑ ከባድ ጥፋት እየጋበዙ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ መቀጠል ስለማይቻል ኢትዮጵያ ከገባችበት አረንቋ ውስጥ በፍጥነት ትውጣ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...

አይ የእኛ ነገር!

የዛሬው ጉዞ ከጀሞ ወደ ፒያሳ ነው፡፡ መንገዱ ለሥራ በሚጣደፉ፣...

የዓለም ኢኮኖሚ መናጋት ለወቅታዊው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 16...

የተዘነጋው የከተሞች ሥራ የመፍጠር ተልዕኮ

በንጉሥ ወዳጅነው አሁን አሁን የአገራችን የሥራ ዕድል ፈጠራ ጉዳይ አንገብጋቢና...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሰላም ዕጦትና የኑሮ ውድነት አሁንም የአገር ፈተና ናቸው!

ማክሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በርካታ ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡ ጥያቄዎቹ በአመዛኙ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ...

ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ለአገር አይበጅም!

ሰሞኑን የአሜሪካና የኢትዮጵያ መንግሥታት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች መግለጫ ላይ አልተግባቡም፡፡ አለመግባባታቸው የሚጠበቅ በመሆኑ ሊደንቅ አይገባም፡፡ ነገር ግን...

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...