Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ከ12ኛ ፈተና ውጤት ጋር በተያያዘ ጉዳዩ ትልቅ ፕሮጀክት ሆኖ መጠናት አለበት›› ብርሃነ መስቀል ጠና (ዶ/ር)፣ የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት

ሰሞኑን ይፋ የሆነው የ12ተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት እጅግ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ጉዳዩ በኢትዮጵያ የመማር ማስተማር ሒደት ስለመበላሸቱ ትችት እያሰነዘረ ነው፡፡ የትምህርት ጥራት ማሽቆልቆል ዋና መገለጫ ሆኖ በመቅረብ ላይም ይገኛል፡፡ ይህን ሰሞነኛ ጉዳይ በተመለከተ፣ እንዲሁም ከወቅታዊው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ጥያቄ ጋር በተያያዘ ዮናስ አማረ ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርሃነ መስቀል ጠና (ዶ/ር) ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤትን ትምህርት ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ የተመዘገበው ውጤትም እጅግ ዝቅተኛና አስደንጋጭ በመሆኑ ምን ዓይነት አስተያየት አለዎት?

ብርሃነ መስቀል (ዶ/ር)፡- የዘንድሮው ብሔራዊ ፈተና ውጤት እንደተባለው አስደንጋጭና ዝቅተኛ ነው፡፡ በአንድ በኩል ደግሞ በፈተና አሰጣጥ ሒደት የተሠራው ሥራ በጣም አበረታች ነው፡፡ ምክንያቱም ወደ ውስጥ ገባ ብለን ባለማየታችን ብዙ ችግር ተሸክመን መኖራችንን ያወቅንበት አጋጣሚ ነው፡፡ ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ሲመጡ አንዳንዶቹ ስማቸውን መጻፍ የማይችሉ ልጆች ሲያጋጥም ቆይቷል፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የሚገባቸውን ዕውቀት ጨብጠው ለመውጣት ብዙ ማገዶ የሚፈጁ ያጋጥሙናል፡፡ በየትኛውም ቋንቋ ስማቸውን በቅጡ የማይጽፉ ብዙ ልጆች እያጋጠሙን እነሱን ለማስተማርም ብዙ ልፋት ሲጠይቀን ቆይቷል፡፡ ይህ ለምን ሆነ የሚለው የሁልጊዜ ጥያቄ ደግሞ አሁን በ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት ተመልሷል፡፡ የመጣው ውጤት 3.3 በመቶ ብቻ ተፈታኝ እንዳለፈ ነው የሚያሳየው፡፡ ልጆቻችን ባዶ እንደሆኑ በዚህ ውጤት ዓይተናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሠሩና ጥሩ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችም አሉ፡፡ በእርግጥ አንድ ፈተና ሲወጣ ሳይንሳዊ መንገዶችን ተከትሎ ነው መውጣት ያለበት፡፡ ዝርዝር መለኪያዎችን ተከትሎ ነው መውጣት ያለበት፡፡ ፈተናው መዛኝ ነው ወይ? የሚለው መሠረታዊ ጉዳይ ሲሆን ይህ ግን የተደረገ አይመስለኝም፡፡ የፈተናው ክብደትና ቅለትም መፈተሽ ያለበት ሲሆን ይህም የተደረገ አይመስለኝም፡፡ ፈተና አውጪዎቹ እነማን ናቸው የሚል ጥያቄም ይነሳል፡፡ ይህ ሁሉ መሠረታዊ ነጥብ መመለስ አለበት፡፡

ነገር ግን እንደ አጠቃላይ ሲታይ ፈተናው የመለየት አቅም እንደነበረው ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በእኛ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ሥር በእኛው በጀት የሚተዳደር ትምህርት ቤት አለን፡፡ ወደ 67 ተማሪዎችን ትምህርት ቤቱ ያስፈተነ ሲሆን መቶ በመቶ አልፈዋል፡፡ ወደ 16 ልጆች ከ600 በላይ ነው ያመጡት፡፡ ሌሎቹም 500 ነው ያመጡት፡፡ አንድ ልጅ ብቻ ነው 375 ያመጣው፡፡ ይህንና የአንዳንድ ትምህርት ቤቶችን ውጤት ስታይ ፈተናው ለሚሠራ ሰው የሚሠራ እንደነበር፣ ጎበዙን ከሰነፍ የሚለይ መሆኑን ታረጋግጣለህ፡፡ ይህን ሊሠራ የሚችል ፈተና ደግሞ ብዙዎች አላለፉም ማለት ራሱን የቻለ ችግር ነው ማለት ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ውድቀት መነሻ ደግሞ ከታች ነው፡፡ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ የትምህርት ፖሊሲያችን ውድቀት ነው ማለት ነው፡፡ አሁን ስለታየ እንጂ ችግሩ የጀመረው ከታች ነው፡፡ ቀደም ብሎ እንደዚህ ቢደረግ ኖሮ መልካም ነበረ ብዬ እቆጫለሁ፡፡ ከታች ጀምሮ እስከ አራተኛ ክፍል ዝም ብሎ ሳይፈተሸና ሳይመዘን በአውቶማቲክ ፕሮሞሽን እያለፈ ይመጣል፡፡ ወደ ሌሎች ክፍሎች ሲሸጋገርም ሆነ ሀይ ስኩል ሲገባ ልል በሆነ ምዘና ክፍል እየቆጠረ ነው የሚያልፈው፡፡ በመጨረሻ ግን ወደዚህ ዓይነት ዝቅተኛና አስደንጋጭ ውጤት ነው የተመለስነው፡፡ ዩኒቨርሲቲም ሲገባ ቢሆን በአብዛኛው መምህሩ እያስታመመ ነው ተማሪውን ለምረቃ ሲያበቃ የቆየው፡፡ ምን ይዞ ተመረቀ ሲባል የሚገባውን ሳይሆን የሚችለውን ያህል ይዞ ተመረቀ ይባላል፡፡ ይህ አካሄድ ነው ትልቁ ችግራችን ሆኖ የቆየውና መታየትም ያለበት፡፡

ሪፖርተር፡- በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለተማሪ የሚመደበው በጀት አይበቃም የሚል ቅሬታ አለ፡፡ የበጀት እጥረት ይገጥማቸዋል ይባላል፡፡ ከመምህራን ጋር የተገናኙ ጥያቄዎችም  አሉ፡፡ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለመማር ማስተማርም ሆነ ለትምህርት ጥራት እንቅፋት ሆኖባቸዋል የሚሏቸው ችግሮችን ቢያብራሩልን?

ብርሃነ መስቀል (ዶ/ር)፡- የትምህርት ጥራት መጓደል ብዙ ምክንያቶች ተደራርበው የሚፈጥሩት ችግር ነው፡፡ ለትምህርት ጥራት የመጀመሪያው ቁልፍ መምህሩ ነው፡፡ መምህሩ ወደ ክፍል ከመግባቱ በፊት ከእንቅልፉ ጊዜ ቀንሶ በአግባቡ ካልተዘጋጀ፣ ሥነ ልቦናውን ዜጋ ለመቅረፅ ካላዘጋጀ፣ ደስ ብሎት ክፍል ውስጥ ካልገባ፣ ደስ ብሎት ካላስተማረ ጥሩ ትምህርት ቤት ስለሠራ ወይም ጥሩ ጥናታዊ ወረቀት ስላሳተመ ብቻ መማር ማስተማሩ ውጤታማ አይሆንም፡፡ ጥሩ ክፍል ወይም ወንበርና ቢሮ ስላዘጋጀህ ብቻ የትምህርት ጥራትን አታረጋግጥም፡፡ መምህሩ ትምህርቱን በአግባቡ ለተማሪው በሚያቀብልበት የተሟላ ቁመና ላይ መገኘት አለበት፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ መምህሩን ማነቃቃት አለብህ፣ ለዜጋ እንዲያስብ ማድረግ አለብህ፣ ትውልድ የመቅረፅ ዘር እየዘራ እንደሆነ በአግባቡ እንዲያውቅ ማድረግ አለብህ፡፡ ትውልድ ቀረፃን ከጥቅም ማግኘት ጋር እንዳያገናኝ ማድረግ አለብህ፡፡ መምህሩ ላይ መሠራት ያለበት ሥራ ብዙ ነው፡፡

ተማሪውን በተመለከተ ከታች አልፎ የመጣበትን የትምህርት መሠረትን በአግባቡ መገንዘብ የመጀመሪያው ሥራ ነው፡፡ በአንድ ጀንበር ሥራ ተማሪውን እለውጣለሁ ብሎ ማሰብ ስህተት ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲ ለሚኖረው የአራትና የአምስት ዓመት የትምህርት ቆይታ፣ እንዲሁም የምርምር ሥራ ብቻ ተማሪውን መቀየር ይቻላል ብሎ ማሰብም ከባድ ነው፡፡ ለ12 ዓመታት የቆየበትን የትምህርት ሕይወት ለመቀየር ብዙ ፈታኝ ሒደት አለው፡፡ ስለዚህ ከታች ጀምሮ ተማሪው የሚሰጠው ትምህርት በዩኒቨርሲቲ ከሚያገኘው ዕውቀትና ክህሎት ጋር የተሳሰረ መሆን አለበት፡፡ ልጆችን ከታች ማውጣት ተደጋግሞ ይባላል፣ ነገር ግን ይህን የሚያደርግ ብዙም አይታይም፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች አሠልጥነው አስተማሪ ያደረጉት ሰው ነው ከታች አዳዲስ ትውልድ እያስተማረ ወደ ዩኒቨርሲቲዎች የሚልከው፡፡ ተማሪው ከታች በአግባቡ ተምሮ ካልመጣ ብቻ ሳይሆን ተማሪውን የሚቀርፀው መምህር በአግባቡ ተምሮ አስተማሪ ካልሆነ ችግሩ ከታችም ከላይም ይሆናል፡፡ ተማሪው ብቻ ሳይሆን ከመንገድ ጎራ ያለ ሰው አስተማሪ የሚሆን ከሆነ ሥርዓት በሁሉም አቅጣጫ የተበላሸ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ኮተቤ በተለይ መምህራንን ማፍራት ላይ ነውና በአብዛኛው የሚታወቀው ብቁ አስተማሪዎችን ለማውጣት የምትከተሉት የተለየ ጥንቃቄ ምንድነው?

ብርሃነ መስቀል (ዶ/ር)፡- መምህርነት ከምንም በፊት ዝንባሌ ነው፡፡ ዕውቀትና ክህሎት ቀጥለው የሚመጡ ጉዳዮች ናቸው፡፡ መምህር ድንጋይ ጠርቦ ሕንፃ ወይም እንጨት ቀርፆ ጠረጴዛ አይደለም የሚሠራው፡፡ ከዚያ በላይ ሕንፃውንም ጠረጴዛውንም የሚሠራ ዕውቀትና ክህሎት የጨበጠ ሰው ነው የምሠራው ብሎ አንድ መምህር መቀበል አለበት፡፡ መምህር ከምንም በፊት ሰው መቅረፅ ላይ ማተኮር አለበት፡፡ ይህን ከምንም ነገር ጋር ሳያገናኝ ለመሥራት ደግሞ ፍላጎቱና ዝንባሌው ያስፈልገዋል፡፡ አሁን  እንደሚታየው ግን ሥራ ያጣ ሰው ወይም ከመንገድ ላይ ጎራ ያለ ሁሉ መቆያ እንዲሆነው እያስተማረ ይገኛል፡፡ በተለይ በታችኛው የትምህርት ዕርከን ይህ አሠራር የተለመደ ነው፡፡ እኛ እንደ ኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ስናቅድ ፈተና አልፎ የገባውን ልጅ አመለካከት መቀየር ላይ አተኩሮ መሥራትን ቅድሚያ እንሰጣለን፡፡ እኛ በተለያዩ ሙያዎች ምሩቃንን መምህራን እናደርጋለን፡፡ ይህ አሠራር አያስፈልግም እያልኩም አይደለም፡፡ ነገር ግን የማስተማር ሳይንሱን ማወቅ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ አንድ በፊዚክስ የተመረቀ ሰውን አስተማሪ ብናደርገው ‹‹ሀው ቱ ኦፕሬት ሜታል ተብሎ ተምሮ ሀው ቱ ኦፕሬት ሜንታል›› በመሆኑ፣ ‹‹ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ›› ዓይነት ነው የሚሆነው፡፡ ፊዚክስ ምሩቁ ወደ ኢንዱስትሪ ቢሄድ ነው የሚሻለው፡፡ ወደ መምህርነት አይምጣ አይደለም፣ ወደ መምህርነት ለመምጣት ግን የሰው ልጅ ዕድገትና ፀባይ (ብሔቬራልና ዴቨሎፕመንታል ሳይንሱን) ማወቅ አለበት ነው የምንለው፡፡

ለሕፃናት የሚሆን ትምህርት ምንድነው? የሕፃናት ልዩ ባህሪ ምንድነው? የታዳጊዎች፣ የጎረምሶችና የጎልማሶች ፀባይና ፍላጎትስ ምንድነው? ብሎ በየዕድሜ ዘርፉ የሰዎችን ባህሪ ተረድቶ መሆን አለበት ዕውቀት ወደ መቅዳቱ ሊገባ የሚገባው፡፡ በዚህ ረገድ ሥራ ውስጥ ያሉ መምህራንን በክረምት በሚሰጡ መርሐ ግብሮች የማብቃት ሥራ እንሠራለን፡፡ ክረምት ወቅትን ለዚህ ማዋል አለብን፡፡ መምህሩ በሙያው የበቃ እንዲሆን በየጊዜው ራሱን በዕውቀት ማደስ ይገባዋል ተብሎ በዚህ በኩል ሰፊ ሥራ እንሠራለን፡፡ መምህራን ለመምህርነታቸው ብቁነት ማረጋገጫ መውሰድ አለባቸው፡፡ አንድ ሰው መንዳት የሚፈቀድለት ተምሮና በተግባር ተፈትኖ ሲረጋገጥ እንደሆነው ሁሉ፣ መምህሩም ለማስተማርና ትውልድ ለመቅረፅ በትምህርት አሰጣጥ ዕውቀት ሰርቲፋይድ መሆን አለበት፡፡ የትውልድ ዕድገት ባህሪን ማወቅ መምህርነት ይጠይቃል፡፡ ትምህርት አሰጣጥን፣ ፈተና አወጣጥን፣ ካሪኩለም ቀረፃን፣ በአጠቃላይ ሙያው የሚጠይቀውን ማወቅ አለበት፡፡ መምህር የተማሪዎቹን አዕምሮ እንዴትና መቼ መክፈት እንዳለበት ማወቅ ብቻ ሳይሆን፣ ዕውቀቱን በአግባቡ ወደ ከፈተው ጭንቅላት ውስጥ የማስተላለፍን ጥበብ የተካነ መሆን አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- የዘንድሮ 12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት መውረድን ተከትሎ አስተማሪዎችም በነካ እጃቸው ተፈትነው ውጤታቸውን ባየነው የሚል ቀልድ የሚመስል ትችት እየቀረበ ነው፡፡ መምህሩ በየጊዜው ራሱን ማሻሻልና መመዘን የለበትም?

ብርሃነ መስቀል (ዶ/ር)፡- ዕውቀት ሁል ጊዜ አዲስ ነው፡፡ ትናንት ከተማርኩት ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬ ዝም ብዬ ሞባይሌን ስነካካና ጉግል ሳደርግ ብዙ ዕውቀቶችን አገኛለሁ፡፡ መምህር ራሱን እያሻሻለና ከወቅቱ ጋር ራሱን እያስተያየ መሄድ አለበት፡፡ ሙያውን የሚያሻሽልና የሚያነብ መሆን አለበት፡፡ የማያነብ መምህር አብዴት ካልተደረገ ኮምፒዩተር ጋር ይመሳሰላል፡፡ ልክ ሥራውን ለመሥራት እንደሚቸገር ወይም ዝም ብሎ እንደሚሽከረከር ኮምፒዩተር ሁሉ፣ መምህሩም ካላነበበና ከወቅቱ ጋር እኩል ካልተራመደ ራሱን አያሻሽልም፡፡ መምህሩ ኑሮ ሊከብደውና ሕይወት ሊጎድል ይችላል፡፡ ነገር ግን ሙያውን ለምንም ነገር መስዋዕት ማድረግ የለበትም፡፡ መምህር ሙያውን ሳይበድል ነው ጥያቄ የሚያቀርበው፡፡

ሪፖርተር፡- የመምህራን ጥያቄ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጎላ ነው መነሻው ምንድነው?

ብርሃነ መስቀል (ዶ/ር)፡- ዋናው ጥያቄ የኑሮ ሁኔታ ነው፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበሩ ውይይቶች በተደጋጋሚ መምህራኑ ያነሱት ይህንኑ የተመለከተ ጥያቄ ነው፡፡ ኑሮ ከብዶናል፣ ገበያውንና ቤት ኪራይን ልንቋቋም አልቻልንም፣ አንዳንዶች መምህራን ደግሞ እስኪርበን ደረስን ብለው ነው የጠየቁት፡፡ አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ በተለይ ጦርነት ውስጥ እንደ መቆየታችን መምህራን ጥያቄያቸውን ለማንሳት የሚያስችል ላይሆን ይችላል፡፡ ኢትዮጵያን ለማድቀቅ ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ ኃይሎች ከአገር ውስጥ ጠላቶች ጋር ተጋግዘው ብዙ ሴራዎች ተሠርተዋል፡፡ በዓለም ዙሪያ እየተፈጠሩ ያሉ የኢኮኖሚ ችግሮች፣ የዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት ሁሉ ሁላችንም ላይ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ ነዳጅ አምራች አገር አይደለንም፣ ወይም ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ገና አልተላቀቅንም፡፡ ይህ ሁሉ እያለ መምህራን ለምን ጥያቄ አቀረቡ ቢባልም፣ ነገር ግን ባለው ተጨባጭ ችግር ዙሪያ ተቀራርቦ መወያየቱ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመምህራኑን ችግር ማድመጣቸው ብቻ ሳይሆን በበጎ ተቀብለው ለመፍትሔው በጋራ እንደሚሠሩ ተስፋ መስጠታቸው ትልቅ ነገር ነው፡፡ እኔ በግሌ በመቀራረብና በመወያየት ብዙ ለውጥ ይመጣል እላለሁ፡፡ በአጭር ጊዜና በረዥም ጊዜ የሚመለሱ ተብሎም በውይይቶቹ መፍትሔ ተቀምጧል፡፡ ከመምህራን ጥቅማ ጥቅም ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በቅርብ ጊዜ ለመመለስ እኛም እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ዩኒቨርሲቲዎች ራስን በራስ የማስተዳደር ነፃነት ሲያገኙና ከመንግሥት ጥገኝነት ሲላቀቁ ይህን መሰል ችግሮች ይፈታሉ?

ብርሃነ መስቀል (ዶ/ር)፡- የመምህራን ጥያቄ እንደ አገር አጠቃላይ ምላሽ የሚፈልግ  ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲዎች በራሳቸው የመቆም (አውቶኖሚ) ግን በሒደት የሚመጣ ጉዳይ ነው፡፡ ካሉን ዩኒቨርሲቲዎች ብዛት አንፃር አንዳንዶች በቶሎ ራስን ወደ መቻል ሊገቡ የሚችሉ ቢኖሩም፣ ቀስ በቀስ ወደ እዚያ የሚሸጋገሩም አሉ፡፡ መጀመርያ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ቀጥሎ ደግሞ ስምንቱ ቀደምት ዩኒቨርሲቲዎች ይገባሉ፣ ከዚያ ሌሎቹ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ይከተላሉ ተብሎ ነው የሚገመተው፡፡ የመምህራን ጉዳይ በአጭር ጊዜ በረዥም ጊዜ ተብሎ የሚፈታ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ቢሆኑ የመምህራኑን ጥያቄ በቀናነት ነው የተቀበሉት፡፡ ከአገሪቱ ኢኮኖሚ አቅም፣ እንዲሁም በአጠቃላይ አገሪቱ ከምትገኝበት ሁኔታ አንፃር በቶሎ የማይመለሱ ጥያቄዎች መኖራቸውን መምህራኑም ቢሆን በቅጡ ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ መንግሥት በበጎ ተቀብሎ ተስፋ መስጠቱ ግን ትልቅ ነገር ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ስንት ዓመት ሞላው ምን ያህል ትምህርቶች ይሰጣል? ለወደፊትስ ምን እያቀደ ነው?

ብርሃነ መስቀል (ዶ/ር)፡- ኮተቤ በየጊዜው ራሱን እየቀያየረ ነው የመጣው፡፡ መጀመርያ ኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ነበር፡፡ ቀጥሎ ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ሆነ፡፡ አሁን ደግሞ ወደ ቀደመ ማንነቱ እየተመለሰ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ኮተቤ መምህራን ትምህርት ዩኒቨርሲቲ አይደለም፡፡ ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ትምህርት ደግሞ ሰፊ ነው፡፡ ለኢንጂነሪንጉ፣ ለመከላከያው፣ ለኢንተለጀንሱ፣ ለመምህርነቱና ለሁሉም ትምህርት ያስፈልጋል፡፡ ጠፈር ላይ ለመውጣት የጠፈር ምርምር ተቋማት ውስጥ ትምህርት መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ማዕድን ለማውጣት እንዴት እንደሚቆፈር የሚያስተምር ሰው ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር መምህራን ትምህርት ካልን ይገደባል፣ ወይም አንድ ሙያ ተኮር ብቻ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ተብሎ ነው የሚገለጸው፡፡ በርካታ ያልተጠቀምንባቸው የትምህርት መስኮች አሉ፡፡ እነዚህን ይዘን ነገ የተሻለ ትውልድ ለማምጣት በትምህርት አሰጣጥ (በፔዳጎጂው) ብዙ ሥራዎችን እየሠራን ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ከ12ኛ ክፍል ውጤት መውረድ ምን መማር ይቻላል? ችግሩን ለመቅረፍስ ምን ቢደረግ ይበጃል?

ብርሃነ መስቀል (ዶ/ር)፡- በኢትዮጵያ የመቶ ዓመታት የትምህርት ታሪካችን የትምህርት ኮሌጅ እንኳን አልነበረንም፡፡ አሁን ግን ይህ ተለውጦ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ አለን፡፡ ይህን መሰል የትምህርት ኮሌጅ ወይም ዩኒቨርሲቲ ባለመኖሩ ነው የሰሞኑ 12ኛ ክፍል ዝቅተኛ ውጤት የተመዘገበው፡፡ መምህርን በሙያ የማይቀርፅ በአንድ ትምህርት ብቻ የሠለጠነ ባለሙያ (ሰብጀክት ኦሪየንትድ) አድርጎ የሚያወጣ አሠለጣጠን ስለተከተልን ነው የትምህርት አሰጣጣችንና የትምህርት ጥራት የተበላሸው፡፡ ‹‹ሀርሞናይዝድ›› በሚባል በአንድ የሆነ ቦታ ላይ ብቻ በተዘጋጀ ካሪኩለም መምህር ማፍራት ውጤቱን ዓይተናል፡፡ መምህሩን ይኸው ካሪኩለም ነው የወለደው፣ የዚህ ካሪኩለም ፍሬም ይኸው ታይቷል፡፡ መምህርነት ከባድ ሙያ ነው፡፡ ያለ መምህር ትምህርት እየተሰጠ ነው ያለው፡፡ የመምህርነት ምንነት በመንግሥትም ሊታወቅ ይገባል፡፡ መምህርነት መምህርነትን የተማረ ሰው ይፈልጋል፡፡ ሙያው ከመንገድ ጎራ የሚባልበት መሆን የለበትም፡፡ በግብርና፣ በኢኮኖሚክስ፣ በምንም ሙያ ሊመረቅ ይችላል፡፡ የተመረቀበት ውጤት 3.8 ነው ተብሎ ብቻ አንድ ሰው መምህር ሊሆን አይገባም፡፡ በመምህርነት መሠልጠን መቻል አለበት፡፡ የማስተማር ክህሎትን ማወቅ አለበት፡፡ አንድ ሙያ ስለያዘ ብቻ ዘው ብሎ አስተማሪ መሆን የለበትም፡፡

ከ12ኛ ፈተና ውጤት ጋር በተያያዘ ጉዳዩ ትልቅ ፕሮጀክት ሆኖ መጠናት አለበት እላለሁ፡፡ ከተፈታኞች ሦስት በመቶ ብቻ አለፉ፣ ውጤቱ አሽቆለቆለ በሚል የአንድ ሰሞን ሆይ ሆይታ ብቻ ጉዳዩን ማለፍ የለብንም፡፡ ትምህርት ሥርዓታችን ወደቀ ብቻ ብለን ማለፍ የለብንም፡፡ ለምንድነው ይህ የሆነው ብለን የሕመሙን ምንጭ መፈተሽና ማወቅ አለብን፡፡ ያን ስናደርግ ነው የትምህርቱን ችግር በአግባቡ ለማከም የሚረዳው፡፡ በእኛ አገር እንደተለመደው ግን አንድ ሰሞን ለሆይ ሆይታ ተወርቶ ተረስቶ ይተዋል፡፡ ይህ ግን የትውልድ ዕጣ ፈንታ ጉዳይ ነውና እንዲሁ ሳይታለፍ ችግሩ ለመፍትሔ በሚረዳ መንገድ መጠናት አለበት እላለሁ፡፡    

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተተገበረው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማ ነው ለማለት ያስቸግራል›› አቶ አሰግድ ገብረመድህን፣ የፋይናንስ ባለሙያና አማካሪ

የዓለም ኢኮኖሚ በተለያዩ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ነው፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ የእያንዳንዱን አገር በር አንኳኩቷል፡፡ መንግሥታት ይህንን ችግር ለማርገብ የተለያዩ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ...

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...

‹‹የግሉን ዘርፍ በመዋቅር መለያየት የነበሩ ችግሮችን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አያመጣም›› አቶ ሺበሺ ቤተማርያም፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በኢኮኖሚክስ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና ዕቅድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለ36 ዓመታት የዘለቀ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፍ...