Wednesday, March 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ስለአገር ኢኮኖሚ ማሰብ የነበረባቸው ጭንቅላቶች በማያባሩ ግጭቶች ተነጥቀዋል!

አገራችን ኢትዮጵያ ውጪያዊና ውስጣዊ ፈተናዎቿ መብዛት ብዙ ዋጋ እያስከፈላት ነው፡፡ ለዓመታት ያልተቋረጠ አለመረጋጋት ተጭኗታል፡፡ አንዱን ችግር ተወጣን ሲባል ሌላ አጀንዳ በቅሎ የሚፈጠረው ውዥንብርና አለመረጋጋት ከማኅበራዊ ቀውሱ ባሻገር ኢኮኖሚውን በእጅጉ እየጎዳው መምጣቱ አሳሳቢ እየሆነ ነው፡፡ 

ግጭትና አለመረጋጋትን የሚፈጥሩ የተለያዩ አወዛጋቢ አጀንዳዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የሚያስከትሉ ናቸው፡፡ በተጨባጭ እንደሚታየውም እያንዳንዱ ግጭትና ጦርነት የአገርን ካዝና በልቷል፡፡ አሁን ደግሞ በተለያዩ ግጭቶችና በሰሜኑ ጦርነት የወደሙ ንብረቶችን ለመተካትና ለመልሶ ግንባታ ተጨማሪ ወጪ እያስወጣ ነው፡፡ ይህ ሳያንስ በላይ በላዩ የሚደረቡ ግጭት ቆስቋሽ አጀንዳዎች ትልቅ ፈተና ሆነዋል፡፡ ስለዚህ በየአካባቢው የሚፈጠሩ ትንንሽ ግጭቶችም ሆኑ ብዙ መስዋዕትነት የጠየቀው የሰሜኑ ጦርነት በኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥሩት ተፅዕኖ ቀላል እንደማይሆን ግልጽ ነው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ ግጭቶችና ያለመረጋጋቶች ተደማምረው ሲታዩ የአገርን ኢኮኖሚ ከመጉዳት በላይ ዘላቂ የሆነ የኢኮኖሚ ልማት እንዳይኖር እያደረጉ ነው፡፡ 

ንግድ፣ ኢንቨስትመንትና አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ጤና የሚሆኑት ሰላም ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ዛሬ ለሸክም የከበደን የዋጋ ንረት ሳይቀር እንዲህ ገዝፎ የሚታየው ያለመረጋጋቱ በፈጠራቸው ጫናዎች ጭምር መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ነጋ ጠባ የብሔር፣ የባንዲራ፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የዘርና የመሳሰሉ አጀንዳዎች እየተነሱ በእነዚህ ላይ የሚጠፋው ጊዜና ገንዘብ የኢኮኖሚው ጉዳይ እንዲዘነጋ ማድረጉ በእጅጉ ያሳስባል፡፡

ሕዝብን ለውዥንበር የሚዳርጉ ፖለቲካዊ ጉዳዮችና ንትርኮች መልካቸውን እየቀያየሩ ያለማቋረጥ መቀጠላቸው ደግሞ የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንዳይኖረንና በዋጋ ንረትና በኑሮ ውድነት ላይ እያሳደረ ያለውን ጫና ለመከላከል ያላስቻለም ሆኗል፡፡

በአንድ ቦታ መንገድ ተዘጋ ሲባል እንቅስቃሴዎች የመገደባቸውን ብቻ አይነግረንም፡፡ በዚያ መንገድ የሚካሄድ የንግድ ልውውጥ የቢዝነስ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ታመሙ ማለት ነው፡፡ 

እንዲህ ያለ ሥጋት ተፈጥሯልና ዜጎች በዚህ አካባቢ አይንቀሳቀሱ ሲባል የንግድና የቢዝነስ እንቅስቃሴውም አብሮ ይገደባል። በየጊዜው የሚቀሰቀሱ አንዳንድ ሕዝብን የሚያነጋግሩ ጉዳዮችም ቢሆኑ፣ የሚፈጥሩት ጡዘት ለኢኮኖሚው የተመቸ አይደለም፡፡ ሸኔ በዚህ መጣ በዚህ ሄደ ዜጎችን ገደለ፣ አፈናቀለ የሚሉ ዜናዎች የዜጎችን ሕይወት ከማሳጣትና ማኅበራዊ ቀውስ ከማሳደር ባለፈ ሀብትና ንብረትም እያወደመ መቀጠሉንና የአገር ሀብት በዛው ልክ በከንቱ እየጠፋ መሆኑን የሚያሳየው። ሸኔ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች እየፈጸመ ነው የተባለውን ድርጊት የሰማ ኢንቨስተር በእነዚህ አካባቢዎች የልማት ሥራዎች ላይ ሊሰማራ አይፈቅድም፡፡ ኢንቨስተሮች ዕቅዳቸውን እንዲሰርዙ ከማድረጉ ባሻገር እየተፈጠሩ ባሉት ግጭቶች ምክንያት ባለፉት ስድስት ወራት ለብሔራዊ ባንክ መቅረብ ያለበት ወርቅ ምን ያህል እንዳሽቆለቆለና በኮንትሮባንድ በሚወጣ የኢትዮጵያ የወርቅ ሀብት ጎረቤት አገራት ምን ያህል እየተጠቀሙ እንደሆነ እየሰማን ነው።

ሰሞኑንና ከዚያም ቀደም ብሎም ሸኔ አማጺ ኃይል ትልልቅ የእርሻ ጣቢያዎች ላይ ያደረሰው ውድመት ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ምርት ላይ ተፅዕኖ ማሳረፉን በምሳሌነት መጥቀስም ይቻላል፡፡ በእነዚህ እርሻዎች ላይ በደረሰው ጥቃት ሥራዎች ተስተጓጉለዋል፡፡ አደጋው ከደረሰ በኋላ አንፃራዊ የሆነ ሰላም ተፈጠረ ቢባል እንኳ በተፈጠረው ሥጋት ለማምረት የተቸገሩ ባለሀብቶች አሉ፡፡ የጠፋውን ንብረት መልሶ ወደነበረበት የማምረት ሥራ ለመመለስ የሚጠይቀው ወጪ ቀላል ያለመሆኑ ሲታሰብ ማንኛውም ግጭትና ጦርነት ሄዶ ሄዶ አገራዊ ኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥረው ጫና ከፍተኛ ነው፡፡

በሚረባውም በማይረባውም ጉዳይ የሚፈጠሩ ግጭቶች፣ ዘር ተኮር ንትርኮች፣ አሁን እያንጃበበ ባለው ሃይማኖታዊ መካረሮችና የግጭት ስጋቶች የሚያስከትሉት ጥፋት እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፡፡ ይብዛም ይነስም መንግሥት ያልታሰበ ወጪ የሚያስወጡ ለልማት የተያዙ በጀቱንም የሚነኩ በመሆኑ ኢኮኖሚያዊ ጉዳታቸው የበረታ ይሆናል፡፡ 

በአጠቃላይ በተለያዩ ሆኔታዎች የሚፈጠሩ ግጭቶች ያለመግባባትን የሚፈጥሩ ትርክቶች እነዚህንም ተከትሎ የሚወሰዱ አንዳንድ ፖለቲካ ውሳኔዎችና ዕርምጃዎች ሁሉ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ማስከተላቸው አይቀርም፡፡

ጥርጣሬ፣ አለመረጋጋት፣ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ መካረሮች ሳያባሩ አንዱ በአንዱ እየተተኩ መቀጠላቸው አገርን ወደ ኪሣራና መቆርቆዝ መክተታቸው አይቀሬ ነው፡፡ 

ዛሬ ላይ ስለአገር ኢኮኖሚ በሚበጁ ጉዳዮች ማሰብ የነበረባቸው ጭንቅላቶች በየጊዜው በሚፈጠሩ ግጭትና አለመግባባትን በመተንተን ብቻ እየጠፋ ያለው ጊዜ በብርቱ ልንሠራበት የሚገባንን ኢኮኖሚያዊ አጀንዳችን እይነጠቀ ነው፡፡ 

ትልቁ ችግር ደግሞ የፈጠሩ መነታረኪያ አጀንዳዎች ያለማቋረጣቸው ሲሆን ለችግሮቹም መፍትሔ ለመስጠት የሚኬድበት መንገድ የተምታታ ሆኖ መገኘቱ ዜጎች ተረጋግተው እንዳይሠሩ፣ ኢኮኖሚውንም ለማሳደግ መሠራት የነበረባቸውንም ሥራዎች ወደኋላ እያስቀረው መምጣቱ በራሱ አደጋ ነው፡፡ 

በመሆኑም እያጋጠሙ ያሉትን ችግሮች አለማቋረጥ መዝለቅ ኢኮኖሚውን በእጅጉ እያሳመመ ላልተረጋጋ የገበያ ሥርዓት መባባስ ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ ለዚህ ችግር ሁነኛ መፍትሔ ካልተበጀና አንድ ቦታ ላይ ማቆም ካልቻለ ኢኮኖሚያችን ተንገጫግጮ ሊቆም የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነውና እዚያ ከመድረሳችን በፊት በዘላቂ ሰላማችን ላይ እንሥራ፡፡ ያለ ሰላም ኢኮኖሚ የለም፡፡ ዕድገትም አይታሰብም፡፡ ፖለቲካዊ ንትርኮች ዘር ተኮር ጭቅጭቆች ዳቦ አያመጡም፡፡ ስለዚህ አገራችንን እየጎተቱ ያሉ ንትርኮችን ትተን ኢኮኖሚያችን ላይ ካልሠራን ነገ የበለጠ ያስፈራናል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት