Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉ‹እኔን!› ባይ ያጡት አሥራ ሁለተኞች

‹እኔን!› ባይ ያጡት አሥራ ሁለተኞች

ቀን:

በአንዋር አወል ሞ. (መምህር)

በንጉሡ ዘመን የአሥራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ደጃፍ እንዳይረግጡ ይደረግ የነበረ ሴራ፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አስቆጥተው ካሳመፁዋቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል አንዱ እንደነበር ያ ትውልድ የሰነደው ታሪክ ነው፡፡ ምክንያቱም ማትሪኩ ይለካ የነበረው የተማሪን ብቃት ብቻ ሳይሆን የመንግሥትን የቅበላ አቅም ጭምር በመሆኑ ነው። እዚህ ነጥብ ላይ ደርግና ኢሕአዴግን ዘልዬ ወደ ዘመናችን ልሻገር።

እ.ኤ.አ. ማርች 22 ቀን 2022 ትምህርት ሚኒስቴር በይፋዊ ድረ ገጹ ከሰቀለው ዜና ላይ ማረጋገጥ እንደሚቻለው፣ በ2013 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱት መካከል የተፈታኞቹን ግማሽ ያህሉ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ ማስመዝገብ ያልቻሉ ናቸው። በወቅቱ ጉዳዩ ‹ፖለቲሳይዝ› ተደርጎ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ላይ የሰላ ትችት እስከ መሰንዘር የደረሱ ክልሎች እንደነበሩ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።

እርግጥ ነው ተሳናባቹ ‹ባች› ትንሽ ጠለቅ ብለን ብናየው ዕድለ ቢስነትም አያጣውም፡፡ ኮቪዱ፣ ጦርነቱና የሚኒስቴሩ ተለዋዋጭ (ስኬጁል) የተፈራረቀበት ምስኪን ‹ባች› ነበረ። በዚሁ ላይ ለሁለት አሥርት ዓመታት ገደማ የቆየው የአሥረኛው ክፍል የማትሪክ ኬላ የተነሳላቸው የመጀመሪያ ልጆች ናቸው። ሲነሳ ታዲያ ከ9 እስከ 12ኛ ያሉትን ‹ግሬዶች› አንብበው ለዚህኛው ማትሪክ መዘጋጀት እንዳለባቸው፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በደብዳቤ ያሳወቃቸው እጅግ ዘግይቶ መጋቢት 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ነበረ፡፡  ይኼ ሁሉ ሲደመር አጨራረሱም እንዳያምር አደረገው።

እንደ አዲሱ ባህላችን መሠረት ለዚህኛው ውድቀትም አንድ ሰሞን ብቻ ሆይ ሆይ አልንና ፋይሉን ዘጋን፡፡ የት ይደርሳሉ የተባሉ የ‹ባቹ› ልጆችም ነጥብ ከድቶዋቸው በሠፈራችን አልባሌ ቦታ ላይ ማየቱን ተላመድን።  የሃያ አሥራ አራቱ ‹ባች› መጣ።

በብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) የሚመራው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ ዩኒቨርሲቲዎችን በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት መፈተኛ ማዕከላት አደረጋቸው። እኔን ጨምሮ አያሌ ሰው ‹ፐ› ያለለት አሠራር ነበረ። ከሰሞኑ ውጤቱ ሲለቀቅ ግን አገር ምድሩን ክው ያደረገ ሆኖ ተገኘ። ምክንያቱም ከተፈታኞቹ መካከል ከ50 በመቶ በላይ ያመጡት 3.3 በመቶ ብቻ ናቸውና። ወደ 97 መቶኛው ተረፈረፈ።

ይኼው አስደንጋጭ የውድቀት አኃዝ ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ የሰው አስተያየት ለየቅል ነው። ለጊዜው እኔ ባልደረቦቼን አነጋግሬ የቃረምኳቸውን ሐሳቦች እንዲህ በአራት ምድብ ሰብስቤያቸዋለሁ።

  1. (ቁጥሩ ቀላል የማይባል ሰው) ‹ውድቀቱ እንደ አገር ምን ላይ እንዳለን ፍንትው አድርጎ ምሥላችንን የሚያሳየን የእኛነታችን ነፀብራቅ በመሆኑ እንኳንም ሆነ!› ባይ ነው።
  2. ‹የትምህርት ሥርዓቱን ዕርባና ቢስነት ለማሳየት ‹ባቹ›ን መስዋዕት ያደረገ መርዶ ነው› ባይ ነው።
  3. ‹መሬት ላይ ያሉ ጥሬ ሀቆች የራሳቸው አፍ አላቸው፣ ውረዱና እዩዋቸው› የሚል ምድብም አለ።
  4. ከአሳዛኝ ዜና መንጋጋ ውስጥም ቀልድን ፈልቅቄ የማውጣት ተሰጥኦው አለኝ ባይ የቧልተኛ ስብስብም አለ።

አንደኛው ‹ካልደፈረሰ አይጠራም› የሚለውን ፈሊጥ እንደ መርህ የያዘው ጎራ ነው። የትምህርት ሚኒስቴር ከሰጠው መግለጫ እንደተገነዘብነውም፣ አኃዙን አፍረጥርጦ በማቅረቡ መምታት የፈለገው ግብ ይኼኛው ነው። ማደፍረስ ቀጥሎ ማጥራት። ምክንያቱም ሚኒስትሩ ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) እንዲያ ደቀቅ ያለው መግለጫ ያስፈለገበትን ምክንያት ሲገልጹ፣ ተቀዳሚ ዓላማቸው አሁናዊ የትምህርት ቤቶችን መልክ ማወቅና ማሳወቅ መሆኑን ጠቅሰዋል። በሽታችንን ከተለየ በኋላ ለፈውሱ ፍቱን መድኃኒቱን ቀምሞ ለማቅረብ ዳገት አይሆንብንም ሲሉም ተደምጠዋል። በቀጣይ ለሚደረጉ አካዳሜያዊ ጥናቶችም ይኼኛውን አኃዛዊ ትንታኔ እንደ መነሻ ያገለግላል ሲሉ ግማሽ ሰዓት በፈጀው ጋዜጣዊ መግለጫቸው ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ሚኒስትሩ ይኼው አደፍርሶ የማጥራት ስትራቴጂ ኩረጃን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማስቀረት፣ አሁን ከገባንበት የሞራል ክስረትም ያላቅቀናል ብለው እንደ ተቋም እንደሚያምኑ ሐሳባቸውን አጋርተዋል። በመጨረሻም በዚህ ፈጦ በመጣው የዓለም ውድድር ሥርዓት ውስጥ ተወዳድሮ የሚያልፍ ትውልድ የመፍጠር ዕቅድን አንግበው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ጠቅሰው ሐሳባቸውን አሳርገዋል።

ሁለተኛው እዚህ ጎራ ያሉት አንደኛዎቹ ባነሳሷቸው ሐሳቦች ከሞላ ጎደል ይስማማሉ። ሆኖም ካሪኩለም ሳይነካ፣ ትምህርት አሰጣጡ የወትሮው ሆኖ ሳለ አፈታተን በማስተካከልና ውጤትን በድፍረት አፍረጥርጦ በመናገር ብቻ ለውጥ አይመጣም ባዮች ናቸው። እስቲ መጀመሪያ አገሪቱ ከአንጀቱ ለተማረው፣ በማዕረግ ለተመረቀውና ሜዳሊያ ላጠለቀው ወጣት ተገቢውን ክብር ትስጠው። ከዚያም የእሱ በጎ ተፅዕኖ ሚሊዮኖች ላይ አሻራውን ሲተው እናየዋለን።

ፊልመኞች በፊልም ውስጥ ‹አትናገር አሳይ!› የሚሉት ሕግ አላቸው። እዚህ አገርም የትምህርት ጥቅምን በተመለከተ መከተል ያለብን ይኼው የፊልመኞቹ ሕግ ነው። በዚህ ሰዓት ዕንቅልፍ አጥቶ ለወጣቶቹ የሚነገር ዲስኩር ማዘጋጀት ብዙ ርቀት አይወስድም። ይልቁንም በትምህርት የተጠቀመ የሚዳሰስ ህያው ምስክር ያስፈልጋቸዋል። ያኔ ወላጅም ልጁን ሲመክር ልክ እንደ ድሮ ኮራ ብሎ ‹እስኪ የእገሌን ልጅ ተመልከቱ! በመማሩ አይደለም ወይ ለዚያ ክብር የበቃው?›› ለማለት ይደፍራል። ልጁም ‹መማር እውነትም ታሪኬን ይቀይርልኛል› ይላል። አለበለዚያ ትውልዱ የመማርን ትሩፋቶች ሳናሳየው ምዘናና ፈተናውን ብቻ ስናጠብቅ፣ ውለን ስናጠብቅ ብናድር ውኃ ወቀጣ ይሆንብናል። ስለሆነም የመጀመርያው መፍትሔ መማርና ማስተማሩን የሚያጓጓ ድባብ ስለማላበስ መሆን አለበት። ከዚያ ውጪ ግን እንዲያው በዚህ አያያዝ ከተቀጠለ አለማለፍን እንደተራ ነገር ከመታየቱ የተነሳ ማለፍን እንደ ነውር የሚቆጥር ትውልድ ስላለመምጣቱ ምንም ዋስትና የለንም።

ሦስተኛው ይህ ምድብ መሬት ላይ ላሉት ጥሬ ሀቆች የቅድሚያ ቅድሚያ ይሰጣል። ለምሳሌ ለመምህሩ በቂ ትኩረት አለመሰጠቱ ዘርፉ እንዲቀጭጭ ማድረጉ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ የአቅም ጉዳይ እንጂ ማንም አካልም አሌ አላለም፡፡ እንዲያውም በያዝነው ወር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዩኒቨርሲቲ መምህራን ጋራ ባደረጉት ስብሰባ ላይ ቃል በቃል፣ ‹‹ትንሽዬ ዘር አለች፣ ዘሯን እንብላት? ወይስ እንዝራት?›› በማለት የአገሪቱ ዝምታ የሚመነጨው ከቸልታ ሳይሆን ከዕጦት መሆኑን ጠቆም አድርገው አልፈዋል፡፡

ሌላኛው ጥሬ ሀቅ፣ ተማሪዎች ትክክለኛው ዝግጅታቸው እንዳያዩ እየጋረዱዋቸው ካሉት ጉዳዮች አንደኛው የተከታታይ ምዘና (Continuous Assessment) አሰጣጡ ላይ ጤነኝነት መጓደሉ ነው። አመዛኙ መምህር ገና ለገና በሴሚስተሩ መጨረሻ ምን ያህል ልጆችን እንዳሳለፍክ ትንተና ሥራ እባላለሁ ብሎ የልጆችን ማርክ የሌለ ይቆልላል። በመጨረሻም ይኼው መረጃ ልጆቹን፣ ወላጅን ብሎም ትምህርት ቤቱን አጭበርብሮ ቁጭ ይላል። ለዚህም ‹እኮ ነው የ12ኛ ክፍል ትራንስክሪፕታቸው ላይ አንደኛ ከተባለባቸው ተማሪዎች ውስጥ 40 በመቶ የሚሆኑት ‹‹ኢንትራንስ›› ፈተናውን ማለፍ አልቻሉም፡፡

ሌላው መሬት ላይ አፍጥጦ የምናገኘው ሀቅ የተማሪዎች የመማር ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ በአስደንጋጭ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መሆኑን ነው። ከራሴ ተሞኩሮ ብነሳ  በ2011 ዓ.ም. 9ኛ ክፍል ያስተማርኳቸው በርካታ ጎበዝ የሆኑ ልጆች ነበሩ። ቀጣዩ ዓመት ላይም እንዲሁ የደረጃ ተማሪነታቸውን እንዳስጠበቁ ነበረ በኮቪድ-19 ሳቢያ መጋቢት ላይ የተለያየነው። በድኅረ ኮቪድ ጊዜ ግን ልጆቹ ከእነ ጭራሹ እነሱ አልነበሩም ማለቱ ይቀላል። እነሆ በመጨረሻ ላይም ብዙዎቹ አላለፉም፡፡

አራተኛው የቧልተኛው ስብስብ ነው። ይህ ስብስብ መለያ ሐሳቡ (ያው ሐሳብ ከተባለ) በዚህ በሶሻል ሚድያ ላይ ወጥቶ ማፌዝ ነው። እዚህ ላይ ተፈታኝ ያልሆነው (ምን አገባኝ ባይ) ብቻ ቢያላግጥ እንችለው ነበር። እኛ አሁን መቋቋም ያቃተን ያልተሳካላቸው ተፈታኝ ተማሪዎቹም ጭምር በዝቅተኛው ውጤታቸው ለማሳቅ ሲሞክሩ ማየትን ነው። ለነገሩ ማሾፍ ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል። ብዙዎቹ ዓመቱን በሙሉ ‹‹ክሬዚ ዴይ››፣ ‹‹ዋተር ዴይ››፣ ምናምን ዴይ እያሉ ትምህርት ቤትን ሲያስቸግሩ የነበሩ ናቸው። ሌላው ቀርቶ ተፈትነው ከየካምፓሱ ሲመለሱም የተጫኑበትን ባስ እንደ ከበሮ እየደለቁና እየዘፈኑ ነበር የገቡት። እኔ እንዲያውም ቸበርቻቻውን አይቼ በቃ ተኮራርጀዋል ማለት ነው ብዬ ደምድሜ ነበር። የኋላ ኋላ እንዲህ ጊዜው ደርሶ ስናይ እንዲያ ከተጠቀጠቀው ባስ ውስጥ ያለፉት በጣም ጥቂቶቹ ናቸው። ደላቂዎቹ ግን ያኔም እንደማያልፉ ያውቁት ነበር ማለት ነው። ካልሠሩ ማለፍ ከየት ይመጣል? አሁን ላይ ሆኜ ድለቃውን ስፈታው፣ ‹እንኳንም ተገላገልን እንጂ ከእንግዲህ ወዲያ ውጤቱ ምንም ቢሆን ግድ አይሰጠንም› ዓይነት መሆኑ ነው።

ማጠቃለያ

አንዱ መምህር ዓምና በወሬያችን መካከል የዘንድሮ ተማሪ እንዴት አየኸው? ሲባል ‹ይመሥገን ነው፣ መቼስ ከቀጣዩ ይሻላል› ብሎ አስቆን ነበረ። ዳሩ ውስጠ ወይራው አስለቃሽ እንጂ አስቂኝ አልነበረም። ብቻ በመምህሩ አነጋገርም ሆነ መሬት ላይ ባለው ሀቅ ተመርኩዘን ስናወራ ካለፈው ይልቅ የሚመጣው ስለሚያስፈራ ልባዊ የሆነ ሥራ ይጠይቃል። እንዲያው ሚኒስትሩ፣ ‹አጠቃላይ አገራዊ ስትራቴጂ ነድፈን በዚህ ዓመት እንጀምራለን› የምትል ሐሳብ ጣል አድርገው ነበረና እኔ ይህችን ትንሽ ሐሳብ ላክልባት።

ተማሪዎቹን ለማዘጋጀት ይረዳ ዘንድ የሚድኑትን ለማዳንም እንዲጠቅም፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከማትሪኩ አስቀድሞ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ያሉትን ክፍሎች በየግሬድ ደረጃው አንድ በአንድ በኦሊምፒያድ ፈተናዎች  (Olympiad Exams) መልክ ቢሰጥ አብዝቶ ይጠቅማል እላለሁ። ኦሊምፒያዱ በመጠኑ ተንተን ሳደርገው እንዲህ ይወጣዋል። ፈተናው በአራቱም የዓመቱ ሩቦች የሚሰጥ ይሆናል። በአንደኛው ሩብ ላይ ልጆቹ ከመደበኛው ትምህርት ጎን ለጎን የ9ኛ ክፍልን  ትምህርቶች ብቻ እንዲዘጋጁ ተደርጎ ኦሊምፒያድ ፈተናውን ይወስዳሉ። ሁለተኛው ሩብ ላይ አሥረኛ እያለ ይቀጥላል። ይህም እንደ መለማመጃ ፈተና (Mock Exam) ሆኖ ስለሚያገለግል ዋናውን የማትሪክ ውጤታቸው ላይ የሚታይ ለውጥ እንደሚያመጣ በፅኑ አምናለሁ። ትምህርት ሚኒስቴር ሐሳቡን ይቀበለው ብቻ እንጂ ሀብትና የሰው ኃይል አያሳስብም። ፈተናውን ከማዕከል በተመሳሳይ ሰዓት የሚለቀቅ የኦንላይን ፈተና ማድረግ ይቻላልና፡፡ እንኳን አንድ ግዙፍ የፌዴራል ተቋም ቀርቶ እኔ በግሌ እንኳን ቴሌግራም ላይ እሑድ እሑድ ኦንላይን እየፈተንኩ ነው።  ሰላም!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው  [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...