Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉበሰላም በሃይማኖትና በትምህርት ላይ የተነሱትን አንገብጋቢ ችግሮች ሰከን ብለን ዘላቂ መፍትሔ እንስጣቸው

በሰላም በሃይማኖትና በትምህርት ላይ የተነሱትን አንገብጋቢ ችግሮች ሰከን ብለን ዘላቂ መፍትሔ እንስጣቸው

ቀን:

በይኄይስ ኅብሩ

አገራችን ኢትዮጵያን በምንገልጽበት ጊዜ በአክሱም ዘመነ መንግሥት ታላቅ ከሚባሉ አራት የዓለም መንግሥታት አንዷ ነበረች፡፡  የክርስቲያንንም ሆነ የእስልምና ሃይማኖቶችን በመጀመርያ ከተቀበሉት አገሮች አንዷ ይችው የእኛ አገር ናት፡፡ የዓለምን ዕድገት የለወጠው የኢንዱስትሪ አብዮት ሲካሄድ፣ አገራችን ነፃ መንግሥት ነበራት፡፡ ኮለኒያሊስቶች አፍሪካን ሲቀራመቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ተከላክሎ፣ ነፃነቷን ሳያስደፍር ቆይቶ፣ ለዓለም ባርነትን እንቢ በማለት ኢትዮጵያ ተምሳሌት ሆናለች፣ ወዘተ እያልን እንተርካለን፡፡ በሌላው በኩል ደግሞ በሚያሳዝን ሁኔታ ኢትዮጵያ በዘመናዊ መንግሥት ሊጠቀሱ የሚችሉ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ማኅበራዊ ዕድገቷ፣ በአሁኑ ጊዜ ከመጨረሻዎቹ አገሮች ተርታ እንድትሠለፍ አድርጓታል፡፡ አንዳንድ ጸሕፍት ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ እየሄደችበት ያለው ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሥርዓት አውሮፓውያን ከመቶ ዓመት በፊት የነበሩበት ደረጃ ነው ብለው የሚያነሱ አሉ፡፡ ለዚህም የሚሰጡት ምክንያት በዚያን ጊዜ በአውሮፓ ብሔርተኞች በየአገሩ ችግር የፈጠሩበት፣ አማፂያን መንግሥትን በአመፅ ያስወገዱበት፣ ፖለቲከኞች ሃይማኖትን ሰበብ በማድረግ ሕዝቡን የከፋፈሉበት ሁኔታን በማነፃፀር ኢትዮጵያ ላይ የሚታየው ይኸው ነው በማለት ያስረዳሉ፡፡ ምክንያቶችን እየደረደርኩ ይኼ እንዳልሆነ ልከራከር አልፈልግም፡፡ ያለንበትን ሁኔታ ያየ ሊያምነኝ ይከብደዋል፡፡

በሌላ በኩል ግን በዓለም ላይ የነበሩት ለውጦች ሲካሄዱ እኛም ሉዓላዊ መንግሥት ሆነን እየተንቀሳቀስን እንደነበረ እሙን ነው፡፡ ለውጡን ተቀብለን መለወጥ ነበረብን፣ ይኼ አልሆነም፡፡ ቴዎድሮስ ዘመናዊ መድፍ በዓለም ላይ እንደተመረተ አውቀው እሱን ለመፈብረክ ጋፋ ላይ የቴክኖሎጂ ማዕከል ለማቋቋም ሞክረው እንደሠሩ እንረዳለን፡፡ አፄ ምኒልክ የባቡር መንገድ ማዘርጋታቸውና ቴሌፎን ማስጀመራቸው በተከታታይ የመጡት መንግሥታትም ዓለም የፈጠራቸውን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በሙሉ በሚባል ሁኔታ ወደ አገር ውስጥ በማስገባት እኛ እንድንቋደስ አድርገዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህን ለውጦች ተቀብለን ዘላቂ በማድረግ አገራችንን አላሠለጠንም፡፡ እነዚህ ለውጦች ለዓለም የሥልጣኔ በር ሲከፍቱ እኛ አዚያው ቆመን በመቅረት ዓለም ስትሠለጥን እኛ ምስክር ሆንን፡፡ ቴክኖሎጂ ተቀባይ እንጂ የፈጠራው አካል ባለመሆን ዘላቂነት ያለው ሥራ ባለመሥራታችን ያገኘነውን ዕድል ተጠቅመን ዕድገታችንን ዘላቂ አላደረግነውም፡፡ እኔ የፋብሪካ ኢንዱስትሪ መምህር ስለሆንኩኝ በአገራችን ላይ የመጡ ፋብሪካዎችን በደንብ አውቃቸዋለሁ፡፡ ሁሉም በሚባሉ ሁኔታ ከውጭ መጥተው የተተከሉ ፋብሪካዎች ተጠቅመንባቸው ምንም ሳናሻሽላቸው በዚያው አርጅተው የምንተዋቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ አንድ ፋብሪካ እንደተተከለ የምርት ውጤቱን፣ ሒደቱንና ቴክኖሎጂውን ለማሻሻል ማዕከል በማቋቋም ጥናት ይደረጋል፡፡ የዚህም ውጤት በየጊዜው ይተገበራል፡፡

ቴሌፎን ዓለም ሲጀምር በማዞሪያ ነበር፡፡ እኛም በዚያው ጀመርን፡፡ ዓለም በቀጥታ መነጋገር ፈጥሮ ሲጀምር እኛም ተቀበልን እንጂ፣ እንደ ጀማሪነታችን ለፈጠራው ያደረግነው አስተዋጽኦ የለም፡፡ የአውራ መንገድ ስንሠራ ከመቶ ዓመት በላይ አሳልፈናል፡፡ መንገድ እንዴት እንደሚሠራም ያሳዩን የውጭ አገር ሰዎች ናቸው፡፡ እኛ ከእነሱ ተቀብለን ያደረግነው የቴክኖሎጂም ሆነ የግብዓት ለውጥ በዚህ ሁሉ ዓመታት የለም፡፡ የስኳር ፋብሪካ ከውጭ አምጥተን የተከልነው በ1950ዎቹ ነው፡፡ ፋብሪካው መሥራት ከጀመረ ወዲህ አንድም የቴክኖሎጂም ሆነ የምርት ለውጥ አላደረግንበትም፡፡ በአሁኑ ጊዜ አንዳንዱን ክፍል አርጅቷል ብለን ዘግተናል፡፡ በጥቅሉ አገራችን ቴክኖሎጂ ተቀባይ በመሆን ዕድል ብታገኝም አድናቂ ባለመሆኗ ለዘላቂና ለአስተማማኝ ዕድገቷ አልተጠቀመችበትም፡፡ አገራችን ብዙ ዕድሎች እንዳመለጡዋት ከማስረጃ ጋር ማቅረብ ብችልም እንደ ማጠንጠኛ ላቀርብ የምሞክረው፣ አሁንም ወደነውም ሆነ በግድ የመጣብንን ችግሮች መፍታት ያለብን በጥሞናና በማሰብ ችግሩን እንደ አጋጣሚ ጥሩ ዕድል በመወሰድ እንዳያዳግም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በዘላቂነት ነው፡፡

ይህንን ግንዛቤ በመውሰድ በመጀመርያ ላቀርብ የምሞክረው የሰሜኑን ጉድ ነው፡፡ የዚህ ችግር መንስዔ አብዛኛው የአውሮፓ አገሮች ከመቶ ዓመት የነበሩበትና መንስዔ ሰጥተው አሁን ታሪክ ያደረጉት የብሔር ንቅናቄ ነው፡፡ ብዝኃ ብሔር ባለበት አገር ውስጥ በ1983 ዓ.ም. ጥቂት ብሔሮች ሌሎቹን ጨፍልቀው በሕገ መንግሥት አገሪቱን ከሁለት አሥርተ ዓመታት በላይ ገዙ፡፡ ከጊዜ በኋላ እነዚህ በብሔር ተሰባስበው አገሪቱን ሲመሩ የነበሩ የኢሕአዴግ አባላት በየቦታው የተነሳውን ንቅናቄ ለመቋቋም በአዲስ መልክ መሪዎቻቸውን መረጡ፡፡ በዚህ ምርጫ ያልተደሰቱት ተገንጣይ ኢሕአዴጎች ‹‹እኔ አገሪቷን ካልመራሁ ኢትዮጵያ ሲኦል ትውረድ›› በማለት ጥያቄውን እዚያው በኢሕአዴግ፣ ውስጥ ከመጨረስ፣ ወደ ‹‹የእኔ ሕዝብ ነው›› ወደሚሉት ክልል በማውረድ ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. የኢትዮጵያን የመከላከያ ሠራዊት በመውረር ጦርነት ከፈቱ፡፡ ጦርነቱም በክልሉ ሕዝብና በተቀሩት ኢትዮጵያውያን መካከል እንዲሆን፣ የክልሉን ወጣትና አዛውንት በመመልመል ለጦርነት ማገዱት፡፡ ይህም ጦርነት በርካታ ዜጎች በተለይ ወጣቶችና አዛውንቶች ሞትና ቁስለኛ አንዲሆኑ አደረገ፡፡ ሴቶች ተደፈሩ፣ አዛውንቶች በዕድሜ ልካቸው ያፈሩትን ሀብት ወደመባቸው፡፡ ተፈናቃይና ተሳዳጅ ሆኑ፡፡ በጦርነት የተጎዱት ነዋሪዎች ቁጥር ትንሽ አይባልም፡፡ በሚሊዮኖች ይቆጠራል፡፡ በየክልሎቹ ያሉ የልማት አውታሮች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ወደሙ፡፡ በአገሪቱ ላይ የደረሰው ውድመት በደንብ ተሠልቶ ባይታወቅም፣ አንዳንድ ለነገሩ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ጦርነቱ በቀጥታ ያጠቃቸው ክልሎች ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ነበረው የልማት አውታር ለማድረስ እሰከ ሃያ ዓመታት ሊፈልግ እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ በጦርነቱም ወቅት የአሜሪካን ፊታውራሪነት በመጠቀም ተገንጣይ ኢሕአዴጎች እስከ ደብረ ሲና ጦር ይዘው በመምጣት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ‹‹አልቆለታል ዜጎች አዲስ አበባን ለቃችሁ ውጡ›› ሲሉ አወጁ፡፡ ፊታውራሪያቸውም የአሜሪካ መንግሥት ልክ እንደ ሶሪያና ሊቢያ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ‹‹የሽግግር መንግሥት በዋሽንግተን ተቋቁሟል፡፡ የውጭ አገር ዜጎች ከአገር ውጡ፣ ወዘተ›› በማለት ለተገንጣይ ኢሕአዴጎች  የፖለቲካና የቁስ ዕገዛ አደረጉ፡፡ የአንድነት ኃይሎች ግን ማለትም የኢትዮጵያ መንግሥት ከመከላከያ ሠራዊቱና ከሕዝቡ ጋራ በመሆን የደም ዋጋ በመክፈል የአገሪቱን ሉዓላዊነት አስጠበቁ፡፡

እንግዲህ ይህ በተገንጣይ ኢሕአዴጎች የመጣን የአገር ቀውስ በሰላም ማስቆሙ እሰየው የሚያሰኝ ነው፡፡ ለሰላሙም ሁላችንም በአንድ ላይ መቆም ግዴታ አለብን፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም ቢሆን በተገንጣይ ኢሕአዴጎች ላይ የተገኘውን ሰላም ዘላቂ እንዲሆን አድርገን ካልቋጨነው፣ ተመልሰን የከፋ ችግር ውስጥ ልንገባ አንችላለን፡፡ ማናቸውም ወደ ጦርነት የገቡት ተፋላሚዎች ዘላቂ ሰላም ሊያመጡ የሚችሉት በእኔ አመለካከት ሰላም በጦርነት (በኃይል)፣ ሰላም በፖለቲካና ሰላም በፍትሕ ሲታገዝ ነው፡፡ አስተማማኝ ሰላም ለማምጣት እነዚህ ሁሉም ሳይለያዩ መተግበር አለባቸው፡፡ ሰላም በጦርነት (በኃይል) ሊመጣ የሚችለው ተፋላሚዎች ሰላምን ረግጠው ወደ ጦርነት ከገቡ፣ ከገቡበት ጦርነት የሚላቀቁት ከሁለቱ ተፋላሚዎች አንደኛው ወገን ሌላውን መቋቋም አቅቶት ሲሸነፍ ነው፡፡ በእኛም ሁኔታ የአንድነት ኃይሉ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት በሰላም የፖለቲካ ልዩነቶችን ለመፍታት ሙከራ እንዳደረገ ተከታትለናል፡፡ ተገንጣይ ኢሕአዴጎች ግን ይህንን አልተቀበሉም፡፡ በጦርነቱ ወቅት አሜሪካኖች በቴክኖሎጂ እያገዙ ተገንጣይ ኢሕአዴጎች ደብረ ሲና በደረሱበት ጊዜ ሰላምን በመርገጥ፣ ‹‹ከማን ጋር ነው የምንደራደረው (ሰላም የምናመጣው)? አሁን የአንድነት መሪዎች ዕጣ ፈንታ እጅ መስጠት ብቻ ነው›› በማለት ተገንጣይ ኢሕአዴጎች በሰላም ይሳለቁ ነበር፡፡ በመስከረም ወር አሜሪካኖቹም እንደ መሰከሩት ተገንጣይ ኢሕአዴጎች ሦስተኛውን ዙር ጦርነት እንደሚያሸንፉ ሙሉ እምነት ስላላቸው ለሰላም ፍላጎት እንደሌላቸው ነበር፡፡ ለዚህም ማረጋገጫ ተገንጣይ ኢሕአዴጎች ‹‹አፍንጫቸውን ይዘን መንግሥት እንይዛለን›› ብለው የዛቱት ምስክር ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የአንድነት ጦር እንደሚያሸንፋቸውና በሰዓታት ውስጥ እጃቸው በካቴና እንደሚገባ የነፍስ አባታቸው አሜሪካ ስለነገራቸውና እነሱም ስላወቁ፣ ‹‹ድሮም ሰላም ፈላጊ ነበርን›› ብለው ዓይናቸውን በጨው አጥበው እጃቸውን ሰጡ፡፡ ስለዚህ ለዚህ ጦርነት የመጀመርያ ረድፍ ሰላም ለማምጣት ተገንጣይ ኢሕአዴጎች መሸነፍ ነበረባቸው፡፡ እነዚህ ቡድኖች መሸነፋቸው ለአንድነት ኃይሎች (ኢትዮጵያውያኖች) በጦርነት እንዳሸነፉና ዘላቂ ሰላም ለማምጠት ዕድል ከመክፈቱ በስተቀር ለብቻው ለሰላም አስተማማኛ አይደለም፡፡

በአሁኑ ጊዜ የጥይት ጩኸት መቆሙ ያስደሰተንን ያህል ሰላሙን ዘላቂ ለማድረግ ሁለተኛውን ሥራ ማስከተል አለብን፡፡ በፖለቲካ ሰላሙን ማስቀጠል፡፡ ከላይ ለመግለጽ እንደ ሞከርኩት የጦርነቱ መንስዔ በአንድ በኩል የቆሙት ተገንጣይ ኢሕአዴጎች ‹‹እኔ የበላይ ሆኜ ካልገዛሁ›› የሚለው ሲሆን፣ ተፋላሚዎቹ ይህንን ደብቀው ሕዝቡን በማሳሳት በጦርነት ልጁን እንዲማግድ ያስደረጉት ‹‹አንተን ጨቁኖ የበታች ሆነህ እንድትተዳር ስለወሰኑ ነው›› ብለው ስለሆነ፣ ይኼ እንዳልሆነ በፖለቲካ ውሳኔ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ በፕሪቶሪያው ስምምነትም መንግሥት የጊዜያዊ አስተዳደር አቋቁሞ ሕዝቡ ከራሱ ውስጥ የሚፈልጋቸውን መርጦ እንዲተዳደር ተወስኗል፡፡ በዚህም ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ መንግሥት የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ፣ ሁሉንም የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማካተት ማቋቋሞ አለበት፡፡ የተቋቋመውም መንግሥት አካባቢውን ከማረጋጋት በተጨማሪ በሐሰት ትርክት ብሔርን ከብሔር ለማጋጨት የተሞከረውን ሁሉንም በሚያካትት ሁኔታ ሕዝባዊ ውይይት በማድረግ፣ በማስታረቅ፣ ብሎም በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት የሚመሠረተው የብሔሮችና የሃይማኖት እኩልነትና መብት ተጠብቆ በዜጋ ላይ እንደሆነ መግባባት ላይ እንዲደረስ ሰፊ ሥራ ይጠብቅበታል፡፡ ይህ ሊሳካ የሚችለው ግን አሁን መቀሌን ተቆጣጥሮ ያለው ተገንጣይ ኢሕአዴግ ድርሻ በጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ውስን መሆን ሲችል ነው፡፡ የእሱ ድርሻ በጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ከበዛ የዴሞክራሲን መርህ ለማምጠት፣ የብሔር እኩልነት ለማስፈን፣ ወደፊት የሚደረገው ፍትሐዊ ምርጫ ወዘተ ዘበት ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ሌሎች የአካባቢው ተወላጆች በፖለቲካ ተቧድነውም ሆነ በተናጠል በጊዜያዊ መንግሥቱ ውስጥ አኩል ዕድል አንዲኖራቸው በጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ መሳተፍ አለባቸው፡፡ አሁን የተገንጣይ ኢሕአዴግ ቡድን እያደረገ ያለው ዝግጅት (50 በመቶ ድርሻ ይኖረኛል) በኢትዮጵያ ሕዝብ ደም ላይ ጨዋታ ነው፡፡ የሰው ደም ነው የፈሰሰው፡፡ ብዙ ቤት በጦርነቱ ምክንያት ለአንዴም ለመጨረሻም ተዘግቷል፡፡ ሕዝቡ ይበጀኛል ብሎ እስኪመርጥ ድረስ ማንኛውም ቡድን/ግለሰብ ተፅዕኖ እንዳይፈጥር ሕዝቡን የመጠበቅ ድርሻ፣ የአንድነት ኃይሉን ይዞ የሚንቀሳቀሰው የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት፡፡

ሌላው የዘላቂ ሰላም ዕድል እንዳያመልጠን መሥራት ያለብን ሰላሙ እንዲደፈርስ ምክንያቱ የሆነውን አውቀን ስናደርገውና ለዚህ ሁሉ ዕልቂትና ውድመት ተጠያቂውን ለይተን ጦርነቱ በፍትሕ ስንቋጨው ነው፡፡ ስለዚህ አንድ በሥርዓትና በሕግ የሚተዳደር አገር ለዚህ ሁሉ የሰውና የቁስ ውድመት መንስዔው ምንድነው? ማነው ተጠያቂው? የሚለውን አጣርቶ ተጠያቂዎቹን ለፍርድ ማቅረብ ግዴታ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ጦርነትና ዕልቂት መንስዔው ምንድነው? የሚለውን ለመፈለግ የኢትዮጵያ ሕዝቡ ብዙ አይቸግረውም፣ ያውቀዋል፡፡ የመከራ ኑሮ ኖሮበታል፡፡ ስንገዛ የኖርንበት አሁንም እየኖርንበት ያለው አንድ ላይ የኖረን ሕዝብ ‹‹የእኔ፣ የእሱ››፣ ‹‹ይኼ የአገር ባለቤት፣ ሌላው መጤ›› ወዘተ በማለት የሚራመደው ፖለቲካ ነው፡፡ እየሄድንበት ያለው ፖለቲካ ብዙ ማንነቶች ባሉበት አገር ውስጥ የጥቂቶችን የብሔር ማንነት ብቻ ማዕከል በማድረግ፣ የፖለቲካ ሥርዓት መፍጠር እጅግ አደገኛ ሆኖ ነው የምናገኘው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ የምትከተለውን ዓይነት የብሔር ፖለቲካ ሥርዓት የሚከተል አገር የለም፡፡ ከዚህም በላይ አሁን ባለንበት ዘመን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገሮች ውስጥ፣ የብሔር ፖለቲካን በሕገ መንግሥት  ደንግጋ  የምትመራ አገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡  በአፍሪካ አገሮችም ውስጥ ከ1,000 በላይ ብሔሮች አሉ፡፡ ሁሉም ብሔሮች ቋንቋቸውን ባህልና ወጋቸውን ተከባብረው ይጠቀማሉ እንጂ፣ በፖለቲካ ሥልጣን ይዘው አይተዳደሩም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ግን በብሔር ካልተደራጀ የፖለቲካ ሥልጣን መያዝ አይችልም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ኮምሽሾ ብሔርተኛ (የአንድነት ጠል ኃይል) ደልቧል፡፡ ካልተሰማማኝ የእኔን ክልል ገንጥዬ አገር አደርጋለሁ፡፡ የሚል ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና አስቀምጧል፡፡ የአንድነት ጠል ልሂቃኑ ‹‹ኢትዮጵያ የምትፈለገው ጎጆ ለመውጫ ነው፤›› በማለት ዘወትር የማስፈራሪያ ንግግር ሲያደርጉ ኖረዋል፡፡ ይህንን ያንገፈገፈው ኢትዮጵያዊ የለውጥ (የአንድነት) ኃይል ከአራት ዓመት በፊት ‹‹የእኔነትን›› ፖለቲካ በማጥፋት፣ ኢትዮጵያ የሁሉም አገር እንድትሆን አደርጋለሁ፡፡ ዜጎቿ ያለ አድልኦ የመንቀሳቀስ በሚፈልጉበት አካባቢ የመሥራት፣ የመኖር፣ የመምረጥና የመመረጥ መብታቸው፣ ወዘተ ሙሉ በሙሉ አስጠብቃለሁ በማለት በፓርላማ ሲነግረው፣ ሕዝቡ ሆ! ብሎ ለውጡን በመደገፍ ተከትሎ የመጣውን መከራ ሁሉ ተቀብሏል፡፡ ይህንን ቃል ለመጠበቅ መንግሥት የዚህ ሁሉ ብጥብጥ ሕገ መንግሥቱ አንዱ ምክንያት እንደሆነ አምኖ ኢትዮጵያ ለሁሉም ዜጋ የሚስማማ፣ አዲስ ወይም የተሻሻለ ሕገ መንግሥት ለማውጣት በመንግሥት ፖሊሲ አስቀምጦ አጋጣሚውን የሰላም ዕድል መጠቀም አለበት እንጂ፣ ፕሪቶሪያ እንደተደረገው ዓይነት ‹‹ጨዋታው ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ›› ብለው እንደሚጫወቱ ሕፃናት ከአሁን በኋላ ሰላም ስለተፈጠረ ጦርነቱን የሚያወራ ውሾ ይሁን ብሎ ዶሴ መዝጋት በኋላ ብዙ ያስከፍላል፡፡ የተጎዱት ወገኖች በአጠቃላይ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕዝብ በተጠያቂዎች ላይ ፍትሕ ይፈልጋሉ፡፡ ፍትሕ ከቅጣቱ በላይ አስተማሪነቱ ነው ጎልቶ የሚታየው፡፡ በተለይ በአገራችን ውስጥ በየቦታው ጦር እየሰበቁ ለሚታዩት የአንድነት ጠል ኃይሎች ትምህርት ይሆናቸዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ሌላ ዕድል ሆኖ የመጣው ሰሞኑን በሃይማኖት ጉዳይ የተነሳው ጭቅጭቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አደገኛ ሆኖ እንደ ሰዓት ቦምብ ሊፈነዳ የሚችለው በብሔር ተለኩሶ በሃይማኖት የሚመጣው ጦርነት ነው፡፡ ዓለማት በሙሉ በአገራቸው በብሔር ተንተርሶ የሃይማኖት ጦርነት እንዳይነሳ ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት በብሔር ስም የሚነግዱት ፖለቲከኞች፣ ሃይማኖትን የእነሱን ዓላማ እንዲያስፈጽምላቸው መሣሪያ አድርገው እንዳይጠቀሙበት በመፍራት ነው፡፡ የተገንጣይ ኢሕአዴግ ቡድን በጦርነቱ ወቅት የትግራይን የሃይማኖት አባቶች ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር ግንኙነታችንን አቋርጠናል ብለው ነበር፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል ከቅዱስ ሲኖዶስ ቀኖና (ሥርዓት)  ውጪ የራሳቸውን ጳጳሳት በመሾም የፅንፈኝነት ዕርምጃ እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ ለዚህ የተገደዱበት ምከንያት ከሚጠቅሱዋቸው ውስጥ በጥቅሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን የሚመሩት ከአንድ ወገን በመሆናቸው እኛ በአመራር ላይ አናሳ ሆነናል፣ የአሮሞ ሕዝብ በቋንቋው ግልጋሎት አያገኝም፣ ወዘተ የሚሉት ይገኝበታል፡፡ እኔ ስለሃይማኖት ስላላጠናሁ ጠለቅ ብዬ ልተነትን አልችልም፡፡ ሙያዬም አይደለም፡፡ ካለኝ ግንዛቤ ግን ሃይማኖት ለሁለት ከዚያም በላይ ሊከፈል የሚችለው በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ዶግማ/የእምነት አስተሳሰብ አስተምህሮ ላይ ልዩነት ሲመጣ ነው፡፡ በአገራችን በተለመዱት ካራ፣ ቅባት፣ ወይም ካቶሊክ፣ ፕሮቴስታንት፣ ወዘተ እንደሚባሉት ክፍፍል፡፡ በኦሮሚያ ያሉት አባቶች እስካሁን የቤተ ክርስቲያኗን ዶግማ ጥያቄ ውስጥ አላስገቡም፡፡ የኦሮሚያ አባቶች እያነሱ ያሉት የሚመሩት የአንድ አካባቢ አባቶች ናቸው፣ የኦሮሞ ሕዝብም በቋንቋው አልተገለገለም ወዘተ የሚሉ ናቸው፡፡ ጥያቄዎቹ በተለያዩ ሃይማኖቶች እስከ ዛሬ የሚነሱ ናቸው፡፡ ችግሮቹም ከሃይማኖቱ አመጣጥ ጋር ይያዛል፡፡

ሃይማኖቱን የሚመሩት የአንድ አካባቢ አባቶች በብዛት ይገኙበታል የሚለውን እንደ ምሳሌ የካቶሊክ ሃይማኖትን ብንወስድ፣ የክርስትና ሃይማኖት (ካቶሊክ) እ.ኤ.አ. በ380 በሮም ንጉሥ ሲታወጅ መሪዎቹ ሁሉ ጣሊያናውያን ነበሩ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስም 266 የካቶሊክ ጳጳሶች የተሾሙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 88 የሮም፣ 196 ደግሞ የጣሊያን ተወላጆች ናቸው፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ከ45 ዓመት በፊት እ.ኤ.አ. በ1978 የመጀመርያው ጣሊያናዊ ያልሆኑ መሪ የፖላንዱ ጳጳስ አቡነ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ (John Paul II) ከመሾማቸው በፊት፣ ሙሉ በሙሉ በሚባል የካቶሊክን ቤተ ክርስቲያንን የመሩት የጣሊያን ተወላጆች ናቸው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ አርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም ስንመጣ ቤተ ክርቲያኗን የሚመሩት ከውጭ አገር የሚመጡ ጳጳሶች ነበሩ፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ናቸው ከውጭ ጳጳስ እየመጣ የሚያሰተዳድረውን በማስቀረት፣ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ፓትሪያርክ አቡነ ባስሊዎስ እንዲሆኑ ያደረጉት፡፡ በአጠቃላይ የብዙ አገሮች የሃይማኖት መሪዎች የሚሆኑት ሃይማኖቱ ከጀመረበት አገር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም የጀመረችው በሰሜኑ በኩል ስለነበረ የጳጳሶቹም መብዛት ከዚያ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ይህ ግን ለዘለዓለም ይኑር ሳይሆን፣ የበቁ አባቶች ሲገኙ እየተሾሙ ከጊዜ በኋላ ሊስተካከል ይችላል፡፡       

የቋንቋውም ጉዳይ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ማንኛውም ሃይማኖት በተለይ አሁን ዕውቀት በተስፋፋበት ጊዜ ምዕመናኑን በማይገባው ቋንቋ ላስተምርህ ማለት አትከተለኝ እንደማለት ነው፡፡ ይህም ችግር የመጣው ሃይማኖቱ ከመጣበት አገር ነው፡፡ ካቶሊኮች ላቲን፣ ሙስሊሞች ዓረብኛ፣ የግሪክ አርቶዶክስ ግሪክኛ፣ የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ግዕዝን እንደ ዋና የሃይማኖቱ መፀለያ በማድረግ ይጠቀማሉ፡፡ ከጊዜ ወዲህ ሃይማኖቶቹ፣ የአካባቢውን ቋንቋ እየደባለቁ ይቀድሳሉ፡፡ ልጅ ሆኜ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚቀደሰው በግዕዝ ስለነበረ ምንም አይገባኝም ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በግዕዝና በአማርኛ ስለሚቀደስ በከፊል ይገባኛል የማይገባኝም አለ፡፡ አሁን በኦሮሚያ ያሉት አባቶች ያነሱት የቋንቋ ችግር አባቶቹም ከልጅነት ጀምሮ የሚያውቁት ስለሆነ፣ እነሱም እዚያው ሆነው ሊፈቱት ይችላሉ፡፡ 

በአጠቃላይ አባቶች ያነሱት በቅዱስ ሲኖዶስ ቀኖና (ሥርዓት)  ላይ ነው እንጂ፣ ቤተ ክርስቲያኗን ለመገንጠል የሚያደርስ አይደለም፡፡ ጥያቄ መነሳቱም ብዙ አዲስ አይደለም፡፡ በተለያዩ ጊዜ በዓለም ቤተ ክርስቲያናት ላይ የአስተዳደር ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ አሁንም እየተነሱ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በየጊዜው የአስተዳደር ችግር፣ የሙስና፣ የግብረ ገብነት፣ ወዘተ እንዳለ ምዕመናኑና አባቶች ሲያነሱ እንሰማለን፡፡ ቤተ ክርስቲያኗም ለማረም እንደምትሞክር ትገልጻለች፡፡ የእኛም የሃይማኖት አባቶች ያላቸውን የአስተዳደር ጥያቄዎች ለቤተ ክርስቲያኗ በማቅረብ መታገል ሐዋሪያዊ ተግባራቸውን መፈጸም ነው እንጂ፣ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለሚራወጡ የብሔር ልሂቃን እሳት ማያያዣ ክብሪት መሆን የለባቸውም፡፡ የሃይማኖት ችግሮች አዚያው በሃይማኖቱ ቀኖናና ዶግማ ይፈታል እንጂ፣ ብሔርና ፖለቲካን አንተርሶ ሊፈታ አይቻልም፡፡ እነዚህን ተንተርሶ ለመፍታት መሞከር ትርፉ ዕልቂት ነው፡፡ ለዚህም ነው ሃይማኖት በፖለቲካ፣ በዘር፣ በብሔር፣ ወዘተ ውስጥ እንዳይገባ አብዛኛው አገሮች በሕገ መንግሥታቸው ሳይቀር ከልክለዋል፡፡ አገራችንም ይህ እንዳይከሰት የከለከለች ሲሆን፣ እንዲያውም በሕገ መንግሥቷ አንቀጽ 11  መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው። መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፣ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ብላ በግልጽ ደንግጓል፡፡ በተለምዶም ‹‹ሃይማኖት የግል ነው፣ አገር የጋራ ነው›› የሚለው አባባል በፖለቲካ ልሂቃን ሲነገር ይሰማል፡፡

ፖለቲካና ሃይማኖት እንደሚለያዩ በአገራችን የታወጀው እንደተጠበቀ ሆኖ ሳለ፣ በአሠራር ግን የተደባለቀ አዝማሚያ ይታያል፡፡ በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ያለውን የቀኖና ችግር ነጥሎ የብሔር መልክ ለመስጠት የኦሮሚያ ቤተ ክርስቲያን ችግር ተብሎ ፖለቲከኛውም፣ አንቂውም ከዚያም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እንደሚደግፍ አስመስሎ ይጮሃል፡፡ ይህ አደገኛ ነው፡፡ አገሪቱን አያረጋጋም፡፡ የፌዴራሉ መንግሥትም ሆነ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከዚህ ውስጥ ገለልተኛ መሆን አለባቸው፡፡ መንግሥት ገለልተኛ ይሁን ሲባል ግን ሕግ አያስከብር ማለት አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥትና በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ሕጋዊ ፈቃድ ያለው የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ የመሾም የመሻር፣ የተሾሙትን ከቦታ ቦታ የማዘዋወር፣ በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ሀብቶቿን (ቤተ ክርስቲያኖችንም) የማስጠበቅ መብቷ ነው፡፡ የፌዴራሉም ሆነ የክልል የፀጥታ ይህንን ማስፈጸም ግዴታ አለባቸው፡፡ ይህንን ማድረግ ካልቻለ የአገሪቱ ፀጥታ ይናጋል፡፡ ይህም ሳይደረግ ለሚመጣው አደጋ መንግሥት በቀጥታ ተጠያቂ ነው የሚሆነው፡፡

አሁንም ወደንም ሆነ በግድ የመጣብንን  የቤተ ክርስቲያን ችግር መፍታት ያለብን፣ በጥሞና በማሰብና ችግሩን እንደ መልካም ዕድል በመወሰድ እንዳያዳግም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በዘላቂነት መሆን አለበት፡፡ ለዚህም የኦሮሞ የሃይማኖት አባቶች በፖለቲካና በብሔር ሳትጠለፉ እዚያው ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆናችሁ ጥያቄያችሁን በማቅረብ፣ በዘላቂነት ወደፊት እንዳይነሳ ለመፍትሔው መታገል አለባችሁ፡፡ እኔ አንዳንድ ኢትዮጵያዊ አባቶችን የምጠይቃችሁ፣ እናንተ የይቅርታ አስተማሪዎች ስለሆናችሁ የበደለም የተበደለም ተያይዛችሁ ይቅር ተባብላችሁ የአንድነት ምልክት የሆነችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከውድቀት ለማዳን ይህንን በእጃቸችሁ ያለውን ሰላም አረጋግጡልን፡፡

በመጨረሻ ላነሰ የምፈልገው እንዲሁ ዘላቂ መፍተሔ የሚሰጥ ዕድል ይዞ መጥቷል የምለው፣ ‹‹ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ ከተፈተኑት ውስጥ ያሟሉት ሦስት በመቶ ብቻ ናቸው›› የሚለው ዜና ነው፡፡ ዜናው የሚያስደነግጥ ነበር፡፡ በአካባቢው ላለነው ግን አዲስ አልሆነብንም፡፡ መንግሥት ይህ ውጤት እንዳለ አያውቅም ነበር እንዴ የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡ ምናልባት በትምህርት ሚኒስቴር ተደብቆ  አሁን ከፓርቲው ውጪ ያሉ ሚኒስቴር በመምጣታቸው እሳቸው አወጡት፡፡ ብዙ የሚያጠያይቅ ነገሮች አሉ፡፡  እኔ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ መስከረም 20 ቀን 2010  ዓ.ም. ‹‹የአገራችን የትምህርት ጥራት ውድቀት በቀላል የሚታይ አይደለም›› የሚልና መስከረም 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ‹‹ወጣቶችን ጥራት ባለው ትምህርት በመቀየር ሰብዓዊነት የተላበሱ እናድርጋቸው›› ብዬ ሁለት መጣጥፎች ማቅረቤ ይታወሳል፡፡ በእነዚያ ጽሑፎች ላይ የአገራችንን የትምህርት ችግሮች ከእነ መፍትሔያቸው ስላቀረብኩ እነሱን አልደግማቸውም፡፡ በአጠቃላይ አብዛኛው የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መማሪያ ሳይሆኑ መዋያ ሆነው ነው ያሉት፡፡ ዩኒቨርስቲዎቹም እነዚሁኑ ምንም ያልተሰናዱ ተማሪዎች አንድም ሳይቀንሱ አንዲያስመርቁ ከመንግሥት፣ ‹‹ተማሪን ያለ መጣል ዘይቤ (Zero Attrition Rate)›› በሚል ፖሊሲ ለዚህም በማስፈጸሚያ መመርያ አነስተኛ ውጤት (የወደቀ ተማሪ) ያመጣውን ተማሪ፣ ‹‹መምህሩ ተማሪውን እንደገና አስተምረህ፣ በሳምንት በማይሞላ ጊዜ እንዲያልፍ አመቻች›› በማለት፣ ጥራቱ የወደቀና በደንብ ያልተማረ ተማሪ እያስመረቅን ነው ያለነው፡፡

አሁን እዚህ ላይ የችግሩ አካል አንተ ነህ ብሎ ጣት መጠቃቀሱ የሚጠቅም አይደለም፡፡ መንግሥትም እዚህ ላይ መጠንቀቅ አለበት፡፡ እንዲያው በአጠቃላይ ሁላችንም እንደ አገር ወድቀናል፡፡ ይህንን ማረም አለብን፡፡ በፊት የችግሩን ጥልቀት አንድ ሆነን አልተረዳነውም፡፡ አሁን ግን ሁላችንም በተገኘው ውጤት ተረድተን የደነገጥን ይመስለኛል፡፡ ችግሩን መረዳታችን እንደ ዕድል ወስደን  ይህም ዕድል እንደ በፊቶቹ ችግሮች ሳንፈታቸው እንዳያመልጠን፣ የሚመለከተን ሁሉ ጠንክረን መሥራት አለብን፡፡ ችግሮቹ ውስብስብ ስለሆኑ መልሳቸውም ውስብስብ ነው የሚሆነው፡፡ ችግሩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ብቻ አይደለም፡፡ ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ ያለው ትምህርት አሰጣጣችን የቤተሰብና የማኅበረሰቡ ኃላፊነት፣ የመምህራን ዝግጅትና ሥነ ልቦና፣ ወዘተ ሁሉም መዳሰስ አለበት፡፡ አንድም ዕርምጃ ከመውሰዳችን በፊት በትምህርቱ ዙሪያ ያሉ ባለሙያዎች መምከር አለባቸው፡፡ እንዴት አንደሚፈታም የረዥም ጊዜ ዕቅድ ማውጣት አለባቸው፡፡ ዕቅዱንም እየገመገመ የሚያስፈጽም አንድ ግብረ ኃይል መቋቋም አለበት፡፡ አሁን ያለው የትምህርት ፖሊሲ ምናልባት የችግሩን ጥልቀት መሉ ለሙሉ ተንትኖ የተዘጋጀ ካልሆነ እንደገና በመከለስ መዘጋጀት አለብን፡፡ ይህንን ዕድል እንደ ዋዛ ሳንጠቀምበት እንዳናልፍ፡፡ ብዙ ችግሮች አጋጥመውን ዘላቂ መፍትሔ ሳንሰጥ እንዲያው የእሳት ማጥፋት ዓይነት አተገባበር ነው የተጓዝነው፡፡ ይህ ይብቃ፡፡ አሁንም ዘላቂ መፍትሔ እየሰጠን አገራችን ከቁልቁለት ጉዞ እናድናት፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...