Wednesday, March 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተቀማጭ ገንዘብ አንድ ትሪሊዮን ብር ሊሻገር ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ እንደሚሻገር፣ እንዲሁም የብድር ክምችቱም በሒሳብ ዓመቱ አንድ ትሪሊዮን ብር ሊሻገር እንደሚችል ተጠቆመ፡፡

ባንኩ የ2015 የግማሽ ዓመት አፈጻጸሙን በተመለከተ በተሰጠው ማብራሪያ የባንኩ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 978.9 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት በ14 በመቶ ብልጫ ያሳየ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ባንኩ አሁን የደረሰበት የተቀማጭ ገንዘብ ከሁለት ሳምንት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ የሚሻገር መሆኑንም፣ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ገልጸዋል፡፡ የመንግሥት ተቋማት በባንኩ የሚያስቀመጡት የገንዘብ መጠን ባይቀንስ ኖሮ በግማሽ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ሊሻገር ይችል እንደነበር አቶ አቤ ከሰጡት ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

‹‹ይህም ሆኖ ግን ከሁለት ሳምንት በኋላ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን አንድ ትሪሊዮን መሻገሩን እናበስራለን፤›› ብለዋል፡፡ የዛሬ ዓመት የባንኩ አጠቃላይ የሀብት መጠን አንድ ትሪሊዮን ማሻራችንን እንደገለጽን ከሁለት ሳምንታት በኋላ በተመሳሳይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን አንድ ትሪሊዮን በማሻገር በአዲስ ምዕራፍ የሚጓዙ ስለመሆኑ አመለክተዋል፡፡

የባንኩ አጠቃላይ የብድር ክምችት 975.7 ቢሊዮን ብር የደረሰ በመሆኑ፣ የብድር ክምችቱም በሒሳብ ዓመቱ ትሪሊዮን ብር ይሻገራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የባንኩ የ2015 የግማሽ ዓመት አፈጻጸምን በተመለከተ ከተሰጠው ተጨማሪ መረጃ መረዳት እንደተቻለው፣ ባንኩ በግሉ ዘርፍና በመንግሥት ለሚካሄዱ የልማት ፕሮጅቶች በባንኩ ከቀረበው ብድር ውስጥ በግማሽ ዓመት 55.8 ቢሊዮን ብር የብድር ተመላሽ መሰብሰብ መቻሉን ጠቅሷል፡፡

የውጭ ምንዛሪ ግኝትና ሥርጭትን በተመለከተም በግማሽ ዓመቱ ክንውኑ ከተለያዩ ምንጮች 1.7 ቢሊዮን ዶላር በመሰብሰብ ዓመቱን ዕቅድ በ111 በመቶ ማሳካት መቻሉንና ለገቢ ንግድና ሌሎች የውጭ ምንዛሪ ለሚያስፈልጋቸው የንግድ እንቅስቃሴዎች 3.9 ቢሊዮን ዶላር ማቅረብ ተችሏል፡፡

ባንኩ በግማሽ ዓመቱ በግሉ ዘርፍና በመንግሥት ለሚካሄዱ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችና የንግድ እንቅስቃሴዎች በአጠቃላይ 66.3 ቢሊዮን ብር ብድር ያቀረበ ከመሆኑም በላይ አጠቃላይ ገቢው 58.7 ቢሊዮን ብር መሆኑ ታውቋል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በፊት 13 ቢሊዮን ብር እንዳተረፈም አቶ አቤ ገልጸዋል፡፡

በ2015 የሒሳብ ዓመት 2.2 ሚሊዮን ብር አዲስ ደንበኞች የቁጠባ ሒሳብ የከፈቱ ሲሆን፣ ይህም ደንበኞች ቁጥር 38.1 ሚሊዮን ማድረስ የቻለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 55 አዳዲስ ቅርጫፎች በመክፈት አጠቃላይ የቅርንጫፎቹን ቁጥር 1,879 ማድረስ መቻሉን በዚሁ የግማሽ ዓመት ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

ሲቢኢ ኑር (ከወለድ ነፃ አገልግሎት) ብቻ የሚሰጡ ቅርንጫፎች ቁጥርም 130 የደረሱ ሲሆን፣ በ1,815 የባንኩ ቅርንጫፎችም ለዚህ አገልግሎት የተመደቡ መስኮቶች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ ተብሏል፡፡

ከዘመናዊ የባንክ አገልግሎት ጋር በተያያዘ የባንኩ የካርድ ተጠቃሚዎች ቁጥር 8.8 ቢሊዮን መድረሳቸውን ባንኩ አስታውቋል፡፡  

የወኪል የባንክ አገልግሎት (ሲቢኢ ብር) ከማስፋፋት አንፃርም በግማሽ ዓመቱ 4.4 ሚሊዮን አዳዲስ ደንበኞች በማፍራት አጠቃላይ ሲቢኢ ብር ደንበኞች ቁጥር 7.9 ሚሊዮን ማሳደግ ተችሏል፡፡ 99 አዳዲስ ኤቲኤም ማሽኖች የተተከሉ ሲሆን፣ የባንኩ የኤቲኤም ቁጥር 3,120 እንዲሁም የባንኩ የፓስ መክፈያ ማሽኖች 4,734 እንዳደረሱት ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለበትን አገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት በስትራቴጂ የተደገፉ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የገለጹት አቶ አቤ፣ ባንኩ ይህንን እያደረገ ያለው በታዋቂ ዓለም አቀፍ አማካሪ የተጠና የለውጥ ትራንስፎርሜሽን በመተግበር ነው ብለዋል፡፡ ይህ የለውጥ ትግበራ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ባንኩ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እየተጫወተ የሚገኘውን ወሳኝ ሚና አጠናክሮ እንዲቀጥልና መጪው በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ እንደሚከሰት ለሚጠበቀው ብርቱ ፉክክር ዝግጁ እንዲሆን የሚያስችለው ይሆናል ተብሏል፡፡

የባንኩ ሠራተኞች ቁጥር ቋሚ ሠራተኞች 39,101፣ እንዲሁም ጊዜያዊ ሠራተኞች 30,792 የደረሱ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 69,893 ሠራተኞች አሉት፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች