Thursday, July 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናለበጋ መስኖ ተጠቃሚዎች የውኃ ፓምፖች ቢቀርቡም የነዳጅ እጥረት መሰናክል መሆኑ ተገለጸ

ለበጋ መስኖ ተጠቃሚዎች የውኃ ፓምፖች ቢቀርቡም የነዳጅ እጥረት መሰናክል መሆኑ ተገለጸ

ቀን:

የመስኖ ዝርጋታ ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች አርሶ አደሮች በበጋ መስኖ እንዲጠቀሙ የውኃ ፓምፖች ቢቀርቡም፣ የነዳጅ እጥረት መሰናክል መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አምሳሉ ጎባው ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ለመስኖ ሥራ የውኃ ፓምፖችን ከመጠቀም አኳያ ከክልሉ ንግድ ቢሮ ጋር በጋራ እየተሠራ ነው፡፡ የውኃ ፓምፖችን በመጠቀም በመስኖ ሥራ የተሠማሩ አርሶ አደሮች በወረፋ መጉላላት እንዳይገጥማቸው፣ ልዩ ትኩረት እንዲሰጣቸው፣ ከንግድ ቢሮው ጋር መነጋገራቸውን አስረድተዋል፡፡

ነገር ግን በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ የውኃ ፓምፕ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች አልፎ አልፎ የቤንዚን እጥረት የገጠማቸው በመሆኑ፣ ቅሬታ እንዳደረባቸው ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በበጋ መስኖ 250 ሺሕ ሔክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ 208 ሺሕ ሔክታር ላይ እንደተዘራ፣ አርሶ አደሮችም የውኃ ፓምፕ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በርካታ አርሶ አደሮች የነዳጅ እጥረት አለባቸው ያሉት አቶ አምሳሉ፣ በደቡብ ጎንደርና በምዕራብ ጎጃም በየመንገዱ ጄሪካን ተሠልፎ እንደሚታይና ይህ ለእጥረቱ በቂ ማስረጃ ነው ብለዋል፡፡

አርሶ አደሩን የውኃ ፓምፕ ተጠቃሚ ማድረጉ ከፍተኛ ጥቅም ቢኖረውም፣ የተዘራው ቡቃያ ላይ ሆኖ በነዳጅ እጥረት ሳቢያ ከደረቀ፣ ጉዳቱ ከባድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በ2015 በጀት ዓመት የአማራ ክልል ከ11 ሺሕ በላይ የውኃ መሳቢያ ፓምፖች በክልሉ ለሚገኙ አርሶ አደሮች እንዳሠራጨ መገለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ የነዳጅ አቅርቦት ከሌለ የውኃ ፓምፕ ማሠራጨት ብቻውን ውጤት እንደማያስገኝ አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልል ባህር ዳር ዙሪያ በተለይም በአምስት አካባቢዎች የውኃ ፓምፕ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች፣ በነዳጅ እጥረት ምክንያት ሰብላቸው ከጥቅም ውጪ እየሆነባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

በባህር ዳር ዙሪያ በወረታ፣ በወንጀጣ፣ በእንዳሳ፣ በወገልሳ፣ በደቡብ ጎንደርና በምዕራብ ጎጃም የሚገኙ አርሶ አደሮች፣ የውኃ ፓምፑን ለመጠቀም የነዳጅ እጥረት ፈተና እንደሆነባቸው፣ በነዳጅ ማደያ ከአንድ ቀን በላይ ተሠልፈው ሳያገኙ እየተመለሱ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካከል አቶ አያልነህ መኩሪያ የተባሉ አርሶ አደር የበጋ መስኖ የውኃ ፓምፕ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመው፣ በማሳ ላይ ያለ ቲማቲም በውኃ እጥረት ምክንያት ከጥቅም ውጪ እየሆነባቸው መሆኑን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ ነዳጅ ለመቅዳት ሰሞኑን ወደ ባህር ዳር ከተማ ቢያቀኑም፣ አንድ ቀን ሙሉ ተሠልፈው ማግኘት እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡

በርካታ አርሶ አደሮች በበጋ መስኖ በአብዛኛው ሽንኩርት፣ ስንዴና ቲማቲም መዝራታቸውን የጠቆሙት አርሶ አደሩ፣ ‹‹የቤንዚን እጥረት መፍትሔ ካልተሰጠው የተዘራው ሁሉ ከጥቅም ውጪ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ያለንበት ወቅት ፀሐያማ ስለሆነ ሰብሉ ውኃ ሳያገኝ አንድ ቀን ቢያድር ይደርቃል፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ ትርፉ ድካም ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ እንኳን የተሻለ ሊመረት አርሶ አደሩ ለቤንዚንና ለዘር ያወጣውን ገንዘብ መሸፈን አይችልም፡፡ ይህ ደግሞ ትልቅ ኪሳራ ነው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡ የክልሉ ንግድ ቢሮ በበኩሉ ሰሞኑን በማደያዎች በርካታ ሠልፍ እየታየ መሆኑን ገልጾ፣ ለሠልፉ መበራከት መንስዔውን እያጣራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው በበኩላቸው አርሶ አደሩ የነዳጅ እጥረት እንደገጠመው በግልጽ እየታየ መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹እየተደናቀፈ ያለው ልማት ነው፤›› ብለዋል፡፡

አርሶ አደር መስለው ነዳጅ የሚቀዱ የጥቁር ገበያ ነጋዴዎች ለችግሩ መፈጠር ምክንያት ስለሚሆኑ ሕግ ማስከበር እንደሚገባ ጥያቄ ቀርቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...