በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትና በሰው ሠራሽ ምክንያት ትግራይን ሳይጨምር ከፍተኛ የሆነ ውድመት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለማቋቋም 51.2 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ፣ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ይህንን የገለጸው ሐሙስ ጥር 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በጦርነትና በሰው ሠራሽ አደጋዎች የፈረሱ 71 ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት፣ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን ሲያስታውቅ ነው፡፡
በሚኒስቴሩ የትምህርት ፕሮግራሞች ጥራት መሻሻል መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮሐንስ ወጋሶ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተለያዩ ቦታዎች በተደረገው ጦርነት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለማቋቋም ጥናት ተደርጎ ሥራ ተጀምሯል፡፡
በዚህም መሠረት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት ከተለያዩ ተቋማት ጋር ቅንጅት በመፍጠር እየተሠራ ነው ያሉት አቶ ዮሐንስ፣ በአፋርና በአማራ ክልሎች አንዳንድ ቦታዎች ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ መደረጉን አስረድተዋል፡፡
በትግራይ ክልል የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለማቋቋምና ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው በፍጥነት እንዲመለሱ ለማድረግ ረዥም ጊዜ እንደሚወስድ ጠቅሰው፣ በጦርነቱም ጉዳት ለደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች መልሶ ለመገንባት፣ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ለግንባታ የሚውሉ ጥሬ ዕቃዎች ሊወደዱ ስለሚችሉ ሌላ ተጨማሪ ገንዘብ ሊያስፈልግ እንደሚችል አብራርተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በጦርነት ምክንያት የተጎዱ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር እየተከናወነ መሆኑን፣ በቀጣይ ዓመታትም ሚኒስቴሩ በርካታ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ዕቅድ መያዙን አክለዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፊሰር)፣ በአሁኑ ወቅት የትግራይ ክልልን ሳይጨምር 3,300 ትምህርት ቤቶች በጦርነቱ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውንና 4,000 የሚሆኑት ደግሞ በከፊል ቢሆንም ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ ዓርብ ጥር 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ትምህርት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋር የሰብዓዊ መብቶች ትምህርት በመደበኛና መደበኛ ባልሆኑ የትምህርት ሥርዓቶች ውስጥ ለማካተት፣ እንዲሁም ለማጠናከር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
በመግባቢያ ስምምነቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ በትምህርት ተቋማት ላይ እየደረሰ ያለውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ለመቀነስ ይህ ስምምነት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡
የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በኢትዮጵያ ፈተና ሆኖ መቆየቱን የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ የሰብዓዊ መብቶች እሴቶችን በትምህርት በኩል ወደ ማኅበረሰቡ ማስረፅ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰላም ሊመጣ የሚችለው የሰው ልጆች ሰብዓዊ መብቶች ሲከበሩ እንደሆነ፣ ይህንን ለማስረፅ መብትና ግዴታውን መለየት የሚችል ማኅበረሰብ መፍጠር ሲቻል ብቻ ነው ያሉት ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) ናቸው፡፡
በትምህርት ሚኒስቴርና በኢሰመኮ በኩል የተደረገው ስምምነትም የሰብዓዊ መብት ትምህርትን በመደበኛው ትምህርት፣ እንደ ግብረ ገብና የዜግነት ትምህርት ውስጥ ትርጉም ባለው መንገድ የሚያካተት መሆኑ ተገልጿል፡፡
የፊርማ ሥነ ሥርዓቱም የትምህርት ሚኒስቴር ደኤታ ፈንታ ማንደፍሮን (ዶ/ር) ጨምሮ፣ የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ወ/ሮ ራኬብ መሰለ፣ እንዲሁም የሁለቱ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተከናውኗል፡፡