- የፌዴራል ፖሊስና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽኖችም ተካተዋል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. አዲስ ቅዱስ ሲኖዶስ አቋቁዋል በተባሉትና በኦሮሚያ ክልል መንግሥት፣ በፌዴራል ፖሊስና በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽኖች ላይ ክስ ለመመሥረት የዕግድ አቤቱታ ለፍርድ ቤት ጥያቄ አቀረበች፡፡
ቤተ ክርስቲያኗ የዕግድ ጥያቄ ያቀረበችው ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ምድብ ችሎት ሲሆን፣ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 205፣ 154፣ 155 እና አዋጅ ቁጥር 1234/13 አንቀጽ 11 (3)፣ እንዲሁም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 191402 የሰጠውን የሕግ ትርጉም መሠረት በማድግ ነው፡፡
የዕግድ አቤቱታው መሠረት ያደረገው በቀድሞ ስማቸው አባ ሳዊሮስ፣ አባ ኤዎስጣቴዎስና አባ ዜና ማርቆስ ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. 25 ኤጲስ ቆጶሳትን መሾማቸውና ‹‹በኢትዮጵያ ኦሮሚያና ብሔር ብሔረሰቦች ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ›› አቋቁመናል ማለታቸውንና ይህንንም ድርጊታቸውን በመገናኛ ብዙኃን ማስተላለፋቸውንና ድርጊቱም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ዶግማና ቀኖና የጣሰ መሆኑን እንደሆነ በአቤቱታው ተብራርቷል፡፡
ዕግድ የተጠየቀባቸው ግለሰቦች (ተከሳሾች) የቤተ ክርስቲያኗን ስምና ዓርማ በመጠቀም፣ በስሟ ይዛ የምትገለገልባቸውን፣ ማምሊኪያ ሥፍራ፣ ይዞታዎች፣ የአምልኮ መፈጸሚያ ንዋያተ ቅድሳቶቿንና ንብረቶቿን በይፋ ወረራ መንጠቃቸውንና እየነጠቁ መሆኑንም አቤቱታው ያሳያል፡፡
ግለሰቦቹ የቤተ ክርስቲያኗን መብት ሲጥሱ፣ በሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ ሦስት ሥር ተደንግገው የሚገኙትን መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ላይ ጥሰት መፈጸማቸውን ጠቁሟል፡፡
ግለሰቦቹ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 14፣ 15 እና 16 ድንጋጌዎችን በመተላፍ፣ በተለያዩ ቦታዎች በሚያደርጓቸው ንግግሮችና ለተከታዮቻች በሚያስተላለፉት መልዕክት፣ የሃይማኖት አባቶችን ሕይወትና የአካል ደኅንነት አደጋ ውስጥ የሚከት ቅስቀሳ ማድረጋቸው በዕግድ አቤቱታ ላይ ተብራርቷል፡፡
ዕግድ የቀረበባቸው ግለሰቦችና ተቋማቶች የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 17 ድንጋጌን በመተላለፍ፣ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስን ጨምሮ፣ ስምንት የቤተ ክርስቲያኗን የተለያዩ አድባራት፣ ኃላፊዎችና አገልጋዮችን በማሰር፣ ሰብዓዊ መብታቸውንና ነፃነታቸው መጣሱ ተብራርቷል፡፡
የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 24 በመጣስ የቅዱስ ሲኖዶሱን ክብርና መልካም ስም ማጥፋታቸውን፣ አንቀጽ 25 ድንጋጌ ሰዎች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል ናቸው የሚለውን በመተላለፍ ሰዎች በዘር፣ በሃይማኖት፣ በብሔር፣ በትውልድና በፖለቲካ ልዩነት እንዲደረግባቸው የአመፅ ጥሪ በማድረግ፣ ዜጎች የደኅንት ሥጋት ውስጥ እንዲወድቁ ማድረጋቸውም በአቤቱታው ተብራርቷል፡፡
በአጠቃላይ ዕግድ የተጣለባቸው ግለሰቦች፣ የክልሉ መንግሥትና የፀጥታ አካላት፣ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 29 (5 እና 6) አንቀጽ 30፣ 32፣ 40 በመተላለፍና በአንቀጽ 11 ተደንግጎ የሚገኘውን በመተላለፍ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መገባቱንም አቤቱታው ያስረዳል፡፡
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 41 (9) የተደነገገውን በመተላለፍ፣ የአገሪቱን ባህልና የታሪክ ቅርስ የመጠበቅ ግዴታን ባለመወጣታቸው፣ በጉዳዩ ላይ ማስረጃዎችንና መረጃዎችን ሰብስቦ ክስ ለመመሥረት ጊዜ ስለሚወስድ፣ እንዲሁም ድርጊቱ እየተከናወነ ያለው፣ በአገሪቱ ክፍሎች ባሉ ከአሥር ሺሕ በላይ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ስለሆነ፣ ተጠርቶ ክስ እስኪቀርብ ድረስ ዕግድ እንዲሰጥ ቤተ ክርስቲያኗ በመወከለቻቸው አምስት ጠበቆች አማካይነት ጠይቃለች፡፡
በአጠቃላይ በአገር ውስጥና በመላው ዓለም ዕግድ የተጠየቀባቸው አካላት የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኗ አባላት፣ በሁሉም ይዞታዎች፣ አኅጉረ ስብከት፣ ገዳማትና አድባራት ሁሉም ዓይነት ንብረቶች፣ ታሪካዊ ቅርሶች፣ መንፈሳዊና ቁሳዊ መገልገያ ንብረቶች ላይ መጠቀም እንዳይቻልና ሁከትና መሰናክል እንዳይፈጠር እንዲደረግ ዳኝነት ተጠይቋል፡፡
ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም. በቅዱስ ሲኖዶሱ አስቸኳይ ጉባዔ የተሾሙት ጳጳሳት የተወገዙና አዲስ የተቋቋመውም ሲኖዶስ ዕውቅና የተነፈገው በመሆኑ፣ አስፈላጊ ውዝግብ እንዳያስነሳ ጉዳዩ ዕልባት እስከሚያገኝ፣ በማንኛውም መገናኛ ብዙኃን መግለጫ እንዳይሰጡ ለብሮድካስት ባለሥልጣን ትዕዛዝ እንዲጥላቸው ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ አቤቱታውን መርምሮ ፍርድ ለመስጠት ለነገ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡