Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮ ቴሌኮም ‹‹ኢትዮ ቴል ኢኖቬሽን›› የተሰኘ ፕሮግራም ይፋ አደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮ ቴሌኮም ‹‹ኢትዮ ቴል ኢኖቬሽን›› የተሰኘ ፕሮግራም ይፋ ማድረጉን አስታወቀ፡፡

‹‹ኢትዮ ቴል ኢኖቬሽን›› የተሰኘው አዲስ ፕሮግራም ይፋ መደረጉን ያስታወቁት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ ናቸው፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ይህን የተናገሩት ሰኞ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በሃያት ሪጀንሲ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡

ተቋሙ ይፋ ያደረገው አዲሱ ፕሮግራም በቴክኖሎጂ ዘርፍ ለተሰማሩ 250 ስታርት አፕ (ጅማሮ ላይ ያሉ) ኩባንያዎች፣ ሰፊ አገልግሎት እንዲሰጡ ዕድል የሚሰጥ እንደሆነ በመርሐ ግብሩ ተነግሯል፡፡

የፕሮግራሙ ዋና ዓላማም በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ ጀማሪ ኩባንያዎችን ሥልጠና በመስጠት ልምድ እንዲያገኙ በማድረግ ለማብቃት፣ ለማቀፍ፣ ለመደገፍና ለማበረታታት መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ወ/ሪት ፍሬሕይወት ጅማሮ ላይ ያሉ ኩባንያዎች ዕድል የሚያገኙት፣ ኢትዮ ቴሌኮም ይፋ ባደረገው ፕሮግራም በሚሰጣቸው የተለያዩ ሥልጠናዎችና ምርቶቻቸውን ወደ ገበያ የሚያቀርቡበትን መንገድ በማመቻቸት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በፕሮግራሙ 250 የሚሆኑ ኩባንያዎችን ዕድል እንዲያገኙ ለማድረግ መታቀዱ፣ ኩባንያዎችን በፕሮግራሙ ተጠቃሚ የሚሆኑባቸው ሦስት ምዕራፎች መቀረፃቸው ተገልጿል፡፡

በመጀመርያው ምዕራፍ 100 ኩባንያዎችን፣ በሁለተኛው ምዕራፍ 150 ኩባንያዎችን በማሳተፍ፣ በሦስተኛው ምዕራፍ ደግሞ ሌሎችን የመመዝገብ ተግባር እንደሚከናወን ተብራርቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር 250 ኩባንያዎች በሚሰማሩበት የሥራ ዘርፍ እንደ አቅማቸው ለሚፈልጓቸው ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚቻል ተጠቁሟል፡፡

ፕሮግራሙን ይፋ ለማድረግ ያነሳሳቸው ምክንያት ምን እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ ዘመኑ የዲጂታል ኢኮኖሚ በመሆኑ ነባር ሥራዎች ደግሞ በቴክኖሎጂ አማካይነት ብቻ ሊያድጉና ሊሳለጡ ስለማይችሉ፣ አዳዲስ ሀብት ይፈጥራል ተብሎ በመታመኑ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

አዲስ ሀብት ለመፍጠር ደግሞ ኢትዮ ቴሌኮም ትልቁን ድርሻ እንደሚወጣ፣ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ከሚያስፈልገው ነገር አንዱም የቴሌኮም ተደራሽነትና ጥራት ነው ተብሏል፡፡

ሰዎች በስልካቸው አማካይነት ጤና፣ ትራንስፖርትና ፋይናንስ ቢያገኙም እነዚህ አገልግሎቶችን አበልፅጎ ለገበያ ለማቅረብ ብዙ ውስንነቶች ይስተዋላሉ ያሉት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ ዛሬ በዓለም ላይ በቢሊዮን የሚቆጠር ገቢ የሚያገኙት አቅም ያላቸው ኩባንያዎች በመጀመርያ ሲመሠረቱ ስታርት አፕ እንደነበሩና ዕገዛ ተደርጎላቸው ለውጥ እንዳሳዩ ሁሉ፣ በኢትዮጵያ ያሉ ስታርት አፖችን ኢትዮ ቴሌኮም ቢደግፋቸው አገር በቀል የሆኑ ብዙ መፍትሔዎችን ይዘው ወደ ገበያ መቅረብ ይችላሉ ተብሎ ስለሚታመን ፕሮግራሙን ይፋ ማድረግ አስፈልጓል ብለዋል፡፡

‹‹ኢትዮ ቴል ኢኖቬሽን›› ፕሮግራም ዲጂታል ኢትዮጵያ ዕውን ለማድረግ ትልቅ ሚና እንዳለው፣ በተለይም ወጣቶችን ተሳታፊ በማድረግ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር አክለዋል፡፡

ከአሁን ቀደም ተቋሙ ይፋ ያደረጋቸው የተለያዩ ፕሮግራሞች ስኬታማ መሆናቸውን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ ሰሞኑን ይፋ በተደረገው አዲስ ፕሮግራምም ስኬታማ በመሆን ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ማድረግ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ 70 ሚሊዮን ከሚሆኑት የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች መካከል 30 ሚሊዮን የሚሆኑት ኢንተርኔት ተጠቃሚ መሆናቸው የተጠቀሰ ሲሆን፣ ይህም ቁጥር አዲስ ይፋ ለተደረገው ኢትዮ ቴል ኢኖቬሽን በርካታ ተሳታፊዎች እንዲኖሩት እንደሚያደርግ በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ተነግሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች