Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአብዛኛዎቹ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከሀብት አስተዳደር ጋር በተያያዘ ሕግ እንደሚተላለፉ ተገለጸ

አብዛኛዎቹ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከሀብት አስተዳደር ጋር በተያያዘ ሕግ እንደሚተላለፉ ተገለጸ

ቀን:

በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አብዛኛዎቹ ከሀብት አሰባሰብና አስተዳደር ጋር በተያያዘ የተቀመጠውን ሕግ እንደሚተላለፉ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ መሠረት እያንዳንዱ ድርጅት ካገኘው ሀብት ውስጥ 20 በመቶ ብቻ የሚሆነውን ለአስተዳደራዊ ወጪ ማውጣት ያለበት ሲሆን፣ የተቀረውን 80 በመቶ የሚሆነውን ለሚሠራው ሥራ (ፕሮግራም) ማውጣት እንዳለበት መደንገጉን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ አስታውሰዋል፡፡

ብዙዎቹ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ይህንን የሀብት አስተዳደር አሟልተው እንደማይገኙ የተናገሩት አቶ ጂማ፣ ካገኙት ሀብት ውስጥ ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆነውን ለአስተዳደራዊ ወጪ የሚጠቀሙ እንዳሉ አስታውቀዋል፡፡

ባለሥልጣኑ እያጋጠሙት ካሉት ችግሮች አንዱ በድርጅቶቹ የማይተገበረው የሀብት አሰባሰብና አስተዳደር ችግር አንዱ መሆኑ ተገልጾ፣ በየጊዜው ከድርጅቶቹ ጋር በመመካከር እንዲሁም ሥልጠናዎችን በመስጠት ሕግ አክብረው የሚንቀሳቀሱበትን አሠራር እየፈጠረ እንደሚገኝ፣ ከዚህ ካለፈ የማስጠንቀቂያና የዕግድ ዕርምጃ እንደሚወስድ ተጠቁሟል፡፡

በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 እንደተደነገገው፣ ማናቸውም ለጠቅላላው ሕዝብ ወይም ለሦስተኛ ወገን ጥቅም መሥራትን ዓላማ አድርጎ የተቋቋመ ድርጅት የአስተዳደር ወጪው ከገቢው ከ20 በመቶ ሊበልጥ አይችልም፡፡

በድንጋጌውም የአስተዳደር ወጪ ማለት ድርጅቱ ከሚያከናውነው የፕሮጀክት ሥራ ጋር ተያያዥነት የሌለው፣ ነገር ግን ለድርጅቱ ህልውና ቀጣይነት አስፈላጊ የሆነና ከአስተዳደር ሥራዎች ጋር የተያያዘ ነው፡፡

አቶ ጂማ እንዳስታወቁት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን የመመዝገብ የመከታተል ተልዕኮ የተሰጠው ባለሥልጣኑ የሲቪል ማኅበረሰብ ዘርፉን ለማሳደግና የተሻለ ድጋፍና ክትትል ሥርዓት ለመዘርጋት፣ የዜጎች የመደራጀት መብት ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ነው፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከውጭና ከአገር ውስጥ ሀብት የሚሰበስቡ ቢሆንም የሀብት ውስንነት ችግር እንዳለባቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ብዙኃኑ ድርጅቶች ፕሮጀክቶችን ቀርፀው በቂ የውጭ ሀብት ካለማግኘታቸው በላይ ከአገር ውስጥ ሀብት ለማመንጨት የሚሳናቸው ድርጅቶች አሉ ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል አልፎ አልፎ የሕግ ጥሰት የሚፈጽሙ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንደሚገኙ፣ በ2013 ዓ.ም. ክረምት ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር ተያይዞ አሉታዊ የሆነ ድርጊት ሲፈጽሙ በነበሩ ድርጅቶች ላይ ዕርምጃ ተወስዶ እንደነበረ፣ አሁንም አንዳንዶቹ ድርጅቶች ላይ ችግሩ እንደሚስተዋል አቶ ጂማ ገልጸዋል፡፡

በተያያዘም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤትና ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ፎረም ጋር በመተባበር፣ በፌዴራል ደረጃ የመንግሥትና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የጋራ ጉባዔ አካሂደዋል፡፡

የጋራ መድረኩ እንዲዘጋጅ ያስፈለገበት ዋና ዓላማ በመንግሥትና በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መካከል ቅንጅታዊ አሠራር ሥርዓትን ለማጎልበት፣ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በመለየት መፍትሔ ለመስጠትና ምቹ መደላድል እንዲኖር ለማስቻል፣ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ መነሻ ሐሳቦችን በማመንጨት የኅብረተሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት ለማረጋጋጥ ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ በሂልተን ሆቴል በተደረገው መድረክ ተገልጿል፡፡

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የፍትሕ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ፈቃዱ ፀጋ፣ በኢትዮጵያ ያለው ሀብት ውስን በመሆኑ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በዚህ ረገድ የማይተካ ሚና እንዳላቸው በመገንዘብ አገልግሎታቸው የተሳለጠ እንዲሆን፣ የጋራ መድረክ ትብብሩን ወደላቀ ደረጃ የሚያደርስ፣ በውስን የሰው ኃይልና የፋይናንስ አቅም ያለውን አስተባብሮ የሚያሠራ፣ ያለውን ውስን ሀብት በተናጠል ከመሥራት ይልቅ ለጋራ ዓላማ በተገናዘበ መንገድ በትብብር ለመሥራት ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡

የመንግሥትና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የጋራ መድረክ በክልሎች የተለመደ፣ በተለይም በባለፉት ዓመታት እየተጠናከረና ውጤት እያስመዘገበ ያለ ፎረም መሆኑን ያወሱት አቶ ጂማ፣ አሁን በፌዴራል ደረጃ የሚመሠረተው መድረክም ዘርፉን ውጤታማ በሆነ ሁኔታ ለመምራት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሔኖክ መለሰ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ አሁን የምትገኝበትን አስቸጋሪ የደኅንነት ችግር ተሻግራ ዘለቂ ሰላምን እንድታረጋግጥ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሚናቸውን ሊያጠናክሩና የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

በተለይ የዘላቂ ሰላም መሠረቶች አንዲጣሉ፣ ግጭቶችን በሠለጠነ መንገድና በውይይት የመፍታት ባህል ሥር እንዲሰድ፣ አካታችነትና መቻቻል እንዲጠናከር፣ የሰላም ባህል እንዲስፋፋና የበላይነት እንዲኖረው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ መንቀሳቀስ እንደሚኖርባቸው አቶ ሔኖክ አሳስበዋል፡፡

በኢትዮጵያ 4,400 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን፣ በአሥር ዓመት ዕቅድ ይህን ቁጥር 14,000 ለማድረስ እንደሚንቀሳቀስ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...