‹‹ደቡብ ኢትዮጵያ›› የተሰኘ አዲስ ክልልን ለመመሥረት ከትናንት በስቲያ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. የሕዝበ ውሳኔ ድምፅ ከሰጡ ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ውስጥ በቡርጂ ወረዳ ድምፅ ለመስጠት ከተመዘገቡ መራጮች መካከል፣ ዳሊኣ በተሰኘ ቀበሌ ምርጫ ጣቢያ ለመምረጥ የተመዘገቡ ዜጎች፣ ከቀበሌው አስተዳደር ጋር አለን ባሉት ቅሬታ የተነሳ ወደ ምርጫ ጣቢያ ብቅ ሳይሉ መቅረታቸው ተገለጸ፡፡
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ሥር የሚተዳደሩት ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋ ዞኖች እንዲሁም ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች የተሳተፉበት ሕዝበ ውሳኔ ሰኞ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ተካሂዷል፡፡
የሕዝበ ውሳኔ ድምፅ አሰጣጥ ሥርዓት መጠናቀቁን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚዲቅሳ በአርባ ምንጭ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከላይ በተጠቀሰው የምርጫ ጣቢያ ከምርጫ ታዛቢ ሠራተኞች ውጭ በምርጫው የተገኘ ነዋሪ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ ሰብሳቢዋ ደረሰኝ ባሉት መረጃ መራጮች ወደ ምርጫ ጣቢያ ያልመጡት ኅብረተሰቡ ከቀበሌ አስተዳደር ጋር ባላቸው ያልተፈታ ቅሬታ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡
ሰብሳቢዋ ‹‹ቀኑን ሙሉ መራጮች ለምን እንዳልመጡ ለማጣራትና ምርጫው እንዲቀጥል ለማድረግ ባደረግነው ጥረት፣ በጣቢያው የተመዘገቡ መራጮች አስተዳደሩ በቀበሌው ውስጥ ያለንን አስተዳደራዊ ችግርና ጥያቄ ስላልፈታልን መጥተን መሳተፍ አንፈልግም በማለት ሐሳባቸውን እንደገለጹና አስተዳደሩም ከነዋሪዎቹ ጋር ለመነጋገር እንደሞከረ ለማወቅ ተችሏል፤›› ብለዋል፡፡
የቡርጂ ልዩ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ማሬ ዓለማየሁ ሪፖርተር ተፈጠረ ስለተባለው ችግርና የሕዝቡን ጥያቄ በተመለከተ አስተያየት እንዲሰጡ የጠየቃቸው ሲሆን፣ ስልካቸውን ካነሱና ጥያቄውን ከሰሙ በኋላ ‹‹ቆይታቸሁ ደውሉ›› በማለታቸው በተደጋጋሚ ቢደውልላቸውም ስልክ አንስተው መልስ ሊሰጡ አልቻሉም፡፡
በ31 ማዕከላት ሥር ባሉ 3771 ምርጫ ጣቢያዎች ለመምረጥ የተመዘገቡ 3,028,770 ዜጎች ድምጻቸውን ሲሰጡ የዋሉ ሲሆን፣ ምርጫው ተጠናቆ ጊዜዊ የድምፅ ቆጠራ ተከናውኗል፡፡ የመጨረሻ ውጤቱም ተጠናቆ በቀጣይ ስምንት ቀናት ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ ሰብሳቢዋ ተናግረዋል፡፡
የሪፖርተር ዘጋቢ ከድምጽ መስጫው ዋዜማ ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የነበረው ድባብ ቀዝቀዝ ያለ እንደነበርና አዲስ ክልል ለመመስረት በዝግጂት ላይ ያለና የተሰናዳ ሕዝብ እንደማይመስል ለመታዘብ ችሏል፡፡ አሰተያየታቸውን ለሪፖርተር ከሰጡ ነዋሪዎች እንደተሰማው፣ በርካታዎቹ ስለሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ካርድ አውጥተው ድምፅ መስጫውን ቀን ከመጠበቅ ባለፈ ብዙም የተለየ ጠንካራ ሐሳብ አላነሱም፡፡
አድነው ዘብዴዎስ የተሰኙ የአርባ ምንጭ ነዋሪ ‹‹ካርድ አውጥቻለሁ፣ ነገ እመርጣለሁ፣ ዋናው ጉዳይ ሰላምና ልማት ነው፣ ዋናው የምፈልገው አገራችን ሰላም እንድትሆን ነው፤›› የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
‹‹ይህንን ላሰማንና እዚህ አድርሶ ይህን ላሳየን እግዚአብሔር ይመስገን፣ ይህን ምርጫ ሳደርግ ለልጆቼ ተስፋ በማድረግ፣ አገራችን እንድታደግና በብዛት ከሥራ ውጭ የሆኑት የአርባ ምንጭ ወጣቶችን ሕይወት የሚቀይርና አሁን ያለውን ነገር የሚለውጥ ክልል ይመጣል ብዬ አስባለሁ፤›› ያሉት ሌላኛዋ መራጭ ብርቱካን ጸጋዬ ናቸው፡፡
አክለውም ‹‹አሁን ኑሮ ተወዷል፣ ሁሉም ከእጅ ወደ አፍ ሆኗል፣ የዕለት ጉርስ ለማግኘት ብዙ እናቶች ተቸግረዋል፣ አሥር ብር የነበረ ሳሙና 50 ብር ገብቷል፣ ልጆች ትምህርት ቤት ሲሄዱ ምግብ ለመቋጠር ሰው ቸግሯል፤›› ብለዋል፡፡
በምርጫው ቀን በበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ መራጮች ድምፅ ለመስጠት ተሠልፈው የታየ ሲሆን፣ በተወሰኑ የምርጫ ጣቢዎች ላይ ሕግ ከሚፈቅደው ውጭ ከማለዳው 12 ሰዓት በፊት ተጀምረው መገኘታቸውን ሰብሳቢዋ ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ በድምፅ አሰጣጥ ሒደት ያጋጠሙ የአሠራር ግድፈቶችን አስመልክተው ሰብሳቢዋ ሲናገሩ፣ ለአካለ መጠን ያልደረሱና 18 ዓመት ያልሞላቸው ዜጎች በመራጭነት ተመዝግበው መገኘት፣ እንዲሁም በወላይታ ዞን የአስተዳደር አካላት አማካይነት የተፈጸሙ የሕግ ጥሰቶች በተለይም የመታወቂያ ወረቀት ማደል ላይ ተሰማርተው መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የምርጫ ቁሳቁስ ጉድለቶች ገጥመው እንደነበር የተገለጸ ሲሆን ለአብነትም በሦስት ጣቢያዎች የማህተም መርገጫ፣ በሦስት የምርጫ ጣቢያዎች የመራጭነት ማረጋገጫ ቀለም፣ የአሻራ መርገጫ በአንድ ጣቢያ፣ የማሸጊያ መመዝገቢያና ቃለ ጉባዔ መመዝገቢያ ቅጾች በሁለት ጣቢያዎች፣ እንዲሁም የማመሳከሪያና ውጤት ማሳወቂያ በአንድ ጣቢያ እጥረት ገጥሞ እንደነበር የገለጹት ሰብሳቢዋ፣ የጎደለውን ቁሳቁስ ከማዕከልና አቅራቢያ ከሚገኙ ጣቢያዎች በማስመጣት እንደተፈታ አስረድተዋል፡፡
ሪፖርተር በተለያዩ የምርጫ ጣቢያዎች መራጮችን ያነጋገረ ሲሆን፣ በዚህም በርካታ መራጮች አዲስ ክልል ቢመሠረት የሥራ አጥነት ችግርን ይቀርፋል፣ ሰላምንና ፍትሐዊነትን ያሰፍናል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ሐሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
ሰላም ዳኛቸው የተባሉ መራጭ አስተያየታቸውን ሲሰጡ፣ ይህ የሕዝበ ውሳኔ ሕዝቡ ከጅምሩ ሲጠይቀው የነበረውን አስተዳደራዊ የሆኑ ችግሮች በተሻለ መልኩ ይፈታል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ እኔም ሕዝቡን ተቀላቅያለሁ፣ ውሳኔዬ በእኔ ሕይወት ላይ ከዚያም የሕዝቡን ኑሮ ሊያሻሻል ይችላል የሚል ተስፋ አለኝ፤›› ብለዋል፡››
አብዮት አረፈው የተባሉ ሌላ መራጭ በበኩላቸው ‹‹ለሕዝበ ውሳኔው ያነሳሳኝ ሥራ አጥ የሆንኩበት የግል ጉዳዬ ነው፣ ምክንያቱም እኔ ሥራ አጥ ነኝ፣ ምርጫው ከተሳካ በሚመሠረተው አዲስ ክልልና በቀጣይ በሚፈጠረው መዋቅር አማካይነት የተሻለ የሥራ ዕድል ይመጣል የሚል እምነት አለኝ፤›› በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ጌጡ በምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ድምፅ ከሰጡ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ዋነኛ ዓላማ ለሁሉም አካል እኩል መስጠት እንደሆነና ይህ ሕዝበ ውሳኔ የዚሁ ማሳያ መሆኑንና ሕዝቡ የወደደውን እንዲያርግ ዕድል የሰጠ ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡
አስተዳዳሪው አክለውም ከዚህ ቀደም የደቡብ ክልል ውስጥ ያሉ ሕዝቦች ክልል ለመሆን ጥያቄ የሚያቀርቡበትን ዋነኛ ምክንያት አስመልክቶ በተደረጉ የተለያዩ ጥናቶች በተገኘ ውጤትና ከሕዝቡ ጋር በተደረገው ውይይት፣ ትልቁና ዋነኛው ችግር ኢፍትሐዊነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የነበረው ዋናው የደቡብ ክልል ከጅምሩ ሲዋቀር በተወሰኑ ሰዎች ፍላጎት የተመሠረተ እንጂ፣ ‹‹በሕዝቡ ፍላጎት አልነበረም›› የሚሉት አስተዳሪው፣ በቀጣይ ዝም ብሎ አዲስ ክልል ከማደራጀት ባላፈ የሕግ ማሻሻያዎችና የአደረጃጀት ለውጦችን በማድረግ ፍትሐዊነት እንዲመጣና በጋራ ማደግ የሚቻልበት አሠራር ይዘረጋል ብለዋል፡፡ በመሆኑም በሕዝብ ፍላጎት የሚዋቀር ክልል በቀጣይ የሚመጡ ችግሮችን በጋራ በመነጋገር እንዲፈታ ያደርጋል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በአርባ ምንጭ ከተማ ድምፃቸውን የሰጡት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የብልፅግና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ እንደተናገሩት፣ ከዚህ ቀደም የነበረው ክልል ሕዝብ ያልመከረበት እንደነበር በመሆኑ፣ በዚህኛው ሕዝበ ውሳኔ ክልሉ የሚመሠረት ከሆነ የሕዝቡን የፖለቲካ፣ የመልካም አስተዳደርና የልማት ሥራዎችን በምክክር እንደሚፈታ ተናግረዋል፡፡
በመዋቅር ጥያቄ ምክንያት ሰው ሊሞት፣ ሊፈናቀል፣ ሊጎዳ አይገባም በሚል በሠለጠነና በሰላማዊ መንገድ ገዥ የሆነውን ሐሳብ በመውሰድ፣ ለሕዝበ ውሳኔ መደረሱን አቶ ጥላሁን አክለው ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን የመዋቅር ጉዳይ ሁሉንም ሊፈታ የማይቸል በመሆኑ፣ ሁሉም ሰው ያለውን አቅም አሟጦ ሊጠቀም እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ የሚገኙትና ጥር 29 ቀን የሕዝበ ውሳኔ ድምፅ የሰጡት ስድስት ዞንና አምስት ልዩ ወረዳዎች በክልል የሚደራጁ ከሆነ፣ ከዋናው ክልል የሚቀሩት ስድስት መዋቅሮች ማለትም የጉራጌ፣ ስልጤ፣ የም ልዩ ወረዳ፣ ከንባታ ጠንባሮና ሀድያ ዞኖች ላይ ሪፎርም ተደርጎ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ዞን በሚል በአዲስ የክልል ሕገ መንግሥት እንደሚቋቋም አቶ ጥላሁን ጠቁመዋል፡፡