በኢትዮጵያ የቲቢ በሽታን መመርመር የሚያስችሉ፣ 300 ሺሕ ዶላር ወጪ የተደረገባቸውና በቴክኖሎጂ የተደገፉ (አርተፊሻል ኢንተለጀንስ የተገጠመላቸው) ሦስት ተንቀሳቀሽ ዲጂታል ኤክስሬይ ማሽኖች የማስተዋወቂያና የማስጀመርያ ፕሮግራም ጥር 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ተከናውኗል፡፡
በቲቢ መከላከልና መቆጣጠር ዙሪያ የሚንቀሳቀሰው ‹‹ሪች ኢትዮጵያ›› የተባለ አገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ‹‹ስቶፕ ቲቢ›› ከተባለው ፓርትነር ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ያስመጣቸው እነዚህ ማሽኖች የቲቢ ምርመራ ሥርዓትን በማፋጠን ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲኖር የሚያስችሉ ናቸው፡፡
የሪች ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መሠረት አሰፋ እንደገለጹት፣ ማሽኖቹ የላቦራቶሪ ምርመራ ሳያስፈልጋቸው ከአምስት ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ በሽታውን የመለየት አቅም አላቸው፣ በሌሎችም አገሮች ተሞክረው ጥሩ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡
ለማሽኖቹ መግዣ የዋለው ገንዘብ የተገኘው፣ የመለያ ቁጥሩ ኢቲ 737 የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማክስ አውሮፕላን መጋቢት 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አካባቢ ወድቆ በተከሰከሰበት ወቅት፣ ለሞት ለተዳረጉ ተሳፋሪዎች የሕይወት ካሳ ከተከፈላቸው ቤተሰቦች መካከል ከአንደኛው ቤተሰብ ነው፡፡ የተሰጠውን ገንዘብ ለማኅበረሰብ አገልግሎት እንዲውል ለስቶፕ ቲቢ ማስከረባቸውን ገልጸዋል፡፡
ስቶፕ ቲቢም የተረከበውን ገንዘብ በቲቢ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዙሪያ ለኅብረተሰቡ ቅን አገልግሎት እያበረከተ ላለው ለሪች ኢትዮጵያ መስጠቱን ከዋናው ሥራ አስኪያጅ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
የጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ምክትል ዳይሬክተር አቶ ታዬ ለታ፣ የቲቢ በሽታን ለማጥፋት በመንግሥት፣ በማኅበረሰብ በአጋር አካላት ትብብር የተካሄደው እንቅስቃሴ ትርጉም ያለው ውጤት ማስመዝገብ ቢቻልም፣ አሁንም ቢሆን ከ140 ሺሕ በላይ የቲቢ ታማሚዎች እንዳሉ፣ በዓመትም ከ19 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በዚሁ በሽታ ለሕልፈተ ሕይወት እንደሚዳረጉ ነው የተናገሩት፡፡
‹‹ይህም ሆኖ ግን የቲቢ በሽታ ከማጥፋት አኳያ በወሳኝ ደረጃ ላይ እንገኛለን፡፡ ጠንክረን ከሠራንና መልካም ተሞክሯችንን አስቀጥለን የምንንቀሳቀስ ከሆነ በአጭር ጊዜያት ውስጥ የቲቢ በሽታ ታሪክ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ካልሠራን ግን ችግር ሆኖ ይቀጥላል፤›› ብለዋል፡፡