የደች ተመራማሪ በደቡብ ማዕከላዊ ቱርክ፣ ጆርዳን፣ ሶሪያ እንዲሁም ሊባኖስ 7.5 ማግኒቲውድ የሚለካ ርዕደ መሬት (የመሬት መንቀጥቀጥ) ሊደርስ እንደሚችል የተነበዩት ዓርብ ጥር 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ነበር፡፡
ተመራማሪው ፍራንክ ሆገርቢትስ በትዊተር ገጻቸው ያሰፈሩትን ጠቅሶ አልዓረቢያ በድረ ገጹ እንዳሰፈረው፣ ‹‹በቅርቡ ወይም ዘግይቶ በአገሮቹ ከፍተኛ ርዕደ መሬት ይከሰታል›› ያለ ሲሆን፣ ትንበያው ዕውን ሆኖም ከተነበዩዋቸው አገሮች በቱርክና በሶሪያ ከአምስት ሺሕ በላይ ነዋሪዎችን የቀጠፈ ርዕደ መሬት ተከስቷል፡፡
ሚስተር ሆገርቢትስ ርዕደ መሬቱ ከተከሰተ በኋላ እንዳሉትም፣ አሁን በሶሪያና ቱርክ የደረሰው ርዕደ መሬት በ115 ዓ.ም. እና በ526 ዓ.ም. ከተከሰተው ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡

(ስካይ ኒውስ)
በ115 ዓ.ም. በቱርክና ሶሪያ ድንበር በተከሰተው ርዕደ መሬትና ተከትሎም በመጣው ከባድ አውሎ ነፋስ (ሱናሚ) ምክንያት ወደ 260 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸውን ኒውስ ስካይ አስታውሷል፡፡
ይህ ከተከሰተ ከ409 ዓመታት በኋላ ተመሳሳይ ርዕደ መሬት ተከስቶ 250 ሚሊዮን ያህል ሕዝብም ሞቷል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1976 በሰሜን ቱርክ በተከሰተ ርዕደ መሬት አሥር ሺሕ ሕንፃዎች ወድመዋል፣ አራት ሺሕ ሰዎችም ሞተዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በሚከሰተው ርዕደ መሬት የሚጠቁ የሶሪያና የቱርክ አዋሳኝ አካባቢዎች ለክስተቱ ተጋላጭ ተብለው የተለዩም ናቸው፡፡
በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በተለያዩ ዓመታት በተከሰቱ ርዕደ መሬቶች ያጡት ሶሪያና ቱርክ፣ ሰኞ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በገጠማቸው የ7.7 ማግኒቲዩድ ከፍተኛ ርዕደ መሬት እስከ ትላንት ጥር 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ከአምስት ሺሕ በላይ ዜጎች ሞተውባቸዋል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ደግሞ፣ የሟቾች ቁጥር ከ20 ሺሕ በላይ ሊደርስ ይችላል፡፡
እ.ኤ.አ ከ1939 ወዲህ እንዲህ ዓይነት አደጋ ገጥሞን አያውቅም ያሉት የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬይፕ ጣይብ ኤርዶዋን፣ 45 አገሮች ለመርዳት መጠየቃቸውንም ገልጸዋል፡፡
በ1939 በተከሰተው ርዕደ መሬት 33 ሺሕ ያህል ዜጎቿን ያጣችው ቱርክ ለርዕደ መሬት ተጋላጭ ተብለው ከተቀመጡ አገሮች ተርታም ትገኛለች፡፡ በአሁኑ ርዕደ መሬት አሥር ግዛቶቿ የተመቱ ሲሆን 14 ጊዜ ያህል መከሰቱ ተገልጿል፡፡
ከቱርክ በተጨማሪ ሶሪያ በርዕደ መሬቱ የተመታች ሲሆን፣ በጦርነት ለተሰቃየው ሕዝብ ድርብ መከራ ሆኖበታል፡፡ 12 ዓመታት ባስቆጠረው ጦርነት በርካቶች ከአገራቸው ወደ ቱርክና ሌሎች አገሮች ተሰደዋል፡፡ ሞተዋል፣ አካል ጉዳተኛ ሆነዋል፡፡ ቤት ንብረታቸው በቦንብ ጋይቷል፡፡
በሶሪያ በርካታ አካባቢዎች መሠረተ ልማት ወድሟል፡፡ በርካታ ነዋሪዎች በፍርስራሽ ቤት ውስጥ ለመኖር ተገደዋል፡፡ በዚህ ችግር ላይ አገሪቷ ከቱርክ በምትዋሰንባቸው አካባቢዎች በርዕደ መሬት ተመትታለች፡፡
ርዕደ መሬቱ የመታቸው ታጣቂዎች በሚቆጣጠሯቸውና የሶሪያ መንግሥት በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎችን ነው፡፡ በሥራፍው የሚኖሩም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ቤት አልባ ሆነዋል፡፡
መሠረተ ልማቶች በጦርነት በወደሙባት ሶሪያ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መሞታቸውንና መጉዳታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ የተጎዱትን ለመድረስ ግን ፈተና ነው፡፡ በሆስፒታል የገቡ ተጎጂዎችን ለማከም የግብዓትና የቦታ እጥረት ተከስቷል፡፡
አልጀዚራ ያነጋገረው በሶሪያ የኢድሊብ ነዋሪው ኦሎውሽ፣ እርሱ አያቱን ከሕንፃ ለማውጣት በመዘግየቱ ሕንፃው ተደርምሶ እጁ ቢጎዳም ስምንት ልጆቹን ለማዳን ችሏል፡፡ ሆኖም በሕንፃው የነበሩ የሁለት ቤተሰቦቹ አባላት ከሕንፃው መውጣት ሳይችሉ ተደርምሶባቸዋል፡፡
በሶሪያ ‹‹ዋይት ሄልሜትስ›› የሚባሉት የአደጋ ምላሽ ሠራተኞች በፍርስራሽ ሥር የተቀበሩትን ለማውጣት ጥረት እያደረጉ ቢሆንም፣ ቀድሞውኑ በጦርነት የፈራረሰው መሠረተ ልማት ፈተና ሆኖባቸዋል፡፡
በሶሪያ 133 ሕንፃዎች ሙሉ ለሙሉ 272 ደግሞ በገሚስ ወድመዋል፡፡ በርካታ ነዋሪዎችም ሙሉ አገልግሎት ወደማይሰጡ ሆስፒታሎች ገብተዋል፡፡ በቱርክ ብቻ ከ5,600 በላይ ሕንፃዎች ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል፡፡
በሶሪያና ቱርክ የተከሰተው ርዕደ መሬት ከጦርነትና ከተፈጥሮ አደጋ የተረፉትን በጥንታዊ ግዛቶች የነበሩ ታሪካዊ ሐውልቶችንና ቅርሶችን መጉዳቱንም አልጀዚራ ገልጿል፡፡