ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በጦርነት፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ በድርቅና በሌሎች ችግሮች ምክንያት በመፈተኗ የጤና ዘርፉ መጎዳቱ ይታወሳል፡፡ በተለይ በጦርነት ቀጣና ውስጥ በነበሩ ቦታዎች ችግሩ ከፍተኛ እንደነበር ይታመናል፡፡ ይህንንም የጤና ሚኒስቴር የ2015 ዓ.ም. የስድስት ወራት ሪፖርት ያሳያል፡፡
የጤና ሚኒስቴር በ2015 ዓ.ም. የመንፈቅ ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበው ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡
ሪፖርቱም በቀረበበት ጊዜ ቋሚ ኮሚቴው ለሚኒስቴሩ 16 ጥያቄዎችን ያቀረበ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የሥነ ምግብ ሁኔታ ልየታ የተደረገላቸው ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑ ሕፃናት የምግብ እጥረት የተገኘባቸው ምጣኔ ከአገር አቀፍ አማካይ ስምንት ከመቶ በላይ ነው፡፡ ይህ ለምን ሆነ? የሚል ይገኝበታል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ያቀረበውን ጥያቄ በተመለከተ ምላሽ የሰጡት ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት የምግብ እጥረት ምጣኔያቸው ከፍ ያለበት ዋናው ምክንያት በድርቅ፣ በግጭትና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የተጎዱ ቦታዎች ላይ የተሠራው ሥራ ዝቅተኛ በመሆኑ ነው፡፡
በተለይም አፋር፣ ሶማሌና ጋምቤላ ክልሎች ከፍተኛ የምግብ እጥረት የታየባቸው ክልሎች መሆናቸውን የተናገሩት ሚኒስትሯ፣ በእንዲህ ዓይነት ችግሮች ውስጥ የተዘፈቁ ክልሎች ላይ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት በቀጣይ ሰፊ ሥራ የሚሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከፍተኛ የምግብ እጥረትን ለመመለስ አብዛኛው ለምግብ የሚሆኑ ግብዓቶች የሚገኙት ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሲሆን፣ ዓምናም ግብዓቶችን ወደ አገር ውስጥ ከማስገባት አኳያ በተወሰነ መልኩ እጥረት በመኖሩ ችግሩ ሊከሰት ችሏል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ከፍተኛ የሆነ የምግብ እጥረት የተከሰቱባቸው ቦታዎች ላይ ተደራሽ ለመሆን ከኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና ከክልሎች ጋር፣ በዋናነት ደግሞ ከአደጋ ሥጋትና መከላከል ኮሚሽን ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፣ ይህንንም በየጊዜው ለመገምገም ሚኒስቴሩ የራሱ አሠራር ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ለቋሚ ኮሚቴው ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ የኩፍኝ በሽታ ዘመቻ ሲደረግ አብሮ የምግብ እጥረት የገጠማቸው ቦታዎችን የልየታ ሥራ እንደተሠራና ችግሩም በተለያዩ ቦታዎች መኖሩ እንደታወቀ ገልጸዋል፡፡
ከበሽታ መቆጣጠርና መከላከል አንፃር በዋነኛነት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራና በተለይም ኤችአይቪ ኤድስን መቆጣጠርና መከላከል ላይ ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የመለየትና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ሊያ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃም ኤችአይቪ ኤድስን መከላከል፣ መቆጣጠርና የሕክምና አገልግሎቱን ሙሉ ሥራ የሚሠራው በጤና ሚኒስቴር በኩል የተዋቀረ ቡድን መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ትኩረት የሚሹ በሽታዎችን ለመቆጣጠር እየተሠራ ቢሆንም፣ አሁንም እየታየ ያለው ችግር ይህንን ያህል ኤችአይኤቪ ያለባቸው ሰዎች አሉ የሚለውን ለመለየት በግምት በመሥራቱ መረጃውን ማግኘት አልተቻለም ሲሉ ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት ተናግረዋል፡፡
የወባ በሽታን ከመከላልና ከመቆጣጠር አንፃር በርካታ ተግባራት ላይ በዝቅተኛ አፈጻጸም የታየው ለምንድነው? የሚለው ጥያቄም ከቋሚ ኮሚቴው ከቀረቡላቸው መካከል ይገኝበታል፡፡
ሚኒስትሯ እንደገለጹት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የወባ በሽታን ምላሽ ለመስጠት ሚኒስቴሩ ከተለያዩ ክልሎች ጋር በቅንጅት ሲሠራ ቆይቷል፡፡
በተለይም ከመድኃኒት አቅርቦት አንፃር ሰፊ ሥራ መሥራቱን የገለጹት ሊያ (ዶ/ር)፣ በአንዳንድ ቦታዎች ላይም በበሽታው ሳይያዙ ትኩሳት ያለባቸው ሰዎች አስቀድሞ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ወረርሽኙን ለመከላከል በአገር አቀፍ ደረጃ 10 ሚሊዮን አጎበር መሠራጨቱን፣ ማኅበረሰቡም የተሠራጨውን አንጎበር በአግባቡ እንዲጠቀም የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡
በቀጣይ ስድስት ወራትም ወረርሽኙን ለመከላከል ከወረዳ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፣ ተፈጻሚ ማድረጉ የሁሉም ተቋማት ድርሻ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን፣ ከሞት አንፃርም ይህንን ያህል ነው የሚባል አለመሆኑንና የተሻለ ሥራ መሠራቱን አስረድተዋል፡፡
ከሕክምና አገልግሎት ማሻሻያ አንፃር ሰፊ ትኩረት የሚሰጥ መሆኑን ከጤና ኬላ ጀምሮ እስከ መጀመርያ ደረጃ ጤና ሆስፒታል ድረስ ያለውን የሕክምና አገልግሎት ማስፋፋት ላይ ሰፊ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡
የጤና ኬላዎችን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ሊያ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ በጦርነቱ ምክንያት የመሠረተ ልማት ውድመት የደረሰባቸውን የሕክምና ተቋማት በተሻለ ሁኔታ መልሶ ለመገንበት ዕቅድ ተይዟል ብለዋል፡፡
እስካሁንም በሚኒስቴሩ በኩል በዋናነት እየተሠራ ያለው ግብዓትና መሣሪያዎችን በማስገባት ሥራ የማስጀመር ሒደት መሆኑን፣ በቅርቡም ከዓለም ባንክ በተገኘው ድጋፍና ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሊውል የታሰበውን ገንዘብ በጦርነቱ ለተጎዱ የሕክምና ተቋማት ለማዋል ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በዚህ መሠረት በአማራና በአፋር ክልሎች የሚገኙ 142 የሕክምና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም ጨረታ መውጣቱን፣ በቀጣይም በኦሮሚያም ሆነ በትግራይ ክልሎች ላይ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል፡፡