Wednesday, March 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እስቲ አንገፋፋ!

እነሆ መንገድ። ጊዜና ሥፍራ ተጋግዘው በውስንነት ይዘውናል። መፍጠን ያቃተው ‘የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም’ እያለ እጁን ሰጥቶና አንገቱን ደፍቶ ይራመዳል። ስለደጉ ጊዜ ይዘምራል፡፡ ክፉውን ይኮንናል። ጊዜን የቀደመው ደግሞ በእጆቹ ሥራ ኮርቶ ይጀግናል፡፡ አንዳንዱም ሰው ከማያየው ህሊናው ጋር እየተሟገተ፣ ‘የፍጥነት እንጂ የጊዜ ጀግና የለውም ያለው ሳይንቲስት ለዘለዓለም ይኑር’ እያለ በወኔ ይጣደፋል። በመሀል በጊዜም በፍጥነትም ነገር ያልገባው ቀኔም፣ ውሎዬም፣ ስሜም፣ እኔም እንደተጻፈልኝ እንጂ እንደምጽፈው የምኖረው አይደለም በሚል ስሜት፣ የሚያየውንና የማያየውን ለአንድ ታላቅ አምላክ አስገዝቶ ውረድ ሲሉት ይወርዳል፣ ተሳፈር ሲሉት ይሳፈራል። አይስቅም፣ አያለቅስም፣ አይደሰትም፣ አያዝንም። ይህም እንደ ተጻፈለት እንጂ እንደ ጻፈው አይደለምና። ከላይ ሰማይ አለ። ከሰማዩ በታች አልፎ አልፎ ደመና፣ አልፎ አልፎ ብርሃን፣ አልፎ አልፎ ጨለማ፣ ከአልፎ አልፎዎቹ በታች ተራራ፣ ወንዝ፣ ባህርና የብስ አለ። ሁሉም አሉ!

በወንዞቹ፣ በተራራዎቹ፣ በየብሳቱ መካከል ክልልና ኬላ፣ ከተማና ገጠር፣ ቀበሌና መንደር አሉ። አንዳንዱ የተጨናነቀ፣ አንዳንዱ ነፃ የሆነ መንገድ መኖሩ ሳይዘነጋ። አንዳንዱ ሕይወት፣ ትዳር፣ እምነት፣ ፅናት የሚያፈርስ ሌላው የልኬቱን ብቻ ታሪፍ የሚቀበል ጎዳና። ከእዚህ ጎዳና በአንዱ እንደ አበቃቀላችንና ኑሯችን የማናምን ተሰብስበን ታክሲ ይዘናል። አቀማመጣችን በሒሳባዊ ቀመር መገለጽ ቢችል ወይም ባይችል የማንደነግጥ የማንደመም፣ ብቻ ወያላው ‘ዛሬ ሒሳብ በእኔ ነው’ ቢለን ጮቤ የምንረግጥ ታካች መንገደኞች ነን። በቅርበትና በርቀት ከአዕምሮአችን በላይ በሆኑ ጥበቦችና ሐሳቦች ከተሠራው ዓለማችን በላይ ተጋፍተን ወንበር መያዛችን የሚያስፈነድቀን ምስኪን የሕይወት እስረኞች ነን። መንገድ የሌለበት የለምና ከደመናው በላይ ባንጓዝ ከደመናው በታችን መጓዝ አላቋረጥንም። መንገድ ውሎ ይግባና!

“ሾፌር ንዳዋ ጊዜያችንን ገደልከው እኮ…” ጋቢና የተቀመጠ ወጣት ሾፌራችንን ይጠዘጥዘዋል። “ምን ጊዜ አለ ደግሞ እዚህ አገር?” አለው ከጎኑ የተቀመጠ ሌላ ተሳፋሪ። “እንዴት?” ግራ ተጋብቶ ዞሮ አየው። ሾፌሩ ወያላውን እየጠቀሰ ትርፍ እንዲጭን ያበረታታዋል። “ኧረ ተወኝ አንዳችንም የለንም…” መለሰ ‘ምን ጊዜ አለ’ ባዩ። “ከማንና ከማን?” ጠየቀው የቸኮለው ወጣት። “ከጊዜና ከእኛ አንዳችን እዚህ አገር ላይ የለንም ብዬ ነው የማምነው…” አለው ኮስተር ብሎ ሐሳቡን ለምጡቅ የፊዚክስ ሊቅ እንደሚያቀርብ  ታታሪ ተማሪ። “ታዲያ እንደ እሱ አትለኝም። መጀመርያውኑም ‘ብዬ ነው የማምነው’ ብለህ ሐሳብህን አቅርበህ ቢሆን ኖሮ ይኼው ገና አሁን ቁርሴን በልቼ ከመውጣቴ ደንግጬ ረሃብ አይሰማኝም ነበር…” አለ በጎን ሾፌሩን እንሂድ እያለ እየወተወተው። እህህ…!

“አልገባኝም…” አለው ደግሞ በተራው ያኛው ግራ ተጋብቶ። “ጊዜ የሚባል ነገር እኛ ዘንድ የለም አልክ። ቀጠልክና ወይ እኛ ወይ እሱ አንዳችን የለንም አልከኝ። ማስረጃ ያለህ መስሎኝ ደግሞ ምን ተዓምር አመለጠኝ ብዬ እህ ብዬ ሳዳምጥም አገር፣ ጊዜና ሕዝብ የመገነጣጠል መላምታዊ ሐሳብህ በእምነት ላይ እንደ ተመሠረተ ነገርከኝ። እንኳን በተጨበጠ የፍጥረት ሕግና ቁጥር ላይ አልተመሠረተ እንጂ፣ በሐሳብና በእምነት ላይ የተመሠረተ የመነጠልና የመገንጠል ቲዮሪ ፍርኃት አይዞህ ለቆናል…” እያለ የባሰ ግራ አጋባው። “ማነው ስለአንቀጽ 39 የሚያወራው?” ብሎ ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጠ ሳቂታ ሰውዬ ጣልቃ ሲገባ፣ “ምናለበት አንቀጽ መቁጠሩን ትታችሁ ዕድሜያችሁን ብትቆጥሩ? አዳሜ ከ39 ዓመት በላይ መቁጠር በማይፈልግበት አገር አሁንም አንቀጹ ላይ ነው?” ብላ ከሰውዬው አጠገብ የተሰየመች ወጣት ሳቀች። እንዲያው የአንዳንዱን ሳቅ ዓይነት ለመግለጽ የሆነ የሳቅ መለኪያ ‘ዩኒት’ በኖረ ያስብላል፡፡  አንዳንዴ!

ወያላው ሒሳቡን ሰብስቦ መልስ ያከፋፍላል። መጨረሻ ወበር የተየሰመ ወጣት ስለሰብዓዊነት ያብራራል። “ሌላው ቢቀር ጓደኛዬ ሠፈር ውኃ የለም እያልን እኛ ሁለት ሰዓት ሙሉ ሻወር ስንወስድ ትንሽ አናፍርም?” አለ። “ማነን እኛ?” አለች መሀል መቀመጫ ላይ ወይዘሮዋ። “ኧረ ቆይ ተይው፣ አሁን ይኼን ከሰብዓዊ አስተሳሰብ ጋር ምን ያገናኘዋል? ውኃ የሚጠፋው ስለማያልፍልን። ሻወር የምንወስደው ስላለፈልን። ቆይ  ምን ለማለት ነው?” ብሎ ሦስተኛው ረድፍ ላይ አጠገቤ የተሰየመው ጎልማሳ አፈጠጠበት። “በሉ ተውት ውኃ በፈረቃ ሲዳረሰን ያልተጣላን ሰዎች በሻወር ልንጣላ ነው?” ሲል አንዱ፣ “ካላችሁስ ዘመኑ ብዙ ሻወር የሚያስወስድ ነው…” አለ ሌላው። “እንዴት?” ሲባል “ታጥቦ የማይጠራው በዝቷላ። ተነግሮት የማይለወጠው፣ ተመክሮ የማይሰማው፣ ተለምኖ የማይራራው እኮ ነው መንገዱን አጓጉል እያደረገ ፍዳችንን የሚያሳየን። ዛሬ ብንነቃ ነገ ፈዘን እንውላለን። እውነቱና ሀቁ እዚህ አፍንጫችን ሥር ተኝቶ አናስተውለውም። ሙሰኛው አጠገባችን እየበላ እየጠጣ ቆይቶ ጋባዥ እኛው ነን። እንዲያው በአጠቃላይ አይደለም የአሥር ደቂቃ የ24 ሰዓት ሻወር ብንወስድ ያንሰናል?” ብሎ እንዳበቃ፣ “የምሩን ነው? በውኃ እጥረትና በመዋጮ ባበደች አገር ተቀምጦ 24 ሰዓት ሻወር ሲል አያፍርም?” ይለኛል። ወዬው በሆነልና ውኃው በባከነ ብዬ በልቤ ዝም። አያሰኝም እንዴ? የውዝግባችን ብዛቱ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡት ወጣቶች መካከል ስለሰብዓዊነትና ስለመተዛዘን ሲሰብክ የነበረው ወራጅ ብሎ አስቆመ። ሲወርድ መሀል መቀመጫ በአነጋገር ዘዬዋና በቀናነቱዋ ቀልባችን ስትስብ የቆየች አንዲት ምስኪን ሠርቶ አዳሪን ረገጣት። “ኧረ ኡኡኡኡ! ኧረ ገደለኝ እናንተ! ኧረ እኔስ እንጃልኝ ወዬው! ወዬው!” እያለች አቀለጠችው። ተሳፋረዎች ከመደንገጥና ምንሆንሽ ከማለት ይልቅ ባደገችበት ሥፍራ ባህልና የቋንቋ አገላለጽ ልማድ አጋና ስታቀርበው፣ እንደ ቴአትረኛ ፈዘው እያዩዋት በሳቅ አሽካኩ። እሷም አፍራ በነጠላዋ ዓይኗን ሸፈነች። ያ ቆሞባት የነበረው ወጣት ግን መለስ ብሎ ‘እኔን’ ሳይል ‘ይቅርታ’ ሳይል ቀጥ ብሎ ሄደ። “አይዞሽ…” አለች ወይዘሮዋ። “ኧረ እኔስ ተርፌያለሁ እሱ ነው እንጂ ቀደም እንዲያ ሲደሰኩር እንዳልነበር እንደ ሰባ ኮርማ መለስ ብሎ ሳያየኝ የሄደው። ኧረ! ወይ አዲስ አበባ አያ!” እያለች ንፅፅር ጀመረች። “እንዴ ቅድም እንዲያ ስለሰውና ሰብዓዊነት ሲደሰኩር እንዳልነበር ምናለበት አሁን ቢያንስ ትዝብቱን ፈርቶ ይቅርታ ብሏት ቢወርድ?” ወይዘሮዋ ነገር ለኮሰች። ልማዳችን ነው!

“ካወራን አይበቃም ብለሽ ነው። ዘመኑ እኮ የወሬ እንጂ የተግባር አይደለም። ከማን አንሼ ‘በቶክ’ ሆኗል። እንጂ ሥራ ድሮ ቀረ…” እያለ አንዱ ነገር ማቀባበል ጀመረ። “ያም ሆነ ይህ ቃል የእምነት ዕዳ ነው። መቼም ልናበዛው፣ ልናሳንሰው እንችላለን እንጂ ምንም ነገር ሳናምንበት አናወራም። አይደለም እንዴ?” ሲል ጎልማሳው “ተወው እሱን። ዘንድሮ ከልብ ሳይሆን ምላስ ላይ ያለውን ብቻ ነው የእኛ ሰው የሚያወራው። ለዚያም እኮ ነው በተግባር የማያሳየውን ነገር ሲዘባርቁ መዋል የበዛው። ሙስና በል የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ ፍትሕ ሆነ የዴሞክራሲ ዕጦት፣ መገንጠልና መገነጣጠል ሳይቀሩ ላያችን ላይ የሚጨፍሩት በዚህ ምክንያት እኮ ነው፡፡ ስንትና ስንት የአገር ሸክም በእኛው በግለሰቦች ደረጃ ሊቃለሉ የሚችሉ እያሉ፣ ወሬያችንና ትችታችን እንዳበቃ ሀሞታችን ይፈሳል። ደግሞ ለሌላ የቃል የዲስኩር ሀሜትና ትችት አጠራቅመን እንመለሳለን…” ብሎ ከመጨረሻዎቹ አንዱ የልቡ እስኪደርስ አወራ። ወያላው “መጨረሻ” ብሎ በሩን ከፈተው። እኛም ‘የወሬ ማብቂያ የተግባራዊነት መጀመርያ ዘመን የትኛው ፌርማታ ላይ ይሳፈርብን ይሆን?’ እየተባባልን ወረድን። አንዳችን በሌላችን ላይ እያላከክን ዘመኑ እንዴት ይገፋ ይሆን? ያ ወጣት እንዳለው አንድ አገር ውስጥ ሆነ ማዶ ለማዶ መሆናችን አይገርምም? እስቲ አንገፋፋ! መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት