Wednesday, March 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚቆጠጠር ገለልተኛ ተቋም ለመመሥረት እንቅስቃሴ ተጀመረ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • 70 በላይ አዳዲስ የፋይናንስ ተቋማት ዘርፉን ሊቀላቀሉ ነው

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኢንሹራንስ ዘርፍ ላይ ቁጥጥርና ክትትል እንዲያደርግ በሕግ የተሰጠውን ሰልጣን በማሻሻል፣ የኢንሹራንስ ዘርፉ ከብሔራዊ ባንክ ውጪ ራሱን በቻለ ገለልተኛ ባለሥልጣን ቁጥጥር እንዲደረግበት ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀመረ።

በዚህም መሠረት የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚቆጣጠርና የሚከታተል ገለልተኛ ተቋም ለማቋቋም አማካሪ ተቀጥሮ ሥራ መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል። ይህ ሥራ ተጠናቆ ተቋሙ ከተመሠረተ በኋላም የኢንሹራንስ ዘርፍ ለውጭ ኩባንያዎች ውድድር ክፍት እንደሚሆን ታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሰሞኑን እንዳስታወቀው የኢንሹራንስ ሪጉላቶሪ ኤጀንሲ ራሱን የቻለ ገለልተኛ ኤጀንሲ እንዲኖረው በመንግሥት በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት ኤጀንሲውን ለማቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን በተመለከተ ትኩረት ተሰጥቷቸው ከሚሠሩ ጉዳዮች አንዱ ይኸው የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ ኤጀንሲ ማቋቋም መሆኑን፣ ሥራውንም ከአማካሪና ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በመሆን እየሠሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ 

ይህ ሥራ ተጠናቆ ኤጀንሲው ከተቋቋመ በኋላ የውጭ ኩባንያዎች በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ እንዲገቡ የሚያስችሉ ፖሊሲዎች ፀድቀው ዘርፉ ለውጭ ኩባንያዎች እንደሚከፈት ገልጸዋል፡፡ 

የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ እንዲገቡ እንደተፈቀደው ሁሉ ለኢንሹራንስ ዘርፉም ሊከፍት ይገባል በሚል የሚቀርበው ተደጋጋሚ ጥያቄ አግባብ ቢሆንም መጀመርያ ሊሠሩ የሚገባቸው ሥራዎች ስላሉ ይህ ከተጠናቀቀ በኋላ ቀጣዩ ዕርምጃ በዘርፉ የውጭ ኩባንያዎችን መጋበዝ ይሆናልም ተብሏል፡፡

እንደ አቶ ሰለሞን ማብራሪያ የኢንሹራንስ ተቆጣጣሪ ኤጀንሲው ሳይቋቋም የውጭ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ የማይፈቀድ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ 

በጉዳዩ ዙሪያ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ‹‹ሁለት ነገር በአንዴ አንሠራም፣ አንዱን ሠርተን ነው ወደ ሌላ የምንሄደው፤›› ብለዋል። የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚቆጣጠር ገለልተኛ ኤጀንሲ ከተቋቋመ በኋላ የውድድር ስትራቴጂ እንደሚዘጋጅ ጠቅሰው ‹‹በዚህም ራሳችን አዘጋጅተን ሌላውን እንጋብዛለን›› ብለዋል፡፡ እንዲህ ያለውን ቅድመ ተከተል ለመጠበቅ እንጂ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው መከፈት ያለበት ትልቅ ገበያ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በሥራ ላይ ከሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት በተጨማሪ 71 የሚሆኑ አዳዲስ የፋይናንስ ተቋማት ኢንዱስትሪውን ለመቀላቀል እንቅስቃሴ ውስጥ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል፡፡ በሥራ ላይ የሚገኙት የፋይናንስ ተቋማት ጤናማ ሆነው እየተጓዙ ስለመሆኑም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ ገልጿል፡፡ 

የአገሪቱን ወቅታዊ የፋይናንስ ተቋማት አቋምና የ2015 የሒሳብ ዓመት የግማሽ ዓመት አፈጻጸማቸውን በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያቀረበው ሪፖርት እንዳመለከተው በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ያሉ የፋይናንስ ተቋማት ቁጥር 109 ደርሷል፡፡ ይህ የፋይናንስ ተቋማት ቁጥር ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ በ27 በመቶ ብልጫ ያሳየ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ የግማሽ ዓመቱን ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንዳስታወቁትም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሚቆጣጠራቸው 109 የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ በቅርቡ ከብድር ቁጠባ ተቋምነት ወደ ባንክ ሥራ የተሸጋገሩትን አምስት ባንኮች ጨምሮ 31ዱ ባንኮች ናቸው፡፡ አሥራ ስምንቱ ደግሞ የኢትዮጵያ የጠለፋ መድን ኩባንያን ጨምሮ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሲሆኑ፣ 44ቱ ደግሞ አነስተኛ የብድርና ቁጠባ ተቋሞች መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ቀሪዎቹ የፋይናንስ ተቋማት ተብለው ከተመዘገቡት ስድስቱ የካፒታል ዕቃዎችና ሊዝ ፋይናንሲንግ፣ ሰባት የክፍያ ሥርዓት አንቀሳቃሾች (ፖይመንት ሲስተም ኦፕሬተርስ)፣ ሁለት የክፍያ አገልግሎት ሰጪ (ፔይመንት) ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሌላ በተለያዩ ዘርፎች የሚሠሩ 2,794 የኢንሹራንስ አገናኞችና ተያያዥ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ኩባንያዎች እንዳሉም ተጠቅሷል፡፡

ከእነዚህ የፋይናንስ ተቋማት ሌላ አሁንም የፋይናንስ ዘርፉን ለመቀላቀል ዝግጅት እያደረጉ ያሉ ተቋማት ከፍ ባለመጠን እየመጡ ስለመሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡  

ከሰሞኑ በቀረበው ሪፖርት ለመረዳት እንደሚቻለው፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ለማግኘት ጥያቄ ያቀረቡና በምሥረታ ላይ ያሉ 71 ኩባንያዎች ያሉ መሆኑን ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ስምንቱ አዳዲስ ባንኮች ሲሆኑ፣ 54ቱ ደግሞ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ናቸው፡፡ ዘጠኝ በፔይመንት ሲስተምና ኦፕሬተር ሥራ ላይ ለመሰማራት የብሔራዊ ባንክን ፈቃድ እየተጠባበቁ ነው፡፡ በኢንዱስትሪው ውስጥ የሚገኙት 109 የፋይናንስ ተቋማትን ወቅታዊ እንቅስቃሴ የሚያሳይ በአኃዝ የተደገፈ ሪፖርትም ቀርቧል፡፡ 

የፋይናንስ ተቋማቱን አጠቃላይ ዕድገት ማሳያ ተብለው ከተጠቀሱት ዋና ዋና ክዋኔያቸው መካከል፣ የቅርንጫፎቻቸውን ቁጥር በየጊዜው እያሳደጉ መሆናቸው አንዱ ነው፡፡ የቅርጫፎቻቸው ቁጥር 12,034 ደርሷል፡፡ ይህ የቅርንጫፎች ቁጥር ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ 24 በመቶ ዕድገት ያሳየ መሆኑን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 10,225 የባንክ ቅርንጫፎች፣ 717 የኢንሹራንስ፣ 1,038 የአነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋሞች ሲሆኑ፣ 54ቱ ደግሞ የሊዝ ፋይናስንግ ቅርንጫፎች ናቸው፡፡ በግማሽ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የባንኮች የብድርና የቁጠባ ተቋማት የቁጠባ ሒሳብ የከፈቱ ደንበኞቻችን ቁጥር ከአገሪቱ የሕዝብ ቁጥር በላይ ስለመሆኑ የሚያመለክት ሆኗል፡፡ አቶ ሰለሞን እንደገለጹትም እጅግ በሚያስገርም ሁኔታ የቁጠባ ሒሳብ ቁጥር በ551 በመቶ አድጎ 122.31 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ የአስቀማጮች ቁጥር በዚህ ደረጃ ለመገለጹ አንዱ ምክንያት አንዳንድ ደንበኞች ሁለትና ከሁለት በላይ የቁጠባ ሒሳብ ያላቸው ከመሆን ጋር ይያያዛል፡፡ ሆኖም የባንኮች ተደራሽነት ከፍ እያለ መምጣቱን ያሳያል ተብሏል፡፡

 122.31 ሚሊየን ከሚሆኑት ቆጣቢዎች ውስጥ አብላጫውን እጅ የያዙት ባንኮች ሲሆኑ፣ በሒሳብ ዓመቱ ግማሽ ዓመት መጨረሻ ላይ ሁሉም ባንኮች ያላቸው የቁጠባ ሒሳብ ደንበኞች ቁጥር 117.6 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 23.11 ሚሊዮን የሚሆነውን ደግሞ በቅርቡ ወደ ባንክ ያደጉት የአምስቱ ተቋማት ድርሻ ሲሆን፣ የአነስተኛ የብድርና የቁጠባ ተቋማት ቆጣቢዎች ደግሞ አራት ሚሊዮን መሆኑ ተብራርቷል፡፡

የ109ኙን የፋይናንስ ተቋማት የሀብት መጠን በተመለከተ እንደተገለጸውም፣ የፋይናንስ ተቋማት አጠቃላይ የሀብት መጠን 2.9 ትሪሊዮን ደርሷል፡፡ ይህ የሰላሳ በመቶ ዕድገት የታየበት ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ የባንኮች የሀብት መጠን 2.8 ትሪሊዮን ብር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ወደ ባንክ ያደጉት አምስቱ ተቋማት ድርሻ 0.09 ትሪሊዮን ብር መሆኑ ታውቋል፡፡ የኢንሹራንስ ኩባያዎች የሀብት መጠን 0.04 ትሪሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የአነስተኛ የብድር ተቋማት ደግሞ 0.05 ትሪሊዮን ብር ነው፡፡ የካፒታል ዕቃዎች ሊዝ ካምፓኒ ደግሞ 0.02 ትሪሊዮን ብር ሀብት አላቸው ተብሏል፡፡

የተቀማጭ ገንዘብ ከማሰባሰብ አንፃር አጠቃላይ የኢትዮጵያ ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት ያሰባሰቡት ተቀማጭ ገንዘብ በ33 በመቶ አድጎ ሁለት ትሪሊዮን ደርሷል፡፡ ከዚህ ተቀማጭ ውስጥ የባንኮች ድርሻ 1.98 ትሪሊዮን ብር ሲሆን፣ የአነስተኛ የፋይናስ ተቋማት ደግሞ 0.02 ትሪሊዮን ብር ነው፡፡ ባንኮች ከደረሱበት የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ውስጥ አምስቱ ወደ ባንክ ያደጉ ተቋማት 0.05 ትሪሊዮን ብር ድርሻ ይዘዋል፡፡ 

ቦንድን ጨምሮ የተሰጠው የብድር መጠን አውትስታንዱ 1.9 ትሪሊዮን ነው፡፡ ይህም 31 በመቶ አድጓል፡፡ የባንኮች 1.98 ትሪሊዮን ብር ነው፡፡ የአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ደግሞ 0.03 ትሪሊዮን ብር ነው፡፡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ደግሞ 0.03 ትሪሊዮን ብር ነው፡፡ 

እነዚህ የፋይናንስ ተቋማት በካፒታል ደረጃም ዕድገት የታየባቸው ስለመሆኑ የሚያመለክተው፣ የግማሽ ዓመቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሪፖርት የፋይናንስ ተቋማቱ የካፒታል መጠን በ32 በመቶ አድጎ 249.2 ቢሊዮን ብር መድረሱን ይጠቅሳል፡፡ ከዚህ ካፒታል መጠን ውስጥ የባንኮች ካፒታል 220 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ 18ቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ደግሞ ያስመዘገቡት ካፒታል 14.8 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የአነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማትም 12.12 ቢሊዮን ካፒታል አስመዝግቧል፡፡ ስድስቱ የሊዝ ፋይናንሲንግ ኩባንያዎች ደግሞ ያስመዘገቡት ካፒታል መጠን 2.3 ቢሊዮን ብር መድረሱ ታውቋል፡፡  

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ ለውጥ ታይቶበታል ተብሎ የሚታነው የፋይናንስ ተቋማት በተለይ ባንኮች በዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎት ዕድገት ነው፡፡ እስከ ግማሽ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ባንኮች በዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎት በ149 ሚሊዮን ትራንዛክሽን ያደረጉ ሲሆን፣ በዚህም 1.4 ትሪሊዮን ብር መንቀሳቀስ ተችሏል፡፡ በዚህ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ደግሞ 104 ሚሊዮን እንደነበር ተገልጿል፡፡ ይህ ትልቅ እመርታ ስለመሆኑ የገለጹት አቶ ሰለሞን፣ በዲጂታል ባንኪንግና ተያየዥ አገልግሎቶች ዙሪያ የአገሪቱ ባንኮች ወደኋላ ቀርተዋል የሚለው፣ ያለ መረጃ የሚሰጠው አስተያየት ትክክል ያለመሆኑንና ትልቅ ለውጥ መኖሩን የሚያሳይ ነው ብለውታል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በቴሌ ብርና በዲጂታል የባንክ አገልግሎት የማክሮ ብድርን እያቀረቡ ያሉ ባንኮች በድምር የሰጡት ብድር 1.17 ቢሊዮን ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ የዲጂታል የባንክ አገልግሎት፣ የብድር ሥርጭት በማስፋቱ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው ተብሏል፡፡ በቴሌ ብርና የዲጂታል ማክሮ የብድር አገልግሎት በመጠቀም የብድር ተጠቃሚዎች የሆኑ ዜጎች ቁጥር ከ670 ሺሕ በላይ መድረሱ ከፍተኛ እመርታ ነው ተብሏል፡፡ የማክሮ ክሬዲት እያደገ ከመጣ የፋይናንስ ተደራሽነትን በእጅጉ ያሻሽሏል የሚል ተስፋ እንዳለ ተጠቁሟል፡፡ 

በአገሪቱ ውስጥ የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ ሌላው ዕድገት የታየበት ነው የተባለው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ነው፡፡ ከአቶ ሰለሞን ገለጻ መረዳት እንደተቻለው፣ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮችና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ስድስት ደርሰዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አራቱ ባንኮች ሲሆኑ፣ ሁለቱ ማክሮ ፋይናንስ ተቋማት ናቸው፡፡ አገልግሎቱ በመስኮት ደረጃ የሚሰጡ ተቋማት 15 መድረሳቸውን ከእነዚህ ውስጥ ዘጠኙ ባንኮች ናቸው፡፡ አራቱ ኢንሹራንስ፣ ሁለቱ ደግሞ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ናቸው ተብሏል፡፡ 

እስከ ሒሳብ ዓመቱ አጋማሽ ድረስ በእነዚህ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ከሚሰጡ ባንኮች 14.35 ሚሊዮን ከወለድ ነፃ የቁጠባ ደብተር የከፈቱ ደንበኞችን በማፍራት 163.5 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ችለዋል፡፡ 

ከወለድ ነፃ ከተሰባሰበው ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ ፋይናንስ የተደረገው (ለብድር) የዋለው የገንዘብ መጠን ግን 63.31 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው፡፡ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የብድር ተጠቃሚዎች 39.451 ብቻ ነው፡፡ አቶ ሰለሞንም ከተሰበሰበው ተቀማጭ ገንዘብ አንፃር ፋይናንስ የተደረገው አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን በከፍተኛ ደረጃ ሊያድግ የሚገባው ዘርፍ በመሆኑ አሁንም ሊሠራበት ይገባል ተብሏል፡፡ 

የምክትል ገዥው ጥቅል መልከታ አንዳንድ ችግሮች ቢኖሩም፣ የኢትዮጵያ የፋያናንስ ተቋማት ጤናማ ሆነው ስለመቀጠላቸው አስታውቀዋል፡፡ 

የባንኮቹን አፈጻጸም በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱም፣ ‹‹በአጠቃላይ ሲታይ የፋይናንስ ዘርፉ በእርግጥም ጤናማ ነው፤› ብለዋል፡፡

አያይዘውም፣ የፋይናንስ ዘርፉ ጤናማ ቢሆንም በእርግጠኝነት ወደ ዝርዝር ጉዳዮች ገብተን እያንዳንዱን ባንክ በተናጠል ብናይ ብዙ ችግሮችን ማየት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡ ለምሳሌ የአሴት ኳሊቲን በተመለከተ ብዙ ልናያቸው የምንችላቸው ነገሮች አሉ ያሉት አቶ ማሞ፣ የብድር ሥርጭት ላይ የሚታዩ ችግሮች እንዳሉም አመልክተዋል፡፡ 

ከዕቅድ ግንባታ አንፃር ብሔራዊ ባንክ ብቻ ሳይሆን ለባንክ ዘርፉ የአቅም ግንባታ ጉዳይ ትልቅ ሥራ እንደሆነ መታየት አለበት፡፡ ከኮርፖሬት ገቨርናንስም አንፃር መታየት ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ የጠቀሱት አቶ ማሞ፣ ስለዚህ ጠቅላላ ካለው ምዘና ባሻገር የእያንዳንዱን ባንክ ጉዳይ ስናይ ብዙ ችግሮች መኖራቸውንና ብዙ ልናስተካክላቸውና ልንበረብራቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንዳሉ ማስተዋል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ‹‹በአጠቃላይ በእኔ ዕይታ ፋይናንስ ዘርፉን በተመለከተ ‹‹ምን ዓይነት አፕሮች መከተል አለብን?›› የሚለውን ጉዳይም መዳሰስ እንደሚገባና አዲስ ዕይታ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች