Wednesday, March 29, 2023

ጥቁር የመልበስ ውዝግብና የእምነት ነፃነት በኢትዮጵያ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኅዳር ወር ላይ በፓርላማ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፣ የሰላምና የጦርነትን ምንነት በሰፊው አውስተው ነበር፡፡

‹‹የሰላም መጥፎ የለውም፡፡ እያሸነፍክ ቢሆን እንኳ የጦርነት ጥሩ የለውም፡፡ ምክንያቱም በጦርነት ሁልጊዜ ሕይወት ብቻ ሳይሆን ሀብትና ንብረትም ማውደም አለ፤›› በማለት ነበር የተናገሩት፡፡

የናፖሊዮንን ‹‹ሰላም ከፈለግክ ትግልህን ጥይት ከመጮሁ በፊት አድርገው፤›› የሚል ንግግር በመዋስ ማብራሪያቸውን የቀጠሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በሰላም ችግሮችን ለመፍታት መንግሥታቸው ሁሌም የቅድሚያ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ነበር አበክረው የገለጹት፡፡

‹‹ሰላም ማለት የጦርነት አለመኖር ብቻ አይደለም፡፡ ሰላም ማለት የሕግና ሥርዓት መከበር ማለት ነው፡፡ ተኩስ ባይኖር እንኳ ሕግና ሥርዓት የማይከበር ከሆነ የሰዎች ሰላም ከሞላ ጎደል ይናጋል፤›› በማለት የተናገሩት ዓብይ (ዶ/ር)፣ የጥይት ድምፅን ከማስቆም እኩል ሕግና ሥርዓትን ማስከበር ለሰላም እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በሰፊው ገልጸው ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ቢሉም የሕግና ሥርዓት ማስከበር ጉዳይ ግን፣ በኢትዮጵያ በበርካታ ችግሮች የተተበተበ መሆኑን ብዙዎች ይገልጻሉ፡፡ መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት ሕግና ሥርዓት ማስፈን አቅቶታል የሚለው ጠንካራ ትችት አሁንም በስፋት ይሰማል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ሕግና ሥርዓት ማስከበር ተብለው በመንግሥት የሚወሰዱ ዕርምጃዎች፣ ከታለመው በተቃራኒ የተጨማሪ ግጭትና ውዝግብ ምንጭ  እየሆኑ ነው የሚል ስሞታም ይቀርባል፡፡

መንግሥት ሕግና ሥርዓት አስከብራለሁ ብሎ የወሰዳቸው ዕርምጃዎች አላስፈላጊ ውዝግብ የቀሰቀሱበት አጋጣሚ በርካታ መሆኑ ይወሳል፡፡ ለአብነት ያህል በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ንፁኃን ዜጎች ላይ ጥቃት ስለመፈጸሙ፣ የጅምላ እስራትና እንግልት እያጋጠመ ነው መባሉ መንግሥት ላይ  ተጨማሪ ጫናዎችን የፈጠረ ጉዳይ እንደነበር ይነሳል፡፡

በኦሮሚያ ክልልና በአንዳንድ አካባቢዎች መንግሥት ሕግ ለማስከበር የሚወስዳቸው ዕርምጃዎች መተቸታቸው የተለመደ ነው፡፡ ሰርጎ ገብ ጥቃቶችን ለመከላከልና ወንጀለኞችን ለማደን በሚል ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ መንገድ የተከለከሉ የክልል መንገደኞች ጉዳይም፣ በሕግ ማስከበር ስም የተፈጠረ ችግር በሚል ይገለጻል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ከሰንደቅ ዓላማ፣ ከምልክትና ከመዝሙር  ጋር በተያያዘ በየጊዜው የሚነሱ ችግሮችና ዕርምጃዎች ተጨማሪ ውዝግብ ሲያስከትሉ መታየቱ በማሳያነት ይጠቀሳል፡፡

ከሰሞኑ በተለይ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ችግር ደግሞ ሌላ ገጽ ያለው ውዝግብ አስነስቷል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ ባዘዘው መሠረት በፆመ ነነዌ ወቅት የእምነቱ ተከታዮች ጥቁር በመልበስ በፆምና ፀሎት እንዲያሳልፉ የተላለፈው ሃይማኖታዊ ትዕዛዝ በመንግሥት አካላት በበጎ የታየ አይመስልም፡፡

አንዳንድ የመንግሥት ድርጅቶች ሠራተኞቻቸው ጥቁር እንዳይለብሱ እያዘዙ እንደነበር በማኅበራዊ የትስስር ገጾች በምሥል ተደግፎ ሲቀርብ ነበር፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች ጥቁር በመልበሳቸው ወደ ቤት ተመለሱ መባላቸው በሰፊው እያነጋገረ ነው፡፡ በማስታወቂያ ሰሌዳዎችና ደብዳቤዎች የተላለፉ ጥቁር መልበስ ክልክል መሆኑን የሚጠቅሱ ትዕዛዞች ሰፊ የመነጋገሪያ ጉዳይ ሆነዋል፡፡

በአዳማ ማሪያም ቤተ ክርስቲያን በራፍ የቆሙ ፖሊሶችና የፀጥታ ኃይሎች ጥቁር የለበሱ የእምነቱ ተከታዮችን ወደ ቤተ ክርስቲያን አትገቡም ብለው ሲመልሱ በቪዲዮ ተቀድቶ መሠራጨቱ አስገራሚ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለሦስት ቀናት ማለትም ከሰኞ ጥር 29 እስከ ረቡዕ የካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. በሚኖሩት የፆመ ነነዌ ቀናት፣ ምዕመናን ጥቁር ልብስ ለብሰውና መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው በአብያተ ክርስቲያናት በቀን ለሰባት ጊዜ በሚደረጉ የፀሎት ሥነ ሥርዓቶች እንዲሰባሰቡ መመርያ አስተላልፎ ነበር፡፡

በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከባድ አደጋ እንደገጠማት የገለጸው ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ የሦስቱ ቀናት የጥቁር መልበስና የፆም ሥነ ሥርዓት ቤተ ክርስቲያኒቱ ያዘዘችው የንሰሐ ፆም ወይም የአስቸኳይ ጊዜ ንስሐ ፆም መሆኑን በመግለጫው አመልክቶ ነበር፡፡

‹‹የሚመቻችሁ በቀን ሁለቴም አንዴም ቤተ ክርስቲያን በመገኘት፣ የማይመቻችሁም በያላችሁበትና በየምትኖሩበት ትዕዛዙን አክብራችሁ የፀሎት ሥነ ሥርዓቱን አካሂዱ፤›› ይላል የቅዱስ የሲኖዶስ መግለጫ፡፡

ከዚህ ውጭ መፈክር ማሰማት፣ የግል መልዕክት ማስተላለፍም ሆነ ከፀሎት መጻሕፍት ውጪ ይዞ መገኘት በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ገልጾ ነበር፡፡

ይህንን የቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪ ተከትሎ በርካቶች ጥቁር ልብስ ቢለብሱም፣ ነገር ግን በመንግሥት አካላት የተለያየ ክልከላ ሲደረግ ነው የታየው፡፡ ይህ ደግሞ ለምንና በምን አግባብ የሚሉ የሕግ ክርክሮችን እያስነሳ ነው የሚገኘው፡፡

ይህን በሚመለከት ማብራሪያ የሰጡት የሕግ ባለሙያና የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ መሱድ ገበየሁ፣ ክልከላ ሊደረግበት የማይችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 11 ሃይማኖትና የመንግሥት የተለያዩ መሆን በግልጽ ተደንግጓል፡፡ አንደኛው በዚህ ሕግ መሠረት ሃይማኖት በመንግሥት፣ መንግሥትም በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገቡ ተቀምጧል፡፡ ሁለተኛ የመንግሥታዊ እምነት የሚባል ሃይማኖት አለመኖሩ ተመላክቷል፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ሁለቱም ርቀታቸውን ጠብቀው እንደሚኖሩ ተደንግጓል፤›› ሱሉ አቶ መሱድ ያስረዳሉ፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 27 ደግሞ ማንም የሃይማኖት ተቋም የሌላውን እስካልነካ ድረስ እምነቱን ማስተዋወቅ፣ በነፃነት መስበክና ማስተማር እንደሚችል በግልጽ መቀመጡን ይጠቅሳሉ፡፡

ከሰሞነኛው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ተከታዮች ጥቁር መልስ ጋር በተገናኘ እየተወሰደ ያለውን ክልከላ፣ እነዚህን መሠረታዊ የሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች ሊጥስ የሚችል መሆኑን ይናገራሉ፡፡

‹‹በሙስሊሞች ዘንድ ሂጃብ የመልበስ ፕሮቶኮል እንዳለን ሁሉ በካቶሊክ፣ በኦርቶዶክስና በሌላው ሃይማኖትም የራሱ የልብስ ፕሮቶኮል አለ፡፡ ሁሉም ሃይማኖቶች በየወቅቱ የየራሳቸው የሆነ የአምልኮና የፀሎት ሥነ ሥርዓት አላቸው፡፡ በሌላ በኩል ማንኛውም ምዕመን የእምነት ተቋሙ የሚሰጠውን መመርያ አክብሮ ይተገብራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የእምነት ተቋማቱ አደጋ መጥቶብናል ብለው ካመኑ በዚያ ጉዳይ ላይ ተቃውሞ፣ ቅሬታም ሆነ ሌላ ሃይማኖታዊ መመርያ ሊተገብሩ ይችላሉ፤›› ሲሉ አቶ መሱድ የእምነት ተቋማትን የሕግ ነፃነት ወሰን ያስቀምጣሉ፡፡

ቤተ ክርስቲያኗ ያወጣቸው መመርያም ሆነ ምዕመኑ ትዕዛዙን መተግበሩ በሕግ የማያስጠይቅ፣ ክልክላም ሊደረግበት የማይችል መሆኑን ነው አቶ መሱድ የሚናገሩት፡፡

‹‹ሲጀመር የእምነቱ አባቶች ትዕዛዙን ሲሰጡ ያለውን ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ ከግምት አያስገቡም ተብሎ አይታመንም፡፡ እንዲህ ያሉ ትዕዛዛትን ከምን አንፃር እንደሚወጡ መንግሥት ራሱ ያውቃል፡፡ መንግሥት ማለት እኮ ሃይማኖት ያላቸው፣ ከእኛው ከማኅበረሰቡ የወጡና በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ ሰዎች ስብስብ ማለት እንጂ ከኅብረተሰቡ የተነጠሉ አይደሉም፡፡ ሃይማኖቱንም ሆነ ያደግንበትና የኖርንበትን ሁኔታ የሚያውቁ ሰዎች ናቸው መንግሥት የሚባለውን ተቋም የሚፈጥሩት፤›› በማለት አቶ መሱድ ያብራራሉ፡፡

የአሁኑ የኦርቶዶክስ ተከታዮች ጥቁር የመልበስ ጉዳይም ለምንና እንዴት እንደመጣ፣ መንግሥትም ሆነ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚገነዘብ፣ ጉዳዩ በቤተ ክርስቲያን የታዘዘ መመርያ እንጂ ጤናማ ያልሆነ ወይ ሌላ አጀንዳ ያለው ነው ተብሎ እንደማይገመትም ያክላሉ፡፡

‹‹ምዕመኑ የእምነት ተቋሙ የያዘውንና የእምነት አባቶቹን ቃል ማክበር ስላለበት ለብሷል፡፡ እንኳን ኦርቶዶክሱ የሌላው እምነት ተከታይም ጥቁር እየለበሰ አጋርነቱን እያሳየ ነው፤›› ሲሉ የጠቀሱት አቶ መሱድ፣ ሕገወጥ ተቃውሞ ወይም የአገርና ሕዝብን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ተብሎ ሊረጎምም ሆነ ክልከላ ሊደረግበት የሚችልበት አግባብ እንደሌለ ነው ያስረዱት፡፡

ሌላው የሕግ ባለሙያ አቶ በላቸው ግርማ በበኩላቸው፣ ጥቁር በለበሱ ሰዎች ላይ ክልከላ የሚደረገው ‹ምን ለማስቀረት ሲባል?› በማለት ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ‹‹እየታየ ላለው ጥቁር በለበሱ ሰዎች ላይ የሚደረግ ክልከላ ምንም ዓይነት የተጨበጠ የሕግ ምላሽ ሊሰጥበት አይችልም፡፡ ጥቁር ልብስ ለብሶ አንድ ሰው ቢንቀሳቀስ ምን የሕግ ግዴታ አጎደልክ ተብሎ ሊወነጀል ይችላል?›› ሲሉ ጉዳዩ ጥያቄ አስነሺ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አንድ ገደብ የሚጣለው ሕግን ተከትሎ እንደሆነ የሚያስረዱት የሕግ ባለሙያው፣ ‹‹ለሕዝብ ደኅንነትና ለአገር ጥቅም ሲባል በሕግ ገደቦች ይጣላሉ፤›› ይላሉ፡፡

‹‹በእኛ አገር ያለው ትልቁ ችግር ግን ገደብ ሲጣል በምን አግባብ እንደተጣለ ወይም ክልከላው ከየት እስከ የት እንደሆነ ተገቢ መሥፈርት በአብዛኛው አለመኖሩ ነው፡፡ በብዙ የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች ስለአንድ ነገር ገደብ ይቀመጣል፡፡ ይሁን እንጂ በአብዛኞቹ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል ተብሎ መሥፈርቱ በዝርዝር ሳይቀመጥ ይተላለፋል፤›› በማለትም መሠረታዊ ችግር ያሉትን ጉዳይ ያስረዳሉ፡፡

በወቅታዊው የጥቁር መልበስ አለመልበስ ውዝግብ ላይም ቢሆን መንግሥት ከእምነት ተቋሙ አባቶች ጋር ተነጋግሮ ሊረታው የሚችል ችግር እንደነበር ነው አቶ በላቸው የሚጠቅሱት፡፡

‹‹መንግሥት ጉዳዩ ከአገርና ከሕዝብ ደኅንነት ማስጠበቅ ጋር ያለውን ተቃርኖ በአግባቡ ለእምነት አባቶቹ ቢያስረዳ፣ የእምነት አባቶቹም ይህን ካመኑበት ውዝግብ ሳይፈጠር ሕጋዊ ክልከላ ማስወሰን ይቻል ነበር፤›› ይላሉ፡፡

‹‹ነገር ግን በአገሪቱ በዘፈቀደና በአሻሚ ሁኔታ ፖሊስም ሆነ ሌላ አካል ክልከላ ማድረጉ በመለመዱና ለምን የሚል ማብራሪያ ጠያቂ በመጥፋቱ፣ አሁንም ጥቁር ለበሳችሁ ተብሎ ክልከላ እያየን ነው፡፡ በእኔ ግምት መንግሥት ከሕዝብ ጋር አጉል እልህ በመጋባቱ ወይም ተቃውሞን ለመቋቋም ትዕግሥት በማጣቱ የሚደረግ ክልከላ ይመስላል፤›› በማለት ነው አቶ በላቸው የተናገሩት፡፡

ሁለቱ የሕግ ባለሙያዎች የሰሞኑን የጥቁር መልበስ ጉዳይ የተመለከተበት መንገድ የተለያየ ነው፡፡ አቶ መሱድ ጉዳዩ ለተቃውሞ ተብሎ የሚደረግ ነው ብለው እንደማያምኑ የጠቀሱ ሲሆን፣ አቶ በላቸው ደግሞ ከወቅታዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የተካሄደ ሰላማዊ ተቃውሞ ነው ብለው እንደሚቀበሉት ተናግረዋል፡፡

የሕግ ምሁራኑ በዚህ ቢለያዩም ጉዳዩ ክልከላ ሊደረግበት የሚገባ ነው ብለው እንደማያምኑ ነው ተመሳሳይ ሐሳብ ያጋሩት፡፡

አቶ በላቸው፣ ‹‹ሕጋዊና ሰላማዊ ተቃውሞ ነው፡፡ መፈክር፣ ሠልፍ፣ መንገድ መዝጋትም ሆነ ሌላ እንቅስቃሴ አላየንም ጥቁር መልበስ ብቻ ነው የተደረገው፡፡ ይህ ደግሞ እንዲያውም የሠለጠነ መልዕክት ማስተላለፊያ እንጂ፣ ፈቃድ የሚጠይቅ ዕገዳ የሚደረግበት ጉዳይ አይደለም፤›› በማለት ነው ሐሳባቸውን የጠቀለሉት፡፡

አቶ መሱድ በበኩላቸው፣ ‹‹ሲጀመር የተቃውሞ ፈቃድ የሚጠየቀው ተቃውሞ የሚባል ነገር ሲኖር ነው፡፡ እንደምናየው የሃይማኖት ተቋም ወይም የእምነት አባቶችን መመርያ የመተግበር እንጂ፣ በፖለቲካ ፓርቲ ወይ በሌላ አካል የተላለፈ የተቃውሞ ጥሪ አይደለም፡፡ የእምነት አባቶች ጥቁር እንዲለበስ በአደባባይ ጥሪ አድርገዋል፡፡ ይህን በግልጽ የተላለፈ መልዕክት ሲያይ ደግሞ መንግሥትም ግንዛቤ ይወስዳል ተብሎ ይታመናል፡፡ በግልጽ እንደተመለከትነው ደግሞ ቤተ ክርስቲያኗ ጥቁር ልበሱ እንጂ ተቃወሙ ብላ ስታዝ አላየንም፤›› በማለት ነበር ስለጉዳዩ የተናገሩት፡፡

በሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ የሚሠሩት አቶ መሱድ ከሰሞኑ ጥቁር ለበሳችሁ በሚል በርካታ የመብት ጥሰቶች ሪፖርት እየደረሷቸው መሆኑን አክለዋል፡፡ ጥቁር ልብስ የሚሸጡ ነጋዴዎችን ማስፈራራትና ሱቅ መዝጋት፣ ጥቁር የለበሱ ሰዎችን በትራንስፖርት አገልግሎት፣ በሥራ ገበታና በመሥሪያ ቤት ጫና ማሳደርና ማስወጣት የመሳሰሉትን ጠቅሰዋል፡፡

ጉዳዩን ከሕዝብና ከአገርና ደኅንነት ጋር በተሳሳተ መንገድ እያገናኙ ሕዝብን የመጫን ዓይነት የመብት ጥሰት ሪፖርቶች በተደጋጋሚ እየቀረቡ መሆናቸውን የሕግ ባለሙያው አስረድተዋል፡፡

ሰኞ ምሽት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ መብቶች ላይ ክርክር እያደረገ ያለው በጠቅላይ ቤተ ክህነት በሕግ አገልግሎት መምርያና በሲኖዶሱ ሥር የተዋቀረው ጊዜያዊ የሕግና የችሎት ክርክር ዓብይ ኮሚቴው በሰጠው መግለጫም፣ ይህንኑ ጉዳይ በይፋ አንስቶታል፡፡

በቤተ ክርስቲያኗ ላይ መሠረታዊ የሕግና ቀኖና ጥሰት መፈጸሙን፣ እንዲሁም የንብረት ወረራ እየተፈጸመ እንደሆነ በመግለጽ የሦስት ወራት ዕግድ ጥያቄ የሕግ ኮሚቴው ለፍርድ ቤት ማቅረቡን ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ የዕግድ ጥያቄ ደግሞ ለረቡዕ የካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ስምንት ሰዓት ቀጠሮ እንደተሰጠው ነው የሕግ ኮሚቴው የገለጸው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በቅዱስ ሲኖዶሱ አቅጣጫ መሠረት ከሰኞ እስከ ረቡዕ እንዲከናወን የተላለፈውን ጥቁር ልብስ ለብሶ በፆም በፀሎት የማሳለፍ መርሐ ግብር፣ ሌላ ገጽታ ለማላበስና ክልከላ ለማድረግ እንቅስቃሴ መኖሩን ኮሚቴው እንደሚረዳ አስታውቋል፡፡

ይህን የቤተ ክርስቲያን ቀኖና የተከተለ መመርያ ማክበር ሃይማኖታዊ ግዴታ ምዕመናን እንዳለባቸው የሕግ ኮሚቴው ገልጿል፡፡ ሆኖም ለምን ጥቁር ለበሳችሁ? ለምን ፀለያችሁ? ተብሎ ክልከላ ማድረግና እንቅፋት መፍጠር የመሠረታዊ መብት ጥሰት መሆኑን ነው የሕግ ኮሚቴው ያስረዳው፡፡ ይህን በማስታወቂያ፣ በደብዳቤና በይፋ እየተካሄደ ያለ የመንግሥት ተቋማት ክልከላ በተመለከተም የሕግ ኮሚቴው ተጨማሪ ክስ ለችሎት ለማቅረብ ማሰቡን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ማክሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ፣ ይህንኑ የጥቁር መልበስ ክልከላ የመብት ጥሰት መሆኑን አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -