- እኔ ምልህ ክቡር ሚኒስትር?
- ክቡር ሚኒስትር ካልሽኝ ችግር አለ ማለት ነው።
- ችግርማ አለ።
- እሺ … እኔ ምልህ ያልሽው ለምን ነበር?
- ልጠይቅህ ነዋ።
- ምን?
- ከጥቂት ሳምንታት በፊት ስትሰብኩት የነበረው ነገር የውሸት ነው ማለት ነው?
- ምን ሰበክን?
- በመጀመሪያ የፓርቲ አባሎቻችሁን ቀጥሎ ማኅበረሰቡን ስለፖለቲካ ማርኬት ፕሌስ ወይም ስለፖለቲካ ገበያ ስትግቱ አልነበረም እንዴ?
- አዎ፣ ስለአገሪቱ የፖለቲካ ገበያ መበላሸት ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ አሁንም እየሠራን ነው።
- ግን እናንተ ራሳችሁ ስለጽንሰ ሐሳቡ ግንዛቤ አላችሁ?
- እንዴት? ምን ዓይነት ጥያቄ ነው?
- መንግሥት ራሱ የፖለቲካ ሸቀጥ ይዞ ገበያ መውጣቱን ስመለከት ጊዜ ግራ ገብቶኝ ነዋ፡፡
- መንግሥት እንዴት እንደዚህ ያደርጋል? ጽንሰ ሐሳቡ አልገባሽም ማለት ነው?
- የፖለቲካ ገበያ ማለት የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ ወይም የመንግሥትን ሥልጣን ለማፅናት ለገበያ የሚያቀርብ ሸቀጥ አይደለም እንዴ?
- ትክክል ነሽ፣ አንዱ መገለጫው እሱ ነው።
- ሥልጣንን ለማፅናት የብሔር ወይም የሃይማኖት ድጋፍ ለማግኘት መትጋት የፖለቲካ ሸቀጥ አይደለም?
- ነው እንጂ፣ እንዲያውም አደገኛው እሱ ነው።
- የፖለቲካ ገበያው መበላሸት የሚያስከትለው ውጤት ተቋምን፣ ቀጥሎም አገርን የማፍረስ አደጋ ያስከትላል ስትሉም ሰምቻለሁ አይደል?
- ትክልል ነሽ? ይህ አዝማሚያ አደገኛ ነው ያልንበት ምክንያት አገር ስለሚያፈርስ ነው።
- ታዲያ አገር በሆነችው ቤተ ክርስቲያን ላይ ለምን መዝመት ፈለጋችሁ?
- እሱ እንኳን ከዚህ ጋር አይገናኝም።
- እንዴት አይገናኝም?
- የሃይማኖት ጉዳይ ስለሆነ።
- የሃይማኖት ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነማ ግልጽ ነው።
- እንዴት?
- ነገሩ የሲኖዶሱን አብላጫ ለመቆጣጠር ወይም አገር ናት ያላችኋትን ተቋም ለመከፋፈል የሚደረግ ጥረት ነው።
- ለምን ብለን እንደዚያ እናደርጋለን?
- ለማፅናት ፈልጋችሁ ይመስለኛል።
- ምን ለማፅናት?
- ሥልጣናችሁን፡፡
- በፍፁም፣ ተሳስተሻል፡፡
- ታዲያ ለምን ችግሩን ለመፍታት ሰነፋችሁ?
- ሰንፈን አይደለም።
- እና ምን ሆናችሁ ነው?
- መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባት ስለማይችል ነው።
- ታዲያ ለምን እናንተ ገባችሁ?
- አልገባንም?
- የቤተ ክርስቲያን ተቋማትን እየሰበሩ መቆጣጠር የጀመሩትን እያያችሁ ዝም ማለታችሁ እኮ ያው ነው።
- ያው ነው ማለት?
- ጣልቃ መግባት ነው፡፡
- በፍፁም! የመንግሥት ፍላጎት ራሳቸው ተነጋግረው ልዩነታቸውን እንዲፈቱት ብቻ ነው።
- የአዲስ አበባ ባለአደራ አስተዳደር በሚል ተጀምሮ የነበረውን እንቅስቃሴ ታስታውሳለህ?
- አዎ፣ እሱን በምን አስታወሽው?
- በወቅቱ የነበረው ጭንቀታችሁ ትዝ ብሎኝ ነው።
- በአንድ ከተማ ላይ ሁለት አስዳደር ለመፍጠር መሞከር ትክልል አይደለም፣ በዚያ ላይ አካሄዱ አስፈሪ ነበር።
- ቢሆንም ከማሰር ይልቅ በውይይት ብትፈቱት ይሻል ነበር።
- እንዴት አድርገን ነው ከእነሱ ጋር የምንወያየው?
- አሁን የቤተ ክርስቲያን ችግር በውይይት ይፈታል እንዳልከው።
- እሱ ሌላ! ያ ሌላ!
- Advertisment -
- Advertisment -