ከቶ እንደምን ሆና እንደምን ከርማለች?
የመገዘዝ አይጥ ምኑን ትበላለች ?
ድርቅ ገብቷል አሉ መኽሩም አልሆነም
ዝናቡም አምርሮ ሳይሸፍት አይቀርም፤
ካልጮኸ ጅራፉ
ካልተንጫጫ ወፉ፤
ያ ነዶ ዘርጣጩ
ዝንጀሮው በሞላ
ከእረኞቹ ጋራ
በዕለት ካልተጣላ፤
ጉድ እየፈላ ነው፤ እኔን የጨነቀኝ …
የሌላውስ ይቅር ታፍራ እና ተከብራ
አገሯ ስትኖር ከሁሉም ተባብራ፤
ድመት እንኳን ሳይቀር አካፍሏት በሰላም
ይኖሩ ነበረ ለእምቅድመ ዓለም፤
ማንን በመጠየቅ አገኛለሁ መልሱን
የመገዘዝ አይጥ ምን ትበላ ይሆን ?
- ፀሐይ ደመቀ (ናሽቪል ቴነሲ)