Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ጥያቄያችን ይቀጥላል!

ሰላም! ሰላም! እንዴት ሰነበታችሁ? ‹መሰንበቻችንንማ የማታውቅ ይመስል ምን ያስጠይቅሃል…› ብላችሁ እንደማታስደነብሩኝ ስለማውቅ ነው፣ የወትሮውን ሰላምታ አስቀድሜ ከተፍ ያልኩት፡፡ ይኼውላችሁ ትንፋሽ የማይሰጥ ትውስታ እየተደራረበ ነው መሰል፣ ያለፉትን ዓመታት ውጣ ውረዳችንን በዓይነ ህሊና እየቃኘሁ ስቆዝም ነው የሰነበትኩት። ድሮ ነው አሉ አንዲት ነገረኛ አዝማሪ፣ ‹‹አቤት አቤት ብለን ያመጣነው አልጋ፣ እንዳንተኛ አረገን እንዳንዘረጋ…›› ብላ ከንጉሡ ጋር ጠብ ጀመረች አሉ። ንጉሡም ምንም ቢናደዱ እሷ ጣል የምታደርጋቸውን አባባሎች መስማት ስለሚፈልጉ፣ ‹‹በነገር ወጋ ብታደርገኝም ስህተቴን ስለምትጠቁመኝ እንዳትነኳት…›› ብለው ለሹሞቻቸው ስለተናገሩ የሚሰማትን እንደ ልቧ እየተናገረች፣ ንጉሡም ስለአስተዳደራቸው ሁነኛ መረጃ እያገኙ ሁሉን ችለው ኖሩ አሉ፡፡ እስኪ አስቡት ሐሳብን በነፃነት መግለጽ ጠላት በሚያስመስልበት ዘመን ላይ ሆነን ያለፈውን ስናስብ፣ ከበፊቱ የአሁኑ ምን የተሻለ ኖሮት ነው የምንራኮተው እላለሁ፡፡ ሰሚ የለም እንጂ!

እኔ የአገሬን ነገር ሳስብ ለአገር የሚጨነቁ ነፍሶች ያሳዝኑኛል፡፡ ለአገር የማይጨነቁ እነ ሆድ አምላኩ ሲበዙ ደግሞ እበሽቃለሁ፡፡ ደንታ ቢስነት በሁሉም የሕይወት ሰበዞቻችን ሲበዛ ‘ሶ ዋት’ እና ‘ሁ ኬርስ’ የሚባሉ ተስፋ አስቆራጭ ነገሮች ይበዛሉ። ለአገር ስንጨነቅና ስንጠበብ አዲሱ ትውልድ ሥርዓት ይዞ ያድጋል፡፡ ደንታ ቢስነት ሲስፋፋ ግን ሰው ከሆዱ በላይ የሚያስጨንቀው ነገር ይጠፋል። ምግባረ ቢስነትና ህሊና አልቦነት የሚንሰራፉት ደንታ ቢሶች ሲበዙ ነው፡፡ እስኪ አስቡት የጋራ ቁስላችን በጋራ መፍትሔ ብቻ መድረቅ በሚገባው በዚህ ጊዜ፣ ‹እንዴት? ወዴት? ለምን?› ካልተባባልን እንዴት ይሆናል? የአንዱን ሐሳብ ሌላው ካልሰማና ካላጤነ በቃ አበቃልን ማለት አይደል? እናም ‹እንዴት? ማለት ደግ ነው› ሲሉ አበው፣ ዘመናቸው ትምህርት ነጠቆች ባይበዙበትም በዲግሪ ብዛት የማይገኝ ማስተዋል ስለነበራቸው ነው። እኔም እስቲ በተራዬ ‹እንዴት?› ልበልና አዛውንቱን ባሻዬን ላዳምጥ። ያዋጣኛል!

ባሻዬ በተቆጣ ዓይናቸው አንፍሰውኝ ሲወጣላቸው፣ ‹‹ምን እንዴት ትለኛለህ?›› ብለውኝ እርፍ። ‹‹አባባሌ መቼም ይኼ ጊዜ እልፍ እየፀነሰ እልፍ ያመክናል። የዲጂታል ዘመን በሽምግልና ቀርቶ በጦር የማይፈታ ቅራኔ ያለው እያስመሰለ ሰውን ‹ከፍትፍቱ ስክሪኑ› ማሰኘት በያዘ ጊዜ ሥጋትዎን ያጫውቱኝ ማለቴ ነው…›› አልኳቸው። ይገርማችኋል ይኼን ጥያቄያዊ ረዥም ዓረፍተ ነገር ተናግሬ ስጨርስ፣ አንድ ኢትዮጵያዊ ጀግና አትሌት ውድድሩን በድል ተወጥቶ ከሳበው ትንፋሽ የማይተናነስ ሳብኩላችሁ። አይገርምም? ማኅበራዊ የትስስር ገጽ ላይ ዓይናችን ብቻውን ሲንከራተት እየዋለ እኮ፣ አንደበትም የእንቅስቃሴ አለርጂክ እንዳለበት ሁሉ ተሳስሮ ኖሮ ተገንዞ እንደሚቀበረው አካላችን ጂምናዚየም ሊከፈትለት ምንም አልቀረለትም። ‹ላንቃ የማላቀቅ፣ አንደበት የመተርተር፣ ምላስ የማፍታታት አገልግሎት እንሰጣለን…› የመሳሰሉት ማስታወቂያዎች በቅርቡ ተለጥፈው ካያችሁ ታዲያ ‹አይዲያው› የእኔ ነው እሺ። መቼም ቀባጣሪው ሁሉ ‹ነብይ› ተብሎ ሰው አናት ላይ ከመውጣቱ በፊት እውነተኞቹ እንደነበሩ አንክድም፡፡ ይታያቸው የነበሩ ለማለት ያህል ነው!

አዛውንቱ ባሻዬ ማብራራት ጀመሩ። ‹‹እንጃ ልመናና ምልጃችን ከሶፍትዌርነት ወደ ሃርድዌርነት እንዳይቀየር ሠጋሁ…›› ሲሉኝ አፌን ከፍቼ ቀረሁ። ‹ሶፍትዌር› እና ‹ሃርድዌር›፡፡ እንግዲህ ከዳዊት መጽሐፋቸውና ከዚያች የዛገች ሬዲዮናቸው ሌላ በማያውቁት ባሻዬ አፍ ተባለ ማለት የአርተፊሻል አስተውሎት ጠቢባን የሮቦት ማኅበረሰብ የመፍጠር ግስጋሴያቸው ምን ያህል እየሰመረላቸው እንደሄደ መገመት አላዳገተኝም። እኚህ አዛውንት በስተርጅና ቅዳሴና ፆማቸውን ትተው የኮምፒዩተር ኮርስ መውሰድ ጀመሩ? እንዴት ነው ነገሩ? ስል በልቤ፣ ‹‹…ሰው ትንሽ ቆይቶ፣  መንግሥቱንና ፅድቁን የምፈልግበት ኃይልና እምነት ጨምርልኝ ከማለት፣ ሀብት በሀብት ላይ የምጨምርበትን መረጃ የምይዝበት ሚሞሪ ጨምርልኝ፡፡ ሃርድ ዲስኬን አብዛው። ፋይሎቼንና ሲስተሜን ከቫይረስ ጠብቅልኝ እያለ መፀለይ የሚጀምር መስሎኛል…›› ብለው ይባስ አጃኢብ አሰኙኝ። እኛ ደግሞ ለምዶብን ከሚነሳው ዋና ሐሳብ የሚማርከን አተራረኩና ተራኪው አይደል? የትረካ ነገር ሲነሳ አንዱ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው፡፡ ‹‹አንበርብር የሰሞኑ የሃይማኖት ውዝግብ ከመጻሕፍት ዓለም ትረካ እየመሰለኝ ነው…›› ሲለኝ የባሰ አታምጣ ብዬ አማተብኩ፡፡ ይደንቃል!

ወዲያው ወደ ምሁሩ ወዳጄ የባሻዬ ልጅ ዘንድ ደውልኩ። የባሻዬ ኮምፒዩተራዊ ቃላት አመራረጥና አጠቃቀም ወትሮው የማውቃቸውን ባሻዬን እንዳልመሰሉኝ እንዳደረገ ስነግረው፣ ‹‹ማን ያውቃል አባዬ ሽፍትን ተጭኖ ዘመኑ ይጠይቅ ወደ መሰለው የዕውቀት ሳይሆን፣ የቃላት ጋጋታ ኢንተር ብሎ ይሆናላ። ደግሞ አይግረምህ መገለባበጥ በእኔ አባት አልተጀመረም…›› ሲለኝ ወይ ዘንድሮ ነገራችን ሁሉ ከመገለባበጥ ጋር ተጣብቆ ቀረ በቃ አልኩ። ‹መፈንቅለ መንግሥት ይባል ነበር ድሮ፣ አሁን ደግሞ መፈንቅል ዓይነቱ ብዛት› ይለኛል አዕምሮዬ፡፡ የሰው ነገር አሳባሪነትና ሰንጣቂነት ትዝ ሲለኝ፣ ‹ምቀኛ ነጃሳውን አርቅልን፣ ፈነቃቃዩን ያዝልን…› ተብሎ ፈጣሪ የሚለመንበት ዘመን ነው፡፡ ቅንነትን የሚያሳጣ ነውረኛ ቫይረስ ወሮን እርስ በርስ ለመበላላት ቀጠሮ የተያያዝን እየመሰለኝ እደነግጣለሁ። ምን ላድርግ!

በነገራችን ላይ ዘመናችንን ስታዘበው በጣት ከመዘወር ወደ ተንቀሳቃሽ ዳስተር ስልክ፣ ከዚያም ወደ ተንሸራታች፣ ተነካኪና አነካኪ ሞባይል ስልኮች በፍጥነት የመገለባበጣችን አጭር ታሪክ ብዙ የሚባልለት ነው። መቼ ዕለት አንድ ገልባጭ ላሻሽጥ (በቴሌግራም እንጂ እጅ በእጅ መጨባበጥ የተውን እስኪ እጅ እናውጣ? ኧረ በቫይበር አላልኩም) በጣቶቼ ስልኬን ወዲያ ወዲህ ሳራግባት አንድ ወዳጄ ትኩር ብሎ ያየኛል። አስተያየቱ ስላልጣመኝ (ጠላት ከሩቅ አይመጣም ስንል ዘንድሮስ ጥላም የለን አሉ ሲያዩን) ኮስተር ብዬ፣ ‹‹በሰላም ነው?›› ስለው፣ ‹‹ኧረ ሰላም ነው። አንዲያው ይኼ ጊዜና ሰዓቱን ጠብቆ ሳንዘጋጅ የመጣብን ቴክኖሎጂ ነገር እየገረመኝ እኮ ነው። ይኼው እንደምታየው ገበያውንም አደራው፣ ሰውንም በየጎራው አሠልፎ አባላው…›› አለኝ። ዳር ዳርታው ገብቶኝ፣ ‹‹ይህ ሊሆን ግድ ነው አልኩት…›› ከባሻዬ የሰማሁትን የመጽሐፍ ጥቅስ የራሴ አስመስዬ። ሰው በሰው ንብረት የፈጠራ ሥራና ሐሳብ የራሱ አስመስሎ እዩኝ ዕወቁኝ እያለ እያየን የእኔ ምን አላት ብላችሁ ነው? ምንም!

ገመድ አልባ ‘ኔትወርክ’ ካመጣልን መልካም ነገር ያመጣብን የመፈላለጥ፣ እንደ ድመት የመሞነጫጨር ትግል ስለበለጠ አስተያየቱ አልጥም ብሎኝ አንዴ ‹እህ…› ያልኩት ወዳጄ ሊላቀቀኝ ፈቃደኛ አይደለም። አንዱ በቴሌግራም ለእጮኛው የጻፈውን መልዕክት ፍፁም ለማያስባት በስህተት ልኮ ጥሩ አቀባባል ተደርጎለት በዚያው መቀጠሉን አጫውቶኝ ሳይጨርስ፣ ሌላ ትኩስ ትዳር ገና በሁለት ወሩ በፌስቡክ ያጫትን ትዳሯን አስፈትቶ በላይዋ ላይ ጓደኛዋን ደርቦ አሳበዳት ሲባል፣ ‹ሰማሁ! አየሁ!› ይለኛል። ከግለሰባዊ ምግባረ ብልሹነት እስከ መዋቅራዊ መበለሻሸት የደረስንበት ጥግ ሲታሰብ፣ ስምንተኛው ሺሕ ደረሰ ወይ ያሰኘኛል፡፡ ለሥጋው መከራ ከሚያየው ለነፍስ መዳን ዋስ ጠበቃ መሆን የሚገባቸው በኪሳራ ጎዳና ላይ ሲወዛወዙ ደግሞ ያስደነግጠኛል፡፡ አይ ጊዜ!

እናላችሁ ያልኳችሁን ገልባጭ ጉዳይ ከዳር አድርሼ መገናኛ አካባቢ ጥሩ ይዞታ ያለው ቪላ ቤት ላሻሽጥ ደንበኞች ቀጥሬያለሁ። ገልባጩን በእጁ ያስገባው ደንበኛዬ የአውቶሞቢል ማሽከርከሪያ ፈቃዱን ሊያድስ ወደ መንገድ ትራንስፖርት ስለሚያመራ፣ በዚያው ገፋ ሊያደርገኝ ተስማምተን ተጓዝን። ሰው መቼም በሕይወቱ ዘመን ከሰው ጋር አንድ ዕርምጃም ቢሆን ከተጓዘ መወዳጀቱ ግልጽ ነው። እንደ አጋጣሚ ቤቱን ላሳያቸው የቀጠርኳቸው ሰዎች ትንሽ እንደሚያረፍዱ ደውለው ስለነገሩኝ፣ ወዳጄንና ደንበኛዬን ተከተልኩ። በመንገድ ላይ ወሬ ተነሳ፡፡ ወሬያችን ደግሞ ከወትሮው የቢዝነስ ውጣ ውረድ ወጣ ብሎ አገር ላይ አረፈ፡፡ ደንበኛዬ ሳግ እየተናነቀው፣ ‹‹ወንድሜ አንበርብር የመጣብን ፈተና ከባድ ነው፡፡ እኛ ስለማንችለው ወደ የሚችለው ፈጣሪ በንፁህ ልብ ፀሎት እያደረግን ምሕረቱን ነው መለመን ያለብን…›› ሲለኝ ልቤ እውነት ነው እያለ ሰማው፡፡ የግድ ነው!

ከደንበኛዬ ጋር ፈጣሪ ሰላሙን እንዲያወርድልን ተመኝተን ከተሰነባበትን በኋላ፣ ቤቱን ዛሬ መጥተን እናያለን ያሉኝ ደንበኞቼ ደርሰናል ብለው እስኪደውሉ እየተጠባበቅኩ ነው። ሆኖም ሞባይሌ የጥሞና መንፈስ ውስጥ የገባች ይመስል ጭጭ ማለቷ ገርሞኝ፣ ‹ደግሞ በግለሰብ ስልክ መስመር ላይ ማስደገም ተጀመረ? ወይስ የዘንድሮ የዶፍ እርግማን ወደ እኔ አካፋ ይሆን?’ እያልኩ ለደንበኞቼ ደወልኩ። ደንበኞቼ ስልካቸው ዝግ ነው። ‹ይኼ ሆነ የለ፣ ይቅርታ የለ፣ ምን የለ፣ ምን የለ። እዚህ ታች ያልተለመደ ግልጽነትና ተጠያቂነት እዚያ ላይ እንዴት የትውልድ ዕድሜ በላህ ተብሎ ይወቀሳል እያልኩ ሳለሁ ስልኬ ጮኸ፡፡ የደዋዩን ማንነት ሳላይ ተቻኩዬ ‹ሃሎ!› ከማለቴ፣ ‹‹አቶ አንበርብር በሳምንት ውስጥ የምመልስልህ 100 ሺሕ ብር እንድታበድረኝ ነው የደወልኩልህ…›› የሚል አሽሙራዊ ድምፅ ያለው ሰው እየሳቀ ጠየቀኝ፡፡ ውስጤ ድንገት በንዴት ብው ብሎ ስለነበር፣ ‹‹ሰማህ፣ እኔ የኮሚሽን ኤጀንት እንጂ አራጣ አበዳሪ አይደለሁም…›› ብዬ ጆሮው ላይ ጠረቀምኩት፡፡ ምድረ አነካኪ!

በሉ እንሰነባበት። ጊዜዬ እንዲህ እንደነገርኳችሁ እንደ በጋ ፀሐይ ተቃጥሎ መልሶ እኔኑ ሲያቃጥለኝ፣ አንጀቴም ድብን እያለ ወደ ቤቴ አዘገምኩ። ስደርስ ማንጠግቦሽ እንደ ወትሮዋ በመተሳሰብና በፍቅር ያሞቅናትን ቤት አሰነዳድታ እራት ስታቀራርብ አላገኘኋትም። ሶፋው ላይ ጋቢዋን ለብሳ እንደ ዘንግ በሚሳብ አንገቷ ላቧ እንደ ፋፋቴ ወደ ደረቷና ጀርባዋ እያሳበረ ወርዶ ልብሷ ውኃ ሆኖ ደረስኩ። ይህን ሳይ ስታሊን መቃብር ፈንቅሎ ተነስቶ ዳግማዊ ትሮትስኪ እኔ እመስል፣ መሀል አናቴን በመጥረቢያ የፈለጠኝ መስሎኝ አናቴን ዳበስኩ። ፈላጭና ቆራጭ ዓይነቱና መልኩ በዝቶ የሽብር በየዓይነቱ ሚዲያውን ሁሉ እጅ እጅ ባስባለበት በዚህ ጊዜ፣ ‹ስታሊን የትሮትስኪን አናት ያስፈለጠበት መጥረቢያ እንዴት እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ቤት መጣ?› ብዬ እንዳሰብኩ ሊገባኝ አልቻለም። ወዲያው ጠጋ ብዬ፣ ‹‹ምነው ፍቅር? ምን ሆንሽብኝ?›› ስላት፣  የሰሞኑ ነገር ጨጓራዬን አቆሰለው…›› አለችኝ። አጠገቧ ምንም የለም። ክሊኒክ እስክወስዳት ቢያስታግስላት ብዬ ወተት ልገዛ ወደ ሱቅ ሮጥኩ። ‹‹ወተት ስጠኝ…›› ስለው ባለሱቁ ፈገግ ብሎ፣ ‹‹ቢራ ነው ያለኝ…›› ብሎ ዓይነቱን ይዘረዝርልኝ ጀመር። ያልተያዘ እያልኩ አንድም ከሰው አፍ እንዳይከተኝ አንድም የሸቀጦቹ ዋጋ ከአኗኗሬ ጋር ስለማይስማማ ወደ የማልደፍረው ሱፐር ማርኬት ገብቼ ስጠይቅ፣ ‹‹በጠዋት ነው ያለቀው…›› ሲለኝ የቀበሌ ኅብረት ሱቅ ትዝ ብሎኝ ከአሁን አሁን፣ ‹ቢኖርም የሚሰጥህ አንድ ሌላ ዕቃ ስትገዛ ነው…› ይለኛል ብዬ ተቀዣበርኩ። በስንት መከራ ላይ ታች ብዬ የገዛሁትን የፋብሪካ ወተት ይዤ ወደ ማንጠግቦሽ ስሮጥ ካልደረሰብን የማይገባንን ችግር፣ ካላጣነው የማንቆጥረውን በረከትና ዕድል ችላ የማለታችን አባዜ መቼ እንደሚለቀን ራሴን እየጠየቅሁ ነበር። በጥያቄዎች የታጠረ ኑሮ ከፍና ዝቅ እያደረገንም ቢሆን ጥያቄያችን ይቀጥላል፡፡ መልካም ሰንበት!         

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት