Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሕንፃቸውን ምድር ቤት ለጭፈራ አገልግሎት ባዋሉ ባለንብረቶች ላይ ዕርምጃ መወሰድ ተጀመረ

የሕንፃቸውን ምድር ቤት ለጭፈራ አገልግሎት ባዋሉ ባለንብረቶች ላይ ዕርምጃ መወሰድ ተጀመረ

ቀን:

  • ሕገወጥ ግንባታና የፕላን ጥሰቶች አላሠራ ያሉ ፈተና እንደሆኑ ተገልጿል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን የሕንፃቸውን ምድር ቤት ከታለመለት አገልግሎት ውጪ ለጭፈራና ሌሎች አገልግሎቶች ባዋሉ ባለንብረቶች ላይ ዕርምጃ እየወሰደ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ባለሥልጣኑ ከሚሰጣቸው 29 የአገልግሎት ዓይነቶች የሕንፃ መጠቀሚያ ፈቃድ አንዱ ሲሆን፣ ግለሰቦች ግንባታቸው ለተጠናቀቁ ሕንፃዎች ፈቃድ ከባለሥልጣኑ እንደሚወስዱ ተገልጾ፣ ይህም በሚደረግበት ጊዜ የደኅንነት ጉዳዮች፣ የአደጋ ጊዜ መውጫ፣ ሊፍት፣ ፓርኪንግ (የምድር ቤት ወለል) ማሟላታቸው ተረጋግጦ የሚሰጥ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

ሕንፃው ከተፈቀደው አገልግሎት ውጪ ጥቅም ላይ መዋል እንደሌለበት በሕንፃ መመርያና ስታንዳርድ 127/2014 በግልጽ ቢቀመጥም፣ ይህንን በመተላለፍ የምድር ወለሉን ለጭፈራ ቤት፣ ለተለያዩ ሱፐር ማርኬቶች በማድረግ የትራፊክ መጨናነቅ የሚፈጥሩ አካላት እንዳሉ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ ዴሲሳ አስታውቀዋል፡፡

በሕንፃ አዋጁ መሠረት የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን አገልግሎታቸው የተቀየሩ ቦታዎች እንዲፈርሱ ወይም በቦታቸው እንዲመለሱ ለሕንፃ ባለቤቶች ይፋዊ ደብዳቤ መጻፉን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አክለዋል፡፡

ከዚያ አልፈው ወለሉን ወደ ጭፈራ ቤት፣ ባህላዊ አዳራሽ (አገልግሎት) የቀየሩና ያልታረሙ አካላትን በተመለከተ፣ ባለሥልጣኑ ለአዲስ አበባ የንግድ ቢሮ፣ ንግድ ፈቃዳቸውን እንዲሰርዝ፣ ከዲዛይንና ከፕላን ውጪ የተገነቡ፣ እንዲሁም የምድር ወለልን ለሌላ አገልግሎት ባዋሉ ላይ የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ዕርምጃ እንዲወስድ መገለጹ ታውቋል፡፡

ለደንብ ባለሥልጣን የተጻፈው ደብዳቤ ይዘትም አገልግሎታቸውን ያለ ፕላን ማሻሻያ የቀየሩ አካላት ላይ ዕርምጃ እንዲወሰድ የሚል ይዘት ያለው ሲሆን፣ በሌላ በኩል የንግድ ቢሮ የእነዚህን አካላት የንግድ ፈቃድ እንዲሰርዝ የሚጠይቅ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የ2015 ዓ.ም. የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን የካቲት 2 ቀን 2015 ዓ.ም.  በአዜማን ሆቴል ከባለድርሻ አካላት ጋር የገመገመው ባለሥልጣኑ፣ በስድስት ወራት ውስጥ ከሕንፃ መጠቀሚያ አኳያ 20 አገልግሎት የቀየሩ (ለመኪና ማቆሚያ የተፈቀደውን ለሌላ ዓላማ ያዋሉ) ሕንፃዎች ላይ ዕርምጃ መወሰዱን አስታውቋል፡፡

በከተማዋ ውስጥ ያሉ የግል ሕንፃዎች በታለመለት መንገድ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን፣ የመከታተልና የመቆጣጠር ሥልጣን የተሰጠው የአዲስ አበባ ከተማ ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ በተለይም የመኪና ማቆሚያ ወለል ለሌላ አገልግሎት አውለዋል ያላቸው በ23 ሕንፃዎች ላይ የንግድ ፈቃድ እንዲታገድ ከዚህ ቀደም መጠየቁን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

አቶ ገዛኸኝ እንዳስታወቁት፣ አስተዳደሩ ‹‹ስማርት ሲቲን›› ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ስታንዳርዶችንና መመርያዎችን አውጥቷል፡፡ ከእነዚህም የሕንፃ ቀለም፣ የውጪ ማስታወቂያን ስታንዳርድ፣ እንዲሁም የመጠቀሚያ ፈቃድ በሚወስዱበት ጊዜ የእሳት አደጋ፣ ሊፍት፣ እንዲሁም የአካል ጉዳተኞችንና ሌሎችንም ጨምሮ ያሟላ መሆኑ ተረጋግጦ የሚሰጥበት ፈቃድ ይጠቀሳል፡፡

በተለይም አሁን ላይ ተሠርተው የሚጠናቀቁ ሕንፃዎች ይህንን ያላሟሉ ከሆነ የመጠቀሚያ ፈቃድ እንደማይሰጣቸው አቶ ገዛኸኝ አስረድተዋል፡፡

የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን በተያዘው የበጀት ዓመት ስድስት ወራት የሕግ ማዕቀፎችን በማሻሻል፣ የኢሰርቪስን ተግባራዊ በማድረግ፣ የመሠረት ልማት አቅራቢ ተቋማትን በማቀናጀት ውጤታማ ሥራዎች መሠራቱን አስታውቆ፣ ከብልሹ አሠራር ተግባር ግኝቶች ጋር በተገናኘ በማዕከል፣ በክፍለ ከተማና ወረዳ ሥር የሚገኙ 77 ሠራተኞች፣ በ23 የግንባታ ተቋራጮች፣ 13 የአማካሪ ባለሙያዎች፣ 103 በተሰጣቸው ፈቃድ መሠረት ያልገነቡ ላይ ዕርምጃ መውሰዱን ገልጿል፡፡

ባለሥልጣኑ በስድስት ወራት ከተለያዩ አገልግሎቶች 73 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት አቅዶ፣ 71 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ገልጿል፡፡

በግማሽ ዓመቱ 5,103 የውጪ ማስታወቂያ ፈቃድ ተሰጥቶ 22 ሚሊዮን ብር የተገኘ ሲሆን፣ የተሰጠው ፈቃድ ቁጥር እንዲቀንስ ምክንያት የሆነው ጉዳይ አዲሱን ስታንዳርድ የሚያሟሉ ተገልጋዮች ቁጥር በመቀነሱ ምክንያት እንደሆነ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

አዲስ የወጣውን የውጭ ማስታወቂያ ስታንዳርድ የማያሟሉ በ11ዱም ክፍላተ ከተሞች ከ70 ሺሕ በላይ የውጭ ማስታወቂያዎችን ከደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ጋር በመሆን ለማስወገድ መቻሉ ተገልጿል፡፡

በተያያዘም በግማሽ ዓመቱ ባለሥልጣኑን ከገጠሙት ችግሮች ውስጥ ሕገወጥ ግንባታና የፕላን ጥሰት መሆኑ ተገልጾ፣ በከተማው የግንባታ ፈቃድ ሳያገኙ የሚገነቡ፣ ለአካባቢው ከተፈቀደው ፕላን ውጪ የሚገነቡ ግንባታዎች መኖራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ስጦታው አከለ (ኢንጂነር) አስታውቀዋል፡፡

ችግሩን ለመከላከል ባለሥልጣኑ ከደንብ ማስከበር ባለሥልጣንና ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የመከላከል ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ፣ ሆኖም ችግሩ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ተቋሙን ያጋጠመው ጉዳይ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...