- ከግንባታ ቦታው ሦስት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ብረት ሲወጣ ተይዞ ክስ ተመሥርቷል
በአዲስ አበባ የተጀመረውን የአደይ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም ግንባታ እያከናወነ የሚገኘው የቻይና ተቋራጭ ባቀረበው የዋጋ ማስተካከያ ጥያቄ ላይ መግባባት ባለመቻሉ ከተቋራጩ ጋር የተገባው ውል እንዲቋረጥ ስምምነት ተደረሰ።
የውል ማቋረጥ ስምምነቱ የተደረሰው ብሔራዊ ስታዲየሙን በባለቤትነት በሚያስገነባው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና ቻይና ኮንስትራክሽንና ዲዛይን ኮርፖሬሽን በተባለው ተቋራጭ መካከል ነው።
‹‹ኩባንያው በቀረበው የዋጋ ማስተካከያ ጥያቄ ላይ በመደራደር ቀደም ሲል በተገባው የሥራ ውል ላይ 225 በመቶ የክፍያ ማስተካከያ በማድረግ 12.5 ቢሊዮን ብር ለመክፈል ተግባብተን ነበር›› በማለት የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጀለ መርዳሳ ባለፈው ሳምንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባህልና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ስለጉዳዩ በሰጡት ማብራሪያ አስረድተዋል።
ነገር ግን በዚህ ዋጋ ላይ ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ተቋራጩ ሌሎች ጥያቄዎችን በማንሳት 17 ቢሊዮን ብር እንዲከፈለው መጠየቁን ሚኒስትሩ አክለው ገልጸዋል።
‹‹ተቋራጩ ያቀረበው ተጨማሪ የክፍያ ጥያቄ ተቀባይነት የሌለው ነው። ተቋራጩ በድርድር የደረስንበት ስምምነትን ከተቀበለ በኋላ የተለያዩ የመሸወድ ሙከራዎችን የሚያደርግ ቅንነት (ኢንተግሪቲ) የሚጎድለው ድርጅት ሆኖ አግኝተነዋል›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ በዚህም የተነሳ ከዚህ ተቋራጭ ጋር ከመቀጠል ይልቅ ውሉን በስምምነት ማቋረጥ እንደሚሻል በማመን ይኸው እንዲፈጸም መወሰኑን ተናግረዋል።
ስለ ጉዳዩ ዝርዝር ሁኔታ አንዲሁም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የደረሰበትን አቋም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጭምር ማስረዳታቸውንም ለቋሚ ኮሚቴው ገልጸዋል።
በጉዳዩ ላይ ለሪፖርተር ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የአደይ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም አንደኛ ምዕራፍ ተጠናቆ ሁለተኛውን ምዕራፍ ግንባታ ለማከናወን በ5.7 ቢሊዮን ብር ውል ተገብቶ ሥራው መጀመሩን ያስታውሳሉ።
በውሉ መሠረት ተቋራጩ ግንባታውን በ900 ቀናት ለማጠናቀቅ ውል የገባ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት መስከረም 2015 ላይ ግንባታውን አጠናቆ ማስረከብ እንደነበረበት፣ ነገር ግን በመካከል ባለው ጊዜ ውስጥ ከአቅም በላይ የሆኑ ችግሮች በመፈጠራቸው በውሉ መሠረት መፈጸም እንዳልተቻለ አስረድተዋል።
ካጋጠሙት ችግሮች መካከል አንደኛው የኮቪድ ወረርሽኝ መከሰት ሲሆን ሌላው ደግሞ መንግሥት በገጠመው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ለተቋራጩ በውጭ ምንዛሪ መከፈል የነበረበት ቅድመ ክፍያ በወቅቱ አለመክፈሉ ነው።
ተቋራጩ በውጭ ምንዛሪ ሊከፈለው ይገባ የነበረ ቅድመ ክፍያ በወቅቱ ባለመከፈሉ ምክንያት ከውጭ አስቀድሞ የሚያስገባቸው የግንባታ ግብዓቶች ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ በመናሩ የዋጋ ማስተካከያ እንደጠየቀ የገለጹት አምባሳደር መስፍን፣ የገንዘብ ሚኒስቴርና የቻይና ኤምባሲ ባሉበት፣ ዓመት የፈጀ ድርድር ከተደረገ በኋላ 12.5 ቢሊዮን ብር እንዲከፈለው ስምምነት ላይ መደረሱን አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ ተቋራጩ ትንሽ ቆይቶ ስምምነት የተደረሰበት 12.5 ቢሊዮን ብር ክፍያ በመጀመሪያው ምዕራፍ የግንባታ ዝርዝር ውስጥ የሚመደቡና የተከፈለባቸው ነገር ግን ያልተጠናቀቁ ሥራዎች ስምምነት ባደረገበት 12.5 ቢሊዮን ብር ክፍያ ውስጥ አይካተቱም የሚል ጥያቄና ክርክር ማንሳቱን አምባሳደሩ መስፍን ለሪፖርተር ገልጸዋል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ የግንባታ ዝርዝር ውስጥ የሚካተቱ ሆነው፣ በግንባታ ቅደም ተከተል ምክንያት ሥራቸው ወደኋላ እንዲከናወኑ ከተደረጉ ሥራዎች መካከል አንዱ ስታዲየሙን ሳር የማልበስ ተግባር እንደሆነ አምባሳደር መስፈን ገልጸዋል።
ተቋራጩ ግን የተከፈለባቸውና በመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ ውስጥ የሚገኙ ያልተጠናቀቁ ሥራዎችን አንድ ላይ ለማከናወን 17 ቢሊዮን ብር በላይ እንዲከፈለው ጥያቄ በማቅረቡ መስማማት እንዳልተቻለ አስረድተዋል።
በዚህም መሠረት በሚኒስቴሩና በተቋራጩ መካከል ንግግር ተደርጎ በስምምነት ውል ለማፍረስ መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።
ተቋራጩ በተሰጠው 12.5 ቢሊዮን ብር ግንባታውን የሚያጠናቅቅ ሌላ የውጭ ኩባንያ ማግኘት እንደሚቻል የገለጹት ሚኒስቴር ዴኤታው፣ በቱርክ ከሚገኙ ፍላጎት ካሳዩ ተቋራጮች ጋር ንግግር መጀመሩንም ገልጸዋል።
ነገር ግን ከቻይናው ኩባንያ ጋር በስምምነት ውል ለማፍረስ ተወሰነ እንጂ ውል የማፍረስ ሒደቱ እንዳልተጀመረና ሒደቱም ቀላል እንደማይሆን ገልጸዋል።
ምክንያቱም የውል ማፍረስ ሒደቱ የሚፈጸምበት ዋጋ ላይ ተግባብቶ ለመወሰን አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ከሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ ውስጥ እስካሁን አሥር በመቶ ብቻ መከናወኑን የጠቀሱት አምባሳደር መስፍን በፕሮጀክት አስተዳደር ረገድም ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
ለዓብነትም በቅርብ ጊዜ ሦስት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ብረት ከግንባታ ቦታው ሲወጣ ተይዞ ተቋራጩ ላይ ክስ ተመሥርቶ በፍርድ ሒደት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
(ለዚህ ዘገባ ዳዊት ቶሎሳ አስተዋጽኦ አድርጓል)
|
|