Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበኦሮሚያ ክልል ግድያን ጨምሮ ሕገ መንግሥቱን የሚፃረሩ የመብት ጥሰቶች መፈጻማቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ

በኦሮሚያ ክልል ግድያን ጨምሮ ሕገ መንግሥቱን የሚፃረሩ የመብት ጥሰቶች መፈጻማቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ

ቀን:

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሰሞኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከተከሰተው ችግር ጋር በተያያዘ በኦሮሚያ ክልል በነቀምቴ፣ በግምቢ፣ በደምቢ ዶሎ፣ በሻምቡ፣ በአሰላ፣ በሻሸመኔ፣ በጭሮ፣ በያቤሎ፣ በጅማ፣ በቡሌ ሆራና በነጌሌ ቦረና ከተሞች በፀጥታ ኃይሎች ግድያን ጨምሮ ከሕግ ውጪ እስራትና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን በምርመራ አረጋግጫለሁ ሲል አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ የካቲት 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. አዲስ ‹‹ቤተ ክህነት›› አቋቁመናል በማለት ያሳወቁት ጳጳሳት፣ በአንዳንድ ቦታዎች በኃላፊዎች ድጋፍ ጭምር በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች የሚገኙ አገረ ስብከቶችን መያዛቸውን አስታውቋል፡፡

ይህንን ተከትሎ ጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተገንጥለው እንደወጡና ‹‹ቤተ ክህነት›› አቋቁመናል ያሉ አካላት የሻሸመኔ ደብረ ስብሐት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንን ለመያዝ ያደረጉትን እንቅስቃሴ ተከትሎ፣ ዕርምጃውን ለመቃወም የወጡ ሰዎችን ለመበተን በመንግሥት የፀጥታ አባላት በተወሰደ ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል ዕርምጃና ከፀጥታ አባሎቹ ጋር ሲተባበሩ በነበሩ ሰዎች ቢያንስ ስምንት ሰዎች በጥይትና በድብደባ መገደላቻውን ኮሚሽኑ እንዳረጋገጠ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም ቁጥራቸው እስካሁን በትክክል ያልታወቀ ሰዎች ለተለያየ ዓይነትና መጠን ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን፣ እንዲሁም በርካታ ሰዎች ለተለያየ የጊዜ ቆይታ መታሰራቸውን የገለጸው ኮሚሽኑ፣ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች ጠቅሶ በሻሸመኔ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 13 መሆኑን ለኮሚሽኑ ማሳወቃቸውን ተከትሎ የማጣራት ሒደቱ ስለመቀጠሉ አስታውቋል፡፡

መንግሥት የፀጥታ አባሎች ተመጣጣኝ ባልሆነ ኃይል አጠቃቀም በጥይትና በድብደባ የተፈጸሙ ግድያዎች፣ ከሕግ ውጭ የተፈጸሙ እስሮችና የእንቅስቃሴ ገደቦች፣ እንዲሁም ሲኖዶሱ ያቀረበውን የጥቁር መልበስ ጥሪ የተቀበሉ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ እስሮች፣ ከአገልግሎትና ከሥራ ቦታ ማግለልና ማንገላታት ፍፁም ተገቢ ያልሆኑና የዜጎችን በሕይወት የመኖር፣ በነፃነት ሃይማኖታቸውንና ሐሳባቸውን የመግለጽ ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን የሚፃረሩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መሆናቸውን ኮሚሽኑ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

በመሆኑም መንግሥት የተሟላና ተገቢውን የማጣራት ሥራ አካሂዶ ተገቢውን ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወስድና ለተጎዱት ካሳ እንዲክስ ያሳሰበው ኮሚሽኑ፣ በተጨማሪም የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ሰላማዊ ተቃውሞ በሚያደርጉ ሰዎች ላይ ኃይል ከመጠቀም፣ ከማንገላታት፣ ከሕገ ወጥ እስርና የሰዎችን እንቅስቃሴ ያለበቂ ምክንያት ከመገደብ እንዲቆጠቡ ጠይቋል፡፡

ኮሚሽኑ ከመደበኛው የክትትልና የምርመራ ሥራው ጎን ለጎን ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በሙሉ በማነጋገርና በመመካከር፣ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ የተፈጠረው ችግር፣ የሃይማኖት ነፃነት መሠረታዊ መብትና የሃይማኖት ጥበቃ ሕገ መንግሥታዊ መርህ መሠረት በቤተ ክርስቲያኗ የውስጥ ሥርዓት መሠረት እንዲፈታ፣ የመንግሥት ሰላምና ፀጥታ የማስከበር ተግባርና ኃላፊነት በሕጋዊ ሥርዓት እንዲመራ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋህደ ቤተ ክርስቲያን ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ባስተላለፈችው ውሳኔ ‹‹የኦሮሚያና የብሔር ብሔረሰቦች ቤተ ክህነት›› ተብሎ የሚጠራ አዲስ ቤተ ክህነት የተቋቋመውን አካል ውድቅ በማድረግ ሦስቱን ጳጳሳት ጨምሮ እነሱ የሾሟቸውን የሃያ ስድስት አባቶችን ማዕረግ በማንሳት ከቤተ ክርስቲያኗ በውግዘት እንዲገለሉ የተደረገ መሆኑ ይታወሳል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...