Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ኢንዱስትሪዎችን ስናያቸው የማምረት አቅም አጠቃቀማቸው 50 በመቶ ላይ ነው›› አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ

ኢትዮጵያ የተቸራት የተፈጥሮ ሀብት ወደ ሥራ በመቀየር የዜጎቿን የኑሮ ሁኔታና የአገሪቱን ክፍለ ኢኮኖሚ ማሳደግ የምትችል አገር እንደሆነች በተደጋጋሚ ሲገለጽ ይሰማል፡፡ በተለይም ከማዕድን እስከ ሰብል ያለውን መጠነ ሰፊ ሀብት ወደ ገንዘብ በመቀየር በአኅጉረ አፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነች አገርን ለመፍጠር እንደሚቻል ይጠቀሳል፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ዕውን እንዲሆን አገሪቱ አምራች ዜጋ ብቻም ሳይሆን አምራች ኢንዱስትሪ መፍጠር እንደሚገባት ዕሙን ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በአገሪቱ  የግብዓትና  የውጭ  ምንዛሪ  አቅርቦት ዕጥረት፣  ደካማ  የኢንዱስትሪዎች  ትስስር፣  የሰው  ኃይል  ምርታማነት ዝቅተኛ መሆን፣  የመፈጸምና  የማስፈጸም  አቅም  ውስንነትና  ከፀጥታ  መደፍረስ  ጋር  የተያያዙ  ችግሮች  የኢንዱትሪ  ዘርፉን  የማምረት  አቅም  አጠቃቀም  ዝቅተኛ  እንዳደረጉት ይገለጻል። ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ከዓለም አቀፍ ችግሮች፣ አንስቶ በኮቪድ-19 በጦርነትና ባለመረጋጋት ሳቢያ የተፈተነውን የአምራች ኢንዱስሪ ለመምራት ኃላፊነት የተሰጠው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በተለይም ከቀድሞው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተነጥሎና ራሱን ችሎ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ዘርፉን እንዴት እየመራው ነው? በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዴት እየተፈቱ ነው? ካለፈው ዓመት የግንቦት ወር አንስቶ ወደ ሥራ ያስገባው ‹‹የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ›› ምን ፋይዳ አስገኘ? በሚሉና በመሳሰሉት ላይ ኤልያስ ተገኝ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ደኤታ ከሆኑት ከአቶ ታረቀኝ ቡሉልታ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ራሱን ችሎ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሲቋቋም ምንን ታሳቢ ያደረገ ነበር? ምን ዓይነት የለውጥ ሥራዎችስ ሠርቷል?

አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ፡- እንደሚታወቀው የመንግሥት አደረጃጃት በሚወስነው በአዋጅ ቁጥር 1263 መሠረት ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም ራሱን ችሎ እንደ አዲስ ተደራጅቷል፡፡ ከዚህ በፊት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከንግድ ሚኒስቴር ጋር አንድ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ብቻቸውን የወጡበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ዋናው አዋጁ ላይ እንደሚመለከተው የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማነቃቃት፣ ዘርፉን በልዩ ትኩረት እንዲመራ ለማስቻል ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ደግሞ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት ወደ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ እንዲገቡ የማድረግ፣ ስለ አምራች የኢንዱስትሪ ዘርፉ የፖሊሲ ቀረፃ፣ የስትራቴጂ ቀረፃ፣ ከዚያም አልፎ የደንብ ቀረፃ፣ ራሳቸውን ችለው እንዲደራጁ ለማስቻል ነው፡፡ ስለዚህ ይህ አደረጃጀት ከዚህ በፊት ኢንስቲትዩት የነበሩትን ስድስት ተቋማት ወደ አንድ ኢንስቲትዩት አምጥቷቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የትኞቹ ኢንስቲትዩቶች ናቸው ስድስቱ?

አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ፡-  ለምሳሌ ጨርቃ ጨርቅ፣ ቆዳ፣ ምግብና መጠጥ፣ ኬሚካል፣ ብረት፣ ካይዘን የሚባሉ ለብቻቸው ስድስት የተለያዩ ኢንስቲትዩቶች ነበሩ፡፡ ነገር ግን አሁን አንድ ላይ አንድ ሆነው የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን መደገፍና ጥናትና ምርምር ላይ ማዕከል ማድረግ በሚችሉበት መልኩ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ኢንስቲትዩት ተብሎ ተደራጅቷል፡፡ ስለዚህ ይህም አዋጅ ፀድቆ አደረጃጀታቸውን ጨርሰው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ሁለተኛው ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተጠሪ የሆነው የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ነው፡፡ ለሥራ ዕድል ፈጠራው ኢንተርፕራይዞችን ከመደገፍ አኳያ ተደራጅቷል፡፡ ስለዚህ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አሁን ላይ ሁለት ተጠሪ ተቋማት ነው ያሉት፡፡ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ኢንስቲትዩትና የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ኢንስቲትዩት የሚባሉት ናቸው፡፡ ስለዚህ በዚህ አዋጅ መንፈስ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንደገና ራሱን አደራጅቷል፡፡ ሁለቱ ተቋማትን ራሱን በቻለ ደንብ ፀድቆ የሰው ኃይል ምደባውን ጨርሷል፣ ዋናው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ትኩረቱ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ላይ ትኩረት አድርጎ ነው የሚሠራው፡፡ ስለዚህ በዚህ አዋጅ መሠረት ተቋም የመገንባት፣ ተመልሶ ራስን ከማደራጀት አኳያ፣ ደንብን ከማውጣት አኳያ፣ የአሠራር ሥርዓትን ከማሻሻል አኳያ፣ ይሄ ተጠናቆ ወደ ተጨባጭ ሥራ የገባንበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡ ይሄ ለኢንዱስትሪው ትልቅ አጋጣሚ አድርገን የምንወስደው ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡ በአገሪቱ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ዕድገት የሚገዳደሩ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ በተለይም ከሰው ኃይል፣ ከካፒታል፣ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ያሉ ችግሮችን መግለጽ ይቻላል፡፡ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ራሱን ችሎ ከተቋቋመ ወዲህ ግን ይህን ለማሻገር ምን ያህል ርቀት ሄዷል? ምን ዓይነት ውጤትስ ተገኘ?

አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ፡- ዋናው የአምራች ኢንዱትሪ ዘርፉ ለአገራችን ዕድገት ወሳኙ ሴክተር ነው፡፡ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ላይ ካልሠራን እንደ አገር ተወዳዳሪ ሆነን መቀጠል አንችልም፡፡ ስለዚህ ይህ የሕግ ማሻሻያዎችን ይጠይቃል፣ አዲስ ፖሊሲ ይጠይቃል፡፡ ከነባር ፖሊሲ በተለየ የኢንዱስትሪ ፖሊሲው ተከልሷል (ሪቫይዝ) ተደርጓል፡፡ ብዙ ማነቆዎች ያሉበት፣ ብዙ ተግዳሮቶችና ችግር ያለበት ነው፣ ይህ ፖሊሲ ተግባራዊ ሲሆን የተሻለ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ይኖረናል ብለን እንጠብቃለን፡፡ ዋናው ፖሊሲ ነው፣ እሱ ተዘጋጅቶ በመፅደቅ ሒደት ላይ ይገኛል፡፡ ሁለተኛው መንግሥት የጣለበት ኃላፊነት ነው፡፡ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ምንድነው መንግሥት ከኢንዱስትሪው የሚጠብቀው? በጣም ትልቅ ግብ ነው የተቀመጠው፡፡ ለምሳሌ ኤክስፖርትን ወደ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር ማድረስ ነው፣ የሥራ ዕድል ፈጠራውን ወደ አምስት ሚሊዮን ለማድረስ ነው፡፡ ከተኪ ምርት አኳያ አሁን ያለው የአገር ውስጥ ምርት ድርሻ ወደ 30 በመቶ ነው ይህንን በዕጥፍ ማሳደግ ነው፡፡ ያ ማለት ከውጭ ጥገኝነት መላቀቅ አለብን፣ ራሳችን አምርተን፣ አገር ውስጥ ተጠቅመን ትርፍ ምርቶችን ኤክስፖርት ማድረግ አለብን፡፡ ሌላው የአቅም አጠቃቀም ነው፡፡ ለምሳሌ ኢንዱስትሪዎችን ስናያቸው የማምረት አቅም አጠቃቀማቸው በተለያየ ችግር ምክንያት 50 በመቶ ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን አሻሽለን የማምረት አቅምን ወደ 85 በመቶ የማሻሻል ዕቀድ ታቅዷል፡፡ ስለዚህ ወደ 11 ሺሕ አዳዲስ ኢንተርፕራዞችን በአሥር ዓመት ውስጥ የማሳካት ዕቅድ ታቅዷል፡፡ ይህ ዕቅድ ብዙ ሪፎርሞችንና ሥራዎችን ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ በጠቅላላው ሲታይ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ፈተናዎች (ቻሌንጆች) ምንድናቸው? የሚለውን ፖሊሲው ለይቷቸዋል፡፡ የዓመትና የአምስት ዓመት ዕቅድ ስናቅድ ለይተናቸዋል፡፡ ስለዚህ ትልቁና ዋናው ሥራ የቅንጅት አሠራር ነው፡፡ ምክንያቱም ኢንዱስትሪውን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጀምሮ የሚጨርሰው ሥራ አይደለም፡፡ የብዙ ዘርፎች ስብስብ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ኢንዱስትሪን ለማቋቋም ቢፈለግ መሬት ይጠይቃል፣ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መሬት ማቅረብ አይችልም፡፡ ነገር ግን መሬት ከሚያቀርበው አካል ጋር ተቀናጅቶ መሥራት አለበት፡፡ የፋይናንስ አቅርቦት ይጠይቃል፣ ሚኒስቴሩ ፋይናንስን አያቀርብም የፋይናንስ ተቋማት ናቸው የሚያቀርቡት፣ ይህ ቅንጅት ይፈልጋል፡፡ ሌላው የሠለጠነ የሰው ኃይል ይጠይቃል፣ ይህ የሠለጠነ የሰው ኃይል ከዩኒቨርሲቲና ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ በሌላ በኩል ገበያ ይጠይቃል፡፡ ኤክስፖርት ለሚያደርጉ አምራቾች የተለያየ የውጭ የገበያ መዳረሻዎችን ማፈላለግ አለብን፣ የአገር ውስጥ ገበያዎችን ማስፋፋት አለብን፡፡ ይህ ቅንጅት ይፈልጋል፡፡ ከዚህም በላይ ከሕግ አኳያ ቅንጅት ይፈልጋል፡፡ የተሻለ የኢንዱስትሪ ሕግ አገር ውስጥ እንዲኖርና በኢንዱስትሪው አከራካሪ ሕጎች ሲኖሩ የሚዳኝበት አግባብ ቀላል የሆነ ሕጉ የሚደግፈው ያስፈልጋል፡፡ ይኼንን ቅንጅታዊ አሠራር በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተወሰነ ተቀናጅተን ለመሥራት እየሞከርን ነው፡፡ እንደ ምሳሌ የምናነሳው ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር ጥሩ እየተናበብን ችግሮች እንዲፈቱ እያደረግን ነው፡፡ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር አዳዲስ የሚወጡ መመርያዎች አሉ፣ ከኤሌክትሪክ (መብራት) ኃይል ጋርም እንደዚያው፡፡ ይህ ቅንጅት በሕግ የተደገፈ ሳይሆን እንደ ትብብር ነው፡፡ ተጠያቂነት ያለበት አይደለም፡፡ ነገር ግን የተጀመረ ነገር አለ፡፡ ወደፊት በሕግ የተደገፈ ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ፣ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ወደ ፊት ሊያራምድ የሚችል ዓይነት አዋጅ ማውጣት አለብን ብለን እናስባለን፡፡ ጅምሮቹ ጥሩ ናቸው፣ ችግሮቹም ሰፊ ናቸው፡፡ ለምሳሌ አብዛኛው ኢንዱስትሪዎቻችን ከግብዓት አኳያ ጥገኝነታቸው ከውጭ ነው፡፡ ለምሳሌ ልብስ ለማምረት ጨርቅ ከውጭ ማምጣት ይፈልጋል፡፡ ማሽነሪ ለመትከል ከውጭ ማምጣት ይጠይቃል፣ መለዋወጫ ከውጭ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ አንዳንዶች የሰው ኃይል ጭምር፡፡ ለምሳሌ የሰው ኃይል ገና ኢንዱትሪውን እስኪለምድ፣ ዕውቀት እስኪሸጋገር ድረስ የሰው ኃይልን ጭምር ከውጭ ማምጣት ይጠይቃል፡፡ እነዚህ ሁሉ የሚጠይቁት የውጭ ምንዛሪ ነው፡፡ ስለዚህ የውጭ ምንዛሪ አሁን ካለንበት ወቅታዊ ሁኔታ በሚገባ ከማቅረብ አኳያ እሱም አንድ ችግር ተደርጎ የሚታይበት ሁኔታ አለ፡፡ ወደፊት ግን ግብዓትን ከውጭ ማስገባት ሊቀር ባይችልም አብዛኛውን የአገር ውስጥ ትስስር፣ የአገር ውስጥ አቅምን ማዕከል ያደረጉ፣ ሰፊ አቅሞች አሉ፡፡ ለምሳሌ ጎንደር አከባቢ ጥጥ አለ፡፡ ሰፊ ጥጥ የሚመረትበት አካባቢ ነው፡፡ ስለዚህ ጥጥን ወደ ጨርቅ ሊቀይር የሚችል ኢንዱስትሪ እንዴት ሊስፋፋ ይችላል?

አንዳንድ ቦታ ደግሞ የተለየ አቅም አለ፡፡ ስለዚህ የአገር ውስጥ አቅምን ተጠቅሞ አምራች ኢንዱስትሪው ወደዚያ የሚሄድበትን ዕድል ማስፋፋት ይኖርብናል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢንዱስትሪው አካባቢ በተለይ ትልልቅ የሚባሉት የሲሚንቶ፣ ብረታ ብረት አካባቢ በርካታ ችግሮች ይነሳሉ፡፡ አንዳንዴ ጉዳዩ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም ሊሆን ይችላል ወይም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች ተቋማትም ጋር ችግሩ ሊገናኝ ይችላል፡፡ በእነዚህ አካባቢ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በእናንተ በኩል ምንድነው እያደረጋችሁ ያላችሁት?

አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ፡- ኢንዱስትሪዎችን ስናያቸው ብዙ ዓይነት ኢንዱስትሪ ነው ያለው፡፡ ለምሳሌ ምግብና መጠጥ ብንወስድ ዕድል ያለው ነው፡፡ የራስን ተነፃፃሪ ዕድሎችን ተጠቅሞ የሚመራበት ነው፡፡ የምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪ አብዛኛው ግብዓቱን ከአገር ውስጥ ነው የሚጠቀመው፡፡ ስለዚህ እነዚህን የእሴት ጭማሪ እንዲበዛም መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ስንዴ ወደ ዱቄት፣ ወደ ብስኩት፣ ፓስታ ከዚያ በኋላ ወደ ኤክስፖርት፣ አንዳንድ አልሚ ምግቦችን የማልማቱን ጉዳይ ብናጠናክር የተሻለ ዕድሎች አሉን፡፡ ከብረት አኳያ አንደኛ ከውድቅዳቂ ብረታ ብረቶችን እየሰበሰበ መልሶ በመጠቀም (ሪሳይክል) የሚደረጉ አሉ፡፡ ሌላው ቢሌት የሚባል ከውጭ መጥቶ እንደ ግብዓት የሚያገለግል አለ፡፡ ወደፊት በጥናት የተለዩ የብረት ክምችት አገራችን ውስጥ አለ፡፡ እሱ ቢለማ ከብረት ግብዓት ጋር ተያይዞ ያለው ችግር ይፈታል፡፡ ስለዚህ አንደኛ የብረት ግብዓትን ከማምረት አኳያ ያለው ነው፡፡ ሲምንቶንም ስናይ ሰፊ ዕድል አለው፡፡ ተወዳዳሪ ሊያደርገን የሚችሉ አቅሞች አሉ፡፡ ነገር ግን በተደጋጋሚ ጊዜ ከሲሚንቶ ጋር ተያይዞ እጥረት የመፍጠር፣ ከዋጋ ጋርም ተያይዞ ያሉ ጉዳዮች አሉ፡፡ ይኼ ግን በቅንጅት የሚሠራ ነው፡፡ የዋጋ ጉዳይ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር ይሠራል፡፡ ሲሚንቶ ማዕድን ከመሆኑ የተነሳ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ይሠራል፡፡ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም ኢንዱስትሪን ከመከታተል አኳያ በጋራ የምንሠራቸው ሥራዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ከኃላፊነት አኳያ ማነው የሚከታተላቸው በሚለው ተለይቶ አንዱ የማዕድን ሚኒስቴር፣ ገበያን ከመወሰን አኳያ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያሉበት ነው፡፡ ያሉትን ክፍተቶች ከመሙላት አኳያ እንደ መንግሥት በቅንጅት የመሥራት ሒደትን ነው መከተል ያለብን፡፡ የማምረት አቅማቸው ውስንነት ያለው ፋብሪካዎች ላይ ነው፡፡ ፋብሪካዎች ማምረት የሚገባቸውን እያመረቱ አይደለም፡፡ ከገበያ አኳያ ደግሞ መካከል ላይ ያለ ደላላ አለ፣ እጥረት የሚፈጥር፡፡ እነዚያን ችግሮች በቅንጅት ከፈታን ሲሚንቶን ከእኛ አልፈን ለሌሎች አገሮችም ማቅረብ እንችላለን፡፡ ዕድሉ ስላለን ነው፡፡ በተለይ ወደፊት በሒደት ላይ ያሉ ኢንዱስትሪዎች አሉ፡፡ እነሱ ቶሎ ከተጠናቀቁ የተሻለ ዕድል ይኖረናል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በተለይም የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የማምረት አቅማቸው ከፍተኛ ቢሆንም የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የሚያመርቱት በጣም ዝቅተኛ ነው ይባላል፡፡ ከዚህ ችግር ጋር ተያይዞ ያያችሁት ነገር ካለ ቢያስረዱን?

አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ፡- የማምረት አቅም የሁሉም ኢንዱስትሪ ችግር ነው፡፡ በተለይ ብረትና ሲሚንቶ ላይ ደግሞ ያንሳል፡፡ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከሚከተለው የቴክኖሎጂና የኢንጂነሪንግ ዘርፍ ከ30 በመቶ ያልበለጠ የማምረት አቅም አጠቃቀም ነው ያለው፡፡ ሌሎቹ የምግብ አምራቾች ሲታዩ 60 በመቶዎቹ ቤት ውስጥ ነው ያሉት፡፡ ዋናው ችግራቸው ከግብይት ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ የሚፈለገውን ግብይት በጥራትና በወቅቱ ካለማግኘት ጋር ነው የሚያያዘው፡ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ደግሞ ዕድሳት በሚደረግላቸው ወቅት የሚወስዱት ጊዜ ረዥም ስለሆነ ነው የማምረት አቅማቸው የሚወርደው፡፡ ከመለዋወጫ፣ ከውጭ ምንዛሪም ጋር የሚነሳ ነገር ስላለ እነዚያን ካሻሻልናቸው የተሻለ አቅም ያለን ቦታ ቢኖር ሲሚንቶ አካባቢ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ጋር ተያይዞ ካለፈው ዓመት አንስቶ ሰፊ ንቅናቄ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ውጤትም አግኝተንበታል እያላችሁ ስለሆነ የንቅናቄው መነሻ ምን ነበር? በቀጣይስ የሚጠበቀው ነገር ምንድነው?

አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ፡- ኢትዮጵያ ታምርት አንዱ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን አብዮት ወደ አገራችን እናመጣለን ብለን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የጀመረው ንቅናቄ ነው፡፡ ይኼ ንቅናቄ የእኛ ብቻ ሳይሆን ዓለም ላይ ያለው ተሞሮ እንደሚያሳየው ከኢንዱስትሪ አብዮት ጀምሮ በአብዮት የጀመረ ነው፡፡ ለምሳሌ የብዙ አገሮችን ልምድ ስናይ ራሱን የቻለ ንቅናቄ በማድረግ ያሳኩት ሒደት ነው፡፡ የተሳካላቸው አሉ፣ ያልተሳካላቸውም አሉ፡፡ ይኼን መሠረት አድርገን ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት የጀመርነው ስንጀምረው ዋና ዓላማ የነበሩ ሦስት ጉዳዮች ናቸው፡፡ አንደኛው የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ትኩረት እንዲያገኝ ነው፡፡ ከላይ ጀምሮ ሁሉም አመራሮች በትኩረት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን እንዲያውቁት፣ እንዲከታተሉት ማድረግ አንደኛው ዓላማ ነበር፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የቅንጅት አሠራርን ከላይ እንደጠቀስኩት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በቅንጅት የሚሠራ ነው፡፡ ስለዚህ ከቅንጅት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን መፍታት ሁለተኛው ዓላማ ነው፡፡ ሦስተኛው መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳለጥ ነው፡፡ ምክንያቱም እንደ አገር ኢንዱስትሪው እንዲመራ እንፈልጋለን፡፡ ታቅዷልም፡፡ ስለዚህ ይኼን ዕቅድ ለማሳካት እንደዚህ ዓይነት የተለየ ትኩረት፣ ሀብት (ሪሶርስ)፣ ጊዜ፣ የባለቤትነት መንፈስ የሚፈጥር፣ ከላይ እስከ ታች የተቀናጀ በፌደራል ደረጃ ብቻ የሚቀር ሳይሆን እስከ ክልል የሚወርድ፣ ከክልልም እስከ ዞኖች የሚወርድና አመራሩም ባለቤት ሆኖ የሚያንቀሳቅሰው ዓይነት እንቅስቃሴ ስለሚያስፈልግ ነው የተጀመረው፡፡

ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ትልቅ ፋይዳ አስገኝቶልናል፡፡ ግንቦት ወር ላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለቡት ነው ይኼ ንቅናቄ የታወጀው፡፡ ካገኛቸው ፋይዳዎች አንዱ ትኩረት ማግኘት ሲሆን በሁሉም ክልል ላይ ፕሬዚዳንቶች ኢንዱስትሪን ሲመርቁ፣ ሲመሩ፣ አቅጣጫ ሲሰጡ ማየት ትልቅ ትኩረት ነው፡፡ አንድ ነገር በአመራር ደረጃ ትኩረት ከተሰጠው የመቀየር ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ሁለተኛ ችግሮችን ከመፍታት አኳያ ስናይ ወደ 479 ኢንዱስትሪዎች ተዘግተው የነበረ ሲሆን፣ ከዚያ ውስጥ ወደ 200 ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ መመለስ ችለናል፡፡ አንዳንዶቹ ከግብይት በተገናኘ፣ አንዳንዶቹ ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር፣ አንዳንዶቹ ከወሰን ማስከበር ጋር በተገናኘ እንዲሁም ከባንክ ጋር ከግብር ጋር ክርክር የነበረባቸውና በትንሽ ነገር ታንቀው የነበሩ ወደ ምርት እንዲመለሱ ያደረግንበት ሁኔታ አለ፡፡

ሌላው ክልሎች አካባቢ ከተሰጠው ትኩረት የተነሳ የመሬት አቅርቦቱ ጨምሯል፡፡ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ የጨመረበት ዕድል ነው ያለው፡፡ መሬት ወስደው ያላለሙት ተወስዶባቸው ማልማት ለሚችሉ ተላልፎ የተሰጠበት ዕድል ነው ያለው፡፡ እስካሁን በኢትዮጵያ ታምርት እንቅስቃሴ የተገኘው ፋይዳ ትልቅ ነው፡፡ ወደፊት  ተቋማዊ አድርገነው መቀጠል አለብን፡፡ ንቅናቄው እንደዚሁ የተጀመረ ነበር አሁን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አድርገነዋል፡፡ ወደ ፊት ከዚያ አልፎ ራሱን የቻለ እንደ ጃፓኖች ምርትን እንደሚያሳድግ ተቋም ይህም ተቋም ሆኖ ወደፊት ኢንዱስትሪውን ሊደግፍ የሚችል ሆኖ የሚወጣበት ትልቅ ዕድል በእጃችን ነው፡፡ ከተንቀሳቀስንና የጋራ ካደረግነው ይህች አገር ትልቅ አቅም ያላት አገር ነች፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በግብይትና በፀጥታ መደፍረስ ምክንያት የተዘጉ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ ለመመለስ ያሰበ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በተለይ ሰፊ የኢንዱስትሪ መገኛ የነበሩት የአማራና የትግራይ ክልሎች ከጦርነቱም ጋር ተያይዞ ያሉበት ሁኔታ ምን ይመስላል? ከንቅናቄው ጋር ተያይዞ እነዚህ የተጎዱ አካባቢዎች ላይ ምን ተሠርቷል?

አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ፡- የኢትዮጵያ ትምርት ንቅናቄ አንደኛ የተዘጉ ኢንዱስትሪዎችን የማስከፈት ተልዕኮ ነው ያለው፡፡ ከዚያ አኳያ የተጎዱ ኢንዱስትሪዎች፣ ግጭትና ጦርነት በነበረባቸው አካባቢዎች በተለይ አማራና ትግራይ ክልሎች የተጎዱ ኢንዱስትሪዎች አሉ፡፡ የአማራና አፋር ክልሎች ቀድመን ሠርተናል፡፡ አስቀድመን የተጎዱት ኢንዱስትሪዎች ስንት ናቸው? የጉዳታቸው መጠን ምን ያህል ነው? ያንን ችግር እንዴት ልንፈታ እንችላለን? የሚለውን ከኢንዱስትሪ ባለቤቶች ጋር ውይይት አድርገናል፡፡ አንዳንዶቹ ችግሮች ባለሀብቱ ራሱ የሚፈታው ናቸው፡፡ ለምሳሌ ብድር ያለባቸውን የብድር ጊዜያቸውን በማራዘም፣ አንዳንዱን ፋብሪካቸውና መኪናቸው የተቃጠለውን ከቀረጥ ነፃ እንዲገባላቸው፣ አንዳንዶቹ ግብዓታቸውን የተዘረፉባቸው የውጭ ምንዛሪ ቅድሚያ አግኝተው ያንን ግብዓት ሊያሟሉ ይችላሉ በሚል ተለይቶ የመፍትሔ አቅጣጫ ተቀምጦ እየሠራንበት እንገኛለን፡፡ የአማራና የአፋር ክልልም ቢሆን መቶ በመቶ አልተፈታም፡፡ በሒደት ላይ ያለ ጉዳይ ነው፡፡

ነገር ግን ከችግር ልየታ አኳያ የተሻለ ቡድን ገብቶ ጥናቱ ተደርጎ ችግሩ የተለየበትና በመፍትሔዎቹ ላይ መግባባት የተደረሰበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤትን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮችም ሔደው እንዲጎበኙ አቅጣጫ የተሰጠበት፣ በተለይም ባንኮች፣ ኢንዱስትሪዎች የተጎዱበት አካባቢ ቅድሚያ ፋይናንስ ማግኘት እንዲችሉ፣ ጉምሩኮችም ቅድሚያ ሰጥተው በራሳቸው መስኮት (ዊንዶ) መገልገል እንዲችሉ አቅጣጫ ስለተቀመጠ እሱ በዚያ አግባብ መፍትሔ ያገኛል፡፡

ከትግራይ ክልል ጋር ተያይዞ አሁን ጥሩ የሰላም ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ የፌደራል መንግሥትና የትግራይ መንግሥት መግባባት ፈጥረው ጥሩ የሰላም ጅማሮ አለ፡፡ ያ ጅማሮ በኢኮኖሚም መጠናከር አለበት የሚል ዕምነት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አለው፡፡ ከዚህ የተነሳ ባለሙያዎችን አዋቅረን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍና ከኢንተርፕራይዝ ልማት የመጀመሪያ ደረጃ ጥናት ተካሂዷል፡፡ ስለዚህ ያ የመጀመሪያ ደረጃ ጥናት በመቀሌና አካባቢው ያሉ ኢንዱስትሪዎች ምን ይመስላሉ የሚል ነው፡፡ ከዚያ ባሻገር የአመራሩ ቁርጠኝነት ምን ይመስላል? ምክንያቱም እኛ ብቻ ስለሠራን ሳይሆን በትግራይ ክልል ያለው አመራር ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል፡፡

ሦስተኛ ላይ የባለሀብቱ ተነሳሽነት ምን ይመስላል? ባለሀብቱ ራሱ መንቀሳቀስ አለበት፡፡ ምክንያቱም የሰው ኃይል ማሰባሰብ ይኖርበታል፡፡ የጉዳት መጠን መለየት ይኖርበታል፡፡ ከፌደራል መንግሥት የሚፈልገውን መለየት ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ ይኼ የመጀመሪያ ደረጃ ጥናት መቀሌና ከአካባቢው እንደ ውቅሮ ያሉ አካባቢ  ኢንዱስትሪዎችን ዓይቷል፡፡ ሪፖርቱን ካየን በኋላ ደግሞ ቀጣይ ጥናት ያስፈልገዋል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ጥናት ስለሆነ ልዑካችንም እዚያ የቆየው ከሳምንት ላልበለጠ ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ችግሩ ከተለየ በተመሳሳይ ሁኔታ እንዴት ወደ ሥራ እንገባለን? የሚለውን ጉዳይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይተን የምንሠራ ይሆናል፡፡ 

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ከአጎዋ ዕድል መሠረዝ አንዱ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ከፈተኑት ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳል፡፡ ይህንንም ዕድል ለመተካት የኢንዱስትሪ ምርቶች በአገር ውስጥ እንዲሸጡ የተሰጠውን ዕድል ከማስቀጠል ባሻገር የአጎዋን ዕድል ለማስመለስ ምን እየተሠራ ነው?

አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ፡- አጠቃላይ የተያዘው ዓመት የስድስት ወር የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አፈጻጸምን ስንገመግመው የተሻለ መሆኑን ዓይተናል፡፡ ይህም የራሱ የሆነ መለኪያዎች አሉት፡፡ ለምሳሌ ከኤክስፖርት አኳያ ስናይ ወደ 194 ሚሊዮን ዶላር አግኝተናል፡፡ ይኼ ካቀድነው አፈጻጸሙ 81 በመቶ ያሳየንበት ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ተኪ ምርት ነው፡፡ ተኪ ምርቶችን ሰናይ ወደ አንደ ቢሊዮን ዶላር ነው የተካነው፡፡ ስለዚህ ይኼ ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ከተሠራበት ወደፊት መተካት እንደምንችል ነው ያሳየው፡፡ ይኼን ዕድል ከፈጠሩት አንዱ አጎዋ ነው፡፡ የተዘጋው የአጎዋ ዕድል ቢኖርም ነገር ግን በልዩ ሁኔታ የአገር ውስጥ ሽያጭ ተፈቅዷል፡፡ ከዚህ በፊት ኤክስፖርት የሚያደርጉ በተለይ ከቀረጥና ታክስ ነፃ ግብይት ስለሚጠቀሙ አገር ውስጥ መሸጥ የሚችሉበት ሁኔታ ባለፈው ስድስት ወር ተፈቅዶ ነበር፡፡ አሁንም ተጨማሪ ስድስት ወር ተፈቅዷል፡፡ የአገር ውስጥ ሽያጭ ዕድላቸው እንዲያድግ የተደረገበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ አጎዋም የተዘጋው በራሳቸው በፖለቲካ ሁኔታ ኢትዮጵያ ምንም ባላጠፋችው፣ በራሳቸው የፖሊሲ ፍላጎት ነው፡፡

ኢትዮጵያን እንደ ራሳቸው ፍላጎት ለመጠምዘዝ ካላቸው ፍላጎት ነው፡፡ ወደፊት ያስቀመጡት ቅድመ ሁኔታ ሰላም ከሆነ ሰላማችን ተመልሷል ስለዚህ አጎዋም ይመለሳል ብለን እንጠበቃለን፡፡ ነገር ግን አሁን ያለን ትልቅ ችግር ምርት የመሸጥ ሳይሆን የማምረት ችግር ነው፡፡ ገና ማምረት ይኖርብናል፡፡ ካመረትን የአገር ውስጥ ዕድል አለ፡፡ ውጭ አገርም ሰፊ ዕድል አለ፡፡ አገር ውስጥ ያለው 100 ሚሊዮን ሕዝብ ነው፡፡ ውጭ አገር ደግሞ ስምንት ቢሊዮን ሕዝብ ነው፡፡ የውጭው ሕዝብ ስለሚበልጥ ነው የውጭ ገበያ ላይ የምናተኩረው፡፡ የመግዛት አቅማቸውም ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ አምርተን አገር ውስጥ ከተቻለ ደግሞ ብዙ አምርተን ወደ ውጭ ስንሸጥ የተሻለ ተጠቃሚ እንሆናለን፡፡

በስድስት ወራት ውስጥ ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንፃር 112 ሺሕ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለናል፡፡ የብድር አቅርቦትን ስንመለከት በተለይ ሁለት ቢሊዮን ብር ለኢንተርፕራይዝ ልማት፣ 1.3 ቢሊዮን ብር ለሊዝ ፋይናንስ የቀረበበት ሁኔታ አለ፡፡ የተኪ ምርትን ለማሳለጥ ወደ 128 ሚሊዮን ዶላር መንግሥት ቅድሚያ የሰጠበት ሁኔታ አለ፡፡ ጅምሩ የተሻለ ነው፡፡ ወደፊት ደግሞ አጠናክረን መሥራት እንዳለብን ያሳየናል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች