የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ወይም ማሻሻያ ስለሚሰጥ ማበረታቻ አፈጻጸም አዲስ መመርያ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ ይህ መመርያ ነባር ኢንቨስትመንቶቻቸውን የሚያስፋፉ ወይም የሚያሻሽሉ ባለሀብቶች ከማስፋፊያው ወይም ከማሻሻያው የሚያገኙት ተጨማሪ ገቢ ከግብር ነፃ መሆን የሚያስችላቸው ነው፡፡
እንዲህ ያሉ ማበረታቻዎች ለንግድና ኢንቨስትመንት ዕድገት የራሳቸው አስተዋጽኦ እንዳላቸው ይታመናል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ሽበሺ ቤተማርያምም እንዲህ ያሉ መመርያዎች የጎላ ጠቀሜታ አላቸው ይላሉ፡፡ ነገር ግን ማበረታቻው ሌሎችንም ጉዳዮች መመልከት እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡ ለምሳሌ የማስፋፊያ ሥራዎች የግዴት መሬት ይጠይቃል፡፡ ለማስፋፊያ የሚሆን መሬትና ሌላ መሠረተ ልማት ከሌለ የማስፋፊያም ሆነ የማሻሻያ ሥራዎችን መሥራት ስለሚያስቸግር እንዲህ ያሉ መመርያዎች መሠረታዊ የሚባሉ ጉዳዮችንም አካተው ቢቀርቡ መመርያው ውጤታማ ሊሆን ይችላል፡፡
በዚህ መመርያ ውስጥ የሚሰጠው ዕድል ሁለት ነገር ነው፡፡ የውጭ የካፒታል ዕቃና ለኮንስትራክሽን የሚያስፈልጉ ዕቃዎችን ለማስገባት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ አምርተህ የምታገኘውን ትርፍ ግብር መቀነስ ነው፡፡ ስለዚህ ማስፋፊያ ሲባል መሬት የሚጠይቅ በመሆኑ ይህንን የመሬት ጉዳይ ታሳቢ ማድረግ የሚል እምነት አላቸው፡፡ ሌላው ደግሞ በዚህ መመርያ መሠረት ተጠቃሚ ለመሆን የሚቻለውና ብቁ የሚሆነው ካፒታሉን አሳድጎ የንግድ ፈቃዱን ካሳደገ በኋላ ነው የሚለው ይህ ዓይነቱ አገላለጽ ደግሞ ሌላ የቢሮክራሲ መንግድ የሚከፍት ነው፡፡
‹‹እርግጥ የንግድ ፈቃድ ምዝገባው ኦላይን ሆኗል፡፡ ዘምኗል ነገር ግን ከእኛ የንግድ ኅብረተሰብ አባሎቻችን የምንሰማው አሁንም ችግር ያለ መሆኑ ነው፤›› የሚሉት አቶ ሽበሺ ስለዚህ የንግድ ምዝገባ ላይ ያለውም ችግር ካልተቀረፈ በሚፈለገው ፍጥነት መመርያውን ለመተግበር የሚያስቸግር ይሆናል የሚል ሥጋት አላቸው፡፡
በጥቅል ሲታይ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የቢዝነስ ኮሙዩኒቲው ማኑፋክቸሪንግ፣ እርሻ አገልግሎት ላይ ያሉት የገጠማቸው ችግር ብዙ ከመሆኑ አንፃር ብዙዎቹ ኩባንያዎች ኪሳራ አውጀው ከሥራ ወጥተዋል፡፡
በዚህ መመርያ ሊጠቀሙ ይችላሉ የተባሉ አንዳንዶቹ ኩባንያዎች ሳይቀሩ ሥራ አቁመዋልና እንዲህ ያሉትን ኩባንያዎች መልሶ ለማስነሳት ራሱን የቻለ ማበረታቻ የሚያስፈልግ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የሰሞኑ መመርያው ግን ባለፉት ዓመታት ኪሳራ አውጀው ሥራ ያቆሙትን የማይመለከትና እነዚህ ኩባንያዎች ሊስተናገዱ የሚችሉት በ2014 ዓ.ም. በወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ መሠረት የሚስተናገዱ ናቸው፡፡ ይኼ ጥሩ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ከሥራ የወጡትንም ታሳቢ ያደረገ አሠራር መከተል ማበረታቻዎችና የግዴታ እነዚህን ሊደግፉ የሚችሉ መሆን አለበት ይላሉ፡፡ የመንግሥት ማበረታቻዎች በተመሳሳይ ሊመለከታቸው ይገባል ያሏቸውን ሌሎች ጉዳዮች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ ሽበሺ ለምሳሌ የቆዳና የቆዳ ኢንዱስትሪዎችን ነው፡፡ ይህ ዘርፍ ቀድሞ ከነበረበት ደረጃ አሽቆልቁሎ ከ18 ፋብሪካዎች ወደ አምስት ፋብሪካዎች ለመውረዱ አንዱ ምክንያት እነዚህ ፋብሪካዎች ለምን ወደ ቁልቁለት ተጓዙ? ብሎ ችግራቸውን ዓይቶ ሊሰጣቸው የሚገባ ማበረታቻ ባለመሰጠቱ ነው፡፡
ያሉትም እያመረቱ ያሉት ከአቅም በታች ከመሆኑ አንፃር ምርታቸውን ከፍ እንዲያደርጉ ለውድቀት ያደረጋቸውን ችግር የሚቀርፍ ማበረታቻ መዘጋጀትና ሥራ ላይ መዋል ነበረበት፡፡ ስለዚህ ነባርና ጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ እንዲህ ያሉ ኢንዱስትሪዎችንም ነጥሎ በማየት ማበረታታት እስካልተቻለ ድረስ ኢንዱስትሪውን ማሳደግ ከባድ እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡
‹‹ለምሳሌ ይህ የቆዳ ኢንዱስትሪ የተለያዩ ከውጭ የሚገቡ ኬሚካሎች ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት የግድ ነው ግን ይህ ድጋፍ የለም፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ግን አንዳንዶቹ የግዥ ትዕዛዞች ከውጭ ያላቸው ሆነው ሥራቸውን ለመሥራት አልቻሉም፡፡ ስለዚህ የታክስ ማበረታቻዎች ሲሰጡ እያንዳንዲ ዘርፍ በየጊዜው በመመልከት ያለውን እንቅፋት ሊቀርፍ በሚችል መልኩ መሆን ይገባዋል፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በተለይ የቆዳ ኢንዱስትሪው ለውድቀት የተዳረገበት አንዱ ምክንያት የዘርፉ ላኪዎች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ 70 ከመቶውን ለብሔራዊ ባንክ የሚያስረክቡ በመሆኑ መጎዳታቸውን ይገልጻሉ፡፡ የዚህ ኢንዱስትሪ መዳከም በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ አምርታ አሳይታበት የነበረውን እሴት የመጨር ውጤታማ አሠራር መልሶ ወደታች እንዳወረደው የሚናገሩት አቶ ሽበሺ፣ ይህም ትልቅ ጉዳት በመሆኑ መንግሥት የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን መልሶ መላልሶ እንዲፈትሽ ምክረ ሐሳባቸውን አካፍለዋል።
እንደ አቶ ሽበሺ ገለጻ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች የበለጠ ውጤታማ የሚሆኑት ተገቢው ጥናት ተደርጎ ሲተገበሩ ነው፡፡ እስካሁን የተሰጡ ማበረታዎች ያስገኙት ውጤትም መመዘን እንዳለበት ያምናሉ፡፡ ስለዚህ የምንሰጠው ማበረታቻ በተለያዩ ምክንያቶች የወደቁ ነገር ግን በቀላሉ ተነስተው አገራዊ ኢኮኖሚውን ሊደግፉ የሚችሉ እንደ ቆዳ ዘርፍ ያሉ ኢንዱስትሪዎችን መደገፍ ትርጉም ይኖረዋል ይላሉ፡፡