Saturday, September 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከባንክ ውጪ ያለ ገንዘብ በከፍተኛ ደረጃ መጨመር ችግር እየፈጠረ ነው!

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሰሞኑን የአገሪቱን የፋይናንስ ተቋማት ወቅታዊ አቋም የሚያመላክት መረጃ ይፋ አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት በሒሳብ ዓመቱ የደረሱበትን ደረጃም አመላክቷል፡፡ በአኃዝ ተደግፈው ከቀረቡት መረጃዎች ውስጥ የኢትዮጵያ ባንኮች የተቀማጭ ገንዘብ መጠን በ31 በመቶ ማደረጉን የሚያመለከተው መረጃ አንዱ ነው፡፡ 

በዚህም መሠረት ከብድርና ከቁጠባ ተቋማት ወደ ባንክ ያደጉትን አምስት ባንኮች ጨምሮ 31ዱ ባንኮች ያሰባሰቡት የተቀማጭ ገንዘብ በሒሳብ ዓመቱ አጋማሽ ላይ ከሁለት ትሪሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡ በእነዚህ ባንኮች የቁጠባ ደብተር ያላቸው ቆጣቢዎች ቁጥርም አስገራሚ በሚባል ደረጃ ጨምሮ፣ ከ122 ሚሊዮን መድረሱም ተገልጿል፡፡ ይህ ቁጥር በእርግጥም አስገራሚ ነው፡፡ የባንኮች ቆጣቢዎች ከአገሪቱ ሕዝብ ቁጥር ልቆ መገኘቱን ያሳያል፡፡ የቆጣቢዎች ቁጥር በዚህ ደረጃ ለመጨመሩ አንድ ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው ጥቂት የማይባሉ ደንበኞች ሁለትና ከሁለት በላይ ደብተር ያላቸው ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ቀድሞም ቢሆን ከባንኮች በላይ ቆጣቢዎች ያላቸው አምስቱ የብድርና ቁጠባ ተቋማት ወደ ባንክ ሲሸጋገሩ የቁጠባ ደንበኞቻቸውን ይዘው እንደ ባንክ መንቀሳቀስ መጀመራቸው የአገሪቱን ቁጥር ወደ ላይ ሰቅሎታል፡፡ ለማንኛውም በሒሳብ ዓመቱ አጋማሽ ላይ የኢትዮጵያ ባንኮች የቁጠባ ሒሳብ ቁጥር የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ጨምሯል፡፡ በሌሎች አፈጻጸማቸውም ቢሆን አሁንም ዕድገት እያስመዘገቡ ስለመሆኑ ይኼው የብሔራዊ ባንክ መረጃ አመላክቷል፡፡ በኢንዱስትሪው የሚንቀሳቀሱ ባንኮች ቁጥርም ቢሆን 31 መድረሱ በራሱ የሚነግረን ነገር አለ፡፡ 

በአንፃሩ ግን ከባንክ ውጪ ያለው የገንዘብ መጠን በ27 በመቶ መጨመሩን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማስታወቁ ደግሞ አነጋጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ በባንኩ መረጃ መሠረት ከባንክ ውጪ ያለው የገንዘብ መጠን ከ187 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ ከባንክ ውጪ ያለው የገንዘብ መጠን በዚህን ያህል ደረጃ መጨመሩ ጤናማ አካሄድ ነው ተብሎ አይታመንም፡፡ 

በዚህ ጉዳይ ላይ አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ፣ ከባንክ ውጪ ያለውን የገንዘብ መጠን በ27 በመቶ አድጎ፣ 187 ቢሊዮን ብር መድረሱ ባንኮች ተጨማሪ ተቀማጭ ገንዘብ ለማሰባሰብ ዕድል የሚሰጥ ነው ብለውታል፡፡ 

ሁኔታው ግን ተጨማሪ የተቀማጭ ገንዘብ ለማሰባሰብ ዕድል የሚሰጥ ብቻ ነው ተብሎ የሚታለፍ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከባንክ ውጪ የሚንቀሳቀስ ገንዘብ መጠን ማደጉ ይብዛም ይነስም በሕገወጥ መንገድ የሚንቀሳቀስ ገንዘብ ከፍ ማለቱን ስለሚያሳይ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ከሁለት ዓመት በፊት የገንዘብ ኖት በተቀየረበትና ከዚሁ ጋር ተያይዞ አንዳንድ ተፈጻሚ የሆኑ መመርያዎች ከባንክ ውጪ የነበረን ገንዘብ ወደ ባንክ እንዲመለስ ቢያደርግም፣ እንደገና ከባንክ ውጪ ያለው ገንዘብ እየበዛ መሆኑን የሚጠቁምም ነው፡፡   

የገንዘብ ኖት ለውጡ ከባንክ ውጪ የሚንቀሳቀስን ገንዘብ ወደ ባንክ እንዲመጣ ማድረጉ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጎላ እንደነበርም በተለያዩ መንገዶች ሲገለጽ ነበርና አሁን ደግሞ ከባንክ ውጪ ያለው ገንዘብ አድጓል መባሉ እንደ መልካም ዕድል የሚታይ ሳይሆን፣ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው ላይ ጫና እያሳረፈ እንደሆነ ያመለክተናል፡፡  

በአንድ ዓመት ከባንክ ውጪ ያለው የገንዘብ መጠን 27 በመቶ መጨመሩ ከሁለት ዓመት በፊት በአስዳጅ ሁኔታ ወደ ባንክ የተመለሰው ገንዘብ መልሶ እየወጣ መሆኑን ያሳያል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በግለሰብና በኩባንያ ደረጃ በእጅ መያዝ ያለበት የገንዘብ መጠንን የሚደነግገው የባንኩ መመርያ ተፈጻሚ እየሆነ አይደለም ወደሚል ምልከታ የሚወስድም ነው፡፡

ይህንን ያህል መጠን ያለው ገንዘብ ከባንክ ውጪ ሊሆን የቻለበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን ይህ ገንዘብ ለሕገወጥ መንገድና ለሕገወጥ ተግባራት ማስፈጸሚያ የሚውለው የገንዘብ መጠን እየጨመረ ነው ማለት ነው፡፡ 

የፋይናንስ ሥርዓቱን በአግባቡ ለማሳለጥ ደግሞ አንዱ ሥራ ከባንክ ውጪ ያለን ገንዘብ ሕጋዊ መስመር ማስያዝ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑ ከታወቀ፣ ከባንክ ውጪ ያለው ገንዘብ ወደ ባንክ መምጣት አለበት፡፡ 

ከዚህ አንፃር አሁን ከባንክ ውጪ ያለው የገንዘብ መጠን በሁለት ዓመት ልዩነት እዚህ ላይ መድረሱ እንደ ዋዛ የሚታይ አይሆንም፡፡ ገንዘቡ ሕጋዊ የክፍያ ሥርዓትን ያልተከተለ ግብይት ማስፈጻሚያ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ በቀጣይ የገንዘብ መጠኑ አድጎ ሕገወጥ ግብይትን የበለጠ እንዳይስፋፋ ሁነኛ መፍትሔ የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው፡፡

ከኮንትሮባንድ ንግድና ሕገወጥ የንግድ ግብይት ምክንያት የሚሆነው ከባንክ ውጪ ያለ ገንዘብ በግብይት ሥርዓት ውስጥ የሚፈጥረው ችግር ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ማስከተሉ ግልጽ ነው፡፡ ከዚህም በላይ የዋጋ ንረትን በማባባሱም ረገድ ቢሆን የራሱ አስተዋጽኦ ስላለው ከባንክ ውጪ ያለው ገንዘብ ባንኮች ተጨማሪ ገንዘብ ለማሰባሰብ ዕድል ይሰጣል ተብሎ ሊታለፍ የሚችል ጉዳይ አለመሆኑ ያስገነዝበናል፡፡ 

በእርግጥ አዲሱ ገዥ እንዲህ ባለው መንገድ ጉዳዩን መግለጻቸው በውጭ ያለ ገንዘብ መሰብሰብ እንደሚኖርበት በተዘዋዋሪ መናገራቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ እንዲህ በቀላል ቋንቋ የማይገለጽ ከመሆኑም በላይ፣ ይህ የገንዘብ መጠን ለምን በዚህን ያህል መጠን ጨመረ? ገንዘቡስ እንዴት ተመልሶ ከባንኮች ወጣ? ብሎ በመፈተሽና ብሔራዊ ባንክ መፍትሔ የሚሆን ውሳኔ ሊያሳልፍ ይገባዋል፡፡ የቁጠባ ደብተር ከዚህ በኋላ ከባንክ ውጪ ያለው ገንዘብ እንዳይጨመር ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

ስለዚህ ከባንክ ውጪ ያለ ገንዘብ መጠን ወደ ባንክ እንዲሰበሰ፣ ይህንን ማስፈጸሚያ ሥልት ማበጀት ብቻ ሳይሆን፣ ባልተገባ መንገድ ከባንክ ውጪ ገንዘብ እንዳይወጣ የሚያስችል አሠራር መዘርጋትንም ይጠይቃል፡፡ የታመመውን የማክሮ ኢኮኖሚ ለማከምም ሆነ ሕገወጥ የገንዘብ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር፣ ከዚህም በላይ ጤናማ የግብይት ሥርዓት እንዲኖር ከባንክ ውጪ ያለን ገንዘብ በአግባቡ መቆጣጠር የዋጋ ንረትን እንዳያባብስ ይረዳል፡፡ በመሆኑም ከባንከ ውጪ ያለ ገንዘብ መጠን እንዳይጨምር፣ የወጣውም እንዲመለስ ብሔራዊ ባንክ ጊዜ ሳይሰጥ ይሥራ፣ ባንኮችም ይህንን ገንዘብ ማሰባሰብ የሚችሉት የእሱ ዕገዛ ሲኖበት ጭምር መሆኑ ሊሠመርበት ይገባል፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት