Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዘንድሮ የተማሪዎች እጥረት እንደሚያጋጥማቸው ተገለጸ

የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዘንድሮ የተማሪዎች እጥረት እንደሚያጋጥማቸው ተገለጸ

ቀን:

ትምህርት ሚኒስቴር ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የማለፊያ ውጤት ከ50 በመቶ በላይ እንዲሆን መወሰኑ የተማሪ ድርቅ ሊያስከትል እንደሚችል፣ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማኅበር ገለጸ፡፡ ከዚህ ቀደም ዝቅ ባለ የመቁረጫ ነጥብ ተማሪዎችን ሲቀበሉ የቆዩት የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ፣ ዘንድሮ ግን የማለፊያ ነጥብ ከተፈተኑት ከግማሽ በላይ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች መባሉ ለግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ቁጥር ሊቀንስባቸው እንደሚችል የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አስታውቀዋል፡፡

በአገሪቱ ከ300 በላይ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መኖራቸውን፣ ከእነዚህ ውስጥ አምስት ዩኒቨርሲቲዎችና 15 ዩኒቨርሲቲ ኮሌጆችን ጨምሮ በአጠቃላይ 162 ተቋማት የማኅበሩ አባል መሆናቸውን ፕሬዚዳንቱ አረጋ ይርዳው (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹እነዚህ ተቋማት ላለፉት 17 ዓመታት ትምህርት ሚኒስቴር በሚያወጣው ዝቅተኛ የመቁረጫ ነጥብ ተማሪ ሲቀበሉ ቆይተዋል፡፡ በአንዳንድ ዓመቶች ከተፈተኑት ትምህርቶች እስከ 25 በመቶ አጠቃላይ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ወደ ግል ከፍተኛ ትምህርት እንዲገቡ ሲፈቀድ ቆይቷል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ዘንድሮ ግን ከግማሽ (50 በመቶ) በላይ ብቻ የማለፊያ ነጥብ ይሁን መባሉ ወደ ግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎችን ቁጥር በእጅጉ ሊያወርደው እንደሚችል ነው የማኅበሩና የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አረጋ (ዶ/ር) ያለውን ሥጋት ያስገነዘቡት፡፡

‹‹ለትርፍ ወይም ለቢዝነስ ሲባል የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በወረደ ነጥብ ተማሪ እንዲቀበሉ ካልተፈቀደ አንልም፡፡ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለጥራት መተባበር አለብን፡፡ በትምህርት ጥራት ማሻሻያ የድርሻችንን ልንጫወት ይገባል፤›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ዘንድሮ መቁረጫ ነጥብ ባለመታወቁ ወደ ግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር ይቀንሳል የሚለውን ሥጋት፣ ትምህርት ሚኒስቴርም እንደሚጋራውና ተቋማቱን ባለፈው ሳምንት ለምክክር ጠርቶ እንደነበር ፕሬዚዳንቱ አስታውሰዋል፡፡

በዚህ ውይይትም ከ50 በመቶ በታች ያመጡ የ12ኛ ክፍል የተወሰኑ ተማሪዎች እንዲወስዱ በተባለው የአቅም ማሻሻያ (Remedial Program) የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይሳተፉ የሚል ውሳኔ መወሰኑን አመልክተዋል፡፡ ለአራት ወራት ለሚሰጠው የአቅም ማሻሻያና ዳግም ፈተና መርሐ ግብር የሚያበቃ፣ ከ30 በመቶ በላይ ውጤት ያላቸውን ተማሪዎችም የግል ተቋማቱ እየመዘገቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ከዚህ የትምህርት ፕሮግራም ለማትረፍ ሳይሆን ቢያንስ መደበኛ ወጪዎችን በሚችል ክፍያ ብቻ ተማሪዎች በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተስተናገዱ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሆኖም ከአራት ወራት በኋላ በሚወስዱት ዳግም ፈተና ምን ያህሉ እንደሚያልፉ አለመታወቁ የግል ተቋማት ላይ የተማሪ እጥረት ሊፈጥር እንደሚችል አመላክተዋል፡፡

የትምህርት ጥራት ቅድሚያ የሚሰጠው አገራዊና የትውልድ ጉዳይ ቢሆንም የግል ትምህርት ተቋማትም ለብዙ ሰዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ፣ ግብርና የቤት ኪራይ እየከፈሉ የሚሠሩ በመሆናቸው ጉዳዩ ይታሰብበት ሲሉ ነው የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ሥጋት ያሉትን የተናገሩት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...