Saturday, September 23, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በካፒታል ገበያ የሚሳተፉ የኢንቨስትመንት ባንኮች 100 ሚሊዮን ብር የካፒታል ፈንድ ማሟላት ይጠበቅባቸዋል

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባሥልጣን ባወጣው ረቂቅ መመሪያ በካፒታል ገበያ ውስጥ ተዋንያን እንደሚሆኑ የሚጠበቁ የኢንቨስትመንት ባንኮች እስከ 100 ሚሊዮን ብር የደረሰ የተጣራ የካፒታል ፈንድ ምጣኔ ማሟላት እንደሚጠበቅባቸው አስቀመጠ፡፡

የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ለመጀመርያ ጊዜ ሦስት የሚደርሱ ረቂቅ መመሪያዎችን ለሕዝብ አስተያየት ክፍት ያደረገ ሲሆን፣ ባለሙያዎች ምክረ ሐሳቦችን እንዲሰጡባቸው ይፋ የሆኑት ረቂቅ መመሪያዎች የሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ እና የግብይት መድረኮች የፍቃድ አሰጣጥና አሠራር መመሪያ (Licensing and Operating Securities Exchanges and Trading Platforms)፣ ራስን በራስ የሚቆጣጠሩ ድርጅቶች ዕውቅና አሰጣጥ መመሪያ (Recognition of self-regulatory Organizations) እንዲሁም የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪ ፍቃድ አሰጣጥና ክትትል መመሪያ (Capital Market Service Providers Licensing and Supervision) ናቸው፡፡

በሰነድ መዋዕለ ንዋይ ገበያና የግብይት መድረኮች የፍቃድ አሰጣጥና አሠራር ረቂቅ መመሪያው እንደሰፈረው፣ ፍቃድ ፈላጊዎች የሚያቀርቧቸው መረጃዎችና ሰነዶችን መሠረት በማድረግ የቀረበው የፍቃድ ጥያቄ የሰነደ መዋዕለ ንዋዮች ገበያ (Securities Exchange)፣ የተዛማጅ ውሎች ገበያ (Derivatives Exchange) ያልተማከሉ የጠረጴዛ ዙሪያ ግብይት መድረኮች (over-the Counter Facility) እንደሆነ ይለያል፡፡

ለግብይት የቀረቡት ሰነደ መዋለ ንዋዮችና ለመገበያየት የቀረቡ ባለሀብቶች ይለያሉ፣ የሰነደ መዋለ ንዋይ ፍቃድ፣ የተዛማጅ ውሎች ገበያ ፍቃድ በመመሪያው ክፍል ሁለት ላይ በተቀመጠው መሠረት፣ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን አመልካቾች በቂ ዓቅም ያለውና ያለምንም የአገልግሎቶች መቆራረጥና እንከን መሥራት ይችላሉ የሚለውን ባመነ ጊዜ የሚሰጥ ይሆናል፡፡

የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪ ፍቃድ አሰጣጥና ክትትል ረቂቅ መመሪያው ላይ እንደተቀመጠው፣ ባለሥልጣኑ የካፒታል ገበያ ተዋንያን ዝቅተኛ የካፒታል ዓቅም መጠንን እንደሚወስን ተገልጾ፣ ይህም የተከፈለ ካፒታል ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኝ የንግድ ባንክ በጥሬ ገንዘብ ተቀማጭ የሚከፈል እንደሆነ ያሳያል፡፡

በረቂቅ መመሪያው እንደተደነገገው እያንዳንዱ የካፒታል ገበያ አገልግሎት አቅራቢ አስፈላጊውን የተጣራ ባለአክሲዮኖች ገንዘብ ወይም የሚጠበቅበት የተጣራ ባለአክሲዮኖች ፈንድ  መሥፈርት ተቀምጧል፡፡

በረቂቅ መመሪያው ሰንጠረዥ አንድ ላይ እንደተቀመጠው እንደ ባንክ የሚወሰዱ የኢንቨስትምንት ባንኮች (Investment Bank-within a Banking Group) እስከ 100 ሚሊዮን ብር የተጣራ የባለአክሲዮኖች ፈንድ ማሟላት የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ እንደ ባንክ የማይወሰዱ የኢንቨስትመንት ባንኮች (Investment Bank- Not Part of a Banking Group)  ደግሞ የአገልግሎት ፍቃድ ለማግኘት 25 ሚሊዮን ብር የተጣራ የባለአክሲዮኖች ፈንድ ማቅረብ (ማሟላት) እንደሚገባቸው ተጠቅሷል፡፡

በሌላ በኩል የጋራ ኢንቨስትመንት ፈንድ አገልግሎት ሰጪዎች (Collective Investment Scheme Operator) 25 ሚሊዮን ብር የተጣራ የባለአክሲዮኖች ፈንድ ማሟላት የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ የብድር የመመለስ ብቃት ምዘና አገልግሎት አቅራቢዎች (Credit Rating Agency) 15 ሚሊዮን ብር፣ የሰነደ መዋለ ንዋይ ደላሎች (Securities Broker) ስድስት ሚሊዮን ብር፣ የሰነደ መዋለ ንዋይ ገበያ አከናዋዮች (Securities Dealer) አራት ሚሊዮን ብር የተጣራ ፈንድ ማሟላት እንደሚጠበቅባቸው ተገልጿል፡፡

ከሶስቱ መመሪያዎች የሰነደ መዋለ ንዋይ ገበያና የግብይት መድረኮች የፍቃድ አሰጣጥና አሠራር መመሪያ ላይ እንደተመለከተው ሕጋዊና ዕውቅና ባላገኘ የግብይት እንቅስቃሴ ውስጥ በሚገኙ አካላት የአስተዳደራዊ ዕርምጃን ጨምሮ የተለያዩ ቅጣቶች የሚተላለፍ ይሆናል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች