Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትቪዛ ለማግኘት ውጣ ውረድ ያሳለፈው የአትሌቲከስ ቡድን ወደ አውስትራሊያ አቀና

ቪዛ ለማግኘት ውጣ ውረድ ያሳለፈው የአትሌቲከስ ቡድን ወደ አውስትራሊያ አቀና

ቀን:

  • ስድስት ባለሙያዎች ቪዛ ተከልክለዋል

በአውስትራሊያ ባቱረስት ከተማ በዓለም አቀፍ አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ አትሌቲክስ ቡድን ወደ ሥፍራው አቅንቷል፡፡

ከወራት በፊት የአገር ውስጥ ቅድመ ውድድር አድርጎና አትሌቶችን ለይቶ ሲዘጋጅ ከነበረው ብሔራዊ ቡድን ቪዛ በከፊል መከልከሉን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቆ ነበር፡፡

ለብሔራዊ ቡድኑ ቅዳሜ የካቲት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ሽኝት ባደረገበት ወቅት ወደ አውስትራሊያ ከሚያመራው ልዑካን ቡድን ውስጥ ስምንት አትሌቶች እንዲሁም ስድስት ባለሙያዎች፣ በአጠቃላይ 14 የልዑካን ቡድኑ አባላት ቪዛ መከልከላቸው ተገልጾ ነበር፡፡

በተለይ ቪዛ ከተከለከሉት አትሌቶች መካከል ስድስቱ በውድድሩ ላይ ቋሚ ተሠላፊ ሲሆኑ፣ ሁለቱ ተጠባባቂ መሆናቸውን፣ ብሔራዊ ቡድኑን ሥጋት ውስጥ ከቶት እንደነበር አሠልጣኞቹ አስረድተዋል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በ44ኛው የዓለም አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ የሚሳተፉ የብሔራዊ ቡድን አትሌቶች ሱሉልታ ላይ ባሰናዳው ቅድመ ውድድር 14 ወንዶችና 14 ሴቶች አትሌቶች መርጦ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት በወጣት ሴቶች 6 ኪሎ ሜትር 6 አትሌቶች፣ በአዋቂ ሴቶች 10 ኪሎ ሜትር 6 አትሌቶች፣ በወጣት ወንዶች 8 ኪሎ ሜትር 6 አትሌቶች፣ በአዋቂ ወንዶች 10 ኪሎ ሜትር 6 አትሌቶች በድብልቅ ሪሌይ ሁለት ወንዶችና ሁለት ሴቶች አትሌቶች፣ በአጠቃላይ 28 አትሌቶች ወደ ሥፍራው ለማቅናት ቪዛ ለማግኘት አመልክተው ነበር፡፡  

ሆኖም ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ ለስምንት አትሌቶች ቪዛ መከልከሉና በመጨረሻ ሰዓት ብሔራዊ ቡድኑን አጣብቂኝ ውስጥ የከተተ ጉዳይ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

እንደ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ማብራሪያ ከሆነ፣ መቀመጫውን በኬንያ ናይሮቢ ያደረገው የአውስትራሊያ ኤምባሲ የቪዛ አጣሪ ክፍል፣ በተለይ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ አትሌቶችን ወደ ሥፍራው ካቀኑ በኋላ ‹‹መመለሳቸውን ያጠራጥረኛል›› የሚል ምክንያት በማቅረብ መከልከሉን ጠቅሷል፡፡

ያልተሟላ ብሔራዊ ቡድን ይዞ ለመጓዝ ከጫፍ ደርሶ የነበረው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ፣ ጉዳዩን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችለውን ጥረት ማድረጉን ገልጿል፡፡

በዚህም መሠረት የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት፣ የውጭ ጉዳይ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴሮች፣ ናይሮቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ የዓለም አትሌቲክስ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚገኘው የአውስትራሊያ ኤምባሲ በመረባረብ አትሌቶቹ ቪዛ እንዲያገኙ መደረጉ ታውቋል፡፡

እንደ ፌዴሬሽኑ ማብራሪያ ከሆነ ድጋሚ ቪዛ ለማመልከት በድጋሚ በአዲስ መልክ ካመለከቱ በኋላ ክፍያ በመፈጸም ሰኞ የካቲት 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ምሽት ላይ መሳካቱን አብራርቷል፡፡፡

በመጨረሻም ሰዓት ቪዛ የተፈቀደለት ብሔራዊ ቡድኑ ምሽቱን በረራ ማድረጉ ተገልጿል፡፡

ቪዛው የተፈቀደው በሻምፒዮናው ላይ ለሚካፈሉ አትሌቶች ብቻ ሲሆን፣ አንድ አሠልጣኝ፣ የማሳጅ ቴራፒስትን ጨምሮ ስድስት ባለሙያዎች ቪዛ መከልከላቸው ተጠቁሟል፡፡

ቅዳሜ የካቲት 11 ቀን በአውስትራሊያ ባቱረስት ከተማ የሚከናወነው 44ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ከፍተኛ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች ደምቀው የሚታዩበት በዚህ ሻምፒዮና አገሮች ከ48 አገሮች 453 አትሌቶች ተካፋይ ይሆናሉ፡፡

እ.ኤ.አ. 2020 እና 2021 በ5,000 ሜትር 14፡06፡62 በማጠናቀቅ 10 ሺሕ ሜትር 29፡01፡03 በመግባት የዓለም ክብረ ወሰን በእጇ መጨበጥ የቻለችው ለተሰንበት ግደይ፣ በሻምፒዮና ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች ስሟ ይጠቀሳል፡፡ የ24 ዓመቷ ለተሰንበት በአዋቂ ሴቶች ትካፈላለች፡፡ እ.ኤ.አ. 2015 እና 2017 ከ20 ዓመት በታች በተከታታይ ማሸነፏ ይታወሳል፡፡

ለተሰንበት በጃንሜዳው ሻምፒዮና ካሳየቸው ድንቅ ብቃት አንፃር በዓለም ሻምፒዮናው ላይ ወርቅ ልታሳካ እንደምትችል ከፍተኛ ግምት አግኝታለች፡፡

በሌላ በኩል ሌላዋ ኢትዮጵያዊት በግማሽ ማራቶን 1፡06፡37 የራሷን ምርጥ ሰዓት ያሳካች፣ እንዲሁም በቅድመ ማጣሪያው የጃንሜዳ ውድድር ሁለተኛ ደረጃን  ይዛ ያጠናቀቀች ጌጤ ዓለማየሁ ተጠባቂ ነች፡፡

ኤርትራዊቷ ራሔል ዳንኤል ኢትዮጵያውያንን አትሌቶችን ሊፈትኑ ከሚችሉ አትሌቶች መካከል ቀዳሚ ግምት የተሰጣት አትሌት ነች፡፡

አትሌቷ ዘንድሮ ስኬታማ ጊዜ እያሳለፈች ሲሆን፣ በ5,000 ሜትር ብሔራዊ ሪከርድ በመጨበጥ 14፡36፡66፣ እንዲሁም በ10 ሺሕ ሜትር 30፡12፡15 በማጠናቀቅ በኦሪገን ዓለም ሻምፒዮና አምስተኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡

ኬንያዊቷ ቢትሪሲ ቺቤት ሌላዋ የምሥራቅ አፍሪካ ተቀናቃኝ አትሌት ናት፡፡ ኬንያዊቷ አትሌት በዓለም ሻምፒዮናው በ5,000 ሜትር የብር ሜዳልያ ማሳካት የቻለች ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. 2019 የዓለም አገር አቋራጭ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮን መሆኗ ከፍተኛ ግምት እንዲሰጣት አስችሏታል፡፡

በአዋቂ ወንዶች ሰለሞን ባረጋ፣ በሪሁ አረጋዊ እንዲሁም ጌትነት ዋለ ይጠበቃል፡፡ በሻምፒዮናው እንደሚሳተፍ ተገልጾ የነበረው ታደሰ ወርቁ በጉዳት ምክንያት ከስብስቡ ውጪ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በታዳጊዎች ተስፋ የተጣለባቸው አዳዲስ አትሌቶች በሁለቱም ፆታ ይጠበቃሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...