በደቡብ ክልል አርባ ምንጭ፣ ወልቂጤ እንዲሁም ቡታጅራን ማዕከል በማድረግ መንግሥት ያስቀመጠውን አቅጣጫ በመከተል የዘይት አቅርቦት ላይ ተሰማርተው ቆይተዋል። እንደ ዛሬው የሲሚንቶ እጥረት ባልነበረበት ወቅት በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች በማከፋፋል ሥራ ላይም ይታወቃሉ፡፡ በኮንስትራክሽን ዘርፍ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንዲሁም በአዲስ አበባና አዲስ አበባ ዙሪያ የተለያዩ ግንባታዎችን አከናውነዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች ጋር በመሆን በርካታ ትምህርት ቤቶችን ገንብተዋል። በቅርቡም በቡልቡላ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ቦታ ተረክበው የዘይት ፋብሪካ እየገነቡ ይገኛሉ። ባለሀብቱ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ከመሳተፍ በላይ በኢትዮጵያ አለመረጋጋቶች በነበረ ወቅት በማሸማገል አገልግለዋል፡፡ በበጎ አድራጎት ሥራዎች የሚታወቁት ሐጂ ቶፊክ ከድር ቲኢኬ ቢዝነስ ግሩፕ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ በንግድና በኢንዱስትሪ ዙሪያ ያላቸውን እንቅስቃሴ አስመልክቶ ዳዊት ቶሎሳ አነጋግሯችዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው እንደነበር ይገለጻል፡፡ በክልሉ ወደ ንግዱ ዓለም የገቡበትን አጋጣሚ አስታውሱን?
አቶ ቶፊክ፡- ከበርካታ ውጣ ውረድ በኋላ የቡና ንግድና የተለያዩ ጥቃቅን ሥራዎችን ከባለቤቴ ጋር እየተረዳዳን ስንሠራ ነበር፡፡ ለረዥም ዓመታት በተለያዩ ንግዶች ላይ ጠንክረን ከሠራን በኋላ በ1993 ዓ.ም. ንግድ ባንክ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ላይ ለጨረታ ያቀረበውን ቦታ በ30 ሺሕ ብር በመግዛት ቦታው ላይ በከተማው የመጀመርያውን ሕንፃ መገንባት ቻልን። ሕንፃውን ለክልሉ ወጣት ማሠልጠኛነት አከራይተን ሥራዎቻችንን እያሰፋን ሄድን፡፡ በ1996 ዓ.ም. የኮንስትራክሽን ፈቃድ በማውጣት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የሚገኙ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች በሚያወጡት የሥራ ጨረታ በማሸነፍ በርካታ ትምህርት ቤቶችን መገንባት ችለናል። ሙያችንን በአገር ውስጥ እንዲሁም በውጭ አገር በሥልጠና እያዳበርን በኮንስትራክስሽን ዘርፍ ለአምስት ዓመታት የዘለቀ ሥራ ሠርተናል። ከ2000 ዓ.ም. ወዲህ ወደ አዲስ አበባ ገብተን ሥራችንን እያስፋፋን ዛሬ ላይ ደርሰናል።
ሪፖርተር፡- በቅርቡ በተገነባው የቡልቡላ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ውስጥ ቦታ ተረክበው የዘይት ፋብሪካ እየተከሉ ይገኛሉ፡፡ ወደ ዘይት ኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዴት ገቡ?
አቶ ቶፊክ፡- መንግሥት በአገር ወስጥ ለሚገኙ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዲሰማሩ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኩል ጥሪ አቀርቦ ነበር። በወቅቱ እኔ አገር ውስጥ አልነበርኩም። በአንፃሩ ቢሮዬ ተጋባዥ ነበር። ምንም እንኳ በአገር ውስጥ ባልኖርም እያንዳንዱ ዝርዝር ይደርሰኝ ነበር። በዘርፉ ብሰማራ ምን ያህል ውጤታማ መሆን እችላለሁ የሚለውን ማጤን ጀመርኩ። አማካሪዎቼና የተለያዩ ሰዎች ይቅርብህ የሚል አስተያየት ሰጡኝ። በመጨረሻም ኢንዱስትሪያል ፓርኩ ውስጥ ለመግባት ወሰንን። ለስምንት ባንኮች የምንሠራውን ሥራ አብራርተንና የሦስት ባንክ ፕሬዚዳንቶች ጋር ተወያይተን ከብሔራዊ ባንክ የመጀመርያውን ክፍያ ተፈቅዶልን ማሽን ተከላ ጀመርን።
ሪፖርተር፦ በቡልቡላ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ውስጥ ቦታ ተረክባችሁ የዘይት ፋብሪካው የግንባታ ሒደትና የምርት ዓይነቶች ቢያብራሩልን?
አቶ ቶፊክ፦ አምስት እህት ኩባንያዎች ሆነን ነው ወደ ኢንዱስትሪያል ፓርኩ የገባነው፡፡ ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት ለማድረግ አቅደናል፡፡ ለጊዜው በፓርኩ ውስጥ በአምስቱም እህት ኩባንያዎቹ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ ተሰማርተን ለመሥራት ስድስት ሚሊዮን ዶላር የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ብሔራዊ ባንክ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ፈቅዶልን፣ አንዳንድ ግዥዎችን ፈጽመናል። ከዚህም በተጨማሪ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የተነሳንበትን ዓላማና በተለይ ለአርሶ አደሩ የሰጠነውን ትኩረት ካጤነ በኋላ 285 ሺሕ ዶላር ተፈቅዶልናል። በፋብሪካው በተለይ ለመድኃኒትነት የሚለውን ደረጃውን የጠበቀ የጥቁር አዝሙድ ዘይት ለማሌዥያ፣ ለአሜሪካ፣ ለሳዑዲ ዓረቢያ እንዲሁም ለዱባይ ለማቅረብ ተነጋግረናል። የመጀመሪያ ምርትም በ2016 ዓ.ም. ሰኔ መጨረሻ ላይ ይቀርባል ብለን አቅደናል። ሌላው የአኩሪ አተር ሲሆን ምርቱን ፕሮሰስ በማድረግ ዘይቱን እንዲሁም ዱቄቱን ለተለያዩ ፍጆታነት ለማዋልና በተለያዩ የዓለም አገሮች ለማቅረብ ተነጋግረናል።
ሪፖርተር፦ በርካታ ባለሀብቶች በተመሳሳይ የሥራ ዘርፍ ላይ ለመሰማራት ምንዛሪ ከተፈቀደላቸው በኋላ፣ በተደጋጋሚ በቂ የግብዓት አቅርቦት ችግር እንዳለ ሲያነሱ ይስተዋላል። እርስዎ ይህንን ችግር እንዴት ሊቀርፉት አቅደዋል?
አቶ ቶፊክ፦ እኛ ወደ ኢንቨስትመንቱ የገባነው ዶላርን ፍለጋ ወይም መኪና እያስመጡ ለመሸጥ አይደለም። አርሶ አደሩን ለማነቃቃትና ለመቀየር ነው። ይህንን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሠርተን የምናረጋግጠው ይሆናል። ከግብዓት ጋር በተያያዘ ግብርና ሚኒስቴር ለኦሮሚያ ክልል፣ ለአማራ ክልልና ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ደብዳቤ ጽፎልናል። ክልሎችም ተግባራዊ አድርገውት ግዥም ጀምረናል። በመጀመሪያ ዙር 120 ሺሕ ኩንታል አኩሪ አተር ከገበሬው ለመሰብሰብ አቅደናል። በቀጣይ ደግሞ በሦስቱ ክልሎች የእርሻ መሬት ተረክበን ኑግ፣ ሰሊጥና አኩሪ አተር ለማልማት ዕቅድ አለን።
ሪፖርተር፦ አሁናዊው የንግድ እንቅሰቃሴ በርካታ ችግሮች የሚስተዋሉበት ከመሆኑም በላይ፣ የምግብም ሆነ የግንባታ አቅርቦት በችግሮች የታጠረ ነው። ችግር ምንድነው ይላሉ?
አቶ ቶፊክ፦ የንግድ ሥርዓቱ በርካታ ችግሮች ያሉበት ነው። በተለይ የሰው ልጅ ለዕለት ተዕለት የሚጠቀምበት ለምግብና ለግንባታ ፍጆታነት የሚውሉ እንደ ሲሚንቶ ያሉ ምርቶች ከፖለቲካ ጉዳዮች ነፃ መሆን አለባቸው። እነዚህ ጉዳዮች በነፃ ገበያ መስተናገድ አለባቸው። ለምሳሌ የሲሚንቶ ገበያ በነፃ ገበያ ባለመስተናገዱ ዋጋው ሊንር ችሏል። በአንፃሩ በነፃ ገበያ ይገበያይ ሲባል ዋጋው ከ2,200 በአንድ ጊዜ ወደ 1,400 መውረድ ችሏል። ይህ በቂ ነው ማለት ሳይሆን፣ ዕርምጃው ግን የሚበረታታ ነው። በሒደት ደግሞ ሌሎቹም ላይ ተመሳሳይ ጥናት በማድረግና በመወያየት ሁሉንም እያሻሻሉ መሄድ ይቻላል የሚል እምነት አለኝ።
ሪፖርተር፦ ከኢንቨስትመንቱ ባሻገር በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ ምን እየሠሩ ነው?
አቶ ቶፊክ፦ በኢትዮጵያ በተለይ ባለፉት ዓመታት ከፖለቲካ ጋር ተያይዞ አለመረጋጋት በነበረበት ወቅትና ከለውጡ በፊት ጀምሮ በአሸማጋይነቴ እታወቃለሁ። በአንፃሩ ኢትዮጵያ ወደ ጦርነት መግባቷን ተከትሎ፣ ሰብዓዊ ሥራዎችን ስንሠራ ቆይተናል። በጦርነቱ በአፋርና በአማራ ክልሎች ላይ የተጎዱትን ዜጎች ለመርዳት በንግድ ባንክ አካውንት ከፍተን መንቀሳቀስ ጀመርን። ከራሴ ጀምሮ ገንዘብ ማሰባሰብ ጀመርን። ሰብዓዊ ዕርዳታ አሰባሰብን፡፡ ለአፋር ክልል ከተለያዩ የቁሳቁስ ድጋፎች ውጪ በጥሬ አምስት ሚሊዮን ብር እንዲሁም በአማራ ክልል ምግብ ነክ ድጋፎች ጋር በጥሬ አሥር ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገናል። ከዚህ በኋላም ዜጎቻችን ለመርዳት ሁሌም ዝግጁ ነኝ።