የዛሬው መንገዳችን ከመገናኛ ወደ ኮተቤ ነው። የተሳፈርንበት ሚኒ ባስ ታክሲ ውስጥ መካከለኛው የጥንዶች ረድፍ ላይ፣ አባት የልጁን የፈተና ወረቀት ዘርግቶ ‘ኤክሶቹን’ ይቆጥራል። ልጅ አብዛኞቻችን የዕድሜ ልክ ደመወዛችን ቢደመር የማይሸምተው፣ ከፍሬው ቀድመን ያወቅነውን አፕል ስልክ የመጨረሻ ምርት ይዞ ጌም ይጫወታል። ‹‹…እንዴት ይኼን ትሳሳታለህ?›› አባት በድንገት ወደ ልጁ ተቆጥቶ ዞረ። ልጅ ቀናም አላለ። ‹‹የቱን?›› በሚጫወተው ጌም በለስ ከቀናው ቦምብ እያፈነዳ ይጠይቃል። ‹‹ይኼኔ ይህንን የመሰለ ስልክ ዳያስፖራ ወንድም ወይም እህት እንጂ ይህ ምስኪን አባት ገዝቶለት አይደለም አይደል?›› ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመች ደርባባ ወይዘሮ ትጠይቀኛለች። ‹‹በዚህ የኑሮ ውድነት እንኳን አይፎን ፕሮማክስ ተራ ስልክ ለመግዛት እኮ ወገቤን ያስብላል…›› ይመልሳል መሀል ወንበር የተቀመጠ ወጣት፡፡ አባትና ልጅ እርማቱን ሆድና ጀርባ ሆነው ቀጥለዋል፡፡ ዘንድሮ ሁሉም ነገር ሆድና ጀርባ ከሆነ ቆየ እኮ!
‹‹አንተን እኮ ነው የማናግረው፣ ይኼን እንዴት ‘ኤክስ’ ልትሆን ቻልክ?›› አባት ብስጭቱ ጨምሯል። እግዜር ባርኮለት ምንም እንኳ በሁለተኛው ዙር ቢሆንም ልጁም ደነገጠለት። ‹‹መቼ ያሳፍራል የእሱ ስጦታ ከሆነ?›› ብሎ ያጉተመተመውን ተሳፋሪ ልለየው አልቻልኩም። ‹‹አባዬ እኔ ልክ ነኝ፣ አስተማሪው ነው የተሳሳተው…›› ልጅ በኩራት አባቱን ያስረዳዋል። ‹‹ጥያቄው ‘ገፀ ባህሪያት ቀርፀን ታሪክ ስንጽፍ ስንት ዓይነት የግጭት ዓይነቶችን መጠቀም እንችላለን?’ ነው የሚለው። መልሱ ‘ሰው ከሰው ጋር፣ ሰው ከራሱ ጋር፣ ሰው ከተፈጥሮ ጋርና ሰው ከፈጣሪ ጋር’ ነው። አስተማሪው ግን ‘ሰው ከፈጣሪ ጋር’ አልክ ብሎ ‘ኤክስ’ ሰጠኝ…›› ብሎ እንዳበቃ፣ ‹‹ተባረክ ልጄ፣ ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ ማለት አንተ ነህ። ስንቱ ከፈጣሪ ተጣልቶ እንዳይሆኑ ሲሆን፣ ስንቱ ፈጣሪን አልፈራ ብሎ ምስኪኖችን ሲያሰቃይ እያየ ያንተን መልስ ‘ኤክስ’ ካደረገ መምህሩ መገምገም አለበት…›› ብላ ወይዘሮዋ ደነፋች። ይኼ ዘመን ስንቱን ያሳየናል!
ጉዟችን ከተጀመረ ጥቂት ደቂቃዎች አምልጠዋል። ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየመ ጎልማሳ ያዙኝ ልቁኝ እያለ ነው። ‹‹ኧረ እባካችሁ አገር ስጡኝ ተው? የት ሄጄ ልፈንዳ በፈጣሪ?›› እያለ ይወራጫል። ‹‹ኧረ ቀስ፣ በተረጋጋ ቀጣና ውስጥ ምንድነው እንደዚህ ማተራመስ?›› ወይዘሮዋ ናት። ‹‹ምንድነው የሚለው? የት አለና ነው እንቆቅልሹ አገር ስጡኝ የሚለን?›› ይኼን የምትለው ከኋላ ከተደረደሩት መካከል አንዲት የቀይ ዳማ ናት። ‹‹አይ እንቆቅልሹንስ ተይው። እንዲያው ለእንቆቅልሾቻችን የሚበቃ አገር አለ እንዴ?›› እያለ በከፊል ደመናማ የአየር ፀባይ ላብ የሚያጠምቀው ህያው ገፀ ባህሪ ከጎኗ ያሽሟጥጣል። ‹‹ተልባ ቢንጫጫ በአንድ ሙቀጫ ተብሏል። እንቆቅልሾቻችን የበለጠ ሲወሳሰቡ እንጂ ሲፍታቱ አይታዩም። ከዚህ በላይ ምን ይምጣ?›› ሲል ጋቢና መሀል ላይ የተቀመጠ ወጣት ዞሮ ታክሲያችንን በምትሃት ወደ ክብ ጠረጴዛነት የተቀየረች መሰለች። ያዝ እንግዲህ!
‹‹ዓይኔ ነው ጆሮዬ?›› ትላለች ከጎልማሳው አጠገብ የተቀመጠችው ደግሞ ተደናግራ። ‹‹ምን የሆነው?›› ጎልማሳው መወራጨቱን ቀነስ አድርጎ ሲጠይቃት፣ ‹‹በአንዴ እንቆቅልሹን በፖለቲካ ፈቶ ያሳየኝ ወይ ያሰማኝ ነዋ?›› ስትለው ቀልደኛው ጎልማሳ፣ ‹‹የለም! የለም! የአላዲንና የፋኖሱ ነገር ነው። ሳናስበው ዴሞክራት፣ ስናስበው ደግሞ አውቶክራትና ታይራንት የሚያደርገን፣ የአላዲንና የፋኖሱ ጂኒ ነው…›› ይላታል። ‹‹ዳዲ ጂኒ ምንድነው?›› ሲል ብላቴናው ጌሙ ላይ እንዳፈጠጠ ዓይኑን ከስልኩ ባትሪ እኩል እያዳከመ ይጠይቃል። ‹‹ወጋ… ወጋ… ጠቅ… ጠቁ… ተራ ወሬ ቢመስልም ሰውን ግን ያስተነፍሰዋል። ታክሲ ሳንባን የመተካት አቅም እንዳለው ሳይንስ ደርሶበት ይሆን? እንጃ!
ቀዘዝ ያለው ወያላችን ነገረ ሥራው ሁሉ ዝግ ያለ ነው። ‹‹አንተ እንኳንም ‘ቪዛ’ ሰጪ አልሆንክ…›› ትለዋለች ከጀርባ። ‹‹እውነት ነው፣ ቆይ አንተን እንደ ምንም ብዬ በዘመድም ቢሆን ክፍለ ከተማ ማስቀጠር አለብኝ…›› ስትል ደግሞ ከጎልማሳው አጠገብ ያለችው ትቀልዳለች። ‹‹እንዴ በዘመድ መቅረት አለበት አልተባለም እንዴ?›› መሀል ላይ የተሰየመው የብላቴናው አባት ልሳኑ ተከፈተ። ‹‹ቢባልም አይተገበርም፣ ቢተገበርም አይዘልቅም በሚል ለምን አንይዘውም?›› ልጅት ፈገግታዋ ከፊቷ ላይ ሳይከስም ጨዋታውን አደራችው። ‹‹ለምን እንይዘዋለን እንዳንቺ ዓይነቷን ነው እንጂ ማስያዝ…›› ሰውዬው የምሩን ነው። ልጅት ቀልድ ያለችው መምረሩ ሲገባት ፊቷን አዙራ ድምጿን አጠፋች። ወዲያው መሀል የተሰየመችው ወይዘሮ ባረጋጋው ብላ ነው መሰል፣ ‹‹እንደ እሷ ያለውን ከማስያዝ አንደኛውን አገሪቱን ማስያዝ አይቀልም ብለህ ነው?›› ብሎ ሳቁን ለቀቀው፡፡ የውሸት ሳቅ!
‹‹ወያላው እስቲ አርቴፊሻል ሳቃችን የሚለውን ዘፈን ጋብዘን…›› መጨረሻ ላይ ካሉት ጓደኛማቾች አንደኛው ነው። ወይዘሮዋ ግን ያሰበችው ተሳክቷል። ‹‹ልክ ነሽ፣ እንክርዳዱ ማሳውን ሞልቶት እሱን ከፍሬው መለየት ምን ያህል አድካሚ መሆኑን የሚያውቀው የገባው ነው…›› ብሎ ሰውዬው ተንፈስ አለ። ‹‹እንዴት ነው ነገሩ ጎበዝ? ‘ እናት አባት ቢሞት በአገር ይለቀሳል፣ አገር የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል?’ ብለን መስሎኝ ያደግነው? ፍሬውስ ጎተራ ሳይኖር ተመርጦ ቢታጨድ ምን ይረባል?›› ብሎ ጎልማሳው ገባበት። ‹‹ምን እናድርግ ጠፍቶን መሰለህ እሱ?›› ሲለው ሰውዬው ጎልማሳው ይመልሳል ብለን ስንጠብቅ፣ ‘8100’ በጩኸት አቋርጦት ገባ። ‹‹የህዳሴ ግድባችንማ የፈለገው ቢሆን ዕውን ይሆናታል እንጂ ወደኋላ ብሎ ነገር አይታሰብም…›› እያለ ተሳፋሪው ሞባይሉን አውጥቶ መዋጮውን ጠቀጠቀ። የሞት ሽረት ማለት ይኼም አይደል? በሚገባ!
ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ሾፌራችን እስኪያወርደን ከመቸኮሉ የተነሳ መንገዱ ሲዘጋጋበት እግረኛው መንገድ ላይ ተጠምዝዞ ወጥቶ ‘ቼ’ ይላል። ‹‹አሁን ምናለበት መንገድህን ይዘህ ብትነዳ? አናልቅ አልናችሁ አይደል? በዚህ እናንተ አላችሁ፣ በዚያ ጉልበተኞች ያናፋሉ፣ ዘንድሮ ጉንፋንም በአቅሙ የ13 ወራት ደዌ ሆኖ ሥራ አላሠራን ብሏል። ‘በሞቴ አፈር ስሆን’ ቀርቶ ‘በኩላሊቴ ይዤሃለሁ’ ማለት እስክንጀምር ይኼው ኩላሊት ማሳጠቢያ አጥቶ ወገን ይረግፋል። የልብስ ማጠቢያ ሳሙና መግዛትም አልሆነልን እንኳን ኩላሊት ልናሳጥብ…›› ወይዘሮዋ ትለዋለች። ‹‹ምን ይደረግ? የዚህ ዓለም ነገር ይኼው ነው። አንዱ ሲመጣ አንዱ ይሄዳል። ዓለም ሐዘን ሲለመድ ዕንባ እንደሚደርቅ አውቃ በሽታውን፣ መጥፊያ መክሰሚያውን ትለዋውጠዋለች…›› ጎልማሳው ነው ከንፈር እየመጠጠ የሚያስተክዘው። ድንገት ዘወር ሲባል ‘ወገንን ያለ ስስት ማብላት ጀምረናል’ የሚል ማስታወቂያ የተጻፈባት ያዘመመች ቤት አየንና ዓይናችንን ማመን ቢያቅተን ወያላው፣ ‹‹ወገን ተረጋጉ፣ በቅናሽ ዋጋ ግቡና ብሉ ነው የተባለው…›› ብሎ አረጋጋን። ይሻላል!
‹‹እና ስም አልቆባቸው ነው ‘ወገንን ያለ ስስት ማብላት ጀምረናል’ የሚሉት?” ሲለው ጋቢና የተሰየመው፣ ‹‹በዚህ ጊዜ ከዚህ የበለጠ ድንቅ ስያሜ ምን አለ? ስስት አይደል እንዴ ደህናውን ሁሉ ሰይጣን ያደረገው? ሥልጣን በሉ ሀብት፣ ክብር በሉ ዝና በስስት ተወረው አይደል እንዴ መላ ቅጣችንን ያጣነው? እዚህ ምግብ ቤት ሁለት ጥብስ ፍርፍር በላይ በላዩ ጭማሪ እየተደረገ ለአራት አጥቅታችሁ ጥግብ ብላችሁ ሻይ ቡና፣ አምቦ ውኃ ውኃ አክላችሁ 145 ብር ከከፈላችሁ ምን ትፈልጋላችሁ?›› ሲል ወያላው ተሳፋሪዎች የተመካከሩ ይመስል በአንድነት፣ ‹‹ወራጅ…›› ብለው ከመቀመጫቸው ተነሱ። ጎልማሳው ብቻ ከመቀመጫው ንቅንቅ ሳይል፣ ‹‹ቅድም ምን ስትሉ ነበርና ነው አሁን እንዲህ የሚያደርጋችሁ?›› ብሎ ተቆጣ። ‹‹ቅድም የዓለም ሴራዋ፣ በሽታዋ፣ ሥቃይዋ፣ ጦርነቷ፣ ስደቷ፣ ፍትሕ አልባነቷ፣ ወዘተ. ምን ያላላችሁት ነበር። አሁን ደግሞ ዓለም አታላይ ሆዬ ‘ይውጋሽ ብላ በይማርሽ’ ሥልቷ ምግብ በቅናሽ በእጅ አዙር ስታቀርብ ትሻማላችሁ? የወጋ ቢረሳ የተወጋም ይረሳ?›› ብሎን አረፈው። ‹‹ቆይ ግን በየመንገዱ ቂም ይዘን፣ ባለፉት ሥርዓቶች ቂም ይዘን፣ በፍትሕና በዴሞክራሲ ዕጦት፣ በሐሳብ አፈናው ካሁኖቹ ጋር ሳይቀር ተኮራርፈን፣ በሃይማኖት ጣልቃ ገብነት ተካሰን፣ ይኼ ሁሉ አልበቃን ብሎ ደግሞ በዓለም ላይ ቂምና ኩርፊያ? ጉድ ሲንተከተክ እንዲህ ነው ይኼውላችሁ…›› ብላ ያቺ ወይዘሮ የጉዞውን ማጠናቀቂያ ትችት ስታቀርብ ተግተልትለን ወረድን፡፡ መልካም ጉዞ!