Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የስንዴ ምርት ኤክስፖርት ጅማሮና የአገር ውስጥ ዱቄት አምራቾች ዕሮሮ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዓለም አቀፍ ደረጃ የስንዴ ምርት ፍላጎት በእጅጉ በጨመረበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ ስንዴን ለዓለም ገበያ ማቅረብ መጀመሯን በይፋ አሳውቃለች፡፡ በኢትዮጵያ በስንዴ አምራችነት ከሚታወቁት አካባቢዎች አንዱ በሆነው ባሌ ዞን ተገኝተው ኢትዮጵያ የስንዴ ምርትን በይፋ ወደ ውጭ ገበያ ልትልክ መሆኑን ያበሰሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ይህ የስንዴ ኤክስፖርትም አዲስ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማግኛ እንደሚሆን ተናግረዋል።

‹‹ኢትዮጵያ ስንዴ ከውጭ አታስገባም የሚለው ራዕይ ለብዙዎች የሚዋጥ አልነበረም፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ ማኅበረሰቡም ሆነ በርካታ የመንግሥት አመራሮች ይህንን ሐሳብ ተጋርተው ለመሥራት ተቸግረው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ አሁን ግን ይህንን ውጥን ማሳካት ስለመቻሉ በተግባር ማሳየት ተችሏል ብለዋል፡፡  

ይህንኑ መረጃ ተከትሎ የግብርና ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መረጃ ስንዴን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን፣ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ተግባር መሆኑን አስታውቋል። በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታው መለሰ መኮንን፣ ‹‹ራሷን መመገብ የማትችል አገር ተደርጋ ትወሰድ የነበረችው አገር ስንዴን ከውጭ ማስገባት አቁማ ራሷን ችላ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ደረጃ ላይ መድረሷ ሕዝባችን ቀና ብሎ ሊሄድ እንዲችል የሚያደርግ ትልቅ ሥራ ነው፤›› ብለውታል፡፡

ኢትዮጵያ ታሪካዊ የተባለውን የስንዴ ኤክስፖርት (የወጪ ንግድ) በይፋ መጀመሯ አዲስ ምዕራፍ ቢሆንም፣ መንግሥት ስንዴን ኤክስፖርት ለማድረግ የወሰነው የአገሪቱ የስንዴ ምርት ፍላጎት ተሟልቶ ነው? የሚለው ጥያቄ ግን የብዙዎች ነው፡፡ ስንዴን ወደ ውጭ አገር መላክ የተጀመረው በተለይ በ2015 ዓ.ም. የምርት ዘመን ለአገር ውስጥ ከሚያስፈልገው ፍላጎት በላይ ትርፍ ምርት በመገኘቱ ጭምር መሆኑን መንግሥት አስታውቋል፡፡  

ሚኒስትር ዴኤታው መለሰ ሰሞኑን በሰጡት ማብራሪያም፣ ዘንድሮ በመኸር ምርት 112 ሚሊዮን ኩንታል፣ እንዲሁም በመስኖና በበጋ ስንዴ ምርት ደግም 52 ሚሊዮን ኩንታል ይገኛል ተብሎ መተንበዩን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም የተተነበየው የምርት መጠን የአገር ውስጥ ፍላጎት አንፃር ትርፍ ምርት እንደሚገኝ ማመላከቱን ገልጸዋል፡፡ በባለሙያዎች ዝርዝር ጥናት መሠረት በ2015 ዓ.ም. የአገር ውስጥ ፍላጎት 97 ሚሊዮን ኩንታል መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ የፍላጎት መጠኑ ይገኛል ተብሎ ከተተነበየው አጠቃላይ የስንዴ ምርት መጠን ጋር ሲነፃፀር ትርፍ ምርት በመኖሩ 32 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንደሚቻል አስረድተዋል። 

ከሚዲያ ብዙ ርቀው የቆዩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋና የኢኮኖሚ አማካሪና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቦርድ ሊቀ መንበር አቶ ግርማ ብሩም በስንዴ የውጭ ንግድ ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ ስንዴን ኤክስፖርት የማድረግ ውሳኔ በጥናት ላይ የተመሠረተና የአገር ውስጥ ፍላጎትን በማሟላት የሚተገበር መሆኑን ገልጸዋል።

አማካሪው በዚሁ ጉዳይ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ‹‹በመጀመርያ ስንዴ የምናመርተው የራሳችንን ስንዴ ፍላጎት ለማሟላት፣ ቀጥሎ ደግሞ ኤክስፖርት ለማድረግ ስለሆነ፣ በመጀመርያ አንዴ ሳይሆን ሁለት ሦስት ጊዜ አጣርተን እንድናቀርብ ነው የተደረገው፤›› ብለዋል፡፡ ከዓምናው ክረምት የተገኘውና በዘንድሮ የበጋ ምርት የሚሰበሰበውን ጨምሮ አጠቃላይ የዘንድሮ ዓመታዊ የስንዴ የምርት መጠን ከአገሪቱ ሕዝብ ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ፍጆታ አንፃር ተለክቶ የሚተርፈው ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ መወሰኑን ገልጸዋል። በጥሩ ግምት ላይ ተመሥርቶ የሚሰበሰበው የስንዴ ምርት ከአገሪቱ ዓመታዊ ፍጆታን አሟልቶ ወደ 32 ሚሊዮን ኩንታል እንደሚተርፍ ተረጋግጦ ወደ ተግባር መገባቱንም አስረድተዋል፡፡ የግብይት ሒደቱም ከተለያዩ አገሮች ጋር የተደረገ በመሆኑ፣ የገበያ ችግር እንደሌለም አቶ ግርማ ገልጸዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ ታሪካዊ የተባለውን የስንዴ የወጪ ንግድ ጅማሬዋን እንዲህ ያሉ ሰፊ ማብራሪያዎችና ትንታኔዎች የተሰጡበት ቢሆኑም፣ ካለፉት አምስትና ስድስት ሳምንታት ወዲህ ግን የስንዴ ገበያ ችግር ውስጥ እንደገባ እየተነገረ ነው፡፡ በተለይ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች በዚህ የመኸር ወቅት በከፍተኛ ደረጃ ሲጠበቅ የነበረ የስንዴ ምርት ገበያ ላይ ማግኘት አልተቻለም፡፡ ከተገኘም ዋጋው በአንድ ኩንታል ከአንድ ሺሕ ብር በላይ ጭማሪ ማሳየቱ ተጠቅሷል፡፡ 

ከ220 በላይ አባላት ያሉት የዱቄት አምራቾች ማኅበር እንዳመለከተውም፣ የስንዴ ዋጋ በሚረክስበትና በአብዛኛው ዱቄት፣ ብስኩት፣ መኮሮኒና መሰል ምርቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ስንዴውን የሚሰበስቡት በዚህ ወቅት ቢሆንም፣ ምርቱን ማግኘት ተቸግረዋል፡፡ 

የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉነህ ለማ እንደሚገልጹት፣ ለዱቄትና ተያያዥ ምርቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ስንዴን ገበያ ላይ ማግኘት ካቆሙ ከአምስት ሳምንታት በላይ ሆኗቸዋል፡፡ በተለይ አዲስ አበባ ውስጥ ያሉት ፋብሪካዎች በየዓመቱ እንደሚያደርጉት በዚህ ወቅት ከአዲስ አበባ ከተማ ገበያ ስንዴ ማግኘት ባለመቻላቸው ብዙዎቹ ዱቄት ማምረት ወደማቆም እየገቡ ነው፡፡ በተለይ ከፍተኛ የስንዴ ምርት ከሚመረትበት የኦሮሚያ ክልል እንደቀድሞው ስንዴ እንዳይገባ መከልከሉ ለችግሩ መባባስ ምክንያት መሆኑም ተገልጿል፡፡

ይህ ያልተጠበቀና ያልታሰበ የስንዴ የማግኘት ችግር ከታወቀ ወዲህ ማኅበሩ ምክንያቱን ለማወቅ ያደረገው ጥረት ብዙም ውጤት ስላላመጣ ሁኔታው በእጅጉ እንዳሳሰባቸውም ፕሬዚዳንቱ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡  

እንደ አቶ ሙሉነህ ገለጻ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ425 በላይ የሚሆኑ የዱቄት አምራቾች ያሉ ሲሆን፣ የስንዴ እጥረቱ በአዲስ አበባ የሚገኙትን ብቻ ሳይሆን፣ በክልል ከተሞች የሚገኙ ዱቄት አምራቾችን እየፈተነ መሆኑን ነው፡፡  

‹‹ኢትዮጵያ የስንዴ ምርቷን ማሳደጓን በመስክ ምልከታ ጭምር አረጋግጠናል፤›› የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፣ በዚህ ወቅት የስንዴ ምርት እጥረት እንደማይኖር እርግጠኛ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡ ይሁን እንጂ ከአንድ ወር ተኩል በላይ የስንዴ ግብይት መስተጓጎሉ የማኅበራቸው አባላት የሆኑ የዱቄት አምራቾች ምርቱን ለማግኘት ባለመቻላቸው ሥራ ወደ ማቆም እየገቡና አንዳንዱም በኮንትሮባንድ ይገባል የተባለን ስንዴ በውድ ዋጋ በመግዛት ሥራ ላለማቋረጥ እየሠሩ ስለመሆናቸው ይገልጻሉ፡፡  

ኢትዮጵያ ስንዴን ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሯን በእጅጉ የሚደግፉ ቢሆንም፣ የወጪ ንግዱ የአገር ውስጥ የስንዴ ግብይት ላይ ችግር ይፈጥራል ብለው እንዳልገመቱም አክለዋል፡፡ አሁን ያለው የስንዴ ገበያ ለዱቄት አምራቾች እንቆቅልሽ መሆኑ፣ ጭራሽ በኮንትሮባንድ መልክ በውድ ዋጋ መሸጥ መጀመሩ ለምን የሚል ጥያቄ ከማስነሳቱም በላይ፣ ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ ደግሞ የዱቄት አምራቾች ችግር ውስጥ እንደሚገቡ አስታውሰዋል፡፡ ከዱቄት አምራቾቹ ተረክበው ዳቦና ተያያዥ ምርት የሚያመርቱ ተቋማቶችም አገልግሎታቸውን ሊያስተጓጉል ይችላል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ፕሬዚዳንቱ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ 

‹‹እኛ እንደተረዳነው፣ ኅብረተሰቡም እንደሚያውቀው አገራችን ስንዴን ኤክስፖርት ታደርጋለች የሚል መርሐ ግብር ተይዞ እየተሠራበት ነው፡፡ ጥሩ ውጤትም እየታየበት ነው፡፡ በዚህ ዓመት በአገር ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ ምርት ተመርቷል፤›› የሚሉት አቶ ሙሉነህ፣ ምርቱ በጥሩ ሁኔታ ተመርቶ ኸርቨስቲንግ ታይም ላይ ቢሆንም፣ ለአገር ውስጥ አምራቾች መቅረብ የነበረበት የስንዴ ምርት ግብይት ላይ ግን ለምን ችግር እንደተፈጠረ ግልጽ ሊሆንላቸው እንዳልቻለ ያመለክታሉ፡፡

በእርግጥ ኢትዮጵያ ስንዴን ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደተጀመረ ከአንድ ወር ተኩል በፊት እንደተነገራቸው ያስታወሱት አቶ ሙሉነህ፣ የአገር ውስጥ ግብይት ሒደቱን መተመለከተ ግን ግልጽ መረጃ ማግኘት እንደተቸገሩ ይገልጻሉ፡፡ በእኛ ግምት ከኤክስፖርት የሚሆን ምርት እስኪሰበሰብ ድረስ ከኦሮሚያ አካባቢ የሚመጣ ስንዴ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገባ መደረጉ በቀጣይስ እንዴት ምርቱን እናድናገኝ ሊያደርጉ ነው? የሚለው ጉዳይ እንደሚያሳስባቸው ያመለክታሉ፡፡ ከኦሮሚያ የሚገባው ስንዴ በድንገት በመቋረጡ ምክንያት በአንድ ወር ተኩል ጊዜ ውስጥ የስንዴ ዋጋ እንዲጨምር ሆኗል፡፡ እሱም ገበያ ላይ ከተገኘ የሚገዛ ሲሆን፣ ምርቱ ይረክሳል በሚባልበት ወቅት  እንዲጨምር ምክንያት ሊሆን ችሏል፡፡ አብዛኛዎቹ ፋብሪካዎች ምርት ካቆሙ ከአንድ ወር በላይ ያስቆጠሩ በመሆኑ ወደ 50 ፋብሪካዎች የሥራ መሪዎች ተሰብስበው የሚመለከተውን መሥሪያ ቤቶች ለማነጋገር የተደረጉ ጥረቶችም ውጤት አላመጡም፡፡ በተለያዩ መንገዶች ምርቱን ሲያገኙ የነበሩና በእጃቸው ላይ ምርት የነበራቸውም አሁን ላይ ሥራ ወደ ማቆም በመግባታቸው፣ በሌላ ሥራ ሠራተኞችን ይዘው ለመቀጠል ሊፈተኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹እኛ ስንዴ የምንሰበስበው በዚህ ወቅት ነው፡፡ እስከ ክረምት የሚያበቃንን ስንዴ የምንገዛበት ወቅት ነበር፡፡ ለውጭ የሚቀርበው ምርት ከተከለከለ በኋላ ለአገር ውስጥ አምራቾች የሚሆነው መቼ ያልቅልናል እያልን እየጠበቅን ነው፡፡ ለውጭ ንግዱ የሚያስፈልገው ምርት ከተሰበሰበ በኋላ የአገር ውስጥ ግብይቱ ይለቀቅልናል ብንልም ጊዜው እየረዘመ መምጣቱ ግን አሳስቦናል ይላሉ፡፡  

ፋብሪካዎች ከዚህ ቀደም በነበራቸው ልምድ በምርት ወቅት፣ በተለይ ከኅዳር ጀምሮ የሚሰበስቡት ስንዴ ከተያየ አቅጣጫ ይመጣ እንደነበር ከጎጃም፣ ከአዋሽ፣ ከባሌ፣ ከአርሲና ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመረተውን ስንዴ ምርቱ እንደደረሰ እንሰበስባለን፡፡ ብዙው የሚኘው ከባሌ ነው፡፡ አሁን የተያዘብንም ከዚህ አካባቢ ያለው ስንዴ ነው፡፡ ሌላም አማራጭ እያገኘን ባለመሆኑ ተቸግረናል ይላሉ፡፡  

አሁን የተፈጠረው የስንዴ ግብይት መስተጓጎል ከሰሞኑ ለዱቄት ዋጋ መወደድ ምክንያት እንደሆነም ነው፡፡ አንድ ኪሎ ዱቄት ዋጋ እስከ 85 ብር እየተሸጠ ለመሆኑ አንዱ ምክንያት፣ ፕሬዚዳንቱም አንድ ወር ተኩል ምርቱ ወደ አዲስ አበባ እየገባ ባለመሆኑ ዋጋው ሊወደድ መቻሉ ተጠባቂ ነው ይላሉ፡፡ 

ምክንያቱም በኮንትሮባንድ የሚገባውም ቢሆን 4,700 ብር ይሸጥ የነበረ አንዱ ኩንታል እስከ 5,700 እየተሸጠ በዚህ ዋጋ የተገዛ ስንዴ ዱቄት ሆኖ ለዳቦ ቤቶች እያቀረበ ያለው አንዱ ኩንታል ዱቄት ከ7 ሺሕ ብር በላይ ነው፡፡ ስለዚህ የስንዴ ግብይት ጉዳይ አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠለ የዳቦ አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችላል የሚል ሥጋት አላቸው፡፡  

ይህም ቢሆን ግን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ፣ በድጎማ መልክ ለእነ ሸገርና ከረዩ ዳቦ ፋብሪካዎች የሚያቀርበውን ስንዴ አንዳንድ ፋብሪካዎች እየፈጩ ነው፡፡ ለመከላከያ የሚፈጭ አለ፡፡ ይህንን በመፍጨት ከሚንቀሳቀሱ ውጪ በአቅሙ እየሠራ ያለ ዱቄት ፋብሪካ የለም፡፡ 

ማኅበሩ ችግሩ ከተከሰተ ወዲህ እስካሁን ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ለገንዘብ ሚኒስቴርና ለመሳሰሉት በደብዳቤ እያሳወቀ ሲሆን፣ በግንባርም በመሄድ እያደረጉ ያሉት ጥረት ውጤት ያስገኝልናል የሚል እምነት ግን አላቸው፡፡ 

ይህ ያልታሰበ ነው የተባለው የስንዴ ግብይት ችግር መነሾው ግልጽ ባይሆንም፣ አንዱ ምክንያት በተለይ የኦሮሚያ ክልል የስንዴ ግብይቱን በተመለከተ እንዲተገበር ያወረደው መመርያ በአግባቡ ሊተገበር ካለመቻሉ ጋር የተያያዘ መሆኑን ግን ይነገራል፡፡ እንደ አቶ ሙሉነህ ገለጻም በጉዳዩ በአዳማ በተደገ አንድ ስብሰባ ዩኒየኖች ከገበሬው አንዱን ኩንታል ስንዴ  3,200 ብር እንዲገዙ በዚያም አማካይነት ለፋብሪካዎች 3,381 ብር እንዲሸጥ መወሰኑን መስማታቸውን ይገልጻሉ፡፡ 

‹‹እኛም ከየትኛው ዩኒየኖች ጋር ተሳስረን ነው የምንሠራው ብለን ስንከታተል ዩኒየኖች በቂ የሆነ ፋይናንስ ባለማግኘታቸው፣ ከዚያ በኋላ ደግሞ 12 የሚሆኑ ባለሀብቶች ይህንን ግዥ እንዲፈጽሙና ትስስሩም ከእነሱ ጋር ይደረግላቸዋል የሚል በወሬ መስማታቸውን ነው እንጂ በደብዳቤ የተሰጠ ነገር የለም፡፡  

‹‹ዋናው እኛን የረበሸን ነገር ተቀራርበን ያሉትን ችግሮች በመነጋገር መፍትሔ ያለማስቀመጣቸው ነው፤›› የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፣ አሁንም ተቀራርቦ መነጋገሩ መፍትሔ ያመጣል የሚል እምነት አላቸው፡፡ ምርት እንዳለ እርግጠኞች መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ሙሉነህ፣ ነገር ግን በትክክል ለወጪ ንግዱና ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚሆነውን እያመጣጠነ እየሄደ ነው ወይ? በደንብ ተጠንቶ ነው ወይ? የተሠራበት የሚለው ላይ ጥርጣሬ ማሳደሩ ነው፡፡ መጀመርያ ዩኒየኖች ይሠራል የተባለው ግብይት ቀርቶ ባለሀብቶች በኩል ይከናወን መባሉ የዚህ አሠራር ሁኔታ ግራ ሊያጋባቸው መቻሉን ጠቁመዋል፡፡ ይህ ችግር እንዲህ ባለ ሁኔታ እየተገለጸ ቢሆንም፣ በቅርቡ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ይገበያያል መባሉ ግን ለዱቄት አምራቾች የተሻለ ምርጫ ተደርጎ እንደሚወሰድ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

ማኅበሩም ቢሆን ይህንን ይደግፋል፡፡ እስካሁን ድረስ የስንዴ ግብይት ጤናማ እንዳልነበረ ያስታወሱት አቶ ሙሉነህ፣ መንግሥት ትክክለኛ ነጋዴዎች መጥተው እንዲነግዱና የስንዴ ግብይቱ በዶክመንት የተደገፈ እንዲሆን ማኅበሩ የብዙ ጊዜ ምኞት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ምክንያቱም ስንዴ ሲገባ ዶክንመት የለውም፡፡ ዱቄት ሆኖ ሲወጣ ግን ከዶክመንት ጋር ስለሚወጣ ከገቢዎች ጋር ጭምር እያወዛገበን በመሆኑ፣ የስንዴ ግብይት በትክክኛው መንገድ ይካሄድ በሚል ሲወተውት የነበረው ማኅበሩ ሲሆን ግብይተ በምርት ገበያው በኩል ይሆናል መባሉን ይደግፋሉ፡፡  በምርት ገበያው ኩል ስንዴ ይገበያያል ተብሎ ሥልጠና ሰጥተው በትክክለኛው መንገድ እየሄዱ ነው፡፡ ይህ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ግብይት እስኪጀመር እየጠበቅን ነው፡፡ አሁን ግን አዲሱ የግዥ ሒደት እነሱን ከሥራ እያስተጓጎለ በመሆኑ፣ ግራ እያጋባቸው ነው፡፡ 

የክልሉ መንግሥት ወሰነ በተባለው መንገድም ቢሆን ስንዴ ለማግኘት በተለይ የኦሮሚያ ንግድ ቢሆን በቀን ሁለት ጊዜ ማኅበራችን መፍትሔ እየጠየቀ ነው፡፡ ይህ ክልሉ እተገብረዋለሁ ያለው ትስስር ይተገበራል ተብሎ የተነገረ በመሆኑ እስካሁን ያለመተግበሩ ያሳስበናል ይላሉ፡፡ እንዲህ ያለው ትስስር የሚፈጸመው ግብይትም ቢሆን ጥያቄ ያስነሳል፡፡ በዚህ መንገድ ብንገበያይ እንኳን የምንገዛው ስንዴ ለዳቦ ይሆናል አይሆንም የሚለው ያጠራጥረናልና ለዚህም መመካከር እንደሚያሻ ፕሬዚዳንቱ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ 

ስለዚህ የስንዴ ግብይት ፈር መያዝና በአግባቡ እንዲከናወን እንሻለን የሚለው ማኅበሩ፣ አሁን ላይ የምርት እጥረት ሳይሆን የግብይት ሒደቱ ላይ በደንብ ያለመሠራቱ እያመጣ ላለው ችግር መፍትሔ የሚያስፈልገው መሆኑንም ይጠቁማል፡፡ ኤክስፖርት ቢደረግም እጥረት እንደማይኖር ግን ማኅበሩ እርግጠኛ መሆኑን ያምናል፡፡ 

   

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች