Sunday, March 26, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

[ክቡር ሚኒስትሩ ከፓርቲያቸው የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለመወያየት ቢገናኙም፣ ውይይቱ ከዚህ ቀደም ባልለመዱት መልኩ ሙግት የቀላቀለ ሆኖባቸዋል]

  • ክቡር ሚኒስትር ፖለቲካውን የምንመራበት መንገድ ትክክል አልመሰለኝም፣ መንገድ እየሳትን ነው።
  • እንዴት፣ ለምን እንስታለን?
  • ምክንያቱም ከሁሉም ጋር እየተጋጨን ነው። ሥልጣን ስንይዝ የነበረን የማኅበረሰብ ድጋፍ ተሸርሽሮ እያለቀ ነው።
  • አይምሰልህ። አሁንም ድጋፋችን እንዳለ ነው!
  • ክቡር ሚኒስትር፣ ከማኅበረሰባችን ምን ያህል እየተለየን እንደመጣን ላስረዳዎት እችላለሁ።
  • እሺ ቀጥል።
  • በጦርነቱ ምክንያት ከትግራይ ማኅበረሰብ ጋር ተለያይተናል።
  • እሱ በእኛ ምክንያት የመጣ አይደለም።
  • በምንም ምክንያት ይምጣ አሁን ላይ ግን ከዚህ ማኅበረሰብ ተለይተናል። በቀላሉም የምንመልሰው አይደለም።
  • ሊሆን ይችላል።
  • በኦሮሚያ ሸኔ አሁንም ሊለቀን አልቻለም። በበርካታ አካባቢዎች መዋቅራችንን እያፈረሰ ከማኅበረሰቡ እየነጠለን ነው።
  • የኦሮሚያ ችግር የለውም፣ ይስተካከላል።
  • እርሶ እንዳሉት በቀላሉ የምንመልሰው ከሆነ ጥሩ ነገር ግን ከማኅበረሰቡ እየተነጠልን መሆኑ ግን ሐቅ ነው። በሌላ በኩል
  • በሌላ በኩል… ምን?
  • በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ የነበረውን ችግር መፍታት ብንችልም አሁንም በእኛ ላይ ያለው ጥርጣሬ አልተቀረፈም።
  • ኃይማኖትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ድጋፍ ለእኛ አይጠቅመንም።
  • እንደዚያ ዓይነት ሥርዓት ገንብተን ቢሆን ጥሩ። ነገር ግን እውነቱ እንደዚያ አይደለም።
  • እውነቱ ምንድነው?
  • ሰሞኑን በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ውስጥ የተፈጠረው ችግር በእኛ ላይ ያመጣውን አደጋ ብቻ መመልከት በቂ ነው።
  • ምን አደጋ አመጣብን?
  • ክቡር ሚኒስትር የእውነት ሳይገባዎት ቀርቶ ነው?
  • ከገባኝ ለምን እጠይቃለሁ?
  • አይመስለኝም። ለማንኛውም ሰሞኑን በተፈጠረው ችግርና ከእኛ በኩል ስለጉዳዩ በተሰጠው መግለጫ ምክንያት የቀረንን ማኅበራዊ መሠረት የማጣት አደጋ ደቅኖብናል።
  • ከየትኛው ማኅበራዊ መሠረታችን?
  • በአማራ፣ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች የሚገኘው ማኅበረሰብ ብቻ ነበር የቀረን፣ አሁን ግን ይህንንም የማጣት ጫፍ ላይ ደርሰናል፡፡
  • ለምን? ከዚህ ማኅበረሰብ ጋር ምን ያጣላናል?
  • መንግሥት ሃይማኖቴን ሊንድ እጁን አስገብቷል ብሎ አምኗል። በዚህ ምክንያት በአንድ ጊዜ የዚህን ማኅበረሰብ ድጋፍ የማጣት አደጋ ውስጥ ገብተናል።
  • መንግሥት ግን እጁን አላስገባም?
  • ማኅበረሰቡ ግን መንግሥት እጁ እንዳለበት አምኗል።
  • ታዲያ ስህተት መሆኑን ለምን አታስረዱም?
  • ሞክረናል። ነገር ግን የሃይማኖቱን ተከታይ ይቅርና የእኛኑ ፓርቲ አባሎች እንኳ ማሳመን አልቻልንም።
  • ችግር የለውም። የአንዱ መሄድ ሌላውን መልሶ ያመጣል።
  • እንዴት?
  • የዚህን መሄድ ተከትሎ በተቃራኒ የቆመ ሌላው ማኅበረሰብ ወደ እኛ ይመለሳል።
  • ክቡር ሚኒስትር ሥልጣን የያዝነው እኮ በተቃርኖ ለመምራት አይደለም። ከምንከተለው መርህም ተቃራኒ ነው።
  • የትኛው መርህ?
  • ‹‹መደመር››!
  • አሁንም በ‹‹መደመር›› መርህ ነው እየመራን ያለነው።
  • ከሁሉም የፖለቲካ ማኅበረሰብ እየተጋጨን? እንዴት ያለ መደመር ነው ይኼ?
  • የመደመርን መርህ አልገባህም ማለት ነው።
  • እንዴት?
  • የእኛ ‹‹መደመር›› ከሒሳባዊው የመደመር ቀመር የተለየ ነው።
  • እንዴት? ምን ይለየዋል?
  • በእኛ ‹‹መደመር›› ውስጥ መደመር ብቻ አይደለም ያለው።
  • ሌላ ምን አለ?
  • መቀነስም አለ።
  • እ…?
  • መቀነስ ብቻ ሳይሆን ማካፈልም፣ ማባዛትም አሉ።
  • ክቡር ሚኒስትር እርሶ ሌላ ዓለም ላይ ያሉ ነው የሚመስለው።
  • እንዴት?
  • አገሪቱ በግጭቶች ውስጥ እየተናጠችና የችግሩን ጥልቀት ያስተዋሉ አልመሰለኝም፡፡
  • ችግሮቹን እኛ አልፈጠርናቸውም።
  • እና ከየት መጡ?
  • በውርስ።
  • ምን አሉ?
  • የወርሰናቸው ችግሮች ናቸው!
  • ወደ ሥልጣን ላይ የመጣነው ችግሮችን ለመፍታት እንጂ ባለቤት ለማበጀት አይደለም። ለዚህ ደግሞ ኃላፊነት አለብን።
  • ትክክል ነው። ሥጋትህ ይገባኛል።
  • ታዲያ?
  • አንድ ነገር አረጋግጥልኃለው!
  • ምን?
  • ኢትዮጵያ አትፈርስም!
  • መጀመሪያ እኛን ነው የሚያፈርሰው፣ ከጥሎ ደግሞ ተቋም ይፈርሳል። ከዚያ በኋላ…
  • ከዚያ በኋላ ምን?
  • ከዚያማ እርሶም በዚህ ሥልጣን ላይ መቀጠል አይችሉም።
  • ለምን አልችልም?
  • አይሆንማ! እንዴት ሆኖ?
  • አለኝ እኮ፣ ገና ይቀረኛል።
  • ምን?
  • የአገልግሎት ዘመን!

[ሚኒስትሩ ጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ ሆነው ‹‹ገና ይቀረኛል›› እያሉ ያወራሉ፣ በሁኔታው የደነገጡት ባለቤታቸው ሚኒስትሩን ቀሰቀሷቸው] 

  • እስኪ በስመ አብ በል? ምንድነው እንዲህ ያስጨነቀህ?
  • እ… አይ ጭንቀት አይደለም።
  • ታዲያ ምንድነው? ፊትህ ሁሉ ተለዋውጦ ስትጮኽና ስታወራ ነበር እኮ?
  • ብዙ አወራሁ እንዴ? ምን እንዳልኩ ሰምተሻል?
  • አልገባኝም እንጂ ደጋግመህ ‹‹ይቀረኛል›› ምናምን ስትል ነበር።
  • ይቀረኛል ብቻ ነው ያልኩት?
  • ‹‹ይቀረኛል›› እና ሌሎችም የማይሰሙ ነገሮችን ስትል ነበር።
  • ይህን ብቻ ነው የሰማሽው?
  • በዚያኛው ጫፍ የሚያዋራህ አልተሰማኝም።
  • እስኪ አትቀልጂ…?
  • ግን ማነው?
  • ምኑ?
  • እንዲህ ያስጨነቀህ? ማለቴ ጉዳዩ ምንድነው?
  • ቅዠት እኮ ነው።
  • በእውንህም ይህንን ነገር ስትል ሰምቼ አውቃለሁ።
  • መቼ? ምን ስል?
  • ሰሞኑን በነበሩህ ስብሰባዎች ላይ በተደጋጋሚ ይቀረኛል… ሦስት ዓመት አለኝ ስትል በቲቪ ሰምቻለሁ። ከዚህ ጋር የሚገናኝ ነው?
  • በጭራሽ አይደለም።
  • ታዲያ ከማን ጋር ነው?
  • ከአንድ የውጭ አገር ባለሥልጣን ጋር እየተከራከርኩ ነበር። አዎ እንደዚያ ነው።
  • በአማርኛ?
  • እሱም በአማርኛ ነበር ያወራኝ የነበረው… እንደዚያ መሰለኝ።
  • ወይ አስተርጓሚም ይዞ ይሆናል።
  • ቅዠት ነው አልኩሽ ኦኮ። ይልቅ የምጠጣው ውኃ ስጪኝ
  • እሺ… እንደው ግን እንዲህ ከምትጨነቅ ብትተወውስ?
  • ምኑን?
  • ይቀረኛል ያልከውን?
  • በፍጹም። ‹‹ይቀረኛል!››

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ጉራጌን በክላስተር ለመጨፍለቅ የሚደረገውን ጥረት እንደሚቃወም ጎጎት ፓርቲ አስታወቀ

ለጉራጌ ሕዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እንደሚታገል የሚናገረው አዲሱ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

‹‹ኢኮኖሚው ላይ የሚታዩ ውጫዊ ጫናዎችን ለመቀልበስ የፖሊሲ ሪፎርሞች ያስፈልጋሉ›› ዓለም ባንክ

በዓለም ደረጃ ከተፈጠረው የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ጋር በተገናኘ፣ በኢትዮጵያ ውጫዊ...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

ብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ይፋ ሊያደርግ ነው

የፋይናንስ ዘርፉን ለማረጋጋት የሚረዳ ሪፎርም ማጠናቀቁን የገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር ሚኒስትር? እርሶዎማ ቀጠሮ መያዝ አያስፈልግዎትም። ምን ገጠመዎት? እኔማ ምን ይገጥመኛል፣ አንተኑ ልጠይቅህ እንጂ? ምን? እውነት ለመናገር የማየው ነገር አሳስቦኛል። ይንገሩኝ...

[የባለሥልጣኑ ኃላፊ የቴሌኮም ኩባንያዎች የስልክ ቀፎ የመሸጥ ፈቃድ እንዳላቸው ለማረጋገጥ ክቡር ሚኒስትሩ ጋር ደወሉ]

ክቡር ሚኒስትር ዕርምጃ ከመውሰዳችን በፊት አንድ ነገር ለማጣራት ብዬ ነው የደወልኩት። እሺ ምንን በተመለከተ ነው? የቴሌኮም ኩባንያዎችን በተመለከተ ነው። የቴሌኮም ኩባንያዎች ምን? የቴሌኮም ኩባንያዎች የሞባይል ቀፎ እንዲሸጡ በሕግ...

[ክቡር ሚኒስትሩ ተቋቋመ ስለተባለው የሽግግር መንግሥት ከአማካሪያቸው መረጃ እየጠየቁ ነው]

እኛ ሳንፈቅድ እንዴት ሊያቋቁሙ ቻሉ? ስምምነታችን እንደዚያ ነው እንዴ? በስምምነታችን መሠረትማ እኛ ሳንፈቅድ መቋቋም አይችልም። የእኛ ተወካዮችም በአባልነት መካተት አለባቸው። ታዲያ ምን እያደረገ ነው? ስምምነቱን መጣሳቸው...