የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ሆነ የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት ዋና መቀመጫቸውን አዲስ አበባ አድርገው፣ ኢትዮጵያን የአፍሪካውያን መሰባሰቢያ ማዕከል ካደረጉ ድፍን ስድሳ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና በብርቱዎቹ ሚኒስትሮቻቸው ትግል፣ በፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ግንባር ቀደም በነበሩ አፍሪካውያን ድጋፍና በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ርብርብ ፀንቶ የቆየው የአፍሪካ ኅብረት ዛሬም የኢትዮጵያን ማዕከልነት አድምቆ ቀጥሏል፡፡ በየዓመቱ አንዴ በአዲስ አበባ የሚደረገው የኅብረቱ የመሪዎች ጉባዔ አንዱ የድምቀቱ ማሳያ ሲሆን፣ ለበርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መገኛ በመሆንም አዲስ አበባን ከኒውዮርክና ከጄኔቫ በመቀጠል ሦስተኛዋ የዲፕሎማቲክ ከተማ አድርጓታል፡፡ ይህንን የመሰለ መልካም ዕድል የተገኘው ግን እንዲሁ በዋዛ አይደለም፡፡ ቀደምቶቹ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን፣ ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ዓይን ከፋች የሆነ ታላቅ ውለታ በመዋላቸው ነው፡፡ ይህ ውለታ የተዋለው ደግሞ በዘመኑ ታላቅ ከሚባሉት ኮሎኒያሊስቶች አንዱ የሆነውን፣ የጣሊያን ወራሪ ኃይል በታላቁ የዓድዋ ጦርነት በማንበርከካቸው ነው፡፡ ይህ ድል ነበር ለብዙዎቹ የአርነት ንቅናቄዎችና ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መሠረት የጣለው፡፡
መላው አፍሪካ በአውሮፓ ኮሎኒያሊስቶች መዳፍ ሥር ሆኖ የቅኝ አገዛዝን መረራ ፅዋ ሲጋት፣ በአፍሪካ አኅጉር ብቻዋን እንደ አብሪ ኮከብ ታንፀባርቅ የነበረችው ኢትዮጵያ ብቻ ነበረች፡፡ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ አገዛዝ መዳፍ ለመላቀቅ እንቅስቃሴ ሲጀምሩ፣ ዓይኖቻቸውም ሆኑ እጆቻቸው ለድጋፍ ያማተሩት ወደ ኢትዮጵያ ነበር፡፡ ኢትዮጵያም ጥሪያቸውን ፈጥና በመቀበል በሞራል፣ በገንዘብ፣ በዲፕሎማሲና በወታደራዊ ድጋፍ የበኩሏን ድርሻ በመወጣት፣ ታሪክ የማይረሳው ኃላፊነቷን በከፍተኛ ክብርና ሞገስ ተወጥታለች፡፡ አፍሪካውያን የመሰባሰቢያ ማዕከላቸውን ኢትዮጵያ ከማድረግ በዘለለ፣ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የነፃነታቸው እናት እንደሆነች በየአደባባዩ ሲገልጹ ኖረዋል፣ አሁንም አላቋረጡም፡፡ አፍሪካውያን ለኢትዮጵያ ይህንን ሁሉ ክብርና ማዕረግ ሰጥተው ኩራታቸውን ሲገልጹ፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ግን ምን እያደረግን ነው ብለን ራሳችንን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ ያሳፍራል፡፡ ከሃምሳ በላይ የአፍሪካ አገሮች ኅብረት ፈጥረው ኃላፊነቱን በክብር ቢሰጡንም፣ እኛ ግን እያደር ቁልቁል እየወረድን በጎሳና በመንደር ለመተላለቅ ጎራዴ እንስላለን፡፡ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የማይመጥን ቁመና ይዘን እንንከላወሳለን፡፡
የግለሰብ ዕለታዊ ፀብን ከመቅጽበት ወደ ብሔር ወይም ወደ እምነት በመለወጥ ግጭት ማስነሳት፣ ሕግና ሥርዓት አስፍኖ ሰላማዊ ድባብ ከመፍጠር ይልቅ ግጭት ማባባስና ማዛመት፣ ለሐሳብ ልዩነት ቦታ አለመስጠት፣ አገርን ከግላዊና ከቡድናዊ ጥቅም በታች ማሳነስ፣ ሥልጣን ላይ ለመቆየትም ሆነ ሥልጣን ለመያዝ ሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ከመምረጥ ሸርና ሴራ ላይ መበርታት፣ ሀቀኞችንና ትጉሆችን በማባረር አድርባዮችንና አስመሳዮችን ማሰባሰብ፣ ከዕውቀትና ከልምድ በላይ ለብሔርና ለእምነት ትስስር ቅድሚያ መስጠት፣ አሁን ደግሞ ዓለማዊ ጥፋቶች አልበቃ ብለው ቤተ እምነቶችን መበጥበጥና ማስበጥበጥ ትልቅ ሙያ ተደርጓል፡፡ በዚህ ድርጊታችን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ መንግሥታት፣ ምሁራን፣ ሚዲያዎች፣ የሲቪክ ተቋማትና ሌሎችም እየታዘቡን ነው፡፡ ለሁለት ዓመታት ያህል ሕዝባችንን ካስፈጀንበት፣ በሚሊዮኖች ካፈናቀልንበትና የደሃ አገራችንን አንጡራ ሀብት ካወደምንበት ጦርነት በቅጡ ሳንወጣ ሌላ አደጋ ራሳችን ላይ ደቅነናል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የገባንበት የለየለት ዕብደት ሳይታከም፣ ለሌላ ዙር ዕልቂት መመቻቸታችን በአፍሪካውያን ዘንድ እያስገመተን ነው፡፡
በግለሰብም ሆነ በመንግሥት ደረጃ በፍጥነት ከዚህ ቅርቃር ውስጥ መውጣት የግድ ነው ተብሎ ካልታመነ ከፊታችን ያለው ክፉ ጊዜ ነው፡፡ አንዱ የሌላው ወዳጅ ሆኖ አገርን በፍቅርና በመተሳሰብ ካለችበት አዘቅት ውስጥ ማውጣት በጣም ቀላሉ ሥራ ሆኖ ሳለ፣ ለምን ዘወትር በሴራ ትንተና ሃልዮት አንዱ የሌላው ጠላት እየተደረገ ለሚያልፍ ቀን የማያልፍ ድርጊት ይፈጸማል? አንዱ አሳዳጅ ሌላው ተሳዳጅ፣ አንዱ አሳሪ ሌላው ታሳሪ፣ አንዱ ገዳይ ሌላው ሰለባ፣ ወዘተ ውስጥ መውጣት ያቃተን ለምን ይሆን? ባለታሪኮቹ ኢትዮጵያውያን ከራሳቸውና ከምንም ነገር በላይ አገራቸውን አፍቅረው፣ በዓለም አደባባይ ታሪክ ሠርተውና አገርን በክብር አስረክበው ማለፋቸው እየታወቀ፣ እንዴት ሆኖ ነው አንዱ ሌላውን ደመኛ ጠላት አድርጎ አንዴ በብሔር ሌላ ጊዜ በእምነት እያገለለ ኢትዮጵያ አትፈርስም ሊባል የቻለው? ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ደረሱ በተባሉ ጭቆናዎች የሚከፋቸው ቢኖሩ እንኳ፣ የትናንቱ ላይ ተቸክሎ ማላዘን የሚቀለው ወይስ የነገዋን የተሻለች አገር መገንባት ነው የሚሻለው? አፍሪካውያን በትዝብት እያዩን ነው፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን ቤት ሆና መቀጠል የምትችለው ከገባንበት አሳፋሪና አስደንጋጭ ዝቅጠት ውስጥ በፍጥነት ስንወጣ ነው፡፡ አፍሪካውያን አንድ እንሁን ብለው በአጀንዳ በ2063 አማካይነት አኅጉሪቱን አንድ አገር ለማድረግ ሲጥሩ፣ እኛ በተቃራኒው የአንድነት አርዓያዋን ኢትዮጵያን ዘጠኝ ቦታ ትንንሽ ለማድረግ የቁልቁለት ጉዞ መጀመራችን የዘመኑ እንቆቅልሽ ነው፡፡ በሚያጋጥሙ ክስተቶች ላይ ተቀምጦ ለመነጋገር ፈቃደኝነት በሌላቸው ጽንፈኛ የፖለቲካ ልሂቃን ምክንያት አገር ለውድመት ስትዘጋጅ፣ ችግሩን በፅሞና መርምሮ የማስተካከያ ዕርምጃ ለመውሰድ በግራም ሆነ በቀኝ ተነሳሽነት ሲጠፋ ዝምታው ያስፈራል፡፡ አገር ዙሪያዋን እሳት እየተንቦገቦገባትና 120 ሚሊዮን ያህል ሕዝብ ሥጋት ውስጥ ሆኖ፣ ከጥቅምና ከሥልጣን ባሻገር ያለውን አደጋ ለማየትና መፍትሔ ለመሻት አለመፈለግ የታሪክ ተጠያቂ ማድረጉ አይቀሬ ነው፡፡ ዜጎች ከዚህ ቀደም በተፈጸሙ ጥቃቶች የደረሱ ዕልቂቶችን፣ ውድመቶችንና መፈናቀሎችን እያሰቡ ይህ ሁሉ መከራ እንዲያበቃ በየእምነታቸው ሲፀልዩ፣ ከበፊቶቹ የባሰ መዓት ሊመጣ ነው ብለው ሲሳቀቁ ከማየት በላይ የሚያሳዝንም የሚያስቆጭም ነገር የለም፡፡ ይህም ብዙዎችን አፍሪካውያን ያሳስባቸዋል፡፡
የሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ የምጣኔ ሀብት፣ የሥነ መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር ሊቅ የነበሩት ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ፣ ‹‹የነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ሥራዎች›› በሚል ርዕስ በ2003 ዓ.ም. በታተመው መጽሐፋቸው፣ ‹‹…የዱሮውም ያሁንም ኑሯችን እጅግ ያሳዝናል። በመላው ዓለም ላይ ሰላም ሲሰፋ አዕምሮም ስትበራ እኛ በጨለማ እንኖራለን። እርስ በርሳችን መጠራጠርንም አልተውንም። ሕዝቦቹ ሁሉ እርስ በርሳቸው በፍቅር ተቃቅፈው ስለልማታቸው ባንድነት ሁነው ሲደክሙ፣ እኛ አንድ ዘርና ወንድማማች መሆናችንን ገና አልተገለጸልንም። እርስ በርሳችን መፋጀትም እስከ ዛሬ ድረስ ጀግንነት ይመስለናል። ስለዚህም እግዚአብሔር ለብርታት የሚሆነውን ስጦታ ሁሉ ሰጥቶን ሳለ፣ ባለቤቶቹ ሰነፍን። ሌሎቹም ነገሥታት እንደ ሰነፎች ይቆጥሩናል፣ ይንቁናልም…” ሲሉ ከ100 ዓመታት በፊት በቁጭት የጻፉት ጆሮ ዳባ ተብሎ እዚህ ደረጃ ደርሰናል፡፡ እኛ አፍሪካውያንን ከፊት ረድፍ ሆነን መምራት ሲገባን እርስ በርስ እየተፋጀን ነው፡፡ በሁሉም ነገሮች መግባባት አቅቶን ከተጫረስን በኋላ የሚገላግሉን ባዕዳን ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት አፍሪካን ከፊት የምትመራውን ኢትዮጵያ መሳቂያና መሳለቂያ እያደረግናት ነው፡፡ ይባስ ብሎም የአፍሪካ ጭራ አድርገናት እየተገመትን ነው!