የክልሎችን ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በአገር መከላከያ ሠራዊት ተጠባባቂ ኃይል ውስጥ ለማስገባት፣ ጥናት እየተደረገ መሆኑን የአገር መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የመከላከያ ሚኒስቴር ደኤታ ወ/ሮ ማርታ ሉጂ የሚኒስቴሩን የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሲያቀርቡ በተለይ በቅርቡ በሰሜን ኢትየጵያ ሲካሄድ በነበረው አገራዊ የህልውና ዘመቻ ልዩ ኃይሎችና ሚሊሻዎች ዋጋ የከፈሉ በመሆናቸው፣ ወደፊት በተጠባበቂ ኃይል ሊያዙ የሚችሉበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ጥናት እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ ጠንካራ የአገር መከላከያ ተጠባባቂ ኃይል የማደራጀት ሥርዓት እየተዘረጋ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ደኤታዋ፣ በዚህ ሒደት የተጠባባቂ ኃይል ምንነት፣ አስተዳደርና የሥራ ሥምሪት ምን መምሰል አለበት በሚሉት ጉዳዮች ግልጽነት ላይ ለመፍጠር የሚረዳ የአሠራርና የአደረጃጀት ሥርዓት ዝግጅት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
ምንም እንኳ ከዚህ ቀደም ተጠባባቂ ኃይል ያለ ቢሆንም የነበረው ኃይል የተደራጀ ባለመሆኑ፣ ወደፊት የነበሩትን የአሠራርና የአደረጃጀት ክፍተቶች ለመሙላት የሚያግዝ ማሻሻያ ለማድረግ በተያዘው ዓመት ዕቅድ መያዙን አስረድተዋል፡፡
ጥናቱ እንደተጠናቀቀ ተጠባባቂ ኃይል ምን መምሰል እንደሚገባው ተለይቶ፣ ኃይሉን በአደረጃጀት የማዋቀርና በአሠራር የመጠበቅ ሥራ እንደሚከናወን አብራርተዋል፡፡
የአገር መከላከያ ሠራዊት ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 69 ሺሕ ምልምል ወታደሮችን አሠልጥኖ ማስመረቁን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ የሠራዊቱ ቁጥር ቀድሞ ከነበረው በእጅጉ የላቀ መሆኑንም አክለዋል፡፡
የመከላከያ ሠራዊትን ዝግጁነት የሚያረጋግጡ የኢንዱስትሪ ምርቶች በጥራትና በመጠን በራስ አቅም እየተመረተ መሆኑን፣ በስድስት ወራት ውስጥ 4.7 ሚሊዮን የቀላል መሣሪያ ተተኳሽ ጥይቶች ለማምረት ታቅዶ 2.6 ሚሊዮን መመረታቸውን፣ እንዲሁም 230 ሺሕ መካከለኛና ከባድ ጥይቶች ለማምረት ታቅዶ 246 ሺሕ ጥይቶች ማምረት እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ውስጥ ከወታደራዊ ምርትና አገልግሎት ሽያጭ 637 ሚሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዶ፣ ከዕቅድ በላይ 2.3 ቢሊዮን ብር ገቢ እንደተገኘ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትር ደኤታዋ መንግሥት ከውጭ አገር የተገዙ መሣሪያዎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት፣ ከጦር መሣሪያ ጋር በተገናኘና የአስመጪነት ፈቃድ ለማግኘት አዳጋች እንደሆነበት ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡