Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትመንግሥትና ሃይማኖት ምንና ምን ናቸው?

መንግሥትና ሃይማኖት ምንና ምን ናቸው?

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ሃይማኖትና መንግሥት ምንና ምን ናቸው? የሚሉ ዓይነትና መሰል ጥያቄዎች አዘውትረውም፣ ደጋግመውም፣ በዋነኛነትም እግረ መንገድም የሚነሱት ለምሳሌ ያህል የሚያወጉ የአገር ጉዳዮችንና ጥያቄዎችን እየተፈተሹ እየተብላሉ የመፍትሔ ፍለጋ የጥናት የውይይት መደበኛው ሥራ በሚሠራባቸው በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ፣ ወይም የአገር ከፍተኛ ሕግ መሻሻል፣ መለወጥ፣ እንደ አዲስ፣ እንደገና መሠራት በሚፈለግበት የትግል ወይም የንቅናቄ ወቅት ነው፡፡ አንዳንዴም አልፎ አልፎም ሲዳላና አነሰም በዛም፣ ከፋም ለማም መደበኛው መፈናፈኛ፣ መተንፈሻ መነጋገሪያ ሲኖርና ሲፈቅድ እኛም ወጉ እየደረሰን ይህንን የሪፖርተር ጋዜጣን በመሳሰሉ ገጾች፣ ‹‹የዓመት በዓላት አከባበር የመገናኛ ብዙኃን ሚና እየገረመን፣ የመንግሥት ወይም የአገር መሪዎች ወይም የባለሥልጣናቶቻችን በዓሉን አጋጣሚ ያደረገ ንግግር/ዲስኩር እየቀሰቀሰን፣ ወዘተ) ስለመንግሥትና ሃይማኖት ግንኙነት፣ ስለ‹‹አገር የጋራ ነው ሃይማኖት የግል ነው›› መነጋገራችንና መጻፋችን የተለመደ ነበር፡፡ በጣም እያስደነገጠ ጭምር በሚገርም ሁኔታ አሁን የምንገኝበት የ‹‹ዕድገት›› ደረጃ ግን፣ ይህንን የተለመደና ተራ ርዕስ የ‹‹ፈንጂ ወረዳ›› ወይም ‹‹የቀይ መስመር››ን የተላለፈ አደርጎታል/አስመስሎታል፡፡

(በነገራችን ላይ ከፍ ሲል ‹‹መፈናፈኛ›› ብዬ የጠቀስኩት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ‹ሲቪል ስፔስ›› ብለው የሚጠሩትን ዕሳቤ ነው፡፡ በዋናው ጉዳይ መካከል ጣልቃ አስገብቼ ትንሽ ማፍታታት የፈለግኩት ይህንን ዕሳቤ ነው፡፡ ‹‹ሲቪል ስፔስ›› ማለት ሰዎች በመብታቸው የሚገለገሉበት ይህ መልክዓ ምድራዊም/አካላዊም፣ እንዲሁም የሕግ ቦታና ሥፍራ ነው፡፡ ሐሳብን በነፃ የመግለጽ መብትና አፈጻጸሙ፣ እንዲሁም ይህንኑ ማድረግ የሚያስችል ቦታ/መሣሪያ ሁኔታዎችን ሁሉ መቀዳጀት፣ ውይይትን ማደራጀት፣ እዚያ ውስጥ መሳተፍ፣ የዚያ አካል አባል መሆን፣ ወዘተ ሁሉ እዚህ ሥፍራም፣ ቦታም በሕግ የተደነባና የጠበቀ ምንነት ባለው ሲቪል ስፔስ ውስጥ ይካተታል፡፡ የዴሞክራሲያዊ መልካም አስተዳደርና ፖለቲካዊ ሰላሙ የሰፈነ ኅብረተሰብ የመሠረተ ድንጋይ ከሚባሉት መካከል አንዱና ዋነኛው፣ እንዲህ ያለና በሕግ የተከበረና የሕግ ማስከበር ሥራም የሚያስከብረው ሲቪል ስፔስ ነው)፡፡

እንዲህ ያለ ይዘቱንና ቅርፁን ሕግ በደነባው ሥፍራና ቦታ ለ‹‹መገንባት›› እና ግባታውንም የፀና መሠረት ለማስያዝ፣ ዘላቂነቱንም ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም የትኛውም ዓይነት ርዕደ መሬት እንዳያናውጠው መተማመኛ ለማግኘት መብቶችን ሕገ መንግሥት ውስጥ ከማሥፈር በላይ በርካታ ሥራዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ሰላማችን ሁሉ የፖለቲካም ሆነ የሃይማኖት ሰላማችን በሙሉ መብትን በሕግ ከመደንገግ በላይ በርካታ የግንባታ ሥራዎች ይሻሉ፡፡

የያዝነው የ2015 የካሌንደር ዓመት የጥር ወር አጋማሽ ጀምሮ ያለው ጊዜ በዓይናችን አሳይቶና አስጎብኝቶ መልሶ የ‹‹ማረን›› አደጋ፣ ምንም ዓይነት ሕገ መንግሥታዊ መተማመኛ (ዕድሜ የጠገበ ጭምር) ያለ አጣማጅ አቻው የአውታረ መንግሥት ግንባታ ጭምር ዋጋ ቢስ እንደሆነ የሚያስተምር ነው፡፡ ችግሩ ሃይማኖትን ምክንያት ወይም ሰበብ ወይም እሱን ተገን አድርጎ የተጫረው፣ የተቀጣጠለው እሳትና መከራው መክሮናል ወይ? ነው፡፡

ጸሑፌን የጀመርኩት ሃይማኖትና መንግሥት ምንና ምን ናቸው? ብዬ ነው፡፡ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥታዊ ታሪክ ውስጥ የሃይማኖትና የመንግሥት ግንኙነት ለብዙ ጊዜ ‹‹የጆሮ ጉትቻና የአንገት ማኅተብ›› ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ማለት ይቻላል ያልኩት እንደ ዘመኑ የባለሥልጣናት፣ የካድሬዎችና የቢጤ ጋዜጠኞቻቸው ‹‹ብሎ መውሰድ ይቻላል›› ዓይነት ትርጉሙን ያጣና፣ የነተበ መጥፎ ‹‹አመል›› (ወልፍ) ውስጥ ገብቼ አይደለም፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፣ የ1948 ዓ.ም. የተሻሻለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት እስከታገደበት እስከ 1967 ዓ.ም. ድረስ (ኋላም በመጨረሻ የ1980 ዓ.ም. የኢሕዲሪ ሕገ መንግሥት በይፋ በአገር የመጨረሻው ከፍተኛና የበላይ ሕግ ሃይማኖትንና መንግሥትን እስከለያየ ድረስ)፣ ‹‹በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በቅዱስ ማርቆስ ትምህርት መሠረት የተቋቋመችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት መሠረታዊት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ስለዚህም በመንግሥት የተደገፈች ናት፡፡ የንጉሠ ነገሥቱ ሃይማኖት ሁልጊዜ የኢትዮያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት መሆን አለበት፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎት በሚደረግበት ሁሉ የንጉሠ ነገሥቱ ስም ይጠራል›› (የ1948 የተሻሻለው ሕገ መንግሥት አንቀጽ 126) በዚህ ሕገ መንግሥትና በሌሎች ሕጎች እንደተወሰነው ሲወርድ ሲዋረድ በመጣውም የተቋቋመ አሠራር መሠረት አገሩም፣ መንግሥቱም፣ መሠረታዊት ቤተ ክርስቲያን ነበራቸው፡፡

ይህ ‹‹ቀስ በቀስ›› እየቀረ እየተለወጠ መጣ፡፡ ‹‹የሕዝብን መልካም ፀባይ ወይም ፀጥታን ወይም በፖለቲካ ረገድ የሚያውክ ካልሆነ በቀር፣ በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ግዛት የሚኖሩ ሰዎች የሃማኖታቸውን ሥርዓት አክብረው በነፃ ከመፈጸም አይከለከሉም›› (የ1948 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 40)፣ ‹‹(1) የኢትዮጵያውያን የህሊናና የሃይማኖት ነፃነት የተረጋገጠ ነው፡፡ (2) የሃይማኖት ነፃነት አጠቃቀም የአገርንና የአብዮትን ደኅንነት፣ እንዲሁም የሕዝብን መልካም ሥነ ምግባርና የሌላውን ዜጋ ነፃነት የሚነካ መሆን የለበትም›› (የ1980 ሕገ መንግሥት አንቀጽ 46) የሚሉ በዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ የውኃ ልክ የሚባሉ የሃይማኖትና የእኩልነት መብቶችና ነፃነቶች እንኳንስ መሠረትና መደላደል መያዝ፣ በጽሑፍ እንኳን በቅጡ ጠልቀው ሕግ አውጪዎችን አዕምሮ ጨምድደው ባልያዙበት ሁኔታ፣ መንግሥትና ሃይማኖት ዳር ድንበር የላቸውም፣ ይልቁንም በአገር ውስጥ አንድ የተቋቋመ ሃይማኖት አለ የማለትን ትርጉም መረዳት የሚያዳግት አይመስለኝም፡፡

ዛሬ ሥራ ላይ ባለውና ፀንቶ በሚገኘው ሕገ መንግሥት መሠረት መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፡፡ ‹‹መንግሥታዊ ሃይማኖት አይኖርም፡፡ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም›› ተብሏል፡፡ እዚህ ሕግ ላይ የተደረሰው ግን በ1987 ዓ.ም. የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 11 በኩል አይደለም፡፡ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው ያለው የመጀመርያው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (1980) ሕገ መንግሥት አንቀጽ 46(3) ነው፡፡ ዛሬ እዚህም እዚያም ጎራና ወገን ሳይለይ ዴሞክራሲን የሚጎረብጡ፣ ዴሞክራሲ ራሱ የሚተናነቃቸው፣ የገለጽነውን ያህል ብዙ ዓመት የሞላው (ሃምሳ ዓመቱን ሊሞላ የተቃረበው) የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት መርህ ጋር የሚጣሉ አስተያየቶች/አስተሳሰቦች ቢኖሩም፣ አሁን በደረስንበት የዕድገት ደረጃ መንግሥትና ሃይማኖት መለያየት የለባቸውም ብሎ ንቅናቄ በጭራሽ የለም፡፡

እዚህ ላይ ግን የተደረሰው ዝም ብሎ በ1987 ዓ.ም. በተጻፈ ሕገ መንግሥት ወይም ከዚያ በፊት በ1980 ዓ.ም. በወጣ የበላይ ሕግ ድንጋጌ መሠረት አይደለም፡፡ ዛሬ ይህንን ራሱን መናገር፣ በነፃ መናገር፣ ጥላቻና ቅያሜ ወይም ቂም ሳያተርፉ ሐሳብን መግለጽ የሚያስችል ሁኔታ የለንም እንጂ፣ እዚህ የ1980 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት አንቀጽ 46 (3) እና የአሁኑ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 11 ላይ ከመድረሳችን በፊት የቅድመና የድኅረ 1966 ዓ.ም. አብዮተኛነት ያፈጁ ያረጁ ቀኖነኛ አመለካከቶችን እስኪያናጋ፣ ምክንያታዊና ነባራዊ አስተሳሰቦች እስኪጠራና እስኪያጣራ ብዙ መጠበቅ ነበረብን፡፡ በዚህ ጉዞ ውስጥ፣ በዚህ ረዥም መንገድ የተደረገው ጉዞ ሁሉ፣ ሁሉምና ያለ አንዳች ልዩነት ‹‹ወደፊት›› ነበር ባይባልም፣ ከዚያ በኋላም ምክንያታዊና ነባራዊ አስተሳሰብና ግንዛቤ የኋሊት መሄዱ ባይካድም፣ አሁን የምንገኝበት ሴኩላሪዝም ላይ የደረስንነው ግን ከብዙ የንቃትና የግንዛቤ አብዮት በኋላ ነው፡፡

ከፍ ብዬ እንደጠቀስኩት፣ ምናልባትም ፈራ ተባ እያልኩ እንደጠቆምኩት፣ ‹‹መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው›› (ይህ የ1980ውም፣ የ1987ቱም ሕገ መንግሥታችን ቃል ነው) ላይ ለውጥ እሻለሁ የሚል ንቅናቄም ሆነ ግንባር የለም፡፡ የሃይማኖት ነፃነታችን ያለ መሸራረፍ የሚያረጋገጠው ይህ ሲሆን ብቻ ነው ማለትም፣ መንግሥታዊ ሃይማኖት ሲኖር ብቻ ነው የሚሉ አይጠፉም እንኳን ቢባል፣ ይህ የየትኛውን ሃይማኖት ተከታዮች ብዙዎችን ልብ የሚረታም አይደለም፡፡ ከዚህ ይልቅ አገራችን ውስጥ ያለው ችግር የአንቀጽ 11 ይዘትና ትርጉም ግንዛቤያችን ነው፡፡ ‹‹አገር የጋራ ነው፣ ሃይማኖት የግል ነው›› ማለት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ የታወቀ፣ ሁሉም ያለ አንዳች ልዩነት የሚናገረው ለጥቅስ የበቃ፣ ይህንንም ክብርና ሞገስ ተጎናጽፎ ከጥቅሱ ባለቤት የሥልጣን ዘመንና ዘመነ መንግሥት በላይ ለረዥም ጊዜ የዘለቀ አባባል ነው፡፡ በጥር 2015 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ ካስፈራራን አደጋ ወዲህ ግን፣ በሁሉም አጋጣሚ ‹‹ሃይማኖት የግል ነው›› ማለት በየትም ቦታና ሁል ጊዜም የሚሠራ አባባል አይመስልም፡፡

የመሪዎቻችን፣ የገዥው ሐሳብ የሕገ መንግሥቱ የአንቀጽ 11 ንቃትና ግንዛቤም ይህንን ዓለም አቀፋዊና ዴሞክራሲያዊ የሕገ መንግሥትም ድጋፍ ያለው ቤዝላይን የሚረዳም (ሲጠብቅም ሲላላም) አይደለም፡፡ በተለይም በእነዚህ የጥር ወር 2015 ዓ.ም. የመጨረሻ ሳምንታት የተጫረው እሳት ራሱ የዘገባውና የአሸፋፈኑ ‹‹የሥራ አፈጻጸም›› ሪፖርትም፣ ከድጡ ወደ ማጡ አሽቀንጥሮ የጣለው የመንግሥት ሚዲያው አያያዝም ጭምር የአንቀጽ 11 ይዘት ቀርቶ ህልውናውንና ድንጋጌውን ራሱ የሚያውቅ አይደለም፣ አያውቅም፡፡ ከትንሹና ከተራው ነገር እንነሳ፡፡ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው ማለት መሪዎቻችንን ራሳቸውን የሚገዛ የጋራ ግንዛቤ ሆኗል ወይ? ይህንን ጥያቄ ደጋግመን ነገር ግን ፍርኃት፣ ፍርኃት እያለን በተዘዋዋሪ መንገድ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግሮች/ጽሑፎች አጋጣሚ እያደረግን አንስተናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአንዱ ወይም የሌላው ሃይማኖት አማኝ መሆናቸው ከሕገ መንግሥቱ ‹‹መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው›› ድንጋጌ ጋር በጭራሽ አይጋጭም፡፡ ለሚከተሉት ሃይማኖት መታመናቸውና መገዛታቸውም ክልከላ የሌለበት የግል መብታቸው ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያንዳንዱ ሃይማኖታዊ ሕዝበ በዓል በመጣ ቁጥር ሁሉንም በ‹‹እኩል››ነት ሊያስተናግዱ፣ የሁሉንም ሃይማኖት የተካበተ ትምህርት የመልዕክታቸው አካል ሊያደርጉ ይፈልጋሉ፡፡ ፍላጎታቸው በገዛ ራሱ ምክንያት ክፋት ባይኖረውም፣ ለምሳሌ በተራ አንድ ትንሽ ምክንያት (ሁሉንም ሃይማኖቶች እኩል ስለማያውቁ፣ ሊያውቁ ስለማይችሉ፣ ወዘተ) ከልጅ ልጅ መለየት ሊመጣ ይችላል፡፡

ሃይማኖት ከዚያም በላይ የተወሳሰበ ነገር ያለበት፣ ለባለሙያውም እንኳን አስቸጋሪ መስክ ነው፡፡ ከሌሎች መካከል በዚህ ምክንያት መሪዎቻችን ሃይማኖቶችን ሁሉ እኩል እናምናለን፣ እንከተላለን፣ እናውቃለን፣ እናስተምራለን ከሚሉ ‹‹ዝም›› ቢሉ የተሻለ ነው ብለን ደጋግመን ለፍልፈናል፡፡ ልፍለፋችን ብቻ ሳይሆን ራሱ የሕገ መንግሥቱ አስተምህሮ የቁራ ጩኸት ሆኗል፡፡ ከዚህም የተነሳ ለምሳሌ ሃይማኖታዊ ‹‹እምነቶች›› ወይም ከእምነት የተቀዱ (የሚመስሉ) አባባሎች የመንግሥት ፖሊሲ ሆነው የመሪዎቻችን የዓይን ብርሃን፣ የእግር መንገድ፣ የሕዝብ መቀስቀሻና ማስተባበሪያ መሣሪያዎች ሆነዋል፡፡ ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ኢትዮጵያ አትፈርስም›› ይላሉ፡፡ ሕዝብን አስተባብሮ፣ በሚገባ መርቶ ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ መሥራትና ዝም ብሎ ተጨባጭ ምክንያት ሥራ ላይ ያልተመሠረተ ‹‹ኢትዮጵያ አትፈርስም›› ብሎ ጩኸትና ምኞት ግን የተለያዩ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ተዘጋጅቶ፣ ተጽፎ፣ ተፈርዶና ተወስኖ ያለቀ ጉዞ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን ‹‹መፍረስ›› ወይም አለመፍረስ፣ የሕዝቦቿን ‹‹መጨራረስ››፣ ‹‹መተላለቅ›› ወይም በሰላም አብሮ መኖር የሚወሰነው ተግባራችን፣ ሥራችን፣ ትግላችን፣ ፖሊሲያችንና ዓላማችን እንጂ፣ ምኞታችን ወይም አስቀድሞ የተወሰነ ‹‹ዕጣ ፈንታችን›› አይደለም፡፡ እዚህ ‹‹ታሪክ ሥራ›› ውስጥም ብዙ ጎራዎች፣ የተለያዩ አሠላለፎች፣ ልዩ ልዩነት ያላቸው የኃይል ሚዛኖች አሉ፣ ይፋለማሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ውስብሰብ ነገር ላይ ሌሎች እኛ የማናዝባቸው፣ አስቀድመው ተፈጽመው ያገኘናቸው፣ ተወስነው የተላለፉልን የታሪክም የተፈጥሮም መነሻዎች ዳራዎች አሉ፡፡ የታሪክ ውጤት የብዙ ነገሮች የተደባለቀ ግንኙነት ቅመማ/የተቀመመ ነው፡፡ ለዚህ ነው ፈላስፎች ጠቢባን ‹‹Nothing is inevitable in history.›› የሚሉት፡፡ ‹‹Men make their own history, but they do not make it as they please; they do not make it under self-selected circumstances, but under circumstance existing already given and transmitted from the past.›› የሚባለው፡፡ አዎ ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ፣ ኢትዮጵያውያን እንዳንጨራረስ መሥራት እንችላለን፣ ይገባናልም፡፡

በሰላም አብሮ መኖር፣ ኢትዮጵያ እንዳትፈርለስ መሥራትና መታገል ግን በሌላ በኩል መንግሥት ሕዝብን አስተባብሮና መርቶ ልንወጣው የሚገባ ግዳጅና ግዴታ ብቻ ሳይሆን፣ ህልውናና አማራጭ የሌለው ግብ ነው፡፡ ይህንን ነጥብ ለይቶና አጉልቶ ማንሳት የሚያስፈልገው አብሮ መኖርን የ‹‹መፈቃቀድ›› የቢሻን ውሳኔ የሚያደርግ ፖለቲካ ስላለ ነው፡፡ ይህንን የምንለው የአፍሪካ ኅብረት አሁን ዛሬ/ሰሞኑንና እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ በንግድ ግንኙነት አማካይነት ስለትብብር በሚነጋገርበት/በሚመክርበት ጊዜና ቦታ ነው፡፡ አፍሪካ ውስጥ ብቻ ሳይሆን እንደ አፍሪካ ባሉ ድህነትና ጦርነት መከራ በሚያሳያቸው አገሮችና ኅብረተሰቦች መካከል ግፍንና ድህነትን ተባብሮ ማሸነፍ የመፈቃቀድ ሳይሆን የመኖርና ያለ መኖር ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥትም ይህንን ትግል መምራት ቢያንስ ቢንያስ ማየት ያለበት ዝም ብሎ ‹‹ኢትዮጵያ አትፈርስም›› ከሚል እምነትና ምኞት በመነሳት ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ የሚረዱ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ነው፡፡ መንግሥት ይህን ሲያደርግ ‹‹መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ›› መሆናቸውን በተግባር ማሳየት የቻለበትን ሁኔታ ማስመስከሩ ብቻ ሳይሆን፣ የመንግሥትም ሥራ መሥራቱን የሚያረጋግጥበት ‹አጋጣሚ› ይሆናል፡፡ መንግሥት ሕግ ማክበሩን፣ ሕግ ማስከበሩን፣ ከሕግ በታች መሆኑን የማረጋገጥና የመከታተል የአገር ሥራ ግን የአጋጣሚ ጉዳይና ነገር ሳይሆን ሥርዓት የተዘረጋለትና የሥርዓት መተማመኛ ያለው መሆን አለበት፡፡

ዛሬ ከአምስት ዓመት በኋላ ብቻ ሳይሆን ያኔም ከአምስት ዓመት በፊት በነበረው ሩብ ምዕተ ዓመት በቆየው ጊዜ ውስጥ ለዴሞክራሲ፣ ስለዴሞክራሲ ቆሞ የመታገል ጉዳይ ባለው ሕገ መንግሥት ውስጥ የተደነገጉት የዴሞክራሲ መብቶችን ሕይወት እንዳገኘ የአገርና የሕዝብ የመንግሥት መኗኗሪያ እንደሆኑ የማድረግ ነገር ነው፡፡ ኢትዮጵያን እውነትም ሕገ መንግሥታዊ፣ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እናድርጋት ነው፡፡ እዚህ ውስጥ ሕገ መንግሥቱን የሚቃወሙ፣ እንዲለወጥ እንዲሻሻል የሚፈልጉ ወገኖች ሐሳብና ፈቃድ አልተካተተም የሚል ጥያቄና ተቃውሞ መነሳቱ እውነት ነው፡፡ የጠሉትን፣ አንፈልገውም የሚሉትን ሕገ መንግሥት የመለወጥና የመሻር፣ በአዲስም የመተካት ሥራ ግን አስቀድሞ ዴሞክራሲን ይጠይቃል፡፡ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የተደነገጉት የዴሞክራሲያዊ መብቶችና ድጋጌዎችን (ከ1948 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ጀምሮ ያሉት ሕገ መንግሥቶች ሁሉ ማለት ይቻላል) መኗኗሪያ ላድርግ፣ መንግሥት ራሱ ከሕግ በታች እንዲሆን ማስገደድና ማረገጋጥ ልብቃ ብሎ ያልጀመረ ትግል ግን ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥትም ሆነ ሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ ዘሎ ሊያገኝ አይችልም፡፡

መንግሥትና ሃይማኖት (የሃይማኖት ተቋማት) ምንና ምን ናቸው ብዬ ባቀረብኩትና ይህንን ጽሑፍ በጀመርኩበት ጥያቄ አማካይነት የአገር የበላይ ሕግ፣ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን እንደሚደነግግ ተመልክተናል፡፡ ይህን የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ የማክበር፣ ከዚህ ሕግ በታች የመሆን፣ እንዲሁም የማስከበር የመንግሥት ተግባርና ግዴታ ሕጉን ከማወቅ፣ በሚገባ ከመረዳትና የመንግሥትም ፖለቲካ ንቃትና ግንዛቤ ከማድረግ ይነሳል፡፡ ይህ ዕውቀትና ግንዛቤ ግን መንግሥትን ብቻውን የሚመለከት፣ ሌላውን ግን የማይነካ አይደለም፡፡ ሁሉም ወገኖች የሕጉን ትርጉምና አንድምታ ማወቅ አለባቸው፡፡ ይህንን ማድረግ የመንግሥትን ከሕግ በታች የመሆን ግዴታ፣ ሕግ የማስበርና የሕዝብ ደኅንነትን የመጠበቅ አቅም እንዲጠናከር ማድረግም ጭምር ነው፡፡

ከአምስት ዓመት ወዲህ በይፋ ማለትም ሥልጣን በያዘ/በተረከበ (እንደምናውቀው ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮና መምርያ ውስጥ መግባትና ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን ሁልጊዜም አንድ አለመሆኑን በተረዳ) አመራር የተጀመረውም ሥራ ይኼው ነበር፡፡ የመንግሥትን ለሕግ የመገዛት ግዴታ የማስጀመር፣ የማለማመድ፡፡ ይህ ግን ላይ ላዩን ከሚታወቀው በላይ ከበጎ ፈቃድ፣ ከመልካም ፍላጎት በላይ ተቋማትን ገለልተኛ አድርጎ ማቋቋምን ጠየቀ፡፡ የአገሪቱን መከላከያ ጨምሮ የኢትዮጵያን የመንግሥት አውታራት ኢሕዴጋዊነት/ፓርቲያዊነት የማፅዳት ሥራ ግን ጦርነት ገጠመው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተደነገጉ መብቶችንና ነፃነቶችን መኗኗሪያ የማድረግ የለውጥ ትግል የአገርን ህልውና ከብርቱ አደጋ ከመከላከል ጋር ገጠመ፡፡ ይህንን ጦርነት በድልና በ‹‹ተዓምር›› ጭምር ካጠናቀቅን በኋላ ደግሞ የጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. አደጋ የብራ መብረቅ ሆኖ ጅምራችንን ብቻ ሳይሆን፣ ህልውናችንንም የሚፈታተን ሥጋት ‹‹መዓት›› ይዞ መጣ፡፡ የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በተሰማ ዜና፣ አንድ ከፍተኛ የሃይማኖት አባት እንደገለጹት፣ ‹መዓቱ ተንሳፎ ቆመ› የተባለው አሁንም ‹‹በኪነ ጥበቡ›› እንጂ ከእግዚአብሔር በታች እኛ ራሳችን ባካበትነው፣ ከሕገ መንግሥቱ በተቀዳና በእሱም መሠረት በተቋቋመና በተዘረጋ ጥበብና አሠራር ‹‹ፈጣሪን ረድተነው›› አይደለም፡፡

ከዚህ ሁላችንም፣ በተለይም መንግሥትና የሃይማኖት ተቋማት መመከርና መማር አለባቸው፡፡ በተለይም መንግሥት በዚህ ረገድ ምንድነው ያጋጠመን? ለምንስ እንዲህ ዓይነት ‹‹አጋጣሚ›› ውስጥ ገባን? መከላከል አይቻልም ነበር ወይ? ብሎ ራሱን መጠየቅ አለበት፡፡ መንግሥት ሕግን የማስከበርና የሕዝብ ደኅንነት የመጠበቅ አቅሙ እንዲጠናከር ከሚያግዝና ከሚያበረታታ ድጋፍ ይልቅ፣ የነበረውን ድጋፍ የሚበትን ተቃውሞና ‹‹ትግል›› ጭምር ለምን አጋጠመ ብሎ ራሱን ውስጡን፣ ባለበጀት ጓዳ ጎድጓዳውን ሁሉ መመርመር አለበት፡፡

አገራችን ከሰው አገዛዝ ወደ ሕግ አገዛዝ (ማለትም ሕግ መንግሥትን ራሱን ወደሚገዛበት አስተዳደር) የምታደርገው/ማድረግ የጀመረችው የሥር የመሠረት ዓላማ፣ በርካታ ለውጥና ማሻሻያዎች የሚጠይቁ የተወዘፉ የቤት ሥራዎች አለበት፡፡ ለውጥና ማሻሻያዎች ማካሄድ ያለበት ግን ከየአቅጣጫው እየተርመሰመሱ ለሚመጡ ጥያቄዎች እየተዋከቡና በእነሱም እየተዋጡ መገበር ማለት አይደለም፡፡ ጥያቄዎች ያለ አንዳች ቅደም ተከተል እየተግተለተሉ አዙሪት ፈጠሩ ማለት ተቀዳሚ የለው ተግባር (የመንግሥት አውታራትን ወገንተኛነት ማፅዳትና ነፃና ገለልተኛ አድርጎ ማቋቋም) ከዕይታ እስከ ማጥፋት መንገድ አሳቱን ማለት ነው፡፡ ለውጡ የሚከፋፈሉ ጉዳዮችን እየሸሸ ‹‹መጀመርያ የመቀመጫዬን›› ማለት፣ ይህንን እየመረጠና እየወሰነ ነው መጓዝ ያለበት ማለትን እንኳን ‹‹ጥያቄ አቅራቢዎች›› (ለምሳሌ ክልል እንሁን ባዮች) ራሱ የመንግሥት አመራር በቅጡ የጨበጠው አይመስልም፡፡ ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. የኦሮቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረው ችግር መንግሥታዊ ኃላፊነትን በጨበጠበት መልክ (ጥያቄ አቅርቦም ይሁን ጥያቄ ሳያቀርብ) የተስተናገደበት ሁኔታ ይህንን የመንግሥት ‹‹ጅልነት›› ወይም ገና አለመብሰል የሚያጋልጥ ነው፡፡   

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...