አማራ ኢንሹራንስ ኩባንያ በሁለት ቢሊዮን ብር ካፒታል ሊቋቋም መሆኑ ተገለጸ። እህት ድርጅቱ አማራ ባንክም በሚቋቋመው ኢንሹራንስ ኩባንያ ውስጥ ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ ይይዛል ተብሎ ይጠበቃል።
ከአማራ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር አደራጅ ኮሚቴ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው አማራ ኢንሹራንስ ኩባንያን ለማቋቋም 34 አባላት ያሉት አደራጅ ኮሚቴ ተዋቅሮ ኩባንያውን ዕውን ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡
የአደራጅ ኮሚቴው ዋና ፀሐፊ አቶ ሰለሞን አለባቸው ለሪፖርተር እንደገለጹት የአደራጅ ኮሚቴው ተሰብስቦ የሥራ ኃላፊነት ምደባ ተደርጓል፡፡ በዚሁ ምደባ መሠረት የአደራጁ ኮሚቴው ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢና ፀሐፊ እንዲሁም የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተሰይሞ መረጃውን ለብሔራዊ ባንክ ለማስገባት ዝግጅት ተጠናቋል፡፡
የአማራ ባንክ እህት ኩባንያ እንደሚሆን የሚጠበቀውን የዚህን ኩባንያ ስያሜ ‹‹አማራ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር›› ለማለትና ስያሜውን ለመጠቀም ለሚመለከተው መንግሥታዊ መሥሪያ ቤት መመዝገቡም ተገልጿል።
ከዚህ በኋላ የአደራጅ ኮሚቴውን ሙሉ መረጃ ለብሔራዊ ባንክ ካስገቡ በኋላ ብሔራዊ ባንክ በሚፈቅደው መሠረት ወደ አክሲዮን ሽያጭ እንደሚገባም ከአቶ ሰለሞን ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ኩባንያው ኢንዱስትሪውን ሲቀላቀል ይዞት የሚገባው የካፒታል መጠን ሁለት ቢሊዮን ብር እንደሚሆን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል። ይህ የሚሰካ ከሆነ የሚቋቋመው አማራ ኢንሹራንስ ማኅበር በአገሪቱ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ሁለት ቢሊዮን ብር ካፒታል ይዞ የሚቋቋም የመጀመርያው ኩባንያ ያደርገዋል፡፡
እስካሁን በኢንዱስትሪው ውስጥ የሚንቀሳቀሱት የግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ወደ ሥራ ሲገቡ ይዘውት የተነሱት ካፒታል ከሦስት ሚሊዮን ብር እስከ 15 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ በሥራ ላይ የሚገኙት ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ካፒታላቸውን እያሳደጉ በመምጣት በአሁኑ ወቅት የተፈረመ ካፒታላቸውን እስከ ሦስት ቢሊዮን ብር ማድረስ የቻሉ ቢሆንም የአብዛኞቹ የተፈከፈለ ካፒታል መጠን አሁንም ድረስ ከ500 ሚሊዮን ብር በታች መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ 18 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አጠቃላይ የካፒታል መጠናቸው 14 ቢሊዮን ብር እንደሆነ በቅርቡ የወጣው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ ያመለክታል፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ለማቋቋም በቅርቡ ባወጣው መመርያ አንድ ኢንሹራንስ ኩባንያ ለማቋቋም ዝቅተኛው የካፒታል መጠን 500 ሚሊዮን ብር እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል፡፡ ከ27 ዓመታታ በፊት በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኩባንያ ለማቋቋም ይጠየቅ የነበረው የካፒታል መጠን ሦስት ሚሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም አንድ ኢንሹራንስ ኩባንያ ለማቋቋም የሚጠየቀው የካፒታል መጠን 75 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡
በግዙፍ ካፒታል የባንክ ሥራን የተቀላቀለው አማራ ባንክ በአማራ ኢንሹራንስ ኩባንያ ውስጥ ከፍተኛውን የአክሲዮን ድርሻ ይይዛል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑን ከአቶ ሰለሞን ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የኢንሹራንስ ኩባንያውን በሁለት ቢሊዮን ብር ለመመሥረት የታቀደበት አንዱ ምክንያትም የአማራ ባንክ ከፍተኛውን የአክሲዮን ድርሻ ይወስዳል ተብሎ በመታመኑ ጭምር ነው፡፡
አማራ ኢንሹራንስም አንደ አማራ ባንክ ከፍተኛ ካፒታል ይዞ ወደ ኢንሹራንስ ኢንዱሰትሪው ለመቀላቀል ዝግጅት እያደረገ ሲሆን ሥራ ሲጀምርም የሕይወትና ሕይወት ነክ ያልሆኑ የኢንሹራንስ አገልግሎቶችን አጣምሮ የሚሠራ ይሆናል ተብሏል፡፡
አማራ ባንክ በ2014 መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያፀደቁለት ከ141 ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖች ያሉት ነው፡፡ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ 8.7 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ የሰበሰበ ሲሆን ካፒታሉንም ወደ 20 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወስኗል፡፡