Saturday, September 23, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የአቅርቦትና የግብይት ችግር የሚስተዋልባቸው ምርቶች ሊያገበያይ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በግብይት ውስጥ ከፍተኛ ችግር አለባቸው የሚባሉ የተለያዩ ምርቶችን፣ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ለማገበያየት የሚያስችሉ ጥናቶች እየተደረጉ መሆኑ ተጠቆመ፡፡ 

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ እስካሁን ከሚያገበያያቸው ምርቶች በተጨማሪ፣ በተለይ በግብይት ውስጥ ችግር የሚታይባቸው እንደ ሲሚንቶ፣ ስኳርና የኢንዱስትሪ ጨው ያሉ ምርቶችን በምርት ገበያው በኩል እንዲገበያዩ ጥናት እየተደረገ ስለመሆኑ ታውቋል፡፡ እነዚህ ምርቶች ብዙውን ጊዜ የግብይት ችግር ያለባቸው በመሆኑ፣ በምርት ገበያው በኩል ቢገበያዩ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ እንደሚያስችል ታምኖ ጥናት እየተደረገባቸው ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከእነዚህ ምርቶች ሌላ የተለያዩ የማዕድን ምርቶችን በምርት ገበያው በኩል ለማገበያየት ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር መፈራረሙ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህንን ስምምነት ዳር ለማድረስ በአሁኑ ወቅት ተጨማሪ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡  

የማገበያየቱ ሥራ እስካሁን ያልተጀመረበት አንዱ ምክንያት ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

ለምሳሌ ሲሚንቶን በምርት ገበያው ማገበያየት ፍትሐዊ ሥርጭት እንዲኖር ያስችላል፡፡ ገዥም ሆነ ሻጭ በትክክለኛው የታክስ ሥርዓት ያልፋል፡፡ ከሁሉም በላይ ‹ማን ገዥ›፣ ‹ማን ሻጭ› እንደሆነ በቂ መረጃ የሚገኝበት ነው፡፡ ለቁጥጥርም የሚያመች በመሆኑ ገበያ ውስጥ ያለው ችግር ይቀረፋል፡፡ 

በምርት ገበያው በኩል እንዲገበያዩ የሚጠበቁ ማዕድናት፣ በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው በሕገወጥ መንገድ ግብይታቸው የሚያከናውኑ ናቸው፡፡ በኮንትሮባንድ ከአገር ከሚወጡ ምርቶች መካከል በዋናነት ከሚጠቀሱት የማዕድን ምርቶች መካከል እንደ ኦፓል ያሉ ምርቶች ተጠቃሽ በመሆናቸው፣ ግብይታቸው በምርት ገበያው በኩል መከናወን ሕጋዊ ግብይትን ከመፍጠር ባለፈ፣ ከእነዚህ ምርቶች አገር በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ እንድትሆን ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 

በገበያ ውስጥ ችግር ያለባቸውን ምርቶችም ሆኑ ሌሎች ምርቶችን በምርት ገበያው በኩል ለማገበያየት የተያዘውን ውጥን በተመለከተ ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኮርፖሬት ኮዩሙኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ነፃነት ተስፋዬ፣ ‹‹ማንኛውም ግብይት በዘመናዊ ግብይት የሚካሄድ ከሆነ፣ በሕግና በቴክኖሎጂ ስለሚመራ ሁሉም የግብይት ተዋንያንን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥርዓት እንዲፈጠር ያደርጋል፤›› ይላሉ፡፡

ይህም ለአገር፣ ለተገበያዮች፣ ለአርሶ አደሩ፣ ለአቅራቢና ለገዥው ጭምር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ያብራሩት አቶ ነፃነት፣ ማንኛውም ምርት፣ ምርት ገበያው ጋር ሲመጣ በጥራት መሥፈርቱ መሠረት ደረጃው ተለክቶ በላቦራቶሪ ተመርምሮ ደረጃ ስለሚሰጠው ገዥዎች፣ በጥራቱ ላይ ሳይቸገሩ የሚፈልጉትን ምርት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡

ሻጮችም ለሸጡት ምርት ዋስትናቸው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ስለሚሆንና ክፍያቸውም በሚቀጥለው ቀን በባንክ አካውንታቸው እንደሚገባ እርግጠኛ ስለሚሆኑ ጤናማ የግብይት ሥርዓት እንዲፈጠር ያግዛል ብለዋል፡፡ ስለዚህ ይህንን የኢኮኖሚ እንቀስቃሴ ሥርዓት ባለው መልክ ሁሉም የግብይት ተዋንያንና በግብይት ውስጥ ያሉትን ተዋንያን ሁሉ ተጠቃሚ የሚያደርግ ጭምር በመሆኑ፣ በምርት ገበያው በኩል የሚፈጸም ግብይት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ያስረዳሉ፡፡

በአገር ደረጃ ደግሞ በዚህ ግብይት የሚሰበሰበው መረጃ ለአገር ኢኮኖሚና ማክሮ ኢኮኖሚውን ለሚመለከቱ ውሳኔዎች የሚጠቅም በመሆኑ ጠቃሚታው የጎላ ይሆናል ብለዋል።

ምክንያቱም ዳታው በየቀኑ ስለሚያዝ ወደፊም የረዥም ዓመትን መረጃ ወስዶ ለማጥናት ቢፈለግ እንኳን መረጃው በዘመናዊ ግብይት ውስጥ ስላለ ለተለያዩ የፖሊሲ ውሳኔ ጭምር የሚያገለግል ይሆናል፡፡ ማንኛውም ምርት ላይ የሚደረግ ግብይት በገበያ መረጃ ላይ የተመረኮዘ መሆን አለበት ያሉት አቶ ነፃነት፣ ለምሳሌ ነዳጅ ሲጨምር ወይም ሊቀንስ የሚችለው በዓለም ገበያ ዋጋ ላይ ተመርኩዞ ነው፡፡ ምክንያቱም ዋጋው የሚወሰነው በዓለም ትልልቅ ኤክስቼንጆች ተመሥርቶ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያም የሚገበያየው ግብይት ማንኛውም ግብይት ከዕለታዊው የገበያ መረጃ በግብይት ሰንሰለት ውስጥ ላሉ አካላት ተደራሽ መሆን አለበት፡፡ 

ስለዚህ የገበያው መረጃ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የተጠናከረ፣ በቴክኖሎጂ ታግዞ ሁሉም የገበያ ተዋንያን እንዲደርሳቸው ያደርጋል፡፡ አርሶ አደሩ ምርቱን ወደ መጀመርያ ደረጃ የግብይት ማዕከላት ሲወስድ አስቀድሞ ይህ ግብይት መረጃ ስለሚደርሰው በዋጋ ላይ ደላላ አያታልለውም፡፡ በዋጋ ላይ ተደራዳሪ ይሆናል፡፡ ተገማች የሆነ የግብይት ሥርዓት ይኖረናል ማለት ነው፡፡ ይህ የግብይት መረጃ ደግሞ የእኛን ብቻ ሳይሆን የውጭ ገበያን የሚጠቅም ነው፡፡ 

ዓለም ገበያ አምስት ሺሕ ብር የሚሸጥ እዚህ ሰባት ሺሕ ብር ሊገበያይ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም አገር ኪሳራ ላይ ወድቃ ምርት ኤክስፖርት ሊደረግ አይችልም፡፡ ስለዚህ እስካሁን በግብይት ውስጥ ያሉ ምርቶችና አዲስ እንዲገቡ የሚፈለጉ ምርቶች በዚህ መልክ ወደ ምርት ገበያ መምጣትና መገበያየቱ ሥርዓት ባለውና ዘላቂነት ባለው ግብይት እንዲከናወን ያስችላል፡፡ ከዚያም በላይ ለማክሮ ኢኮኖሚው በሚበጅ መንገድ ሁሉም የግብይት ተዋንያን በሚጠቅምና ሕጋዊ የሆነ የግብይት ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ ስለሚያስችል ይሆናል ብለዋል፡፡ 

በመሆኑም እስካሁን ከአምና ገበያቸው ምርቶች በተጨማሪ፣ ከኢንዱስትሪ ምርቶች ስኳር፣ የኢንዱስትሪ ጨው፣ የጌጣጌጥ ማዕድናት፣ ሲሚንቶና የመሳሰሉን በምርት ገበያው በኩል ለማገበያየት ጥናት እያደረግን ያለነውም እንዲህ ያለውን ዘመናዊ ግብይት ለማስረፅ ነው፡፡

አንድ ጥናት ለማካሄድ ግን ሰፊ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ምክንያቱም ምርቱ የሚመረትበት አካባቢና አምራች ጋር ያለው ፍላጎት ግብይቱ ጋር ያለው ፍላጎት ላለፉት አምስትና አሥር ዓመታት ወደ ኋላ ሄደን ግብይት ዋጋው ምን ያህል እንደሆነ ማየት ስለሚያስፈልግ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፣ ኤክስፖርት የሚደረገውን ምርት እነ ማን ናቸው የሚገዙት? ገዥዎች ፍላጎታቸው ምን ያህል ነው? አገር ውስጥ የሚመረተው ምርት ደግሞ የቤተሰብ ፍጆታና ለገበያ የሚውለው ምን ያህል ነው? የሚሉትን ተዓማኒ ቁጥሮችና መረጃዎች ተወስደው ባለሙያዎች መስክ ወጥተው መረጃ ሰብስበው ጭምር የሚሠሩት ነው፡፡ ስለዚህ ጥናቱ ጊዜ ሊወስድ ከመቻሉ ውጪ በምርት ገበያው በኩል መገበያየታቸው አስፈላጊ መሆኑንም አቶ ነፃነት አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሚገበያየው ወደ ውጭ አገር የሚላኩ ምርቶች ነው፡፡ ቡና ብቻ ነው ለአገር ውስጥ ገበያም የሚሆን ምርት የሚያገበያየው፡፡ ስለዚህ ምርት ገበያው ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚውሉ እንደ ሲሚንቶና ስኳር ያሉ ምርቶችን ማገበያየት አቅም አለው፡፡ ስለዚህ የገነባነው መዋቅር አለው፡፡ ይህንን በመቀጠም ሲሚንቶንም ሆነ ስኳር ማገበያየት ይቻላል፡፡ ከዚያ አልፎ ወደ ውጭ አገር መላክ ቢያስፈልግ ይህንን ማድረግ የሚቻልበት አሠራር ስላለው የእነዚህን ምርቶች ጥናት አጠናቅቆ ወደ ሥራ መግባቱ ብዙ ጠቀሜታ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ይህንን ውጥን በተለይ የኢንዱስትሪና የማዕድን ምርቶችን በምን መልኩ ግብይት ውስጥ ማስገባት ይቻላል? በሚለው ጉዳይ ላይ የምርት ገበያው ባለሙያዎች ከሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ጋር በመሆን እያጠኑት መሆኑም አቶ ነፃነት ገልጸዋል፡፡  በተለይ ኦፓል፣ ሳፋዬርና ኤመራልድን ወደ ግብይት ሥርዓቱ ለማስገባት ከማዕድን ሚኒስቴርና ከኢትዮጰያ ምርት ገበያ የተውጣጣ ቴክኒካል ኮሚቴ ተቋቁሞ ያዘገጁት ሰነድ ስላለ ከዚህ በኋላ ተከታታይ ሥራዎችን በመሥራት በምርት ገበያው በኩል ግብይታቸው ይፈጸማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እስካሁንም የዘንድሮው ምርቱ በነበረባቸው አካባቢዎች በነበረ የፀጥታ ችግር ነው ተብሏል፡፡ ስለዚህ ለአገር የሚሰጠው ጥቅም ግብይቱን በሥርዓት ከኮንትሮባንድ ነፃ ሆኖና ከሕገወጥ ንግድ ነፃ ሆኖ ሊሠራ ይችላል፡፡ 

በምርት ገበያው የሚገበያዩ ምርቶች ገበያውን ከማረጋጋት አኳያ ያላቸው ሚና ምንድነው? ለሚለው ጥያቄ አቶ ነፃነት፣ ‹‹የገበያ መረጋጋት ስንል የውጭ አገርና የአገር ውስጥ ገበያን መለየት ያስፈልጋል፤›› ይላሉ፡፡

ለምሳሌ ከውጭ መጥቶ የሚሸጥ ምርት አለ፡፡ አገር ውስጥ ምርት በቂ ካልሆነ ኢንፖርት የተደረገ ምርት አለ፡፡ በዚህ ላይ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አላመለከተውም፡፡

‹‹ስኳር፣ ስንዴና የመሳሰሉት ምርቶች መወደድ ሲያጋጥም መንግሥት ከውጭ ያስገባና በራሱ መንገድ ያሠራጫል፡፡ ስለዚህ መንግሥት ባለበት ኃላፊነት ገበያን ለማረጋጋት የሚወሰደው ዕርምጃ ነው የገበያ ማረጋጋት ይህ ነው፡፡ 

በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ግን የሚደረገው ግብይት አቅርቦትና ፍላጎትን መሠረት ያደረገ የዓለም አቀፍ ገበያን ዋጋ መሠረት ያደረገ ነው፡፡ 

ስለዚህ ምርት ገበያው በአቅርቦትና በፍላጎት ላይ የተመሠረተውን ገበያ በሥርዓት መምራት ነው፡፡ ይህም የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ዋጋን እንዳይቆጣጠሩት ማድረግ ነው፡፡ ይህንን ግብይቱን እያካሄድን ቁጥጥር እናደርግበታለን፡፡ በምርት ገበያው የግብይት ደኅንነት ክትትሉ በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል ያለውን ልዩነት ተጠቅመው ጥቂቶች ገበያውን እንዳይቆጣጠሩ የተጋነነ ዋጋ እንዳይቀርብ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ይቆጣጠራል፡፡

አሁንም በገበያ ውስጥ ችግር የሚታይባቸውን እንደ ስኳር፣ ሲሚንቶና መሰል ምርቶች በምርት ገበያው በኩል እንዲገበያዩ ማድረጉ ገበያ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ሊቀርፍ ይችላል ወይ? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ነፃነት፣ አዎ ይቻላል ይላሉ፡፡ ለዚህም የተለያዩ አገሮችን ልምድ ማየት ይቻላል፡፡ 

በሌሎች አገሮች ማንኛውንም ምርቶቻቸውን እንዲገበያዩ የሚደረገው በምርት ገበያዎቻቸውና ቁጥጥር በሚደርግባቸው ተቋሞቻቸው ወይም ግብይት ሥርዓት ነው፡፡ ስለዚህ በመረጃ የሚያዝ ግብይት ስለሆነ ከቁጥጥርና ከክትትል ሊያመልጥ አይችልም፡፡

በምርት ገበያው መግባታቸው ሕጋዊ ግብይትን ከማሳለጥ ባለፈ፣ በእያንዳንዱ ግብ መንግሥት ማግኘት ያለበትን ታክስ እንዲያገኝ ሁሉ ስለሚጠቅም በምርት ገበያው በኩል መገበያየት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል በማለት ገልጸዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች